ፕሮፌሰር በላይ ወልደየስ ይባላሉ። አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉ ሲሆን፤ ትምህርታቸውን በንጉሱ ጊዜ በነበረው ሥርዓተ ትምህርት በየኔታ እግር ሥር ቁጭ ብለው ዳዊት በመድገም ጀምረው የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በመንግሥት ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የዕድሜ ልክ ሙያ የሆናቸውን ትምህርት የጀመሩት በባህርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት ሲሆን፤ በዚያም በከፍተኛ ማዕረግ በኢንዱስትሪያል ኬሚስትሪ በ1964 ዓ.ም አጠናቀው፤ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ የኢንስቲትዩቱን የዓመቱ ሽልማት ተሸልመዋል።
ከዚያም ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ የትምህርት ክፍል በመግባት ትምህርታቸውን ለመቀጠል ቢያስቡም፤ በዚያን ዘመን በነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ፤ ቀጥሎም የዕድገት በህብረት ዘመቻ ስለነበር ሊሳካላቸው ባለመቻሉና ትምህርት የመማሪያ ዕድሜያቸው እያለፈ መምጣቱን በመረዳት፤ መንግስት በውጭ ሀገር ኢትዮጵያዊያንን ለማስተማር፤ ከፖላንድ መንግስት ያገኘውን የነፃ ዕድል ትምህርት በፈተና ተወዳድረው በማሸነፍ ወደዚያ በመሄድ ከሃገሪቱ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ማዕረግ በኬሚካል ምህንድስና ጨርሰው ወደ ሀገራቸው በመመለስ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ተቀጠሩ።
ዩኒቨርሲቲውም፤ የመምህራን አቅም ለማሳደግ ባወጣው መርሐ ግብር መሰረት በወቅቱ አቶ በላይ የአሁኑ ፕሮፌሰር በላይ ወልደየስ ወደ ምዕራብ ጀርመን ለሰባት ዓመታት ልኮ በማስተማር በሦስተኛ ዲግሪና፤ ለመምህራን በተዘጋጀ የድህረ ምረቃ መርሐ ግብር አቅማቸውን እንዲገነቡ አስችሏቸዋል። በዩኒቨርሲቲውም ከ40 በላይ የጥናት ጽሑፎችን በዓለም አቀፍ ተቀባይነት ባላቸው መፅሔቶች እንዲታተሙ በማድረግ ለብዙ የዓለም ክፍል ተመራማሪዎች ማጣቀሻ እየሆኑ ይገኛሉ።
በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ከመምህርነት እስከ ሙሉ ፕሮፌሰርነት የደረሱ ሲሆን፤ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው ያዘጋጀውን የመምህራን ማነቃቂያ ሽልማትና ዕውቅና በሙሉ ከመውሰዳቸውም በላይ፤ በታወቁ ዩኒቨርሲቲዎች በሥራቸው ብልጫ ላገኙ መምህራንና ተመራማሪዎች (Distinguished) ዕውቅና የሚሰጠውን አዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲም በመጀመር፤ ፕሮፌሰር በላይ ዩኒቨርሲቲው ያወጣውን መስፈርት በግምገማ ስላሟሉ የመሪ ፕሮፌሰር ማዕረግ በማግኘት፤ በአሁኑ ጊዜ በዩኒቨርሲቲውም ሆነ በሀገሪቱ በዚህ ማዕረግ ብቸኛው አድርጓቸዋል። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በአገሪቱ አነጋጋሪ ሆነው ባለፉና በአሁኑ ወቅትም የትኩረት ስበት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ፕሮፌሰር በላይ ወልደየስን ቃለመጠይቅ አድርጎ በዚህ መልክ ከትቦ አቅርቦላችኋል።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በኬሚካል ምህንድስና ብቸኛው ሙሉ ፕሮፌሰር እንደሆኑ ነግረውኛል። ከግለሰባዊ ጥረት እንነሳና ለሀገሪቷ ምን ያክል አገለገልገኩ ብለው ያስባሉ?
