ሰሞኑን አንጻራዊ ሰላም ያገኘችው የድሬዳዋ ከተማ ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር ተያይዞ በተነሳው ግጭት ለቀናት ስትታመስ ቆያታለች፡፡ በዚያ ሰሞንም መንገዶች ተዘግተው፣ አንዳንድ ሱቆችም አገልግሎት መስጠት አቁመው ታይተዋል፡፡ በከተማዋ ስለሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ስለ 40/ 40/ 20 የስልጣን ክፍፍል ቀመርና ተያያዥ ጉዳዮች ከድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ጋር ያደረግነው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በድሬዳዋ ከተማ በጥምቀት በዓል ተከስቶ የነበረው ችግር ተረጋግቷል ማለት ይቻላል? መነሻውስ ምን ነበር?
አቶ ኢብራሂም፡- ያለፉት አራትና አምስት ቀናት ሙሉ ለሙሉ ድሬዳዋ ወደ ነበረችበት የሰላም ሁኔታዋ ተመልሳለች፡፡ የግጭቱ መነሻ ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡15 አካባቢ ምዕመናን ታቦት ሸኝተው ሲመለሱ በወጣቶች የተፈጠረ ጸብ የማጫር ተግባር ነው፡፡ በወቅቱ ድንጋይ ተወርውሯል፡፡ በዕለቱ ማታ ዜሮ ዘጠኝ አካባቢ ብዙ ወጣቶች ተሰብስበው ከተለያዩ አካላት የተሰባሰቡ ሰዎች ጋር የተነሳው አለመግባባት ሰፍቶ እስከ ጥር 17 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ ዘልቋል፡፡ ግጭቱ የሃይማኖት መልክ ቢኖረውም የጸጥታ ሃይሎች የገመገሙት ግን ሌላ ነው፡፡ የፖለቲካ አጀንዳ ያለው ከተማዋን የብሄር ወይም የሃይማኖት መልክ የያዘ ግጭት እንዲነሳ አስቀድሞ በማሰብ ዝግጅት ተደርጎበት በገንዘብ ጭምር ሲደገፍ የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም ከጀርባው ሁለት አካላት እንዳሉ ለመመልከት ተችሏል፡፡
አንደኛው ቀደም ሲልም ከሶማሌ ክልል ጋር የተወሰነ ግጭት ነበረ፡፡ ከቀድሞ አመራሮች ጋርም ግንኙነት የነበራቸው ሰዎች ‹‹ሄጎ›› በሚል ስያሜ አደረጃጀት ይዘው ከዚህ በፊትም ድሬዳዋ ላይ ችግር ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡ ጅግጅጋ ላይም ለተፈጠረው ቀውስ ዋና ተዋናይ የነበሩ አካላት ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት ድሬዳዋ ላይ ቅሬታ አላቸው፡፡ እነሱ አጋጣሚውን በመጠቀም ጸብ ሊያጭሩ ይችላሉ የሚል እምነት ተይዞ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ አሁን ያለው መዋቅር እኛን አይመለከተንም፣ አይወክልም በሚል ከይገባኛል ጥያቄ ጋር ተያይዞ የኢህአዴግ በተለይም የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ይህንን አስተዳደር በጋራ እንዲያስተዳድሩ ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ውክልና እንዲኖራቸው የተቀመጠ አቅጣጫ አለ፡፡ ስለዚህ ይህ ውክልና ጠብቧል፣ አንሷል እና አይመለከተንም በሚል በማህበራዊ ድረ ገጽ የተወሰኑ አካላት ርብርብ በማድረግ ረጅም ጊዜ የጥላቻ ዘመቻ ሲያደርጉ ነበረ፡፡ ይህ ውጤት አግኝቶ ከበስተጀርባው የሃይማኖት አጋጣሚን ለመነሻ በመጠቀም ለማባባስ፣ የመዋቅር ችግር በማስመሰል አጋጣሚውን በመጠቀም አጀንዳውን በመቀየር ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት ሲደረግ ነበረ፡፡ አጠቃላይ መነሻው ይሄ ነበር፡፡
ስንገመግምም ከፌዴራል አካላት መጥተው ውይይት ሲደረግም በግልጽ የተነሳው መዋቅሩ የፖለቲካ ጉዳይ እንደሆነ፣ ከማይገናኙ ነገሮች ጋር በማዛመድም ችግር እንደፈጠረባቸው በማስመሰል፣ ማህበረሰቡ የማያውቃቸውን ነገሮች ጭምር በማነሳሳት በተለይ ባለፉት ጊዜያቶች ችግር ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፣ እንቅስቃሴዎች ተገድበዋል፣ ንብረቶች ወድመዋል፣ ግለሰቦችን ለማጥቃት ኢላማ ተደርጎ ነበር፡፡ ማን እንደተኮሰው ባይታወቅም ከጸጥታ ሃይል የሞተ አለ፡፡ ከዚሁ ረብሻ ጋር ተያይዞ አንድ ህጻን ሞቷል፡፡ መልካ የሚባል