አስቴር ኤልያስ
ጽንፈኛው የሕወሓት ቡድን ከዛሬ ሁለት ወር ገደማ በፊት በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱ ይታወቃል ።ጥቃቱን ተከትሎም መንግስት ወደህግ ማስከበሩ ዘመቻ ገብቶ በአጭር ጊዜ ውስጥም በድል አጠናቆ ፊቱን ወደልማቱ መለስ ማድረግ ከጀመረ ሰነባብቷል ።በወቅቱ የነበረውን የሕግ ማስከበሩን ሂደት ይዘግቡ ዘንድ ከተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ ጋዜጠኞች ወደስፍራው ማቅናታቸውም እንዲሁ ይታወሳል ።ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ወደ ስድስት ያህል ጋዜጠኞችና የፎቶ ጋዜጠኞች ወደስፍራው ያቀኑ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል ጋዜጠኛ ጌትነት ምህረቴና ጋዜጠኛ ጌትነት ተስፋማርያም ተጠቃሾች ናቸው ።ጋዜጠኛ ጌትነት ምህረቴ ለ37 ያህል ቀናት፤ ጋዜጠኛ ጌትነት ተስፋማርያም ደግሞ ለ21 ያህል ቀናት ከሰራዊቱ ጎን በመሆን ከስፍራው ዘገባ ሲያደርሱ ነበርና በቆይታቸው ስላጋጠማቸው ሁነት እንዲሁም በወቅቱ ስለነበራቸው ስሜት እንዲያጋሩን አዲስ ዘመን ከጋዜጠኞቹ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ እንደየቅደም ተከተላቸው አሰናድቶ አቅርቧል፤ መልካም ንባብ፡፡
«የህግ ማስከበር ሂደቱ ለጁንታው ሴራዎች መቋጫ ነው ብዬ ስላመንኩበት ለዘገባ ወደስፍራው በማቅናቴ ተደስቻለሁ»
–ጋዜጠኛ ጌትነት ምህረቴ
አዲስ ዘመን፡– ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱን ስትሰማ እንደ አንድ ዜጋ ምን አይነት ስሜት ተሰማህ?
ጌትነት፡– በወቅቱ በጣም ነው የደነገጥኩት፤ ምክንያቱም በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ እንዲህ አይነት የወገን ጥቃት ይሰነዘራል የሚል ግምት ስላልነበረኝ ነው ።ከዚህ ሌላ ትግራይ የነበረው የሰሜን እዝ የትግራይን ህዝብና የክልሉ መንግስት ተረጋግቶ እንዲሰራና የአገርን ዳር ድንበር የሚያስጠብቅ የነበረ ነው ።ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኋላ እንደ ቀበሮ በምሽግ ውስጥ ሲኖር የነበረ ነው ።ስለዚህም እዛ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘር የእናትን ጡት እንደመንከስ አድርጌ እንዳስብ ነው የሚያደርገኝ ።ሌላው ደግሞ የጥቂት ግለሰቦች የስልጣን ጥማትን ለማርካት ሲባል እንዴት እንዲህ አይነት ጭካኔ ላይ ተደረሰ የሚለውን ነገር ሳስብ በወቅቱ አናዶኛልም፤ አሳዝኖኛልም ።
አዲስ ዘመን፡– በእንዲህ አይነት ስሜት ውስጥ እንዳለ መንግስት ህግ ለማስከበር የሚያደርገውን ሂደት እንደ አንድ ጋዜጠኛ እንድትዘግብ ወደስፍራ ትሄዳለህ ተብሎ ሲነገርህስ ምን ተሰማህ?
