የኢትዮጵያ ፖለቲካ በብዙ ተግዳሮቶች የተሞላ ስለመሆኑ ብዙ የታሪክና የፖለቲካ ምሁራን ደጋግመው የተናገሩትና አሁንም የሚናገሩት የአደባባይ እውነታ ነው። ለዚህም በአንድ በኩል የፖለቲካ አስተሳሰባችን ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ እዛው ጅምሩ ላይ መሆኑና አሻጋሪ ባለ ራእይ አጥቶ መቆየቱ ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በየዘመኑ መጥቶ የሚያልፈው ትውልድ ከቀደመው ባለታሪክ ትውልድ ውድቀት መማር አለመቻል የችግሮቻችን አልፋና ኦሜጋ እንደሆነም ይነገራል።
ከሁሉም በላይ በየዘመኑ የነበረው ሀገራዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ መሰረቱን በሴራ ላይ ማዋቀሩ፤ በዘመናት መካከል ከሴራና ከሴረኞች አዙሪት መውጣት አለመቻሉ ዜጎች ተነግሮ ለማያልቅ መከራና ስቃይ እንዲሁም ከዚህ በሚመነጭ ም ሬትና ለቅሶ እንዲያሳልፉ አስገድዷል።
ከዚህ የሚብሰው ደግሞ የፖለቲካ አስተሳሰቡ መሰረት የሆነው ሴረኝነት በየዘመኑ በብዙ ጥረት የተገነቡትን እያፈረሰ ትውልዶች ዘመናቸውን ከዛም በላይ በሰማእትነት ስም መተኪያ የሌለውን ውድ ሕይወታቸውን ፍጻሜ ለሌለው ጅማሬ እንዲገብሩ የማድረግ እውነታ ነው ።
የሩቁን ዘመን ትተን የቅርቡን እንኳን ብናስታውስ በ1950ዎቹ መጨረሻ የተጀመረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ በዘመኑ የነበረውን ትውልድ የሀገር ራዕይ አጉልቶ የሚያሳይ ነበር። ትውልዱ ዘመናት ካስቆጠረውና ተስፋ መሆን በማያስችል ሁኔታ ካረጀው አስተሳሰብ አምርሮ በመውጣት አዲስ ሀገራዊ ጅማሬ ለማምጣት የነበረውን እውነተኛ ጣር ማሳየት ያስቻለም ነበር።
ትውልዱ የቱን ያህል በቀደመው ዘመን ሀገራዊ እውነታ ምሬት ውስጥ እንደነበር፣ ምሬቱን የሚሽር ተስፋ ሰንቆ በሁለንተናዊ መልኩ ልእልና ያላት፣ ለዜጎቿ የተሻለ ተስፋ የሰነቀች እንድትሆን ታላቅ ህልም አልሞ እንደነበር
የታሪክ መዛግብት በአግባቡ ባይተርኩትም እውነቱ ግን በወቅቱ የነበረውን ሀገራዊ ፖለቲካ ገዝቶት እንደነበር በድፍረት ለመናገር የሚከብድ አይደለም።
ይህ የትውልዱ መነቃቃት በብዙ የተስፋ ዜማዎች የሀገሪቱን አደባባዮች ሞልቶ ዳግም የመነሳት ተስፋ በሀገሪቱ ህዝቦች ላይ መፍጠር ቢችልም በቆየው የሴራ ፖለቲካ ተጠልፎ ባለተስፋው ትውልድ ስለተስፋ እያዜመና እየፎከረ አደባባዮቹን ፍጻሜያቸው አምባገነንነት ለሆነ ቡድኖች ትቶ ወደ መቃብሩ ሄዷል። የሄደበት መንገድ እንደ አንድ ትውልድ ለታሪክ ያተረፈው ገጽ ቢኖርም እንዳሰበው ለሀገሩና ለህዝቡ ተስፋ ሳይሆን ቀርቷል።
ከዚህ ይልቅ በነዚህ ተስፈኛ ንጹሀን ዜጎች የመስዋዕት ደም በምድሪቱ ላይ ያቆጠቆጡት አዳዲሶቹ አምባገነኖች ሀገርን በቡድን ተደራጅተው እስከ ማፍረስ የሄደ የሴራ ጉንጓኖ ሲጎነጉኑና በዚህም ዜጎችን ተነግሮ ለማያልቅ ስቃይና በደል ዳርገዋል። በያንዳንዷ የሴራ ጉንጓኖ ከዜጎች ባለፈ ሀገር እንደ ሀገር የምትቀጥልበትን የገመድ እስር እስከ መቁረጥ የዘለለ ተግባሮችንም ፈጽመዋል።
በ1983 ዓ.ም በብዙ የሀገሪቱ ዜጎች መስዋእትነት ወደ ስልጣን የመጣው የህወሓት ጁንታ ገና በድሉ ማግስት በተፈጠረበት የድል ስካር የትግሉ ሰማዕታት ተስፋ ያደረጉትን ሀገራዊ ነጻነትና ዴሞክራሲ ከህዝቡ በመንጠቅ የአዲስ አምባገነናዊ ስርአት ጀማሪ የድንጋይ መሰረት ጥሏል።
ከፍ ባለ ድምጽ ሲያዜም የነበረውን ነጻነትና ዴሞክራሲ ብዙም ሳይቆይ በትግሉ ውስጥ የነበሩ ዜጎችን ሳይቀር ግራ በሚያጋባ ሁኔታ የመስዋእትነት ትግል ድሉ በሴራ በተካኑ ቡድኖች ተነጥቆና እኛ እና እነሱ ወደሚል የለየለት የገዢ መደብ ስነ ልቦና ተቀይሮ ዜጎች በአስተሳሰባቸው ብቻ ሳይሆን በማንነታቸው ጭምር ላልተገባ መገፋት፣ መከራና ስቃይ እንዲዳረጉ ሆነዋል።
በሰማዕታት ታሪክ ላይ ራሱን የገነባው ይህ ቡድን የድል ማግስት ስካሩ ላለፉት 27 ዓመታት ሳይለቀው በስካር አንጎበር ውስጥ ሆኖ እራሱን የሁሉ ነገር አልፋና ኦሜጋ አድርጎ ሀገርና ህዝብን ብዙ ዋጋ አስከፍሏል። ዜጎች በገዛ ሀገራቸው የዜግነት ክብር ሳይኖራቸው እንደ ሰው ማሰባቸው ብቻ ወንጀል ሆኖ በሰማዕታት ደም ተስፋ የተደረገው እውነታ ቅዠት እስኪሆን ይህ ቡድን በአደባባዮች ሳይቀር ስለራሱ ትልቅነት ለራሱ እየሰበከና ስብከቱ በፈጠረለት ሞቅታ በእብሪት ላይ እብሪት እየጨመረ በመጨረሻው በልብስ መስቀያ ገመድና በከፍተኛ የሀይል ተሸካሚ የኤሌክትሪክ ገመድ መካከል ያለውን ልዩነት ማስተዋል ተስኖት በራሱ ላይ የከፋ ሞት ፈርዶ እንደሀገሩ ባህል ለአልቃሽ የማይመች ሞት ለመሞት ተገድዷል!
አዲስ ዘመን ጥር 5 ቀን 2013 ዓ.ም