ጃፓናዊዎቹ አኪያማ እና አካጊ ለረጅም ዘመናት በትዳር ተጣምረው የቆዩና መልካም ስነምግባር መለያቸው የሆኑ ጥንድ አዛውንቶች ናቸው። እ.ኤ.አ በ2005 እኒህን ጥንዶች መነገጋሪያ የሆኑትና የመገናኛ ብዙሃን አጀንዳ ለመሆን የበቁት ከበርድ ፍሉ ጋር በተያያዘ ጉዳይ ነበር። በዚያን ወቅት ማለትም በእኛ ዘመን አቆጣጠር በ1998 ዓ.ም አካባቢ በሀገራችን በርድ ፍሉ መነጋገሪያና የፖለቲካ ሽኩቻ ማዕከል እንደነበርም አይዘነጋም። በሽታው በሩቅ ምስራቅ አገራት ላይ ጥላውን አጥልቶ ለበርካታ ሰዎች እልፈት ምክንያት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የጤና ስጋት ደቅኖ እንደነበርም ብዙዎቻችን እናስታውሳለን።
በወቅቱ የጃፓን መንግስት ማንኛውም ዜጋው በሚያረባቸው ዶሮዎች ላይ የበሽታው ምልክት ከታየ ምንም አፍታ ሳይወስድ በፍጥነት ለጤና ተቆጣጣሪ አካላት እንዲያሳውቅ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶም ነበር። ይሁንና እነዚህ ጥንዶች በሚያረቧቸው ዶሮዎች ላይ አጠራጣሪ ነገር ተመልክተው በቸልታ በማለፋቸው ሁኔታውን የተመለከቱ ጎረቤቶቻቸው ችግሩን ለመንግሰት ያስታውቁና ዶሮዎቹ ላይ በተደረገ ምርመራ ዶሮዎቹ የበሽታው አምጪ ቫይረስ ተሸካሚ መሆናቸው ይረጋገጣል። ለማህበራዊ ግንኙነት ከፍተኛ ዋጋ በሚሰጡት ጃፓናውያን ዘንድ ይህ ስህተት ከፍተኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ከመሆኑም በላይ የማህበረሰቡን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ጉዳይን ችላ ማለታቸው ጥንዶቹ ላይ ከፍተኛ የህሊና ወቀሳ አሳደረባቸው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሁለቱም ጥንዶች በሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን በመቅረብ በእንባ ታጅበው በማህበረሰቡ ላይ ላደረሱት በደል ይቅርታ ከመጠየቃቸውም በላይ በዚያኑ ምሽት ወደቤታቸው በማቅናት ሁለቱም የራሳቸውን ህይወት ያጠፉበትን ሁኔታ የጃፓን መገናኛ ብዙሃን እየተቀባበሉ ይዘግቡት እንደነበር አስታውሳለሁ። ይህ ታሪክ ጃፓኖች ለሀገርና ለህዝብ ያላቸውን ጥልቅ ፍቅርና ፍቅሩ የሚገለጽበት የቁርጠኝነት ጥግ በሚገባ ያሳየናል ብዬ እገምታለሁ። ሀገር መውደድ ሲባል እንዴት? ለሚለው ለጽሁፌ መነሻም ሰናይ መንደርደሪያ እንደሚሆነኝ እተማመናለሁ።
ሁሌም ከመልካም ጎን መነሳቱ ገንቢ ነውና እኛ ኢትዮጵያውያን ሀገር መውደዳችን በተግባር ከሚገለጽበት ዋነኛ ጉዳይ ልነሳ። እውነት ነው እኛ ኢትዮጵያውያን የሀገራችን ሥም ሲነሳ ልንገልጸው የማንችለውና ሰውነታችንን ውርር የሚያደርግ ልዩ ስሜት እንዳለን እኔ ራሴ እማኝ ነኝ። የሀገራችንን ሉዓላዊነት ሊዳፈር የሚቃጣ ኃይል ሲመጣም ሚሊዮኖች መተኪያ የማይገኝለት ውድ ህይወታቸውን አሳልፈው እንደሰጡና አሁንም ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን እንኳን ወዳጅ ጠላትም የማይክደው ሀቅ ነው። በተለይም ወራሪ ኃይል ሲመጣ የሃይማኖት የብሄር የጾታ ወዘተ ልዩነት ሳይገድብን አንድነታችን ክብረት ይጠነክራል። ፍቅራችን ጦዞ በአንድ ሳንባ እስከ መተንፈስም እንደርሳለን። ሀገር መውደድ ተግባርን ይጠይቃልና እንዲህ በተግባር የሚገለጽ የሀገር ፍቅር እጅግ ሊደነቅና ልንከባከበው የሚገባ ጉዳይ ነው። ከዚህም በላይ አኩሪና እንደወርቅ እያብረቀረቀ ለዘላለም ሊቀጥል የሚገባው እሴታችን ነው ብዬ አምናለሁ።
