ግርማ መንግሥቴ
ስለ ጎዳና ተዳዳሪዎችና ተያያዥ ጉዳዮች የሚያጠናው ፍልስፍና ስትሬቲዝም (streetism) በአገራችን እምብዛም የተለመደ አይደለም። ምናልባት መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይጠቀሙበት እንደሆን ባይታወቅም በመንግስት ተቋማት በኩል ግን ቀጣይነት ባለውና ችግር ፈቺ በሆነ መልኩ ሲሰራበት አይስተዋልም። በመሆኑም ይመስላል ጉዳዩን በተመለከተ ብዙውን ጊዜ በጉዳዩ ላይ ቁርጥ ያለ መረጃ እንኳን እማይገኘውና “አካባቢ” የሚል ማጀቢያ የማይለየው ቁጥር የሚሰራጨው። ለነገሩ ሁሉም ነገር እኮ በ”በላይ” እና “… አካባቢ” የታጀበ ነው፤ ብሄር በብሄረሰቦች እንኳን ከ80 በላይ ተብለው ነው የሚገለፁት።
የጎዳና ተዳዳሪነት የሌለበት ሃገር የለም። ጉዳዩ አለም አቀፍ ነው። በመሆኑም ችግሩ የሁሉም ሲሆን መፍትሄ ፍለጋውም የጋራ ነው መሆን ያለበት።
በ1989 (እኤአ)100 ሚሊዮን የጎዳና ተዳዳሪ ህፃናት ይገኙ ነበር። ዛሬ ግን ምኑም በማይታወቅና ውሉ በጠፋ ሁኔታ ቁጥራቸው የትና የት ጨምሮ ይገኛል። በመሆኑም በትክክል ይህን ያህል ናቸው ማለት አልተቻለም። “ለምን?” ለሚለው መልስ የምናገኘው ከወደ ኮንሶርቲዬም ፎር ስትሬት ችልድረን “Consortium for Street Children” ሲሆን ከበርካታ ምላሽና ምክንያቶቹም አንዱ “የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመቁጠር እንደሌላው አይነት ህዝብ ቆጠራ ሁሉ ቀላል አይደለም፤ የተለየ ዘዴ መከተልን ይጠይቃል” የሚል ነው። ለዚህም ነው እኛም ከላይ ስትሬቲዝምን ጠቆም ማድረግ የፈለግነው።
ምንም እንኳን ከላይ የጠቀስነው ተቋም “አይታወቅም” ይባል እንጂ የተለያዩና ጉዳዩን ጉዳዬ ብለው የያዙ ተቋማት የተለያዩ አሃዞችን እየጠቀሱ ያለውን የጎዳና ተዳዳሪዎች ብዛት ለማሳየት እየሞከሩ ያሉ ሲሆን፤ ቁጥሩንም ከ150 እስከ 200 ሚሊዮን ሲያደርሱት ይታያል። ወደ እኛው ጉዳይ ስንመለስም እውነታው ያውና ተመሳሳይ ሆኖ ነው የምናገኘው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማኅበራዊ ቢሮ ይፋ ካደረገው መረጃ መረዳት እንደተቻለው የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር በየጊዜው እያሻቀበ እንጂ ጥቂት እንኳን ዝቅ ሲል አይስተዋልም።
ቢሮው በተሃድሶና ልማት ንዑስ የሥራ ሒደት መሪ በሆኑት አቶ ባህሩ አበበ በኩል ከስድስት አመት በፊት (ኦገስት 11, 2014) ይፋ እንዳደረገው ከሆነ በ1966 ዓ.ም. አዲስ አበባ ውስጥ ከአምስት ሺህ በላይ ጐዳና ተዳዳሪዎች ነበሩ።
የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት በ1996 (እ.ኤ.አ) የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትና እናቶችን ለማቋቋም ባዘጋጀው ጽሑፍ ላይ በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር 150,000 እንደሚደርስ፤ ከዚህ ውስጥ 100,000 ያህሉ በአዲስ አበባ እንደሚኖሩ ተመልክቷል። ይህም የጐዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር በዓመት በአማካይ ከአምስት ሺህ በላይ በሆነ ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱን ያሳያል። ይህ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ አሉታዊ ገጽታን ከማስፈን አልፎ ማኅበራዊ ቀውስን እያስከተለ መሆኑ ሁሌም ሳይገለፅ የማይታለፍ ነው።
