ኃይለማርያም ወንድሙ
ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ ከየካቲት 12 አደባባይ ወደ ምኒልክ ሆስፒታል በሚወስደው መንገድ ላይ ከሩሲያ መንገድ በስተቀኝ ይገኛል፡፡ትምህርት ቤቱ ግማሽ ምዕተ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ዘርፍ ውስጥ ተዋቂ የሆኑ ባለሙያዎችን አፍርቷል፡፡በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለተከፈቱ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶችም መነሻ በመሆን አገልግሏል፡፡
ሎሬት ተክለዮሃንስ ዝቄ የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያው ተመራቂ ናቸው፡፡በሙዚቃ ትምህርት ቤቱ በመምህርነት ከዚያም ለ19 ዓመታት በዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡በአሁኑ ወቅት በጡረታ የተገለሉ ቢሆንም በሙያቸው በኮንትራት ተቀጥረው በሙዚቃ መምህርነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
በሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት ቆይታ ያላቸው ሎሬት ተክለዮሃንስ እንደተናገሩት፤ ያሬድ በ1959 ዓ.ም ሲመሠረት ብሔራዊ የሙዚቃ ትምህርት ቤት ይባል ነበር፡፡በወቅቱ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር ይተዳደር ነበር ።
የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ሲከፈት እኔና ጓደኞቼ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት የጨረሰ የ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ወስዶ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ሲያልፍ ለሙዚቃ ስሜቱና ዕውቀቱ ያለው ተማሪ የመግቢያ ፈተናውን ተፈትኖ ካለፈ እንቀበላለን የሚል ማስታወቂያ አየን ፡፡የሙዚቃ መሣሪያም እንጫወት ስለነበረ ትምህርት ቤቱ ሁላችንንም ተቀበሉ፡፡በወቅቱ 25 ተማሪዎች ሆነን አንድ ክፍል ውስጥ ገባን ፤ ትምህርቱ ለአራት ዓመታት ነበር የሚሰጠው ።ሙዚቃና የቀለም ትምህርት አንድ ላይ ይሰጥ ነበር፡፡
በመጀመሪያ አንድ ዳይሬክተር አንድ አስተዳዳሪ ብቻ ነበሩ፤ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ነበሩ ።ሌሎቹ የአስተዳደር ሥራ የሚሠሩ፤ ጽዳት ተላላኪነት ፀሐፊነት የመሳሰሉት ላይ የሚሰሩ ናቸው፡፡ከመምህራኑ ወደ 95 በመቶ የሚሆኑት የውጪ ዜጎች ናቸው ።ከነዚህም ከአሜሪካ፣ ከቡልጋሪያ፣ ከጀርመን የመሳሰሉ ሀገሮች የመጡ ይገኙበታል ።
እንደ ሎሬት ገለፃ፤ አሁን ከሁለት ፈረንጆች በስተቀር ሁሉም መምህራን ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡በተለይ ባለፉት መንግሥታት ለትምህርት ቤቱ ስኮላርሺፕ ይሰጥ ነበር፡፡ብዙዎች በውጪ ተምረው የተመለሱ በያሬድ አስተምረዋል።
ሙዚቃ ማስተማር ቀላል አይደለም፡፡መሣሪያዎቹ በጣም ውድ ናቸው፡፡ከፍተኛ በጀትና መምህራን ይጠይቃል የሚሉት ሎሬት ተክለዮሀንስ፣በወቅቱ ትምህርቱ ሲሰጥ ተማሪዎች ተመርቀው ምን ይሆናሉ? የሚለውም ይታሰብ እንደነበር ያስታውሳሉ ።ቢያንስ የቀለም ትምህርትና ሙዚቃ ቢማሩ የሙዚቃው ሥራ ባይኖር በቀለም ትምህርታቸው እስከ ዩኒቨርሲቲ ሊቀጥሉ ይችላሉ ተብሎ ይታሰብ እንደነበርም ያብራራሉ፡፡አለዚያም በሙዚቃ አስተማሪነት በብዛት በአንደኛ እና በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሙዚቃ ማስተማር እንደንችል ታስቦ ሥልጠናው ተጀመረ ሲሉ ይናገራሉ፡፡
የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ተማሪዎቹን ለአራት ዓመታት አስተምሮ 1962 ዓ.ም አስመረቀ ።ከተቀበላቸው የመጀመሪያዎቹ 25 ተማሪዎች ሁለቱ ቀደም ብለው በስኮላርሺፕ መልክ ወደ ውጪ ሀገር ሄደው ነበር ።በወቅቱ ሦስት ብቻ ተመረቅን የሚሉት ሎሬት ተክለዮሃንስ፤ እንደተመረቅን አንዱ ወዲያው ወደ ቡልጋሪያ ተላከ ይላሉ ።
ከቀሩት ሁለት ተመራቂዎች አንደኛው ወደ ሐረር መምህራን ማሠልጠኛ ሲሄድ፤የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ የመጀመሪያ ተማሪና ተመራቂ የነበሩት ሎሬት ተክለዮሃንስ በወቅቱ በሙዚቃ ትምህርት ቤቱ በመምህርነት ተመደቡ፡፡በሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ሦስት ዓመት ካስተማሩ በኋላ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ አውሮፓ ተልከው ለስድስት ዓመታት ቆይተዋል ። በዚህም ዲግሪያቸውንና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተው ነው ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ።
የሙዚቃ ትምህርት ቤቱን በእርዳታ መልክ የሠራው የቡልጋሪያ መንግሥት ነው፡፡በወቅቱ ማንኛውም ነገር አስተማሪውም፣ የማስተማሪያ ቁሳቁሱን የትምህርት መጽሐፎችን እና ውድ የሆኑ የሙዚቃ መሣሪያዎችን በብዛት በእነሱ ይሸፈን ነበር ሲሉ ሎሬት ይናገራሉ፡፡