ጌትነት፡– በመጀመሪያ በስራ አስኪያጃችን ተጠርቼ ወደስፍራ እንደማቀና ሲነገረኝ በጣም ነው ደስ ያለኝ ።በቦታው ተገኝቼ በህግ ማስከበር ዘመቻው ሂደቱን ለመዘገብ መመረጥ መቻሌ የራሴን አሻራ ያሳረፍኩ ያህል ነበር ደስ ያሰኘኝ ።ስለዚህ ሲነገረኝ ያለምንም ማንገራገር ሙሉ ፈቃደኛነቴን ነው ያሳየሁት ።
አዲስ ዘመን፡– ደስ ልትሰኝ የቻልከው በህግ ማስከበሩ ሂደት የራስህን አሻራ ከማሳረፍ ባሻገር ሌላ ምክንያት ይኖርህ ይሆን? ጉዳዩ እንደሌላው ዘገባ ቀለል ያለ ባለመሆኑ ስጋት ብጤ አልተሰማህም?
ጌትነት፡– የህይወት መስዋዕትነት እንደምከፍልም ጭምር ተረድቼ ነው የሄድኩት ።ምክንያቱም የሚካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ፍትሃዊ ነው ብዬ አምናለሁ ።ፍትሃዊ ነው የምልበት ምክንያት ደግሞ አንደኛ ጥቃቱ የደረሰው በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ነው ።ሁለተኛ ጁንታው ከሄደ በኋላ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ሲያምስ ነበር ።አልሰመረለትም እንጂ ጁንታው ኢትዮጵያ እንደምትበታተን ሲተነብይ ነበር ።በተለይም የብሄር ግጭት እንዲነሳ ሲቆሰቁስ ነበር ።ስለዚህም የህግ ማስከበር ዘመቻው ለጁንታው ሴራዎች ሁሉ መፍትሄ የሚሰጥና መቋጫ ነው ብዬ ስላመንኩበት ለዘገባ ወደስፍራው በማቅናቴ ደስተኛ ነበርኩ ።
በህግ ማስከበሩ ሂደት ብዙ ጉዳት ሊኖር እንደሚችል ግልጽ ነው፤ ከምንም በላይ የሰው ህይወት ሊጠፋ ይችላል፤ ንብረት ሊወድም ይችላል፤ ዜጎችም ከአካባቢያቸው ሊፈናቀሉ ይችላሉ ።እኔም በዛ ቦታ ተሳታፊ ስሆን ህይወቴን ላጣ አካሌም ሊጎድል እንደሚችል አስቤ ነው የሄድኩት ።
ምክንያት ብትዪኝ አንዳንድ ጊዜ ለፍትህ፣ ለነጻነት ሲባል እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ መክፈል እንዳለብኝ አምናለሁና ነው ።የጁንታውን መወገድ እያሰብኩ ስለሄድኩ
እሱ የፈጠረብኝ ስሜት ፍራቻ እንዲኖርብኝ አላደረገኝም ።ስለዚህም ጥሪውን የተቀበ ልኩት በደስታ ነው ።
አዲስ ዘመን፡– ወደስፍራ ከተጓዝክስ በኋላ በቆይታህ ያስተዋልከውና ያጋጠ መህ ነገር ምንድን ነው?
