አስመረት ብስራት
ሁልጊዜ ራሴን ያመኛል የሚሉ በርካታ ሰዎች ይሰማሉ። አንዳንዶች ደግሞ በከባድ ራስ ምታት ይሰቀያሉ። ይህ እጅግ ከባድ ራስ ምታት መነሻው ምንድነው? በሚል የተለያዩ ድረገፆችን ስናገላብጥ ሁሉም የራስ ህመም በሽታዎች አንድ አለመሆናቸውን የሚገለፅ መረጃ ሰፍሮ ይገኛል። አንዳንድ የራስ ምታት አይነቶች የሌላ በሽታ ምልክቶች ቢሆኑም አንዳንዶቹ ግን በራሳቸው ህመም በመሆናቸው ለዛሬ ማይግሬን የተባለ የራስ ህመም ምንነትንና ስለበሽታው ተያያዥ መረጃዎችን ላካፍላችሁ ወደድኩ።
ለመሆኑ ማይግሬን ምንድነው?(ከፍተኛ ራስ ምታት)
ማይግሬን ከፍተኛ እና በተደጋጋሚ የሚከሰት ራስ ምታት ነው። ይህ በሽታ የተለያዩ ምክንያቶችን ተከትሎ የሚነሳ እና እነዚህ ምክንያቶች ሲወገዱ ደግሞ የሚቀንስ በሽታ ነው ።ይህም በየደም ስሮች እብጠት በዙሪያቸው ከሚገኙ ነርቮች የተለያዩ ንጥረ ነገሮች እንዲለቀቁ ያደርጋል። በሌላ መልኩ ደግሞ እነዚህ የተመረቱ ንጥረ ነገሮች አዕምሮአችን ለህመም ያለውን ስሜት ከፍ ያደርጉታል። በመሆኑም ለትንሽ የህመም መንስኤ ከፍተኛ የህመም ስሜት እንዲሰማ ያደርጋሉ ።በዚህ የሚመጣ ህመምም ወጋ ወጋ የሚያደርግ አይነት ነው ።ህመሙም ከባድና የሚያሰቃይ ህመም ያለው የራስ ምታት አይነት ነው።
ይህ የህመም አይነት በየትኛው እድሜ ይከሰታል?
ይህ በሽታ ከ40 አመት በፊት ይጀምር እና ከ60 በላይ ሲሆኑ በተለይ በሴቶች ዘንድ ይቀንሳሉ እስከ መጥፋትም ይደርሳል ።በዚህ በሽታ ህፃናት ተጠቂ ሊሆኑ ቢችሉም በብዛት ግን አይታይባቸውም ።ምንም እንኳን ፈውስ የሌለው በሽታ ቢሆንም በተለያዩ መድሃኒቶች እና የአኗኗር ዘይቤዎች ይህን ከባድ የራስ ምታት መቆጣጠር ይቻላል፡፡
የማይግሬን ምልክቶች ምንድናቸው ?
ከፍተኛ የሆነ በተደጋጋሚ የሚነሳ እና በመሀል እረፍት የሚሰጥ አይነት የራስ ምታት የመጀመሪያው ምልክት ነው ።ህመሙ ቀስ በቀስ የሚጨምር ሲሆን ከእቅልፍ እንደነቃን ህመም እየተሰማን ከሆነ ግን ከፍተኛው የህመም ደረጃ ላይ ደርሶ ሊሆን እንደሚችል መረጃዎች ያመላከታሉ፡፡
በጭንቅላት ግማሽ ክፍል ብቻ የሚኖር ህመም የተለመደ መገለጫው ሲሆን ከግራ ወደቀኝ (ወይም በተቃራኒው) እያለ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ክፍልን ሊያጠቃ ይችላል ።ህመሙ ከአራት ሰአት እስከ ሁለት እና ሶስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ከጭንቅላት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ ይባባሳል ።ሰውነትህን ሁሉ ከመክበድ ባለፈ ሊያስመልስም ይችላል ።በተጨማሪም ለሽታዎች፣ ለድምፅ እና ለብርሃን ያለን ስሜት ይጨምራል፡ ህፃናት ላይም ተመሳሳይ ምልክቶች ሲኖረው የሚቆይበት ጊዜ ግን አጠር ይላል ። ይህም ከግማሽ ሰአት እስከ አንድ ቀን ቢሆን ነው ።
ራስ ምታቱ ከመምጣቱ አስቀድሞ የሚታዩ ምልክቶች አሉ ።እነዚህ ምልክቶች ሁሉም ህመምተኞች ላይ የሚከሰቱ ባይሆኑም ለሚታዩባቸው ሰዎች ግን ማይግሬን ሊነሳባቸው እንደሆነ ጥሩ ማመላከቻዎች ናቸው ።በአማካይ ከአንድ ቀን በፊት በጣም ንቁ የመሆን በአንዳንዶች ላይ ደግሞ ቶሎ የመድከም ፣ የመናደድ፣ ጣፋጭ ምግቦችን የመፈለግ እና የመሳሰሉ ባህሪዎችን ያሳያሉ ።የአይን ብዥታ፣ የእጅ ጣት መጠዝጠዝና መደንዘዝ፣ የንግግር መጓተት የመሳሰሉት ምልክቶች ማይግሬን ከመምጣቱ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ይታያሉ ።እነዚህ ምልክቶች ከታዩ በኋላ ማይግሬን ሊከተል ይችላል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ራስ ምታቱ ሊነሳ እንደሆነ አስቀድመው ያውቃሉ ።ማይግሬኑ ከሄደ በኋላም ድካም፣ ቶሎ መናደድ፣ መደበት ብሎም የተለያዩ የቆዳ ክፍሎች መበለዝ ሊመለከቱ ይችላሉ፡፡
የማይግሬን መነሻዎች ምንድን ናቸው ?