ቀበሌም የሞተ ሰው አለ፡፡ ረብሻው የንግድ እንቅስቃሴንም አስተጓጉሏል፡፡ ወደ ሀረር የሚያጓጉዘውን ዋና መንገድ ለመዝጋት ጥረት ተደርጓል፡፡ የግለሰቦች ንብረት ባለ ሶስትና አራት እግር ተሽከርካሪ፣ መኖሪያ ቤቶች ጭምር ተዘርፈዋል፡፡ አሁን እየተጣራ ይገኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት 309 ሰዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ ይገኛል፡፡ እንድታሳትፏቸው በስልጠናና በምክር የሚለቀቁ፣ ለህግ የሚቀርቡም ይኖራሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- 40/40/20 በመባል የሚታወቀው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በጋራ እንዲያስተዳድሩ ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ውክልና እንዲኖራቸው የሚተገበረው የአስተዳደር መዋቅር የህገ መንግስት ድጋፍ የለውም ይባላል እንዴት ይመለከቱታል ?
አቶ ኢብራሂም፡- 40/40/20 የአስተዳደር ቀመር ህገ መንግስታዊ ማዕቀፍ ሊኖረው አይችልም፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግ በራሱ የውስጥ አሰራር አለው፡፡ አራቱ ብሄራዊ ድርጅቶች ሲከፋፈሉም በራሳቸው የውስጥ አሰራር ነው የሚሰሩት፡፡ ይህም ተመሳሳይ ነው፡፡ በራሳቸው የውስጥ ክፍፍል የይገባኛል ጥያቄ ስለነበረ በዛን ጊዜ ሁለቱ ክልሎች ኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ወደ ክልላቸው እንዲካለል አንስተውት የነበረው የይገባኛል ጥያቄ ነበረ፡፡ ውሳኔ ባለማግኘቱ ረጅም ጊዜ ተጓትቷል፡፡ እንደሚታወቀው ድሬዳዋ ህገ መንግስቱ ውስጥ የለችም፡፡ የድሬዳዋ አስተዳደር በሕገ መንግስቱ ላይ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ፌዴራል መንግስቱ አካል ሆና በሕገ መንግስታዊ መዋቅሩ እውቅና ባላገኘችበት ሁኔታ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅን ቁጥር 416/1996 ወጥቶ እንድትተዳደር ተደርጓል፡፡
በአዋጁ የራሱ አስተዳደር እንዲኖረው፣ ሁለቱ ፓርቲዎች ኦዲፓና ኢሶዴፓ በጋራ እንዲያስተዳድሩ በዋናነትም ለፌዴራል መንግስት ተጠሪ እንድትሆን በቻርተሩ ተወስኗል፡፡ በኋላም ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ራሷን ማስተዳደር ጀምራለች፡፡ የራሷ ምክር ቤት ተቋቁሞ፣ አስፈጻሚም በምክር ቤት ተሹሞ የመንግስት ሙሉ መዋቅር እንዲኖር ተደርጓል፡፡ 30፣ 40 ወይም 15 በመቶም ቢሆን የሚከፋፈሉት አራቱ ብሄራዊ ድርጅቶችና አጋር ድርጅቶች የሚከፋፈሉት በውስጥ ስምምነት ነው፡፡ ይህም 40/40/20 ውም ቢሆን ክፍፍል የሚደረገው በዚህ መልኩ ነው፡፡
አጠቃላይ 125 አካባቢ የሚሆኑት አመራሮች ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው፡፡ እስከ ወረዳ ድረስ የሚወርድ አይደለም፡፡ በወረዳ ደረጃ ያሉ ቀበሌዎች ማህበራዊ መሰረትን ባማከለ መልኩ ነው የሹመትም የአመራር ምደባም የሚሰራው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በማዕከል ያለ 125 አመራር 40/40/20 ይመለከተዋል፡፡ ለረጅም ጊዜም ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ፓርቲዎችም ከተግባቡ፣ ስምምነትም ካለ፣ ቃለ ጉባኤ ካለ ከዚህ በላይ ህጋዊነት ሊኖር አይችልም፡፡ የሆነውም ይሄው ነው፡፡ የተወሰነው በቃለ ጉባኤ ነው፣ ሁለቱ ፓርቲዎች ተግባቡ፣ በፌዴራል መንግስት ድጋፍ አገኘ ወደ ስራ ተገባ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አብዲ ኢሌ አደራጇቸው የሚባለው የ ‹‹ሄጎ›› ቡድን አባላትና ካቢኔው ውስጥ ያሉ አንዳንድ አመራሮች የችግሩ ፈጣሪዎች እንደሆኑ የሚነሳ ነገር አለ፤ እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት ? ችግሩን ለማጥራትና ለማስተካከል እየተወሰደ ያለው እርምጃስ ምን ይመስላል?