ፕሮፌሰር በላይ፡– በትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች ትምህርቴን በማጠናቀቄ፤ ባደጉት ሀገራት ሠርቶ የመኖር ዕድል እየነበረኝ ሀገሬን ላገልግል ብዬ በምርጫ ነው እዚህ የኖርኩት። እኔ እዚህ ባልመጣ ኖሮ፤ በተለይ በመጀመሪያው ዓመታት፤ የውጭ ሀገር ተወላጅ እኔ የምሠራውን በዶላር እየተከፈለው ይሠራ ነበር። ስለዚህ እኔ እዚህ መምጣቴና መሥራቴ፤ ይሄንን ወጪ አስቀርቻለሁ። እኔ በሦስት አቅጣጫ ተሰማርቼ ሀገሬን አገልግያለሁ ብዬ አምናለሁ።
አንደኛው ማስተማር ሲሆን፤ ላለፉት 40 ዓመታት በቅድመ ምረቃ፤ በድህረ ምረቃ (በሁለተኛ እና በሶስተኛ)፤ በሺህዎች በማስተማርና በማስመረቅ፤ ለሀገሪቱ በኬሚካል ምህንድስና የሰው ሃይል አቅም ግንባታ በማፍራት፤ በተቋም ግንባታ በኩል በከፍተኛ ደረጃ ከምጠቅሳቸው፤ የኬሚካል ምህንድስና ትምህርት ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ የውጭ ሀገር ተወላጅ ጋራ የመሠረትን ሲሆን፤ ይህም የትምህርት ክፍል አድጎ ከመጀመሪያ እስከ ሶስተኛ ዲግሪ በማስተማር ላይ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት
በአገሪቱ በ13 ዩኒቨርሲቲዎች የኬሚካል ምህንድስና ትምህርት ለመስጠት የትምህርት ክፍሉ እርሾ ከመሆኑም በላይ ለእነዚህ ዩኒቨርሲቲዎች መምህራን የሚሆኑትን በማዘጋጀት ላይ እንገኛለን።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ ላለፉት 30 ዓመታት በትምህርት ክፍል ኃላፊነት፤ በፋኩልቲ ዲንነት፤ በሴኔት አባልነት እና ልዩ ልዩ ኮሚቴዎች በመሥራት በአጠቃላይ በትምህርት ተቋማት ግንባታ አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ።
በሁለተኛ በምርምር ሥራ በተለይ ኬሚካል ኢንዱስትሪን ለማስፋፋት እንደ አዳሚ ቱሉ ፀረ ተባይ ማጥፊያ፣ የሰልፈሪክ አሲድ፣ የኮሰቲክ ሶዳ፣ የህንፃ ግብዓቶች ወዘተ ፋብሪካዎች የአዋጭነት ጥናት በማጥናት እንዲቋቋሙ ሠርቻለሁ። በማማከር በኩል ከ10 በላይ የመንግስት እና የግል መሥሪያ ቤቶች በሥራ ቦርድ አመራርነት የቴክኒኩን ክፍል በማጠናከር አገልግያለሁ።
አዲስ ዘመን፡– ሰፊ የሥራ ልምድ እንዳካበቱና እና ጥረት እንዳደረጉ መረዳት ይቻላል። የአገሪቱን ዕድገትና የእርስዎን እርካታስ?
ፕሮፌሰር በላይ፡– የመርካት ነገር በግል ስመለከተው፤ በምገኝበት መሥሪያ ቤት ከረዳት አስተማሪነት ተነስቼ ሙሉ ፕሮፌሰርነት መድረስ፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያሉትን ደረጃዎችና ሽልማቶች ወስጄያለሁ። በዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ለበቁ መምህራን የሚሰጠውን የመሪ (Distinguished) ማዕረግ ዩኒቨርሲቲያችን መስጠት ሲጀምር፤ ዩኒቨርሲቲው ሥራዎቼን አስገምግሞ፤ አጥጋቢ ሆኖ ስላገኘው፤ ሰጥቶኛል።
እንግዲህ አንድ ሰው፤ በሥራው ቦታ መድረስ የሚገባው ደረጃ ከደረሰ የማይረካ ስለሌለ፤ በዚህ ሁኔታ ረክቻለሁ ልል እችላለሁ። በሌላ በኩል ግን፤ ባለኝ ዕውቀት የበለጠ ውጤት ለሀገሪቷ ማምጣት ስችል አለማምጣቴ ይቆጨኛል። ይሄም የመጣው ከእኔ ስንፍና ሳይሆን፤ ሀገሪቷ ለተማረ ሰውና ለቴክኖሎጂ ከምትሰጠው ግምት ጋር የተያያዘም ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በእውቀትዎ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም አመርቂ ሥራ እንዳይሰሩ ምን መሰናክል ነበር?