ጌትነት፡– በመጀመሪያ ከአዲስ አበባ ቢሾፍቱ ድረስ በመኪና፤ ከቢሾፍቱ አየር ኃይል ደግሞ በአንቶኖቭ ቀጥታ ጎንደር ነው የሄድነው ።ከጎንደር እስከ ዳንሻ ደግሞ በመኪና ተጓዝን ።በመጀመሪያ የህወሓት ጽንፈኛው ቡድን ጥቃት የፈጸመው ሶሮቃ በምትባልበት አካባቢ ነው ።ሶሮቃ ላይ ውጊያ ሲካሄድ የነበረ ሲሆን፣ እኛ በጥቅምት 27 ቀን ወደአካባቢው ስንደርስ ዳንሻ ተለቆ ሁመራንና ባካር የሚባለውን የሁመራ አውሮፕላን ማረፊያ ለማስለቀቅ ውጊያ እየተካሄደ ነበር፡፡
አምስተኛ መካናይዝድ ጦር ቅጥር ግቢ ውስጥ ስንገባ ውስጡ የጥይት ቀለሃ ልክ እንደ አሸዋ የተርከፈከፈ ይመስል ነበር ።በአካባቢው ያሉት ዛፎች ሁሉ የቆሙ ይምሰሉ እንጂ ቅጠላቸው የረገፈና በመጥረቢያ የቆራረጧቸው ነበር የሚመስሉት ።ምክንያቱም በአካባቢው ከሶስት ቀን በላይ ውጊያ በመደረጉ ነው ።
የመከላከያ ኃይል በውስን ወታደሮች ቦታዋን ላለማስደፈር ሶስት ቀን ሙሉ ያለምንም ምግብና ውሃ እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ነው ያደረገው። ከጁንታው ቡድን በአብዛኛው ውጊያ ሲደረግ የነበረው ጄኔራል ሙሉዓለም አድማሴን ለመማረክ እንደሆነ በኋላ ላይ ውጊያን በብቃት የተወጡት የሰራዊቱ አባላት ሲናገሩ ሰምቻለሁ ።ጄኔራሉም ቢሆኑ ውጊያው ገፍቶ ቢመጣ በመጨረሻ ችግር ቢፈጠር እንኳ በጁንታው ለመማረክ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ራሳቸውን ለማጥፋት የሚያስችል ቦንብና ሽጉጥ ይዘው እንደነበር ነው የነገሩን ።
እንዲያውም ውጊያውን የከፋ ሲያደርገው የነበረው በሁለት በኩል ያለውን ውጊያ መቋቋም ነው ።ምክንያቱም ጽንፈኛው ቡድን ከውጭ ብቻ አልነበረም ።በውስጥ ያለውንና ያደባውን አደብ ማስገዛት በራሱ ከፍ ያለ ትግል ይጠይቅ እንደነበር ነው የሰማነው ።በመጨረሻ ግን የመከላከያ እና የአማራ ልዩ ኃይል ታክሎበት ጉዳዩ በድል መጠናቀቅ ችሏል፡፡
በቆይታዬ አንዴ ያጋጠመኝና የማልረሳው ነገር ቢኖር ሽራሮን አልፈን አዲ ነብሪ የምትባል ቦታ ላይ ጀብዱ የፈጸሙ ወታደሮችን ለዘገባ ስራ ልንጠይቅ በዝግጅት ላይ እያለን ቢያንስ እስከ 150 ሜትር በሚሆን ርቅት ላይ አጠገባችን መድፍ ወደቀ ።በወቅቱ ሁሉም ትርምስምሱ ወጣ ።በኋላ ላይ ግን ለመረጋጋት ሞክረን ስራችንን መስራት ችለናል ።ይህ ሁሉ በስጋትነት የምጠቅሰው ጉዳይ ነው ።
በቆይታዬ ደስ ከተሰኘሁበት ውስጥ ደግሞ የጁንታው ኃይል ተደምስሶ ሁመራ በተለቀቀበት ወቅት ነበር ።የመከላከያ ሰራዊት አዲ ጎሹ ላይ የጁንታውን ቡድን ተከዜን አሻግሮ ሲሸኘው የነበረው ሁነት አስደሳች ነው ።በወቅቱም የመከላከያ ሰራዊቱ የነገሩን ነገር ቢኖር የጁንታውን ቡድን ተከዜን ማሻገራቸውን ነበር ።ታንከኞች እንዲሁም መድፈኞቹ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው እያውለበለቡ ሲመለሱ ሳይ በጣም ደስ ተሰኝቻለሁ ።ምንም እንኳ በውጊያ አውድ በመታኮስ ደረጃ ባላሳልፍም እንደጋዜጠኛ የነበረውን ሁነት በቦታው በመሆን የየዕለቱን ክስተት
መዘገብ በመቻሌ ደስተኛ ነበርኩ፡፡
አዲስ ዘመን፡– በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞች በጦርነት ዘገባ ላይ ምን ያህል ግንዛቤ ነበራቸው ብለህ ታስባህ? ወደዘገባችሁ ከመግባታችሁ በፊት የተሰጣችሁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ነበር?