ከግማሽ በላይ የሚሆኑ በማይግሬን የተያዙ ህመምተኞች ከቤተሰባቸው ይወርሱታል ።ስለዚህ በቤተሰብ ውስጥ የማይግሬን በሽተኛ ካለ በተለይ ደግሞ እናት፣አባት፣እህት፣ወንድም በዚህ በሽታ ተጠቂ ከሆኑ በበሽታው ተጠቂ የመሆን እድል ይጨምራል ።በሽታው ከተለያዩ ሆርሞኖች ጋር ተያያዥነት ስላለው ሴት መሆን በራሱም በበሽታው የመጠቃት እድል በትንሹ ይጨምራል።ማይግሬንን የሚቀሰቅሱ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
የተለያዩ በሽታዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንደሚነሱ ሁሉ ማይግሬንም የራሱ ቀስቃሽ ምክንያቶች አሉት። ከእነዚህ መካከል ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው ጭንቀት ነው። ጭንቀት በራሱ ራስ ምታትን የሚያመጣ ሲሆን ማይግሬን ላለበት ሰው ግን ዋና ቀስቃሹ ነው፡፡
ረሃብ፣ የፈሳሽ ምግብ ብቻ ተመጋቢ መሆን ወይም የተዘበራረቀ የምግብ ፕሮግራም በሽታውን ሊያባብሱ ይችላሉ ።አልኮል መጠጦች፣ ኮምጣጣ ምግቦች፣ ቸኮሌት እና ቺዝ የመሳሰሉ ምግቦች በሽታንውን ያስነሳሉ ።ብዙ ወይም ትንሸ እንቅልፍ፣ የአየር ሙቀት ለውጦች፣ ሀይለኛ ሽታ፣ፀሃይ፣ ከፍተኛ ድምፆች በሽታውን ከሚያስነሱ ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
በሴቶች በኩል ደግሞ የወር አበባ ኡደትን ተከትለው የሚጨምሩ እና የሚቀንሱ የሴት ሆርሞኖች ይህንን በሽታ ያባብሱታል ።በተለይ የወር አበባ በሚመጣበት ጊዜ በሽታው ከድሮው በበለጠ ይጨምራል ።ስለዚህም አንድ ሴት ስታርጥ የማይግሬን በሽታዋ ከመቀነስ አልፎ ሊጠፋም ይችላል ።እርግዝናም የራሱ የሆነ ለውጥ ያስከትላል፡፡
ማይግሬንን እንዴት መከላከል ይቻላል?
ማይግሬን የማይድን በሽታ ቢሆንም የሚከሰትባቸውን ጊዜያት ለመቀነስ የተለያዩ ነገሮች ማድረግ ይቻላል። በሽታውን ምን እንደሚያስነሳው ለይቶ ማወቅ እና ከእነዚህ ነገሮች እራስን መጠበቅ፤ ራስ ምታቱ በሚጀምር ጊዜ መቼ እንደ ጀመረ፣ ህመሙ ሀይለኛ ወይስ ለዘብ ያለ እንደነበር፣ መድሃኒት ተወስዶ ከሆነ የተወሰደውን መድሃኒትና ሌሎች ምክንያቶችን በመፃፍ እና በተለያዩ ጊዜያት የተያዙ ማስታወሻዎች በማመሳከር ምክንያቶቹን በቀላሉ ማወቅ ይቻላል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአኗኗር ዘይቤን መቃኘት ተገቢ ነው። ጭንቀትን ማስወገድ፣ ምግብ በሰአቱ መመገብ፣ እንቅልፍ በልኩ መተኛት፣ አልኮል መጠጦችን ማስወገድ እና ከላይ የተጠቀሱ ምግቦችን ባለመመገብ ራስ ምታቱን መቀነስ ይቻላል ።የተለያዩ ረጋ ያሉ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን መስራት እና እራስን ከማዝናናት በተጨማሪ ደረቅ መርፌ መጠቀምም ሊረዳ ይችላል ተብሎ እንደሚታሰብ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ራስ ምታቱ ከጀመረ በኋላ መደረግ ያለበት ነገር?
አንዴ ራስ ምታቱ ከጀመረ በኋላ መድሃኒት በመውሰድ ፀጥ እና ጨለም ያለ ቦታ ላይ እረፍት ማድረገ ቀለል እንዲል ያደርጋል ።ቀዝቃዛ ነገር ለምሳሌ በፎጣ የተጠቀለለ በረዶ ግንባር ላይ ማድረግ እንዲሁም ቡና መጠጣት የተወሰነ ለወጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡
የማይግሬን ህክምና ምንድን ነው?
ምንም እንኳን በሽታው የማይድን ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ብዙ መድሃኒቶች እየተፈበረኩ ሲሆን ከብቃታቸው አንፃር በጣም ጥሩ የሚባሉ መሆናቸውን መረጃዎቹ ይናገራሉ ።አንዳንዶቹ ራስ ምታቱ ከመጀመሩ በፊት የሚከላከሉ ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ህመሙ ከጀመረ በኋላ ህመሙን የመቀነስ ስራ ይሰራሉ ።ነገር ግን መድሃኒት ከመጀመሩ በፊት ሀኪምን ማማከር ተገቢነት አለው፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 03/2013