ፕሮፌሰር በላይ፡– በአጠቃላይ በዓለም ላይ አሉ ከተባሉ ምህራን የማይተናነሱ ዕውቀት ያላቸው ምህራኖች በኢትዮጵያ አሉ። ይሄ ሆኖ እያለ፤ የኋላቀርነት አባዜ ተጠናውቶን ይሆናል፤ ምሁሮቻችንን በሚገባው አንጠቀምባቸውም። የሚሰማቸው አካልም የለም። ለመሰማት መንግስት ለሚያራምደው ፖለቲካ ታማኝ ሁን ይባላል።
ብዙ ጊዜ የተማረን ሰው መንግስት እንደ ባላንጣ አድርጎ ይቆጥረዋል። ካድሬዎች መምህራንን ለማክበር ሲቸገሩ ይስተዋላሉ። በዚህም ምክንያት በህዝቡ ዘንድ ለትምህርትም ሆነ ለተማረ ሰው ዋጋ አይሠጥም። ‹‹ከሶስተኛ ዲግሪ አንድ ሱቅ ያለው ይሻላል›› ተብሎ ይዜማል። በሌላ በኩል ህብረተሰቡ በሚጠበቀው ልክ ቴክኖሎጂን አያደንቅም። ጥቅም ላይ ያሉት ቴክኖሎጂዎች፤ ስንት ምሁራን ለፍተውባቸው አሻሽለው እንዳመጡዋቸው አይገነዘብም።
አንድ ምሳሌ በእኛ በቴክኖሎጂ ፋኩልቲ በዕድገት በህብረት ዘመቻ ጊዜ የተፈጠረው ትዝ ይለኛል። አንድ መምህር ሬዲዮ ሰራ። በዚያን ጊዜ ሬዲዮ ያላቸው በሀገሪቱ ጥቂት ሰዎች ናቸው። ለሠፊው ህዝብ ይሄው ሬዲዮ በብዛት ተመርቶ በቀላል ዋጋ እንዲያገኝ፤ ፋኩልቲው ለመንግስት እንዲመረት ጥያቄ አቀረበ። መንግስትም ፈቃድ ለመስጠት እንዲገመገም ኮሚቴ አዋቀረ። ኮሚቴውም፤ ከጃፓን ሬዲዮ መስፈርት ጋር አወዳድሮ ቴክኖሎጂው ዓለም የደረሰበት ደረጃ ላይ ስላልደረሰ ባይመረት ብሎ ሃሳብ በማቅረቡ፤ እዚያው ላይ ቆመ። የሚገርመው በሀገሪቷ በዚያን ጊዜ የነበሩት፤ ሁለት የሬዲዮ ጣቢያ ናቸው።
ከእነዚህ ጣቢያዎች የሚወጡትን መርሐ ግብሮች፤ ሬዲዮው ሊያሰማ ይችላል። አብዛኛው ህዝቡም የውጭ ሀገር ሬዲዮ አይሰማም። መንግስት ግን ዓለም አቀፍ ጣቢያን ሊስብ አይችልም ብሎ ፋብሪካ አላቋቁምም ብሎ ከማገዱም በላይ የሬዲዮ ቴክኖሎጂ እንዳይጀመር አደረገ።
በነገራችን ላይ ጃፓን አሁን ላለችበት የሬዲዮ ቴክኖሎጂ የደረሰችው፤ ያ! መምህር እንዳቀረበው ዓይነት ሬዲዮ በመስራት ተነስታ ነው። በየጊዜው በጥናትና ምርምር ብዙ ለፍታና ዋጋ ከፍላ አሁን ከደረሰችበት የሬዲዮ ቴክኖሎጂ ደርሳለች።
እንግዲህ የተማረን ሰው የሚገባውን ሥፍራ አለመስጠታችን፤ ቴክኖሎጂን እንዳለ መቀበላችን፤ ለምርምርና ስርፀት እንቅፋት በመሆን፤ ሀገራችንን ላናሳድግ ችለናል። የተማሩ ሰዎች የሚያቀርቡትን ጥናት የመንግስት ሹመኞች ለመቀበል ብዙም ጉጉት አያሳዩም። በዚህም የተማሩ ሰዎች የሚያወጡዋቸው ጥናቶች በየመንግስት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በመንደርደሪያ ላይ ተቀምጠዋል። የእኔም ብዙ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ልማት ጥናቶች የዚሁ ሰለባ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡– ‹‹የእኔም ብዙ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ልማት ጥናቶች የዚሁ ሰለባ ናቸው›› ብለዋል ምሳሌ ቢሰጡኝ?