ጌትነት፡– በወቅቱ ወደስፍራው ስናቀና አስተባባሪያችን የነበሩት የመከላከያ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኃላፊ ናቸው ።በወቅቱ ኃላፊው እንዴት መስራት እንዳለብንና በስፍራው ማድረግ ስላለብን ጥንቃቄ ግንዛቤ አስጨብጠውናል ።ለአብነት ያህል አሰቃቂ ምስሎችን በምናይበት ጊዜ በቀጥታ ለአንባቢያንም ሆነ ለተመልካች ማቅረብ እንደሌለብንም በገለጻቸው ውስጥ አካተው ነበር ።በእርግጥም እኛም ብንሆን በትምህርት ካገኘነው ቲዎሪ ጋር በማስተሳሰር ግንዛቤውን ለማዳበርና የተባልነውን ለማድረግ ቁርጠኞች ነበርን ።ስለዚህም ስራችንን በተጣጣመ መልኩ ነበር ስናከናውን የነበረው ።እንደ አገር አቀፍም የተቋቋመ ኮሚቴ ስለነበር በዘገባችን የተቸገርነው ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል ።ከዚህም የተነሳ የጦርነት ዘገባ ውስጥ ያጋጠመን የስነምግባር ጉደለትም አልነበረም ማለት ይቻላል ።
አዲስ ዘመን፡– በስፍራው እያለህ በርካታ ዜናዎችን ለአንባቢያን አድርሰሃልና ከእነዛ መካከል ስሜትህን የሚይዘው የትኛው ነው? ምክንያትህስ ምንድን ነው?
ጌትነት፡– ውስጤን በጣም ቆንጥጦ የሚይዘው ዘገባዬ ብዬ የምለው አንዲት ምርኮኛን አነጋግሬ “የአብረኸት እንባ” በሚል ርዕስ የሰራሁት ዘገባ ነው ።ምክንያቱም በወቅቱ ውስጤን የነካው ስራው ብቻ አልነበረም ።ምርኮኛዋ በወቅቱ የምታሳየው ሁኔታ ነበር ።እየጠየቅኳት ባለበት ወቅት እሷ ደግሞ እያነባች ትመልስ ነበር ።ምንም እንኳ እኔ ጠያቂ እሷ መላሽና አልቃሽ ብትሆንም በወቅቱ እኔም በሆዴ እያነባሁ ነበር ስጠይቃት የነበረው ።ሆዴን ባር ባር እያለኝና ከእንባዬም ጋር እየታገልኩ ነበርና የማልረሳው ዘገባ ነበር ።
በወቅቱ እየጠየቅኳት ባለሁበት ጊዜ አጠገቤ የነበሩ ሌሎች ሹፌሮች አልቅሰዋል ።አብረኸት ስትናገር የነበረውም ነገር ውስጥን የሚፈታተን ነው ።በተለይም ከያዘችው ጥይት አንዱን እንኳ ያለመተኮሷ ምስጢር ጦርነቱን ስለማታምንበት እንደነበረ መሆኑን ስትገልጽ ነበር ።
መከላከያ ማለት የአገር ጠባቂ በኢትዮ-ኤርትራም ወቅት የተዋደቀ ሆኖ ሳለ ስለምን በእነሱ ላይ ፊቴን አዞራለሁ ነበር የምትለው ።ለብዙ ዓመታት ለአገር ዳር ድንበር ሲል ምሽግ ውስጥ ያለን ወታደር እንዴትስ አድርጌ ነው የምወጋው በማለት ነበር ስታነባ የነበረው።
