ከሰሞኑ የመዲናችን ወሬዎች መካከል ሁለቱ ጆሮዬንም ቀልቤንም ስበውት ሰነበቱ። በእርግጥ ጉዳዮቹ «ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር…» የሚያሰኙ ናቸው። እንደው ለማስታወስና የኔን ምልከታ ለማስቀመጥ ብቻ ነው።
የመጀመሪያው «የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል» እንዲሉ የእንጀራ ጉዳይ ነው። የእንጀራ ነገር እንደኛ «እንጀራ ይውጣልህ» ተብሎ ለተመረቀ የተባረከ ልጅ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተመረቅንበት ወቅትም እንጀራው የምንድነው? ብለን ለመጠየቅ አልተነሳሳንም ነበር፡፡ ያንንም ያላዳረግንበት ምክንያት ትሁትና ታዛዥ ስለነበርን እንጂ በወቅቱም ቢሆን እንደ ዘመኑ ልጅ ብናስብ ኖሮ የተሸከመነውን ቅጠል ውርውር አድርገን እማማ አቦዘነች እንጀራው የምንድነው? የጤፍ ወይስ የበቆሎ ደግሞስ ምን ይደባለቅበት ዘንጋዳ ወይንስ ዳጉሳ ብለን መጠየቅ እንችል ነበር።
እኛ ግን የምርቃትንም የእርግማንን ትርጉም ጠንቅቀን እናውቅ ስለነበር፤ አንገታችንን ሰበር አድርገን «ኧረ ምንም አይደል ቀላል እኮ ነች» እንል ነበር። አንዳንድ ጊዜም እግረ መንገዴን ነው እያልን ተሽከምን እየሮጥን እንመረቅ ነበር። መራቂዎቻቻንም ቢሆኑ ምንም እንኳ በርገርና ፒዛን ለማየት ያልታደሉ ቢሆኑም ማርና ወተት ብለው አለመመረቃቸው እንጀራ በራሱ የተለየ ትርጉም እንዳለው የሚያሳየን ይመስለኛል።
ዛሬ ግን አንድ የመጣ ቡድን አለ። ከየት እንደ መጣ እኔ አላውቅም። በእርግጥ በደም የኛው ወገን እንደሆኑ የዲ.ኤን.ኤ ማስረጃ ሳላቀርብ ማረጋገጥ እችላለሁ። ሥራቸው፣ እንቅስቃሴያቸውና ንግግራቸው ግን ምንም ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ አይሸትም። ከዘመኑ ጋር መራመዳቸውን እኔም እደግፋለሁ። ይሄ ማለት ግን እንጀራን ዘመን ካመጣው ሩዝ ጋር ይቀላቅሉ እንጂ ከጀሶና ከሰጋቱራ … እንዴ ምን ቀራቸው በጣም ነው የሚገርመው። ለነገሩ አንድ ጓደኛዬ የሰዎቹን የምርምር ጥበብ መሰረት አድርጎ እንደነዚህ አይነት ብሩህ አዕምሮ ያላቸውን ሰዎች የሚቀበል ዩኒቨርስቲ አለመኖሩ ወደዚህ ክፉ ተግብር እንደገፋፋቸው አስረድቶኛል።
ለምሳሌ ነጭ ጤፍን ከነጭ ጀሶ ጋር መቀላቀል ቢያንስ በቀለም ስለሚመሳሰሉ የምርምር መነሻ አድርጎ መውሰድ ይቻላል። ጤፍን ከሰጋቱራ ጋር ለመቀላቀል ግን ራሱን የቻለ የተሟላ ላቦራቶሪ ያስፈልጋል። ለዚህ የሚሆን ላቦራቶሪ ደግሞ የሀገሪቱ ደረጃዎች መዳቢ ኤጀንሲን ጨምሮ ማንም የለውም። በደረጃዎች መዳቢ ኤጀንሲ ይሄ ላለመኖሩ ማረጋገጫው ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጤናማ ያልሆኑ የታሸጉ የለስላሳ መጠጦች በህጋዊ መንገድ ሀገር ውስጥ ገብተው ሲበተኑ ዝም ብሎ ለህዝብ ከደረሱና ከተጠጡ በኋላ ከየሱቁ ለመልቀም የሚያደርገው መሯሯጥ ነው።
በዚሁ እንጀራን ከባእድ ነገር ጋር በመቀላቀል ጉዳይ በቴሌቪዥን መስኮት እንዲሁም በሬዲዮ፣ በጋዜጣና በማህበራዊ ድረ ገጾች በርካታ አስተያየቶች ቀርቦበታል። ግና ሁሉም ሊባል በሚችል ደረጃ ለዚህ የተዳረገነው መንግሥት ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ ባለመሆኑ እንደሆነ ሲገልጹ አስተውያለሁ። በእርግጥ በርካታ ሰዎችን ሕጻናትና ነፍሰጡሮችን ጨምሮ ለካንሰር፣ ለኩላሊትና ለሌሎች በርከት ላሉ በሽታዎች የሚዳርግ ጥፋት ነው።