ከሌላ ክልል ፈልሰውም ሆነ በከተማዋ የሚገኙ የጐዳና ተዳዳሪዎች እንደማንኛውም ሰው የኢኮኖሚው ተጠቃሚ መሆን አለባቸው በሚል እንደየዕድሜያቸውና አቅማቸው አረጋውያንን በመጠለያ፣ ሕፃናትን በማሳደጊያ እንዲገቡ፤ መሥራት የሚችሉትን የሥነልቦና ተሃድሶ ትምህርት በመስጠትና ማኅበራዊ ድጋፍ በማድረግ ሥራ እንዲያገኙ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት እየተሰራ ከሆነ ሰነባብቷል። እንዲህ ይሰራ እንጂ ችግሩን ግን ሲቀርፈው አይታይም።
ይህንኑ በተመለከተም ከላይ የጠቀስነው ቢሮ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ስለመቆየቱ የገለፀ ሲሆን ከላይ በገለፅነው ወቅት ብቻ ከ9,300 የጎዳና ተዳዳሪዎች ስራ እንዲያገኙና ወደ መደበኛ ህይወታቸው እንዲመለሱ ማድረጉንም ገልጿል።
በወቅቱ እንደተገለፀው ከሆነ ከእነዚህ ውስጥ 85 በመቶ ያህሉም ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ የወጡ ናቸው።
“85 በመቶ ያህሉም ከክልል የወጡ ናቸው” የሚለው በራሱ ለጥናት የተመቸና መፍትሄ ይፈለግለት ዘንድ መጠናት ያለበት መሆኑን የሚያመለክት ሲሆን፤ በክልሎች ያለው የኑሮ ዘይቤ ምን ቢሆን ነው ይህ ሁሉ ፍልሰት ወደ መዲናዋ የሚጎርፈው? የሚለውን ለይቶ በማወቅ መፍትሄ ይፈለግለት ዘንድ የሚያግዝ ነው። (የእርሻ መሬት ያለው ሁሉ እያከራየ ይመጣል የሚባል ጭምጭምታ ሁሉ ስላለ ማለት ነው።)
ከላይ ከጠቀስነው ቢሮ በተጨማሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጎዳና ተዳዳሪዎች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፕሮጀክት አማካኝነት ከ3ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ የጎዳና ተዳዳሪዎች የመኖሪያ ቤት መገንባትና መሰጠቱን፤ ህይወታቸውንም በዘላቂነት ለመለወጥ በሚያስችል መልኩ ድጋፍ መደረጉን በመገናኛ ብዙሀን ሲገለፅም ችግሩ ይቀረፋል እንጂ እየባሰበት ይሄዳል ብሎ ያሰበ አልነበረም። ይሁን እንጂ ከእለት እለት እየገዘፈ ከመሄድ አንድም ነገር ሲያቆመው አይታይም።
ባለፈው አመት (ሰኔ 15/ 2012 ዓ.ም) “የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኢትዮጵያን ማስቻል (Enabling Ethiopia) የተባለ የ5 ዓመት ፕሮጀክት ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ጀመረ።” በሚል ርእስ ለንባብ የበቃ ዜና መስማታችን የሚታወስ ሲሆን፤ ዜናውም “‘ኢትዮጵያን ማስቻል’ ፕሮጀክት ሲቀረጽ የአገሪቱን የ5 ዓመት የስራ ፈጠራ መሪ እቅድ ለማሳካት አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ታምኖበት ነው። ፕሮጀክቱ አገሪቱን የስራ ፈጠራ አጀንዳ እና የኮሚሽኑን አምስት አመት ስትራቴጂ ለመተግበር እንዲያግዝ ሆኖ የተቀረጸ ነው።
እ.ኤ.አ በኦክቶበር 2019 የተጀመረው የኮሚሽኑ የአምስት አመት የስራ ዕድል ፈጠራ መሪ ዕቅድ በግል ዘርፉና በፌደራል እንዲሁም በክልሎች ደረጃ ያሉ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በተናበበ መልኩ አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ፣ ኢንቬስትመንትን በማመቻቸት በ2015 (እ.ኤ.አ) 14 ሚሊዮን የስራ ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ ነው።” የሚል ነበር። በዚህም ብዙዎቻችን ደስ መሰኘታችን አይዘነጋም። “ለዚህ ፕሮጀክት ማስተርካርድ ፋውንዴሽን የ11.8 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።” የሚለውን የዜና አካል ስናክልበት ደግሞ ስለተግባራዊነቱ እንዳንጠራጠር ያደርገናል።