አቶ ኢብራሂም፡- እየጠራ ይገኛል፡፡ ለህግ የቀረበ አመራር አለ፡፡ በቀጣይም መረጃዎች እየተሰባሰቡ እንደሚቀርቡ አስባለሁ፡፡ የ ‹‹ሄጎ›› ቡድን ሰንሰለቱ ይታወቃል፡፡ እንዴት እና ምንን ምክንያት አድርጎ እንደተፈጠረ ይታወቃል፡፡ በዋናነት አንቀሳቃሽ የሚባሉ ከካቢኔ አመራሮች ጀምሮ ተይዘው በህግ ቁጥጥር እየዋሉ ይገኛሉ፡፡ ከዛም በተዋረድ የሚጠየቁ አካላትም አሉ፡፡ አሁንም በዋናነት እኛ ጋር ያሉ ቅሪት የሆኑ አካላት ምቹ ሁኔታ ሲገኝ አመራርን ጨምሮ ለመንቀሳቀስ ጥረት የሚያደርግ አካል አለ፡፡ በሌላ በኩልም እንቅስቃሴውን ከጀርባና ፊት ለፊት ሲመሩ የነበሩ የፀጥታ አካላት ጭምር ተይዘው በህግ እየተጣራ ይገኛል፡፡ የሚቀሩ አካላት ይኖራሉ እነርሱም እንደየ ወንጀል አፈጻጸማቸው ለህግ የሚቀርቡ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የምታጣሩት እንዴት ነው? አጣሪ ኮሚቴስ የተዋቀረው በምን መንገድ ነው?
አቶ ኢብራሂም፡- የተቋቋመ ኮማንድ ፖስት አለ፡፡ እያጣራ ያለውም ኮማንድ ፖስት ነው፡፡ የመከላከያ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ የድሬዳዋ ፖሊስ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በጋራ ሆነው እየለዩ ሊስቱን በጋራ እያጠሩ፣ መረጃ እና ማስረጃ እያሰባሰቡ ስራውን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ድሬዳዋ እንደምትታወቀው የፌዴራል ከተማ ናት፡፡ ሆኖም እንደ ፌዴራል ከተማነቷ የሚገባትን እድገት አላገኘችም ምክንያቱ ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ኢብራሂም፡- ረጅም ነው ታሪኩ፡፡ ድሬዳዋ ያላደገችበት የራሱ ምክንያት አለው፡፡ የፌዴራል መንግስቱ እይታም በራሱ ችግር ነበረበት፡፡ የፌዴራል መንግስቱ ድሬዳዋን ባግባቡ አልመራትም፣ አልረዳትም፣ ድጋፍም አላደረገላትም፡፡ ብዙ መሰረተ ልማቶች፣ ብዙ ኢንደስትሪዎችን በማቋቋም የመጀመሪያ ከተማ ናት፡፡ በማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ሲሚንቶ፣ ጨርቃ ጨርቅ እና በሌሎችም ዘርፎች የመጀመሪያ ከተማ ናት፡፡ እነዚህ ቀስ በቀስ እየወደሙ ሲሄዱ ለህዝቡ አማራጭ ነገሮች ሲሰሩ አልነበረም፡፡ የተቋቋመበት ቻርተርም ብዙ ነገርን የሚገድብ ነው፡፡ በፍጥነት እንዳይሄድ የሚገድቡ ነገሮች አሉ፡፡
የድሮ የባቡር እንቅስቃሴ ሲዳከም በጨርቃ ጨርቅ እና በነበሩ ፋብሪካዎች ላይ ተጽዕኖ ነበረው፡፡ ይህ ሲቆም አማራጭ ነገሮች ለማህበረሰቡ መቅረብ ነበረበት፡፡ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ መንገዶች ለማህበረሰቡና ለወጣቱ በስፋት ሊቀርብ ይገባ ነበር፡፡ ባለመቅረቡ ከተማዋን አዳክሟታል፡፡ ድሬዳዋ አሁን ጥሩ ተስፋ የሚሰጡ ነገሮች አሏት፡፡ ከተማዋ የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ማዕከል ሆና ተመርጣለች፡፡ ከጎረቤት አገራት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር ቅርበት አላት፡፡ ይህ ለአስተዳደሩ ከሌሎች አካባቢዎች በተነጻጻሪነት የከተማዋ ልዩ እድል ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይህን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም መሰረተ ልማት በመዘርጋት ሰፊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ድሬዳዋ ለምስራቁ ኢትዮጵያም የራሷ ሚና እንዲኖራት ተደርጓል፡፡ ይህ በተለይም በኢንደስትሪ ዘርፍም ቀዳሚ ለማድረግ ታስቧል፡፡ በአገራችን የሚገነባው ትልቁ የኢንደስትሪ ፓርክ ድሬዳዋ ላይ እንዲሆን ለማድረግ በአሁኑ ጊዜ ሁሉም ነገር አልቆ በመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፡፡ የባቡር ሃዲዱም ከወደቀበት ተነስቶ ጅቡቲንና ኢትዮጵያን እስከ አዲስ አበባ እያስተሳሰረ ይገኛል፡፡ የኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴንም የሚያሳልጥ ይሆናል፡፡ የደረቅ ወደብ ግንባታው እየተጠናቀቀ ነው፡፡ የአገር ውስጥ 200 የሚደርሱ ባለሃብቶች በራሳችን ከልለን እንዲሰማሩ እያደረግን እንገኛለን፡፡ ብዙ የስራ እድል የፈጠሩ አካላትም አሉ፡፡
ከኢንደስትሪ ፓርክ ጋር ተያይዞ መሰረተ ልማቶች እየተሰሩ ናቸው፡፡ የመንገድ መሰረተ ልማት ከድሬዳዋ ከተማ እስከ ኢንደስትሪ ፓርኩ 14 ኪሎ ሜትር እያለቀ ነው፡፡ ከድሬዳዋ እስከ ጂቡቲ የሚዘረጋው ከ220 ኪሎ ሜትር በላይ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ እነዚህ ለድሬዳዋ ብሩህ ተስፋ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ በውስጥ ያሉ በተደጋጋሚ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከተስተካከሉ ለምስራቅ ኢትዮጵያ ጭምር የስራ ዕድል ይከፍታል፡፡ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከልም ትሆናለች፡፡
አዲስ ዘመን፡- ‹‹ሳተናው›› ግሩፕ የሚባሉ ወጣቶች እየታደኑ እየታሰሩ ነው ይባላል፣ ወጣቶች ከንቲባውን ለማነጋገር ብዙ ጥረት አድርገናል ግን ጊዜም ሁኔታዎችም አልተመቻቸልንም የሚል ወቀሳ ያነሳሉ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ ኢብራሂም፡- ከዚህ በፊት የሳተናውን ቡድን አባላት አግኝቻቸዋለሁ፡፡ ግን ከሶስት ወራት በላይ ይሆናል፡፡ በሳተናው ተደራጅተን እንመጣለን ችግር የለውም አዳራሹ የሚበቃውን ያህል አስገብተን እንነጋገራለን ብለን ነበረ፡፡ ግን አይ ሜዳ ላይ ካላነጋገራችሁን ብለው ነበር፡፡ በሜዳ ላይ ውይይት ማድረግ እንደማይቻል ነግረናቸው አዳራሽ ላይ የሚበቃውን ወደ 180 ወጣት በሙሉ ማወያየት ችለናል፡፡