ከ1962-1965 ዓ.ም አርመናዊው ሙሴ ነርሲስ ናባልዲያን የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ሆነው ቫዮሊንን መሣሪያን በማስተዋወቅ አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡
በትምህርት ቤቱ ወጣቶችን በማሠልጠን ረገድ የትምህርት ቤቱ ምሩቃን ወጣቶች ደግሞ ያልገቡበት የሙዚቃ ዘርፍ የለም፡፡ በሁሉም ቦታዎች ከሙዚቃ ትምህርት ቤቱ በተመረቁ ወጣቶች ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕድገት ከፍተኛውን ወይም ደግሞ ለሙዚቃ ሳይንስ ዕድገት ብዙ ሥራ የሠሩ ወጣቶችን አውጥተናል ይላሉ፡፡
የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ መጀመሪያ በዲፕሎማ ሲያስተምር የነበረውን ወደ ዲግሪ ማሳደጉን ጠቅሰው፣ይህንንም አሁን በድህረ ምረቃ ደረጃ አድርሶታል ሲሉ ይጠቁማሉ፡፡በየጊዜው አንዳንድ ነገሮችን በጥናትና ምርምር የትምህርቱንም ሂደት በማሳደግ እንደማንኛውም ሀገር የሙዚቃ ዕድገት የሀገራችንን ሙዚቃ ዓለማቀፋዊ ለማድረግ የትምህርት ቤቱ አስተዋፅዖ ከፍተኛ ነው ይላሉ፡፡
ረቂቅ ሙዚቃ (ክላሲካል ሙይውዚክ) የሚባለውን ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በማስተዋወቁ ለሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥንም ለፕሮግራም ሥርጭት እንደ መሸጋገሪያ እያገለገለ ይገኛል፡፡ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ የሚታወበቁት እረኛው ባለዋሽንት ረቂቅ ሙዚቃ ከኢትዮጵያ አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትና ዝና አግኝቷል፤ ይሄም የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ አንዱ አሻራ ነው፡፡
በየቲያትር ቤቶቹ በየትምህርት ቤቶቹ በግል ወደ ካሴት የመሳሰሉት ሥራ የሚሳተፉት የትምህርት ቤቱ ወጣቶች ናቸው፡፡አንድ ትምህርት ቤት ነው፤ ግን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ እንደ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እያስተማሩ ላሉት ሙያዊ ድጋፍ ያደርጋል፡፡የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ተመራቂዎችም በደሴ፣ በትግራይ፣ ጅማና ወልቂጤ ባሉት ዩኒቨርሲቲዎች ሙዚቃ እያስተማሩ ነው፡፡
ትምህርት ቤቱ ዩኒቨርሲቲዎቹ የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲከፍቱ ያደረገ ሲሆን ትምህርቱ እንደሙያ ሆኖ እንዲሄድ ያስችለዋል ።በዩኒቨርሲቲዎቹ ውስጥ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ሲከፈት ሥርዓተ ትምህርት (Curriculum) ቀረፃ በማድረግ፣ ወደ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ሲመጡ እንዴት አድርገው መጀመር እንዳለባቸው በማማከር፣ አስፈላጊውን ነገር ኮፒ በማድረግ ረድቷል፡፡
አሁን በዩኒቨርሲቲዎቹ በተከፈቱ የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች ለማስተማር የሚረባረበው የያሬድ ሙዚቃ ትቤት ምሩቅ ነው ።እዛው የተማሩ ልጆች ውጤታማ ከሆኑ እነሱንም በረዳት መምህርነት በማስቀረት እንዲያስተምሩ ይደረጋል፡፡ጥሩ ዕድገት ነው ያለው፡፡አንዳንዶቹ ለተወሰነ ጊዜ ከውጪ እየቀጠሩ ያመጣሉ ።ጥሩ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡
በተለይ በንጉሡ ክቡር ዘበኛ፣ ጦር ሠራዊትና ፖሊስ ማርሽ ባንዶች ላይ የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ አሻራውን አሳርፏል ይላሉ፡፡ፖሊስ ማርሽ ባንድ ውስጥ ብዙ ሠርቻለሁ የሚሉት ሎሬት ኮንዳክቲንግ የሚባል ትምህርት አለ፡፡ማርሽ ባንድ የሚመራው፤ የሚመሩትን ልጆች በማሠልጠን በኩል የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ አሻራዎች ነበሩ ሲሉም ይገልጻሉ ።
በማርሽ ባንዶች ላይ የኛ አስተዋጽኦ አለ፤ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ያሉትን የዘፈኖች መንገድ ለማርሽ ባንዶቹ የሙዚቃ ኖታውን ጽፈን እንሠጣለን፤እንዲሠሩ እናደርጋለን ሲሉ ይናገራሉ፡፡ማርሽ ባንዶቹ ውስጥ የገቡት የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ምሩቃን ጓደኞቻቸው መሆናቸውን ኃላፊ ሆነው የሚሠሩትም እነሱ መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡እነርሱ ባላቸው ዕውቀት ስትጨምርላቸው በጣም ምርጥ ስራ ይሰራሉ ይላሉ፡፡የሙዚቃ ኖታ እያነበቡ በመጫወትም በኩል የያሬድ ሙዚቃ አስተዋፅዖ ከፍተኛ መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡
በ1950ዎቹና 1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ የግል የሙዚቃ ባንዶችም ከስምንት እስከ 10 ሆነው በምሽት መዝናኛ ቤቶች ይሠሩ ነበር ።ሎሬትም ትምህርት እየተማርኩ እዛ ተጫዋች ነበርኩ ይላሉ
አዲስ ዘመን ጥር 2/2013