ፕሮፌሰር በላይ፡– ኢትዮጵያ ከፍተኛ ሸንኮራ ተክለን ለማልማት የሚያስችል የአየር ጠባይና ሰፋፊ ተፋሰሶች ያሉባት ሀገር ናት። ካላት ምቹ ሁኔታ በጣም ባነሰ ሁኔታ ከ50 ዓመት ጀምሮ ስኳርን ከሸንኮራ ተክል እያመረተች ትገኛለች።
እኛ እያመረትን ያለነው በዋናነት ስኳር ሲሆን፤ በሁለት ፋብሪካዎች በጣም በጥቂቱ ለተሽከርካሪ ነዳጅ የሚሆነው ‹‹ኤታኖል›› ይመረታል። ይሄ አሠራራችን በጣም ወደ ኋላ የቀር ነው። ከ50 ዓመት በፊት ለኢትዮጵያ ስኳር ዋና ተፈላጊ ምርት ነበር። እንዲያውም ህዝቡ ስኳር እንዲለምድ በንጉሱ ጊዜ ትምህርት ቤት በነፃ ይሰጠን ነበር። አሁንም የስኳር ምርት እጥረት እንዳለ ቢታወቅም፤ ይህንኑ እያመረትን፤ የሸንኮራ ተክልን በባዮሪፋይነሪ ወደ ተለያዩ ምርቶች በመቀየር ከፍተኛ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ልንሆን እንችላለን።
እንደ ብራዚል፣ ህንድ፣ ኩባ፣ ታይላንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቻይና፣ አሜሪካ ያሉ አገሮች ቴክኖሎጂያቸውን በማዘመን በባዮሪፋይነሪ ወደ ተለያዩ ምርቶች በመቀየር ከሸንኮራ ተክል ጥሬ ዕቃ ኢኮኖሚያቸውን አሳድገውበታል።
ለምሳሌ ብራዚልን ብንወስድ ከሸንኮራ ተክል በመነሳት ኤታኖልን ከ500 በላይ ፋብሪካዎች ውስጥ በማምረት ከ50 በመቶ በላይ የሆኑትን መኪኖቻቸውን ወይንም በአገሪቱ ውስጥ 40 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን ሙሉ በሙሉ ቤንዚንን በመተካት በኤታኖል እንዲነዱ አድርገዋል።
ህንድ በተመሳሳይ መንገድ ምርቶቹን ከመጠቀሟም በላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሸንኮራ ተክል እርሻና፣ በዚሁ ኢንዱስትሪ አሰልፋለች። ኢትዮጵያም ለማደግ ከፈለገች፤ ወደፊት መነሻ የሚሆናት ትልቁ ኢንዱስትሪ ሆኖ ለሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሪያ የሚሆነው የሸንኮራ ተክልን በባዮሪፋይነሪ ወደ ተለያዩ ምርቶች መቀየር ነው።
እንግዲህ ያሉትን የስኳር ኢንዱስትሪዎች ወደ ዘመናዊነት በመቀየር የተለያዩ ምርቶችን ለማምረት በእኔ የሚመሩ ታዋቂ መሃንዲሶች እና ሳይንቲስቶች በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ፣ በፖሊሲ ጥናት ምርምር ኢንስቲትዩትና በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን አስጠኚነት ወደ አራት ዓመት የሚጠጋ ጥናት አጠናን። በዚህም ከስኳር በተጨማሪ፣ በአገራችን በከፍተኛ ደረጃ ተፈላጊ የሆኑ እንደ ኤታኖል፣ ፐልፕ (ወረቀት)፣ ቅንጣጢት ቦርድ (Cheap wood)፣ ማዳበሪያ፣ የእንስሳት መኖ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ወዘተ በስኳር ኢንዱስትሪዎች መመረት እንደሚችሉ አሳየን።
ይህንንም ጥናት ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከነካቢኔያቸው፣ ለሁለት ክልሎች ማለትም ለትግራይ እና ለደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ፕሬዚዳንቶችና ካቢኔዎቻቸው፣ ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች አመራሮች፣ ለስኳር ኢንዱስትሪዎች ኃላፊዎች፣ ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት፣ ወዘተ አቅርበን ነበር። ነገር ግን በመሃል ለውጥ ስለመጣ እንደ ሌሎቹ ፕሮጀክቶች መደርደሪያ ላይ ተቀምጧል።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ የስኳር ኢንዱስትሪ ስኬትና የበለጠ ኢንቨስት ይደረግ ብለው ይመክራሉ። አገሪቱ በዚህ መስክ ኪሣራ ከመግባቷም በላይ ለዕለታዊ ፍጆታዋ እንኳን ስኳር ከውጭ አገር ታስገባለች። እነዚህ ነገሮች እርስ በእርስ አይቃረኑም?
ፕሮፌሰር በላይ፡– ያለመታደል ሆኖ መንግስትና እኛ ባለመናበባችን፤ የታሰበው በቀድሞ ዓይነት አሠራር ጥቂት ምርቶችን ለማምረት ነበር። ይህም ቢሆን በአግባቡ አልተከናወነም፤ተዘረፈ። የሚገርመው በወቅቱ የነበሩት የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ እንዳወቅ፤ ሜቴክ ገንዘቡን አጠፋው እያሉ አቤቱታ ሲያቀርቡ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጆሮ አልሰጡትም ነበር። አሁን ‹‹የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም።››
መንግስት የህዝብ ሃብት የበሉትን ፈልጎ ያስከፍላቸው፤ ዕዳውንም (write off) አድርጎ ልማቱ መቀጠል አለበት። በቀጣይ መሆን ያለበት እንደ ቀድሞው ስኳር ማምረት ብቻ ሳይሆን፤ ከሸንኮራ ተክል በመነሳት በባዮሪፋይነሪ ወደ ተለያዩ ምርቶች መቀየር ያስፈልጋል። ሜቴክ ገንዘቡን በሰረቀ ልማቱ መቅረት የለበትም የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡– ከስኳር ኮርፖሬሽን በተጨማሪ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ላይ እንደሰሩ ይታወቃል። ይህም ስኬት የራቀው ነበር። ለምን ይሆን?