መልካም የሆኑ፣ ጥሩ ጥሩ የሚያስቡና ጠንካራ ወጣቶች አሉ፡፡ ለድሬዳዋ እድገት ይጥራሉ፡፡ አሁን ላሉ ችግሮች ከጎን ሆነው ማገዝ የሚችሉ ወጣቶችን ተመልክተናል፡፡ ሌሎች አካላት ደግሞ የተጠቀሙባቸው ወጣቶችም አሉ፡፡ ሰሞኑን ሰልፍ ሲወጣ ረብሻ ሲከሰት በረብሻ ቦታ ሆነህ ካላወያየህ የሚል ቅሬታ ሲነሳ ነበረ፡፡
እሳት እየነደደ፣ መንገድ ተዘግቶ፣ ትራንስፖርትም ተስተጓጉሎ፣ ሰፊ የጸጥታ ችግር ባለበት ሁኔታ እዛ ድረስ ሄዶ ያንን ሁሉ ህብረተሰብ ማወያየት አይቻልም፡፡ ሰልፍ ላይ ስሜቱ ጥሩ ያልነበረ አካል ነበረና አስቸጋሪ ነው፡፡ ማህበረሰቡን የበለጠ እንዲቆጣ ለማድረግና ለመቆስቆስ ጥረት ሲደረግ ነበር፡፡ መጀመሪያ ተስማምተው ተወካይ እንዲልኩ አንድ ሺ የሚይዝ አዳራሽ አዘጋጅተን ነበረ፡፡ የሚፈለገው እርሱ አልነበረም፡፡ ያ ሁሉ ጎማ እየነደደ፣ ተሽከርካሪ እየተሰበረ፣ የግለሰቦች ቤት እየተዘረፈና እየወደመ ውይይት ለማድረግ ያስቸግራል፡፡ ያልተሳካው ለእዛ ነው፡፡ አሁን ውይይቶች ጀምረናል፡፡ የተወሰኑ ወጣቶችን አግኝተናል፡፡ በስፋት በየቀበሌውና በየመንደሩ ውይይት ተደርጓል፡፡ የአገር ሽማግሌዎች አግኝተናል፡፡ ወጣቶች፣ ሴቶችና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ሂደት ሰው ሰከን ሲልና ወደ እራሱ ሲመለስ ውይይቱ በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለድሬዳዋ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ነው የሚሉት ምንድን ነው?
አቶ ኢብራሂም፡- የድሬዳዋ ትልቁ ችግር ነው ብዬ የማስበው ከአመራር ጋር የሚያያዝ ይመስለኛል፡፡አሁን ተደራራቢ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህ በወቅቱ አልተፈቱም፡፡ የነበረው አገራዊ ችግር የራሱ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል፡፡ መጓተትና መሳሳብ በስፋት አለ፡፡ መምራት እስኪያቅት ድረስ መጓተት አለ፡፡ ይህ ከተስተካከለ ለውጥ ይመጣል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ቻርተሩ በራሱ መፈታት ያለበት ነው፡፡
ምክንያቱም የበጀት ጉዳይ አለ፡፡ ብዙ ፋብሪካዎች አሁን በፒኤልሲ የተቋቋሙት በሙሉ በተዋረድ የሚገኘው ገንዘብ ለእዚህ አስተዳደር እየተሰጠ አይደለም፡፡ በጀታችን ውስን ነው፡፡ የምንሰበስበው፣ ከፌዴራል መንግስት የሚሰጠን ድጎማ አይበቃንም፡፡ የመዋቅር ጥበት ችግርም አለ፡፡ ያሉትን 38 የገጠር ቀበሌዎችን የመሰረተ ልማትና ሌሎች አገልግሎቶችን ማዳረስ አልቻልንም፡፡ ስራዎችንም ለመስጠት ችግሮች ይታያሉ፡፡ መዋቅሩና ያሉ ችግሮች ከተስተካከሉ፣ የፌዴራል መንግስት ድጋፍም በጣም ቅርብ ከሆነ ችግሮቹ ይፈታሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ምላሽ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ!
አቶ ኢብራሂም፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011
ዘላለም ግዛው