እንደመንደር አተካሮ ወንጀለኞቹን በወራት ፍርድ እየቀጡ መልቀቅ ችግሩን ከማባባስ የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው መንግሥት ራሱ ባለፉት ዓመታት ተደጋግሞ ሲከሰት የሚረዳው ይመስለኛል። ምን ይሄ ብቻ ነገሩ በሀሜት ደረጃ ሲሰማ የተጀመረው በከተማዋ ዳርቻ ጸጥ ረጭ ባሉ ብዙም እንቅስቃሴ በማይታይባቸው አካባቢዎች ነበር። ውሎ ሲያድርና ጥቅሙ ጉዳቱ /ቅጣቱ/ ደግሞ ቀላል መሆኑ እየታወቀ ሲመጣ ግን መሀል ፒያሳ ላይ መሰራት ተጀመረ።
እንግዲህ ልብ በሉ እነዚህ ህሊና ቢስ ወንጀለኞች እንደ መትረየስ ተኳሽ ቦታ እየቀያየሩ ሲያጠቁን ፖሊስም ሆነ ደንብ ማስከበር አልያም የሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የሚደርሱት ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ ከረምረም ብለው «ጉድ ጉድ» ተብሎ ካበቃ በኋላ ነው። ለዚህ ደግሞ የእነርሱ መፋዘዝ ፈጣንና ተመጣጣኝ እርምጃ አለመውስድ እንደተጠበቀ ሆኖ ወንጀለኛን አቅፎ ደግፎ ከተቀመጠ ማህበረሰብ መካከል ወንጀለኛን ማውጣት ድንች እንደመላጥ የሚቀል አይደለም።
ባጭሩ ወንጀለኞቹ ያሉት በእያንዳንዳችን ጓዳ መሆኑን እንመንና ራሳችንን ፈትሸን አሳልፈን እንስጣቸው። ከዛ ለምን በደንብ አልቀጣህም ብለን መንግሥትንና የሚመለከተውን አካል ለመኮነንም ሆነ ለመውቀስ ሞራል ይኖረናል ብዬ አስባለሁ።
ካስታወስን ይሄ ነገር ከሁለት ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ግዜ ወሬው ሲሰማ ጉድ ጉድ ተብሎ ነበር። የአንዳንድ ሃይማኖቶች የአውደ ምህርትም ርእስ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል። አሁን ተለመደና «ዛሬም ደገሙት!» ብቻ መባል ተጀመረ። እነርሱ ለምን ደገሙት? ከተባለ ያልተያዙትን ለኛ ትተን በተያዙት ላይ በተጻፈ ህግና በቂ ማስረጃ አለመገኘት ተሳቦ ተመጣጣኝና ሊያስተምር የሚችል እርምጃ ባለመወሰዱ መሆኑን የሚክድ ያለ አይመስለኝም።
ለነገሩ እኛ ባዕድ ነገር ለተቀላቀለበት ምግብ አዲስ መሆን ካቆሞን ቆይተናል። ለዚህ ደግሞ ገበያ ስንወጣ የምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ቋሚ ምስክሮች ናቸው። ቅቤ ስንገዛ «ሙዝ አልተቀላቀለበትም?»፤ ማር ስንገዛ «ስኳር አልተቀላቀለበትም?»እያልን ነው። በየቤታችን ከሚመጣው የለውዝ ቅቤ፣ ዘይት፣ … ምን ያልተበከለ ነገር አለ ? ድሮ ስጋ የበሬ፣ የበግ የፍየል ነበር እድሜ ለእነዚህ ክፉዎች የአህያና የጅብም አቀረቡልን፤ እነዚህ እንግዲህ በየቀኑ በየሆቴሉ ምግብ ሲቀርብልን ያደረ ነው፣ ትኩስ ነው እያልን የምንጠይቀውን ትተን ማለት ነው።
እናም ሃሳቤን ልድገመው! ወደ መንግሥት የያዝነውን ጩኸት እንደተጠበቀ ይሁንና ራሳችንንም በጥያቄ እንጩኽበት። እኛው ቤት አከራይተን፤ እኛው ጎረቤት ሆነን፤ በይሉኝታ ተሸብብን ሸፍነን ይዘናቸው መንግሥት ላይ ብቻ ለምን እናፈጣለን?