ፕሮፌሰር በላይ፡– የሀገራችን ህዝብ 80 በመቶ በላይ የሚተዳደረው በግብርና ነው። ግብርናው ደግሞ ከዓመት ወደ ዓመት ማዳበሪያ ፍጆታው እየጨመረ ነው። ማዳበሪያን ከቢሊዮን ዶላር በላይ እየከፈልን ከውጭ ነው የምናስመጣው። ሀገራችን ደግሞ በብዛት የውጭ ምንዛሪ እጥረት ይፈታተናታል። ይህንን ችግር ለማቃለል ማዳበሪያን በሀገራችን ለማምረት ካለፉት 25 ዓመት ጀምሮ ጥረት ተደርጓል። እኔም በብዙ መንገድ ደክሜበታለሁ። የሀገሪቱ ዕድል ወይም የእኔ ደረቅ ዕድል ሆኖ እስከ አሁን ድረስ ከጫፍ ደረሰ ሊቋቋም ነው ሲባል መልሶ ጥሬ እየሆነ ተቸግሬአለሁ።
አዲስ ዘመን፡– የ25 ዓመታት ጥረቶችን ለምን ወደ ውጤት መቀየር አልተቻለም?
ፕሮፌሰር በላይ፡– ነገሩ ብዙ ነው። ከ25 ዓመት በፊት ይመስለኛል፤ አቶ አሰፋ አብርሀ በሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት ልማት ኤጀንሲ ኃላፊ፣ አንድ በምክትል ሚኒስትርና በኮሚሽነሮች የተዋቀረ ግብረ ኃይል፤ ከካሉብ ጋዝ ማዳበሪያ ለማምረት፤ ከቻይና ኩባንያ የቀረበውን ሰነድ ገምግሞ ለመንግስት ለውሳኔ እንዲያቀርብ ይሰይማሉ። ይህም ግብረ ኃይል ከቴክኒክ ኮሚቴው አንዱን ክፍል እንድመራ ለእኔ ይሰጠኛል። የቻይናው ኩባንያ ያቀረበው የአዋጭነት ጥናት ሰነድ ይዘቱ ከካሉብ ጋዝ ጥሬ እቃ ተነስቶ ዩሪያ ማዳበሪያ ለማምረት የሚጠቀመውን የቴክኖሎጂ ንድፍ እና ለዚህም ቴክኖሎጂ የሚሆን መሣሪያ እና የባንክ ገንዘብ እራሱ እንደሚያቀርብ ወዘተ የሚያካትት ነበር።
የክረምት እረፍት ጊዜ በመሆኑ ለሦስት ወር በየቀኑ እንደ መደበኛ ሥራ አምስተኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ በሚገኘው፤ የካሉብ ጋዝ ጽሐፈት ቤት በመመላለስ የቀረበው ሰነድ ላይ አንዳንድ ነገሮችን በመጨመር አዳብረን ማዳበሪያው እንዲመረት በመስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ለመንግሥት አቀረብን።
መንግሥት ከቻይና ኩባንያው ጋራ ውል ተዋውሎ ወደ ሥራ ይገባል ሲባል የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ። እስከ ዛሬ እንቆቅልሽ ሆኖ መልስ ያላገኘሁበት ሁኔታ ተፈፀመ። እኔ እንደሰማሁት፤ አንድ በኒውዮርክና በጆሀንስበርግ አድራሻ ያለው የአሜሪካ አማካሪ ቡድን፤ ለኢትዮጵያ መንግስት ከካሉብ ጋዝ በመነሳት ማዳበሪያ ለማምረት እንደሚፈልግ፤ ማምረት ብቻ ሳይሆን፤ የአካባቢውን ህብረተሰብ በልማት እንደሚያካፍል ወዘተ የሚል ሰነድ ያቀርባል። መንግስት ይሄንን ሰነድ ሲያይ፤ ቻይናዎቹ ያቀረቡትን ይተውና፤ ወደ አሜሪካ ኩባንያ ፊቱን ያዞራል። ቻይናዎቹ በዚህ ተናደው፤ ፕሮጀክቱን ይተውታል። የኢትዮጵያ መንግስትም የአሜሪካውን ኩባንያ አድራሻ በኒውዮርክና በጆሃንስበርግ ቢያፈላልግ ሊያገኘው አልቻለም።
ይህ እስከዛሬም ለእኔ እንቆቅልሽ ሆኖ ነው ያለው። ብዙ ነገሮች በዚህ ሀገር ላይ ለእኔ ሚስጥር የሆኑ የማላውቃቸው አሉ። ይሄም አንዱ በህይወቴ ላውቃቸው ከምፈልጋቸው ሚስጢሮች አንዱ ነው። መቼስ ይሄ ነገር ምንድነው ብለን መወያየታችን አልቀረም፤ በመላምት ግማሾቻችን የሲአይኤ፤ ሌሎቻችን የኤርትሪያ መንግስት፤ ጥቂቶች ደግሞ፤ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ድርጅት ወዘተ ሴራ ሥራ ሊሆን ይችላል ነበር መልሱ።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ ሜቴክ እና ሌሎች ተቋማትን ሲያወዛግብና መንግስትን ለከፍተኛ ኪሣራ የዳረገው ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ላይም የእርስዎ አስተዋፅኦ ነበረበት። ይህስ እንዴት ወደ ችግር ገባ?