ይሁንና በሰላሙና አገር በሚያሳድጉ ጉዳዮች ዙሪያ የሀገር መውደድ ስሜታችን በትጋት የሚገለጽበት ሁኔታ አጅግ የተዳከመ ነው ብዬ እንዳስብ የሚያደርጉኝ በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቁም ነገር መጽሄት በጅማሬዋ ወቅት ያስነበበችው አንድ መጣጥፍ ልቤ ውስጥ ቀርታለችና ላካፍላችሁ ወደድኩ። ታሪክ እንዲህ የሚል ነበር፦ ፈጣሪ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያን ልጎብኝ ብሎ መዓት ሰራዊቱን አስከትሎ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል። ይህን የተመለከቱ ኢትዮጵያውያን ምን ወራሪ መጣብን ብለው አማራውና አፋሩ፣ ትግራዩና ጋምቤላው፣ ኦሮሞ ትግሬው ወዘተ በአንድነት ይዘምታሉ። በዚህ ወቅት የነበራቸው ፍቅርና መተሳሳብ እጅግ የሚያስቀና ነበርና በኢትዮጵያውያኑ ላይ ባየው ፍቅር ፈጣሪ አጅጉን ይደመማል። ኢትዮጵያውኑ ቀረብ ብለው ሲመለከቱም ጠላት እንዳልመጣባቸውና ፈጣሪ ሊጎበኛቸው እንደተገኘ ተረድተው ሀሴት ያደርጉም ጀመር ፈጣሪም የነበራቸውን ፍቅር ተመልክቶ ለአንዱ ለም መሬት ለሌላው የውሃ ሀብት፣ ወርቅ፣ ማዕድን፣ ነዳጅ ወዘተ ስጦታ በስጦታ ያንበሸብሻቸውና ይመለሳል።
ይሁንና የፈጣሪን መሄድ የተመለከቱትና ወራሪ እንዳልመጣባቸው የተገነዘቡት ኢትዮጵያውያንያ ፍቅራቸው በአንድ ጊዜ ተንኖ ይጠፋና አንዱ ሌላውን ሀብቴን ሊወሰድብኝ ነው ሲል በደፈጣ መተያየትና መጠማመድ ውስጥ ገብተው የተሰጣቸውን ሀብት ሳይጠቀሙበት ይቀራሉ። በዚህ ሁኔታ ሲኖሩ ሳለ ከብዙ ዓመታት በኋላ በሰጠኋቸው ሀብት እንዴት ተጠቅመው ይሆን? ያ የሚያስቀና ፍቅራቸውስ እንዴት ይሆን? ብሎ ፈጣሪ ሊጎበኝ ይመጣል። በዚህ ጊዜ የተመለከተው ነገር አጅግ አሳዛኝ ነበር። ያላቸውን ሀብት በጋራ ከመጠቀም ይልቅ አንዱ ሌላኛው ሀብቴን ይወሰደብኛል ሲል ደፈጣ ይዘው እየተጠባበቁ፤የሚሰራ ጠፍቶና ድህነቱ ከፍቶ ኢትየጵያውያኑ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ነበሩ። በዚህ ጊዜ ፈጣሪ እጅግ አዝኖ የተናገረው ቃል ፍቅራችሁ እንዲጸና ድንበር ገፊ ጠላት አያሳጣችሁ አለ የሚል ነበር።
ይህ ነገር ቀልድ ቢመስልም ልንፈትሸው የሚገባ እውነታን ግን አያጣም የሚል እምነት አለኝ። ይህም እውነታ ወራሪ ጠላት ድንበራችንን በሚጋፋበት ወቅት፣ በአትሌቲክስ እና የእግርኳስ ድሎች በተከሰቱበት ጊዜ የምናሳየው አገራዊ ፍቅርና አንድነት ሌላም ጊዜ አለወይ የሚል ነው።
በእኔ እምነት የለም ነው የምለው። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ያልጠበበች አገር ይዘን የጠበብንበትና ይሄ የእኔ ክልል ነውና ውጣ እየተባለ ወገን የሚሳድድበትን ሁኔታን ማንሳት ይቻላል። በቅርቡ እንኳን በሲድኒ ኦሎምፒክ በእነ ኃይሌ፣ ደራርቱ ገዛህኝና ሌሎችም ድል ከኤርትራ ጋር በነበረ ጦርነትና ሱዳንን አሸንፈን ወደ አፍሪካ ዋንጫ ባለፍንበት ጊዜ የነበረው አገራዊ የአንድነትና የፍቅር ስሜት አሁን ላይ ሩቡ እንኳን ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ። ከዚህ ይልቅ የተሻለ ዜጋ ይገኝባቸዋል ተብሎ በሚታሰቡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሳይቀር ሁላችን የአንዲት አገር ኢትዮጵያ ልጆች መሆናችን ተረስቶ በብሄር ልዩነት ህይወት እየጠፋ፤ አካል እየጎደለ ንብረት እየወደመና የአገር ሰላምና መረጋጋትም እየተበጠበጠ ይገኛል። እውነት አገር መውደድ በውስጣችን ሰርጾ ቢሆንና ከምር የምንዋደድ ብንሆን ኖሮ ይህን መሰል ድርጊት አይከሰትም ብዬ አስባለሁ። ስለሆነ ቆም ብለን ሀገራችንን እንወዳለን እንዴ ከወደድንስ በተግባር ተገልጿልን ብለን ልንጠየቅ ከሚገባን ጉዳዮች አንዱ ይሄ ይመስለኛል።
ሀገር መውደድ ከሚገለጽባቸው ጉዳዮች ሌላው በኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ መዋደድ እና መተዛዘን የሚገለጽ ነው። አዛውንቶችን፣ ሴቶችን፣ህሙማንንና አካል ጉዳተኞችን ማክበርና መንከባከብ የጨዋና የሀገር ወዳድ ማህበረሰብ መለያና ሀገር መውደድ የሚገለጽበት መልካም እሴት ቢሆንም ይህ እሴት አሁን እየተሸረሸረና እየጠፋ በመሄድ ላይ መሆኑ ነው የሚሰማኝ። የታክሲ አሽከርካሪዎች በዕድሜ ገፋ ያሉ ሰዎችን ነፍሰ ጡሮችንና አካል ጉዳተኞችን ማሳፈር በፍጹም አይፈልጉም። ለእናንተ አይመችም ሌላ ፈልጉ ሲሉም ደጋግሜ ሰምቻለሁ። ምክንያቱ ደግሞ አጭቆ ለመጫን ምቹ አይደሉማ። ስለሆነም ወገናዊ ፍቅሩ ጠፍቶ ሳንቲሟን ብቻ በማየት የታክሲ ረዳቶች እነዚህን የኅብረሰተብ ክፍሎች ሲያንገላቱ ማየቱ የሰለቸ ጉዳይ ሆኗል። ህዝቧን ሳይወዱ አገርን እወዳለሁ ማለት ይቻላልን?
የጋራ የሆኑ የህዝብ ሀብቶችን በጥንቃቄና በኃላፊነት መጠቀም አገር መውደድ ከሚገለጽባቸው ተግባራት አንዱ ነው። ከዚህ አንጻርስ እኛ ኢትዮጵያውያን ምን እንመስላለን? ሌላ ሌላውን ለጊዜው እናቆየውና የህዝብ ስልክና መንገድ እንዲሁም በመንግስታዊና ህዝባዊ ተቋማት ያሉ መሳሪያዎችን አጠቃቀም እንመልከት። እነዚህን የህዝብ ሀብቶች የጠላት ገንዘብ ይመስል የሚሰርቃቸውና የሚያበላሻቸው ብዙ ነው። በአዲስ አበባ ከፍተኛ የውሃ ብክነት ካለባቸው ተቋማት መካከል ዋነኛው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሆነ አንድ ወዳጄ ሲነግረኝ ወዴት እየሄድን ነው ስል ራሴን ጠይቄያለሁ። ይህም አገራችንን በአፍ እንጂ ከልብ ላለመውደዳችን ጥሩ ማሳያ ይመስለኛል።
የአንድ አገር ጥንካሬና ዕድገት አገሪቱ ከምትሰበስበው የታከስ መጠን ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት አለው። እናም አገራቸው እንድትጠነክርላቸው የሚፈልጉ ዜጎች ታማኝ ሆነው ግብር መክፈልን የሰርክ ተግባራቸው ያደርጉታል። ግብር አለመክፈል የአገርን ዕድገትና ወታደራዊ ጥንካሬ ማሽመድመድ መሆኑን በሚገባ ይገነዘባሉና! የአሜሪካና ሌሎችም የበለጸጉ አገራት ልምድ የሚያስተምረንም ይህንኑ ነው። እንደ ቻይና፣ ደቡብ ኮሪያና ጃፓንን በመሳሰሉ የሩቅ ምስራቅ አገራትም ግብርን በታማኝነት አለመክፈል አገርን እንደመጉዳትና በዜጎች ላይ እንደተፈጸመ ወንጀል ስለሚቆጠር በዚህ ዙሪያ ስህተት መፈጸም እሳትን በእጅ እንደመጨበጥ ይቆጠራል። እኛስ እንዴት ነን ብለን ብንጠይቅ በዚህ ዙሪያ በርካታ ችግር እንደሚስተዋሉብን ጸሀይ የሞቀው ሀቅ ነው።