ጥሪው የደረሳትም የአገር መከላከያ ሰራዊት አጠቃን በሚል እንደነበርም ነው የነገረችን ።እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይን ተወላጅን አይወደውም ብለው እንደነገሯትም ነው የገለጸችልን ።እነሱ እንዲያ ይበሉ እንጂ በአንዱም እምነት እንደሌላትና ከያዘችው 150 ጥይት ውስጥ አንዱን እንዳልተኮሰች አሳይታናለች ።ይህቺ ወታደር እስክትማረክ ድረስ እንኳ መተኮስ የሚያስችላት እድል ነበራት ።ነገር ግን በወገኗ ላይ መተኮስ እንዲሁም የተሰለፈችበትንም ዓላማ እንደማታምንበት ስለተረዳች አንድም ጥይት ወደማንም አለመተኮሷ ያስገርመኛል ።በመጀመሪያም ቢሆን ወታደር የነበረች ብትሆንም በህመም ምክንያት ትታ ኑሮዋን ትገፋ ነበረ፤ ቢሆንም በዳግም ጥሪ ነው ልዩ ኃይሉን እንድትቀላለቀል የተደረገችው ።በተጽዕኖ ስር በመውደቋ እንጂ የመዋጋት ፍላጎት እንዳልነበራት የነገረችኝ ነገር ውስጤን የነካው እውነታ ሆኖ ስላገኘሁት ነው ዘገባው ከሌሎቹ በተለየ ሁኔታ እንዳስታውሰው የሚያደርገኝ ።
አዲስ ዘመን፡– መንግስት የሕግ ማስከበሩን በድል በማጠናቀቁ የተሰማህ ነገር ምንድን ነው?
ጌትነት፡– በውጊያ አውድ ለዘገባ ስራ ወደ 37 ያህል ቀን ቆይቻለሁ ።በድል ያውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የህግ ማስከበሩ ተግባር መጠናቀቁ በጣም ደስ አሰኝቶኛል ።ለዚህም በምክንያትነት የምጠቅሰው በዋናነት የሰዎች ጉዳት መቀነሱ ላይ ነው ።ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ የኢኮኖሚ ጉዳት እንዳይደርስም ያደርጋል ።የህዝቡንም ስጋት ያሳጥረዋል ።
በሌላ በኩል ደግሞ ጁንታው በየአካባቢው ሲለኩስ የነበረው የብሄር ብሄረሰብ ግጭት ዘላቂ መፍትሄ ያገኛል ብዬ ስለማስብ ደስተኛ ነኝ ።እኔ ለምሳሌ ወደመጀመሪያ አካባቢ የሄድኩባቸው እንደ ወልቃይት፣ ማይካድራ አካባቢ በማንነታቸው ምክንያት ለ30 ዓመት ያህል ግፍና መገለል ሲደርስባቸው ነበርና ጉዳዩ በአጭር መቋጨት በመቻሉ ረክቻለሁ ።ከዚህ ጋር ተያይዞ አንድ አርሶ አደር ትውልዳቸው ከአማራ ቢሆንም ልጆቻቸው አማርኛ እንደማይችሉ ነው ያጫወቱኝ ።ያም ሆኖ ግን በጁንታው ይደርስባቸው የነበረው ግፍ ከፍተኛ እንደነበር ነው የነገሩኝ ።ከዚህ አንጻር አሁን በጁንታው መወገድ ግፎች ይቆማሉ የሚል እምነት አለኝ ።ከዚህ በኋላም ብሄር ተኮር ግጭቶች እንዲቆሙ የተለያዩ ዘገባዎችን በመስራት ጉዳዩ የበለጠ መቋጫ ያገኝ ዘንድ በስፋት መስራት ይጠበቅብናል የሚል እምነት አለኝ ።
አዲስ ዘመን፡– በጣም አመሰግናለሁ ።
ጌትነት፡– እኔም በጣም አመሰግናለሁ ።