ፕሮፌሰር በላይ፡– ከላይ እንደጠቀስኩት ብዙ የኢንዱስትሪዎች ልማት ጥናቶች በመንግስት መስሪያ ቤቶች መንደርደሪያ ላይ ተቀምጠዋል። ህይወቴን በሙሉ ከሚያናድደኝ አንዱ የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ነው። ፋብሪካውን ለመትከል ከ20 ዓመት በላይ በጥናት አሳልፈናል።
ከካሉብ ጋዝ ማዳበሪያ ለማምረት አለመቻሉ በእንቆቅልሽ ከዘጋን በኋላ፤ ኬሚካል መሃንዲሶች የሆንን የቀድሞ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢንጂነር አሥራት ቡልቡላ፣ የሰልፈሪክ አሲድና የአልሙኒየም ሰልፌት ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሌሌሳ ዳባ እና እኔ ሆነን የለፋንበት የካሉብ ጋዝ ፕሮጀከት ቢቀርም ከድንጋይ ከሰል ለማምረት ጥናት እንጀምር ብለን ወሰንን። ጥናቱ ተቋማዊ እንዲሆን፤ ኢንጂነር አስራት መሥሪያ ቤት ኃላፊነት ወስዶ አንድ የጥናት ተቋም እንዲመሠርት አደረግን።
የድንጋይ ከሰል ፍለጋ በተለያዩ ቦታዎች በቻይናዎች አስቆፍረን ያዩ ላይ የተሻለ ክምችት በመኖሩ በዚህ ቦታ ፋብሪካ እንዲቋቋም ወሰንን። ያዩ ላይ የሚገኘው የድንጋይ ከሰል ይዘት ማወቅ ለፋብሪካ ግንባታ አስፈላጊ በመሆኑ ወደ ቻይና ናሙና ልከን እንዲታወቅ አደረግን።
ከያዩ ድንጋይ ከሰል፤ ዩሪያና ተጓዳኝ ምርቶች ለማምረት እንደሚቻል ካወቅን በኋላ፤ የአዋጭነት ጥናት እንዲያጠናልን ለቻይናው ኮምፕላንት ኩባንያ ሰጠነው። ጥናቱን በየጊዜው በእኔ ሰብሳቢነት የሚገመግምልን በሀገር ውስጥ ባለሙያ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ፣ የኢኮኖሚ እና የሳይንስ ፋኩልቲ መምህራን፣ ከማዕድንና ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለሙያዎች እንዲሳተፉበት አደረግን። ቋሚ ጽሕፈት ቤት በባለሙያተኞች በማቋቋም ሥራውን እንዲመሩት አደረግን። እኔ አባል የሆንኩበት የቦርድ አመራር ሰየምን።
በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የሚመራ አንድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በየሦስት ወር ጥናቱን የሚገመግም ክፍል ተቋቋመ። በአንድ ስብሰባ ላይ፤ የኮምፕላንት የመጨረሻ ጥናት ሰነድ ሳይቀርብ፤ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የቀረበው ዋጋ ከፍተኛ ስለሆነ፤ ይሄንን ፋብሪካ አናቋቁምም የሚል አስደንጋጭ ውሳኔ ሰጡን። እኔም ለማስረዳት ብሞክር ሊሰሙኝ አልፈለጉም። ለጥናቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበትን እንዲሁ አስረክበን ወደ ቤታችን ተመለስን።
ከወራት በኋላ አንድ ቀን ማታ ዜና ስከታተል፤ ሜቴክ የያዩን ፋብሪካ ለመገንባት ከመንግስት ጋራ መዋዋሉን ሰማሁ። ከሣምንት በኋላ በዚያን ጊዜ የማዕድን ሚኒስቴር የሆኑት አቶ አለማየሁ ተገኑ ቦርዱን ጠርተው፤ ውሉን እንድናፀድቅና ሦስት ቢሊዮን ብር ለሜቴክ እንድንከፍል እንድናዝ ጠየቁን። እኛ ውሉን አልተዋዋልን፤ የምንከፍልበት ምክንያት የለንም። እኔ እንዲያውም ሜቴክ ይሄንን ለመሥራት አቅም ስለሌለው፤ እንዴት ተሰጠው ብዬ አጉረመረምኩ። መንግስት በራሱ ፍቃድ ከንግድ ባንክ ሙገር ሲሚንቶን ባለዕዳ አድርጎ ተበድሮ ከፈለው። በሦስት ዓመት ገንብቼ አስረክባለሁ ያለው ምኑንም ሊይዘው አልቻለም።