ሌላው ሁለተኛው ነገሬ ደግሞ የመጠጥ ማስታወቂያ ጉዳይ ነው። «መጠጥ ጤናን ይጎዳል»፤ «አደንዛዥ በመሆኑ ትውልድ ይገድላል፤ ቤተሰብ ያፈርሳል ለድህነት ይዳርጋል…» ይባላል። ወደ ማስታወቂያው ስንመጣ ደግሞ ዛሬ በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ስለቀረበ ካልሆነ በቀር እንደማንኛውም ሀገር ኢትዮጵያም የራሷን ማስታወቂያ (ብራንድ) ለብዙ ነገሮች ስትጠቀም መኖሯ ግልጽ ነው። ለምሳሌ የመጠጡን ብናነሳ እኔ ከማውቃቸው ለጠላ ጣሳ ሲሰቀል ኖሯል፤ ለሻሜታ ሰፌድ ይንጠለጠላል። በመሆኑም እኔ እንደተረዳሁት ከሆነ የአሁኑ «የማስታወቂያ መተላለፍ ይታገድ» ጥያቄ ዘመን ካመጣቸው መጠጦች ጋር ብቻ የተያያዘ ይመስለኛል።
እንግዲህ የነገሩ መነሻ «ከመጠጥ ማስታወቂያ» ጋር ያለው ቅራኔ ማለቴ ነው። ሁለት መሰረታዊ ጥፋቶች ስላሉ ይመስለኛል። የመጀመሪያው ልኩን ጠብቆ በመጠን የማይጠጣው እየበዛ በመምጣቱ በመሆኑ ይሄን ተከትለው የሚመጡ ድርብ ድርብርብ ችግሮችን ለማስወገድ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ እድሜያቸው ለአቅመ መጠጥ ያልደረሱና በአንድ በኩል ደግሞ በተለይ በዩኒቨርስቲዎች ያሉ ተማሪዎች በዚህ ተሰናክለው ከአላማቸው እንዳይስተጓጎሉ ነው።
ሁሉም የመጠጥ ፋብሪካዎች «ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ለሆኑ የተከለከለ!»፣ «ከአስራ ስምንት ዓመት በታች ለሆኑ የማይሸጥ!»፣ «በኃላፊነት ይጠጡ!»፣ «አልኮል ጤናን ይጎዳል!»፣«ጠጥተው አያሽከርክሩ!» ወዘተ ማለታቸው አልቀረም። እናም በአንድ በኩል እነዚህ ባለመጠጦች መሸጣቸውና ማጠጣታቸው ካልቀረ በማስተዋወቃቸው ለምን ጎረበጠን። ልጆቹንስ የመቆጣጣር ተቀዳሚ ተግባር የማን ሊሆን ነው? በእርግጥ የትምና መቼም ቢሆን በህግ የሚደገፍ ስራ ውጤታማ እንደሚሆን እሙን ነው። ይሄ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬ ከመጠጡ በላይ በየሰፈሩ የተሰገሰጉት ማስታወቂያ የማይለቀቅባቸው የሺሻ፣ የሀሺሽ ማጨሻና ጫት ቤቶች ከመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ጀምረው የስንቱ መጥፊያ እንደሆኑ ግልጽ ነው።
ይሄ ጉዳይም በጉያችን ታቅፈን ልናጠፋው የምንታገለው እሳት ይመስለኛል። በየመንደሩ በየሰፈሩ አንዳንድ ክፍል ቤት፤ ሲደረጁም ሙሉ ግቢ ቤት ተከራይተው ሱስና ጥፋትን የሚሸቅጡ ሰዎች አላየናቸውም አልሰማናቸውም ብንል ማን ያምነናል?። ይሄ ሁሉ መሸታ ቤትስ በውድቅት ሌሊት አስርሽ ምቺው እያለ የሚያድረው ማን ባከራየው ግቢ ነው። በየጎናችን ዩኒፎርም ለብሰው ጫታቸውን ሸጎጥ አድርገው ሲሄዱ «አላየንም» ብንል ፈጣሪያችንና ህሊናችን የሚታዘበን ይመስለኛል። ለማን ጠቁመን እናውቃለን። ስለዚህ እያንዳንዳችን የኛን የገቢ ምንጭ፤ የኛን ጥቅም፤ አልያም ጉርብትና የሚነካ ሲሆን በጥቅምና በይሉኝታ ተሽብበን በማለፋችን ዛሬ ላይ የደረስን ይመስለኛል። በመሆኑም ነገ እንዳይቀጥል ከማንም በላይ የእኛ ኃላፊነት ዋና ነው እላለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011
ራስወርቅ ሙሉጌታ