ተሳታፊዎች ከፓርላማው የፍተሻ በር ጀምሮ እስከ አዳራሹ መግቢያ ድረስ በጥድፈያ ይተማሉ፡፡ በችኮላ የታጀበ አረማመዳቸውም የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች በቃል የሚሰጡትን ምላሽ ለማዳመጥ ጉጉት ያደረባቸው እንደሆነ አስመስሎባቸዋል፡፡
ከሚተሙት ሌሎች እንግዶችም ያሉ ሲሆን፣ ጋዜጠኞችና የካሜራ ባለሙያዎች ሌሎቹ ተጠቃሾች ነን፤ እኛም በተዘጋጀው ቦታ በመሰየም የአፈ ጉባዔውን የጉባዔ ማስጀመሪያ ቃል እየተጠባበቅን ነው፡፡ ያለንበት ቦታ ከወትሮ በተለየ ተጨናንቋል፡፡ አፈ ጉባዔውና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቀመጡባቸውን ወንበር ለማየት ያልታደሉ ጋዜጠኞች ዓይናቸውን በስክሪኑ ላይ ለማሳረፍ ተገደዋል፡፡ ሁሉም መቅረጽ ድምጹንና ሌሎች የድምጽና ምስል መያዣ መሳሪያዎችን ደግኗል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት የሚጠብቅባቸውን ቁጥር ያህል መምጣት አለመምጣታቸው ከተረጋገጠ በኋላ በሁለት ዙር ጥያቄዎች እንዲቀርቡ በአፈ ጉባዔው አማካኝነት ተነገረ፡፡ ከሁለት ሰዓት በላይ የፈጀው የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄና የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ፈገግታን በሚያጭሩ ቃላትና ዓረፍተ ነገሮች ታጅቦ፣ አንዳንዴም አዲስ ፍልስፍናዊ አተያዮችን አካቶ፣ አለፍ ሲልም ሠላምን የሚሰብኩ አመክንዮአዊ ትርክቶች እየተቀነጨቡ ተደመጡ፡፡ የመጨረሻው ማብራሪያ ተሰጥቶ የዕለቱ ጉባዔ ሲቋጭ በተሳትፎ ላይ የነበሩትን አባላትና ሌሎች አካላትን ስለ ፓርላማው ውሎ እንዲነግሩን መከታተል ጀመርን፡፡
የምክር ቤቱ አባል የሆኑት ዶክተር ገመዶ ዳሌ፤ ‹‹አብዛኞቹ የምክር ቤት አባላት ጥያቄዎች ቀደም ሲል የሚታወቁ፤ ምላሻቸውም በተደጋጋሚ ሲገለጽ የነበረ ሲሆን፤ ያልታየው ተግባሩ ነው፡፡ በተለይ የህግ የበላይነትን ከማስከበር፣ መሠረታዊ የኢኮኖሚ መረጋጋትን ከማምጣት፣ ኮንትሮባንድን ከመዋጋትና ህግ ከማስከበር፣ ልማቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ሕዝቡ ተረጋግቶ እንዲኖር ከማድረግ አንጻር ያለው ተግባር ነው የጎደለው፡፡ በተሰጠው ምላሽ መሰረትም ወደ ተግባር እንደሚገባ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡›› ሲሉ አስተያየታቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹እስካሁን የነበሩ ማነቆዎች ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠቱ ላይ ሳይሆን እርምጃና ውጤቱ ላይ ነው›› ያሉት ዶክተሩ፤ ይህም ከፍተኛ ርብርብ እንደሚጠይቅና ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሰጡት መልስ ይህንኑ ያመላከተ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡ ከተሰጡት መልሶች በተጨማሪ የምክር ቤቱ አባላትም የየድርሻቸውን መወጣት እንደሚኖርባ ቸው በማስገንዘብ፤ የአገሪቷን ልማት፣አንድነትና ሠላም በማይነጣጠል ሁኔታ ከግለሰብ ጀምሮ መስራት፤ አልፎም እንደ ምክር ቤት ህግ አውጭና አስፈጻሚን እንደሚቆጣጠር አካል የተሰጡትን መልሶች መሰረት አድርጎ መሄድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ አባል ወይዘሮ ምንትዋብ ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ ‹‹ጥያቄን ማስተናገድ አንዱ የዴሞክራሲ ተግባር ነው፡፡ በዚህም የተነሱት ጥያቄዎች የፖለቲካውን፣ የኢኮኖሚውንና ማህበራዊውን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ናቸው፡፡ ክፍተት ባለባቸው ሁኔታዎች መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የተሰጡ መልሶች ከዳር መድረስ ይኖርባቸዋል፡፡ መልሶቹ አጥጋቢ ናቸው፡፡ ነገር ግን የመንግሥትንም ቁርጠኝነት የሚጠይቁ፣ የህዝብንም ትብብር ግድ የሚሉ ሥራዎች በቀጣይ በተግባር የሚመለሱ ይሆናሉ፡፡›› ሲሉ ጠቅሰው፤ ‹‹ሁሉም ሥራ የሚሰራው የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ ረገድም የተሰጠው ምላሽ ብዙ ተስፋ እንዳለ ያመለክታል›› በማለት የምክር ቤቱን አባላት ጥያቄዎች ወቅታዊነትና የተሰጠውን ምላሽ ተገቢነትነ ገልጸዋል፡፡