ሜቴክ እንደማይሠራው ላገኘሁት ከፍተኛ ባለሥልጣን መጮሄን ቀጠልኩ። ሁሉም ባለስልጣኖች እኔ በማቀርበው ሃሳብ እንደሚስማሙ ይገልፁልኝና ሄደው ግን ሜቴክን በመፍራት አይናገሩም። እንደዚሁ ስንጨቃጨቅ በግድ ገንዘብ ክፈሉኝ ሲል፤ ሙገርም እያለቀሰ ከንግድ ባንክ እያወጣ ሲከፍል፤ ንግድ ባንክም እዳውን እየቆለለ ሲሄድ እኔንም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰዎች ትምክህተኞች እና ጠባቦች ናችሁ እየተባልኩ፤ ጓደኞቼን በሌሉበት ሳሰድብ ቆይቼ ለውጡ መጣ።
በመጨረሻ አካባቢ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ልማቶች ቋሚ ኮሚቴ፤ በፕሮጀክቱ ላይ ለመወያየት የስራ አመራር ቦርዱና ሥራ አስፈጻሚው እንዲገኙ የሚል ትዕዛዝ ያስተላልፋል። በቦርዱ ስብሰባ ላይ ይሄ ቀርቦ፤ ሰብሳቢው አንተ ሂድ ብሎ እኔን ጠየቀኝ። እኔም በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እላለሁ ብዬ መለስኩ ሁሉም አንተ ነህ የቴክኒክ ጉዳዩን ልታስረዳ የምትችለው ብለው እኔ እንድሄድ በአንድ ላይ ወሰኑብኝ።
እኔም በተባልኩት ቀን ፓርላማ ቀረብሁ። የቋሚው ተጠሪ ሰብሳቢ፤ በሥራ ቦርድ አባልነቴ ችግሩን እያወቁ ጥያቄ ለእኔ ማሽጎድጎድ ጀመሩ። ከጥያቄዎቹም መሀከል ሜቴክ መቼ ነው የሚጨርሰው፣ ሜቴክ ድንጋይ ከሰሉን እያወጣ ሲወስድ እናንተ ምን ትሠሩ ነበር የሚሉት ይገኙበታል።
የእኔም መልስ ‹‹ሜቴክ መቼ እንደሚጨርስ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን እግዚአብሄር ማወቁን እጠራጠራለሁ››፣ ‹‹ሜቴክ ያዩ የሄደው ፋብሪካ እንዲገነባ ነው እንጂ ከሰል እንዲሸጥ አይደለም››፣ ከሰሉ እኮ ለ30 ዓመት ማዳበሪያ ፋብሪካ ማምረቻ ብቁ እንደሚሆን ታስቦ ነው ግንባታው፤ የተጀመረው። አሁን ከሰሉ ተቸብችቦ መሀከል ላይ ለፋብሪካው ቢታጣ ማነው ተጠያቂው፤ ይሄ ሥራ ወንጀል ነው። ብዬ መለስኩ። ሰብሳቢው ከአንድ ምክር ቤት አባል የማይጠበቅ ንግግር አደረጉ። እኔም መልስ ለመስጠት እጄን ባወጣ በመንፈግ፤ ስብሰባውን አቋረጡ። በ15 ቀናት ውስጥ ከመንግስት ልማት ሚኒስቴር፤ ለ20 ዓመት የለፋሁበትን ፕሮጀከት ሳላስመርቅ ከቦርድ አባልነቴ ተነሳሁ። ሜቴክም ጊዜው ደርሶ፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታውን አውድሞ ሄደ።
አዲስ ዘመን፡– በዘርፉ ላይ እንደሚሰራ ምሁር እና በጉዳዩ ተሳትፎ እንደነበረው ሰው አሁን የያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ ተስፋ ምን መሆን አለበት ይላሉ?
ፕሮፌሰር በላይ፡– በአሁኑ ወቅት ስለ ፕሮጀክቱ ብዙ መረጃ የለኝም። እንደምሰማው ሜቴክ የወሰደው ገንዘብ ብዙ ስለሆነ፣ ፋብሪካው አዋጭ ስላይደለ አይቋቋም የሚል ነው። ይሄ ምክንያት ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው። ፋብሪካው ምንም አላጠፋም። ያጠፋው ሜቴከ ነው። በሜቴክ ምክንያት የጠፋውን ገንዘብ፤ ከሜቴክ መፈለግ ነው። ለጊዜው መንግሥት ይህንን ገንዘብ እንደ ተቃጠለ ቆጥሮ (write off) ምናልባት የተረፈ ገንዘብ ካለ በማስላት እንደገና አዲስ ገንዘብ መድቦ መቀጠል ነው። ማዳበሪያ ለኢትዮጵያ ከአስፈላጊነቱ በተጨማሪ እስትራቴጂክ ሃብት ነው።
አዲስ ዘመን፡– እርስዎ በኬሚካል ምህንድስና መምህር፣ ተመራማሪ ብሎም የፕሮጀክቶች አማካሪና የቦርድ አባል ሆነው አገልግለዋል። ከዚህ ልምድና እውቀት በመነሳት የኢትዮጵያ ኬሚካል አጠቃቀምና አወጋገድ ምን ይመስላል?