አቶ አለማየሁ ኮንዴ ኮይራ፣ የማስተርካርድ ፋውንዴሽን በኢትዮጵያ ዳይሬክተርን ጠቅሶ “ይህ ፕሮጀክት በ2030 (እ.ኤ.አ) ለ10 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ ዕድሎችን ለማመቻቸት ከተቀረጸው የማስተርካርድ ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ጋር አብሮ የሚሄድ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ የስራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው” በማለት ያሰፈረው ዜናው የዛሬ 10 አመት አገራችንና የወጣቶቻችን እጣ ፈንታ ምን እንደሚመስል ከወዲሁ ያሳያልና ለተግባራዊነቱ ባለን አቅምና ሀብት ሁሉ ለመተባበር ፈቃደኛነታችንን ከወዲሁ ስናረጋግጥ በደስታ ነው።
በተለይ በትንሹ “በኢትዮጵያ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት ቁጥር እየጨመረ ነው። አንድ መቶ ሺህ ሕፃናት በአዲስ አበባ፣ በሌሎች ከተሞች ደግሞ 600ሺህ ሕፃናት የጎዳና ተዳዳሪ ናቸው።” የሚለው ሲሰማ ለእንደዚህ አይነቱ ተግባር እጁን ወደ ኋላ የሚሰበስብ የለምና የሚተባበረው ወገን ብዙ እንደሚሆን ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
የዚህ አይነት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ህይወት ለመቀየርና ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታት በርካታ አገር በቀልና አለም አቀፍ የበጎ አድራጎትና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሲንቀሳቀሱ እንደ ነበር ይታወቃል። አሁንም እየተንቀሳቀሱ ነው። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ከብቅ ጥልቅ ያለፈ ገፍተው ሲሄዱ አይታዩም። ይህ ደግሞ የሚሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ሲሆን አንዱም የደጋፊ ማጣት ሲሆን፤ ዛሬ እዚህ የምናወራለት “መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት”ም ይህንኑ መከራ ተጋፍጦ በጥንካሬው እዚህ የደረሰ ድርጅት ነው።
በድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ መሰረት አዛገ የግል ተነሳሽነት የተመሰረተው “መሰረት የበጎ አድራጎት ድርጅት” በእልህ አስጨራሽ የግል ጥረት እዚህ የደረሰ ሲሆን ዛሬ በጥቂት ቀና ሰዎች ትብብርና በመንግስት የቦታ ድጋፍ ዛሬ ላይ ደርሶ በርካቶችን ከጎዳና ህይወት በማውጣት እየታደገ ይገኛል። ከእነዚህም አንዷ ሀረግ ሰላም ነች።
ሀረግ የ24 አመት ወጣት ነች። የመጣችው ከላስታ ላሊበላ ሲሆን ወደ አዲስ አበባ የመጣችውም ዝም ብላ እንጂ ስለ ከተማው ባህርይ ገብቷት ወይም በቂ መረጃ ኖሯት አይደለም። በቃ መጣች፣ ጎዳና ዳር ላስቲክ ወጠረች፣ መኖር ጀመረች፣ ልጅ ወለደች። ከእነ ልጁም ያንኑ ኑሮዋን ቀጠለች።
በዚህ አሳዛኝ የጎዳና ህይወት ውስጥ ሆና ነው እንግዲህ “መሰረት የሰብአዊ አገልግሎት ድርጅት” ሳታስበው የደረሳሰላት። አስፈላጊውን የአቀባበል ሂደት በማለፍም በድርጅቱ የሚሰጡ አገልግሎቶች ሁሉ ሙሉ ተጠቃሚ ለመሆን በቃች። ከአገልግሎቶቹም አንዱ ስልጠና ሲሆን ሀረግም የዚሁ እድል ተቋዳሽ ሆናለች።