‹‹በፓርላማው ውሎ አባላቱ በዋናነት ከህግ የበላይነት ጋር ተያይዘው በየአካባቢው እየተነሱ ያሉትን ግጭቶች አስመልከቶ መጠየቃቸው፤ ከውጭ የመጡ የፖለቲካ ፓርቲ ተፎካካሪዎች ሠላማዊ በሆነ መልኩ ትግል ማድረግ እንዳለባቸው ሲታመን አንዳንዶች ከዚህ ባፈነገጠ መልኩ በኅብረተሰቡ ውስጥ ችግር እየፈጠሩ ስለመሆናቸው መነሳቱ፤ የፓርላማው ውሎ በጎ ጎኖች ናቸው›› ያሉት ደግሞ የምክር ቤቱ አባል የሆኑት አቶ አለሙ ገብሬ ናቸው፡፡
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ በተሰጡት ምላሾች ውስጥ ከዚህ ቀደም ችግር እየፈጠሩ ያሉት አካላት ላይ ርምጃ ከመውሰድ አንጻር መንግሥት ሆደ ሰፊ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ ከእነዚህ አካላት ጋር በሚደረጉ ውይይቶችና ድርድሮች አንጻራዊ ሠላም እየተፈጠረ ስለመሆኑና በቀጣይም ጥፋት በሚፈጽሙ ላይ የማያዳግም ርምጃ እንደሚወሰድ መገለጹ ዘላቂ ሠላምን ከማምጣት አንጻር ተገቢ ነው፡፡ ይህ ለህዝብም ግልጽ ሆኖ እንዲታወቅ መነሳቱ በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው፡፡
አክለውም እንደተናገሩት፤ በማይክሮ ኢኮኖሚ በኩልም በርካታ ጥያቄዎች መስተናገዳቸው ወቅታዊ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት ትኩረት ያደረገባቸው ቀጣይ እቅዶች ተገቢ መልሶች ተቀምጠዋል፡፡ መልሶቹ መልስ ብቻ ሳይሆኑ መረጃንም የሰጡ ጭምር ናቸው፡፡
‹‹ምንም እንኳን የተሰጡት ምላሾች አጥጋቢ ቢሆኑም፤ አንዳንዶች ግን ሥራን የሚፈልጉ ናቸው›› የሚሉት አቶ አለሙ፤ በተለይም ግጭቶች ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉት መፈናቀሎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ብቻ የሚቆም ሳይሆን ተከታታይ ሥራ እንደሚፈልግም ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ራሱም ከህግ በታች እንደሆነ በማሳያ ምላሽ መሰጠቱና ህግ የማስከበር ሥራው ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ መጠቀሱም አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ጉዕሽ ገብረሥላሴ በበኩላቸው፤ የቀረቡት ጥያቄዎች ከወቅቱ የአገሪቱ ሁኔታ ጋር የተገናኙ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጧቸው ምላሾችም በተመጣጣኝ መልኩ ቢሆኑም ጥቂት ጉድለቶች አሉባቸው፡፡ መልሶቹ ጠንካራ አይደሉም፡፡ በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በምስራቅና በኦሮሚያ አካባቢዎች ያሉ ችግሮች ይስተካከላል የሚል ግምት የነበረ ሲሆን፤ ነገር ግን ጉዳዩ እያገረሸና ወደ ሌላ አቅጣጫ እያመራ ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልስ ማስጠንቀቂያ አዘል መሆን ነበረበት፡፡›› በማለት አስረድተዋል፡፡ ‹‹በዝርፊያ፣ መፈናቀል፣ መግደል የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጧቸው መልሶች ትክክል ተደርገው ቢወሰዱም፤ ከዚህ ቀደም ይሰጡ ከነበረው አግባብ የተለሳለሰ መልስ አይለይም፡፡›› ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 25/2011
አዲሱ ገረመው