በእኛ አገር ተጨባጭ ሁኔታ ሥራቸው ለታክስ ስወራ በማያመች ሥራ ላይ ከተሰማሩና ከመንግስት ሰራተኞች ውጪ ግብር መክፈልን የዜግነት ግዴታ አድርገው የሚወስዱና ይህንንም በተግባር የሚያስመሰክሩ አጅግ በጣም ጥቂት እንደሆኑ አገሪቱ በየዓመቱ ከምትሰበስበው የግብር መጠን በቀላሉ መረዳት እንችላለን። ከተጣለባቸው አገራዊ ኃላፊነት ይልቅ የግል ህይወትና ተድላ የበለጠባቸው ግብር ሰብሳቢና ተቆጣጣሪ ሰራተኞችም በስርቆት ተዘፍቀው አገሪቱን የኋላት እያስኬዱ መሆኑንም ከግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቶች በየዓመቱ በሚደረግ ግምገማ ከሚባረሩ ሠራተኞች ቁጥር የምንረዳው ነው። እናስ በሰላም ሰርተንና ነግደን እንድንበላ ላደረገችን አገር ታማኝ ግብር ከፋይ መሆን እየተሳነን እንዴት ነው አፋችንን ሞልተን አገራችንን እንወዳታለን ልንል የምንችለው? በጥልቅ ሊጤንና እያንዳንዱ ዜጋም ምላሽ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ ይመስለኛል።
አገር መውደድ የሚገልጽበት ሌላው ነገር በውጪ የሚኖሩ ዜጎች ለአገርና ወገናቸው በሚያደርጉት በጎና አዎንታዊ ድጋፍ ይገለጻል። እንደ ቻይናና ህንድ ከአፍሪካም ናይጄሪያን የመሳሰሉ አገራት በውጪ የሚኖሩ ዜጎቻቸው በሬሚታንስና በቴክኖሎጂና ዕውቀት ሽግግር አገራቸውን ለመጥቀም የሚያደርጉት ጥረትና እገዛ አጀብ የሚያስብል ነው። እነዚህ ዜጎች ለሀገራቸው ያደረጉት በጎ አስተዋጽኦም አገሮቻቸው አሁን ለደረሱበት የእድገት ደረጃ ወሳኝ ድርሻ ነበረው።
በእኛ ሁኔታ ግን በዚህ መስክ ያለው ሁኔታ ዳያስፖራውን አፉን ሞልቶ አገሬን እወዳታለሁ ለማለት የሚያስደፍረው አይመስለኝም። ቀደም ሲል በሀገራችን በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ብዙ ሰው ቅሬታ ስለነበረበት ደስ ብሎት አገሩን ለመደገፍ ተስኖት ነበር ሊባል ይችላል። አሁን ግን ዳያስፖራውን ጨምሮ የብዙ ዜጎችን ቅሬታ የመለሰ ተግባር በመንግስት እየተወሰደ ነውና ኃላፊነትን ላለመወጣት ምንም ምክንያት የለም። ይሁንና ራስን እንደ አንድ አገር ዲፕሎማት በመቁጠር ለአገር ጥቅም የመስራቱ ሁኔታ ደካማ ከመሆኑም በላይ ሬሚታንስን በአቋራጭ መላክ የመሳሰሉ አገርን የሚጎዱ ተግባራት ሲፈጸሙ ነው የሚስተዋለው። ይህ ደግሞ አንድ አገሩን ከሚወድ ዜጋ የማይጠበቅ ነውና በፍጥነት ልናርመው የሚገባ ነው እላለሁ።
ጽሁፌን ሳጠቃልልም ሀገር መውደድ ያለተግባር ባዶ መሆኑንና ከዚህ አንጻር አገራችንን እንወዳለን ብለን የምናወራውን ያህል በተግባር ማሳየት ላይ ብዙ ክፍተት እንዳለብን ሊሰመርበት የሚገባ ነው። እዚህ ላይ ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ግን ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም ታምነው ግብር በመክፈል፣ ዜጎችን በመውደድና በመንከባከብ፣ የህዝብ ንብረት የሆኑ መገልገያዎችን በጥንቃቄ በመጠቀምና ለሀገራቸው ጥቅም ዘብ በመቆም አርአያ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ እንዳልዘነጋሁና እኒህን መሰል ዜጎች ቁጥራቸው በርከት ይልልን ዘንድ ምኞቴ ጽኑ ነው! ሻሎም!
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011
ፍቃዱ ከተማ