ፕሮፌሰር በላይ፡– በዓለማችን ላይ የምንጠቀማቸው ቁሶች በሙሉ ማለት ይቻላል ከኬሚካል ጋር ንክኪ አላቸው። ስለዚህ ይህ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈልግ ነው። ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ኬሚካል ትጠቀማለች። ለአብነት ፀረ አረምና ፀረ ተባይ፣ የአፈር ማዳበሪያና ሌሎች ኬሚካሎችን በሰፊው ትጠቀማለች። ይሁንና ይህ በጥንቃቄ ካልተያዘ እጅግ ከፍተኛ ኪሣራ ሊያደርስ ይችላል።
በቅርቡ ቤሩት የደረሰውን የኬሚካል ፍንዳታ የከተማዋን አንድ ሦስተኛ ከጥቅም ውጭ አድርጎታል። በእንግሊዘም በተመሳሳይ ከፍተኛ ቃጠሎ ያስነሳ ሲሆን ትልቅ ግምት የሚሰጠው ንብረት አውድሟል። መሰል ችግሮች በዓለማችን በርካታ ቦታዎች መጠኑ ከፍ ያለ አደጋ አድርሰዋል።
በሰለጠኑት አገራት የትኛው ኬሚካል መቼ እንደተመረተ፣ ለየትኛ ግልጋሎት እንደሚውል፣ የትኛው ስፍራ እንደሚገኝ፣ አገልግሎቱ መቼ እንደሚያበቃ፣ ኬሚካሉን የሚያስወግደው አካል ማን እንደሆነ በሥርዓት ተመዝግቦ ይያዛል። ይህ በኢትዮጵያም መለመድና መተግበር አለበት። ይህ ሳይሆን ቀረጥ እየተቆረጠ ብቻ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አደጋው የከፋ ነው። በዚህ ላይ ኢትዮጵያ ብዙ ልምድ የሌላት በመሆኑ በእጅጉ ሊታሰበብትና በተቀናጀ መንገድ ሊሰራ ይገባል። በደርግ መንግስት ዘመን ከፍተኛ የሆነ ፀረ አረም ኬሚካል ተከማችቶ ነበር። ይህን በአገር ውስጥ ማስወገድ ስላልተቻለ ወደ ውጭ አገር ተጓጉዞ ለማስወገድ መገደዳችን አስታውሳለሁ። አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ አቅም ሊወገዱ የማይችሉ ኬሚካሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። በእነዚህ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግም ይገባል።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡኝ ሙያዊ ማብራሪያና ለነበረን ቆይታ እያመሰገንኩ ለኢትዮጵያ መበልፀግ በቀጣይ መንግስትና ምሁራን እንዴት መስራት አለባቸው ይላሉ?
ፕሮፌሰር በላይ፡– መንግስት ካልኖረ ሀገር ልትኖር አትችልም። መንግስትም ምቹ ሀገር ለመፍጠር ምሁራን ያስፈልጉታል። ስለዚህ ሁሉም ተከባብረው መኖር አለባቸው። በመንግስት ውስጥ ያሉ አንዳንድ አስፈፃሚዎች፤ የትምህርት ዝግጅታቸው አናሳ በመሆኑ የተማሩ ሰዎችን ሊያቀርቡ አይፈልጉም። ቢቻላቸውም ከህብረተሰቡ ለማራቅ፤ የእነርሱ ትምህርት ወረቀት ብቻ ነው እያሉ ህብረተሰቡ እንዳያከብረው የሀሰት የስም ማጥፋት በማድረግ፤ ብዙ ምሁራን ለሀገራቸው ዕድገት ሊሰጡ የሚችሉትን እርግፍ አድርገው ለመኖር ብቻ መሥሪያ ቤት ይሄዳሉ።
ምሁራን የሚገባቸውን ቦታ ማግኘት አለባቸው። በሙያቸው መንግስት ጣልቃ መግባት የለበትም። መንግስትና ምሁራን በአንድ ላይ ሆነው ሀገሪቷን መገንባት አለባቸው። ‹‹ገለልተኛ የኢኮኖሚ ምሁራን አማካሪ እንደተቋቋመው የኢንዱስትሪና የግብርና አማካሪ ቢያቋቁም ጥሩ ውጤት ይገኝበታል›› ብዬ አምናለሁ። አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 04/2013