በተረጋጋና ጥሩ ስሜት ውስጥ ያገኘናት ሀረግ “በአሁኑ ሰአት ያለው አያያዝ በጣም ግሩም ነም ነው፤ ምግብ፣ መኝታ፣ ንፅህና መጠበቂያና ሌሎችም እንደ ልብ ናቸው። ለእኛም ለልጆቻችንም። ምንም የጎደለ ነገር የለም።” ያለች ሲሆን በአሁኑ ሰአት ለወደፊት ህይወቴ ይበጀኛል ያለችውን ሙያ መርጣ ስልጠና በመውሰድ ላይ መሆኗንም ነግራናለች።
“ልብስ ስፌት እየሰለጠንኩ ነው።” የምትለው ሀረግ “ወደ ፊት ማሽኑን ካገኘሁ በስልጠና ባገኘሁት እውቀት ተጠቅሜ በሙያው በመሰማራት የእኔንም ሆነ የልጄን ህይወት እመራለሁ። ልጄንም አስተምራለሁ።” በማለት የወደፊት እቅዷንም ትናገራለች።
እዚህ ስትመጣ በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳልሆነች የምትናገረው እመቤት አሁን ግን እሷም፣ ልጇም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳሉ ትገልፃለች። “ይህ ሁሉ የሆነው ደግሞ በእናታችን (ወይዘሮ መሰረትን ነው) አማካኝነት ነው።” ስትልም የድርጅቱን መስራችና ስራ አስኪያጅ ታመሰግናለች።
ሀረግን “የቀረ ሀሳብ ካለሽ?” ብለናትም ነበር። እንደ ሌሎች ጓደኞቿ ሁሉ ለእሷም የወደፊት ችግር ሆኖ እፊቷ የተጋረጠውን “ያለኝ አንድ ሀሳብ ነው። እሱም የመጠለያ ማለትም ቤት ጉዳይ ነው። አዲስ አበባ የቤት ጉዳይ በጣም ችግር ነው። አሁን እኔን ከወዲሁ በጣም የሚያሳስበኝ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ነው። ከዚህ ስወጣ ወዴት ነው የምሄደው? ከእነ ልጄ እንደገና ወደ ጎዳና ልንመለስ ነው? እጨነቃለሁ በማለት አጫውታናለች። መንግስትን የማስቸግረው አንዲት ነገር ብቻ ነው።
ሽጉጥ የምልባት ቤት ብቻ። በቃ። እሷን ካገኘሁ አሁን እየሰለጠንኩ ባለሁት ሙያ ሰርቼ እኖራለሁ። ልጄንም ጥሩ ቦታ አድርሳለሁ” በማለት ጎዳናን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትሰናበተው ዘንድ መንግስትን ተማፅናለች።
እኛም እንላለን፤ “መሰረት የሰብአዊ አገልግሎት ድርጅት”ን የመሰሉ ተቋማት ይብዙ፤ ሀረግን የመሳሰሉና ጎዳና ላይ የወደቁ ይነሱ፤ ወደፊት እንደ ሀረግ በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጎዳና ሊወጡ የሚችሉ ካሉ አሁኑኑ መፍትሄ ይፈለግላቸው። ባለፈው አመት “ለከተማዋ ገጽታም ብቻ ሳይሆን የሕፃናቱንና የታዳጊ ሕፃናቱን ሕይወት ከጎዳና ለመታደግና ልመናን ለማስቀረት ሲባል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትና ወጣቶችን ከልመናና ከጎዳና ሕይወት፣ ብሎም ከገቡበት የተመሰቃቀለ የአኗኗር ዘይቤ ለማውጣትና ሕይወታቸውን በመቀየር ብቁ ዜጋ ለማድረግ የትግበራ ዕቅድ” ማዘጋጀቱንና ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ሁሉ መወያየቱን፤ ሥራውም ከ12 እስከ 14 ወራት ብቻ እንደሚፈጅ እንደሰማነው ሁሉ ውጤቱንም በጉጉት እንጠብቃለን። ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የበላይ ጠባቂ የሆኑበት ማኅበራዊ ትረስት ፈንድ፣ በጎዳና ላይ የሚኖሩ ደጋፊ ያጡ አረጋውያንን፣ የአዕምሮ ሕሙማንን፣ አካል ጉዳተኞችንና ለማኅበራዊ ችግር የተጋለጡትን በዘለቂነት ለመርዳት ይቻል ዘንድ ታስቦ የተቋቋመ ነውና ምኞቱ እውን ይሆን ዘንድ የሚመለከታቸው ሁሉ ይተባበሩት ዘንድ አደራ እንላለን።
አዲስ ዘመን ጥር 01/2013