የኢትዮጵያ ውግንና ከብሔራዊ ጥቅሟ ጋር ነው

በዓለም ፖለቲካና አጀንዳ በየጊዜው መቀያየር፣ መብዛትና የዲጂታላይዜሽን መስፋፋት እንዲሁም ጦርነቶች አሁን ላይ ለብዙ ሀገሮች የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ፈተና መሆኑ እሙን ነው። ባለፉት ዓመታት የዓለም ፖለቲካ እና አሰላለፉ እየተቀያየረ ነው፡፡ ከጎረቤት ሱዳን እስከ አውሮፓ እና መካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ጦርነቶች የዓለም አሰላለፍን እያመሰቃቀሉት ነው፡፡

በተለይም ከሦስት ዓመት በፊት ጀምሮ የፈነዳው የራሺያና የዩክሬን ጦርነት፣ ዓመት ያለፈው የእስራኤልና ሀማስ ጦርነት እንዲሁም በቅርቡ እስራኤልና ኢራን የገቡበት ፍጥጫም በርካታ ሀገራትን ጎራ እንዲለዩና በዓለም የፖለቲካ አሰላለፍ እንዲወዛገቡ ሲያደርግ እየተመለከትን ነው። በእዚህ ተለዋዋጭነቱ በፈጠነው አሰላለፍ ወቅት አስቸጋሪውን ጊዜ እንዴት ማለፍ ይቻላል? የሚለው ጥያቄ በሕዝብ ደረጃም መነጋገሪያ መሆኑ አልቀረም።

ሌላውን ወደ ጎን ትተን ኢራንና እስራኤል እያደረጉት የሚገኘውን ጦርነት በርካቶች ባለመረዳት ወይም አውዱን ካለማወቅ ሊሆን ይችላል። የሁለቱን ሀገራት ጦርነት ሃይማኖታዊ ሲያደርጉትና ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለየትኛው መወገን አለባት በሚል አጀንዳ ሲያነሱ ይታያል። በመሠረቱ የሁለቱ ሀገራት ጦርነት ሃይማኖታዊ አንድምታ ያለው አይደለም።

ኢትዮጵያ ደግሞ ከሁለቱም ሀገራት ጋር ወዳጅ ናት። በእዚህ ረገድ የመንግሥትም አቋም እንደ ሁልጊዜውም ገለልተኛ ነው። እንደ ሀገር የሚያዋጣውም ገለልተኝነት መሆኑን ብዙ ምሁራን ይመክራሉ። ለእዚህም ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገረ የዲፕሎማሲ ታሪክ ምስክር ናት።

በ1900 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተቋቁሞ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ተቋማዊ አሠራር ቢጀመርም የዲፕሎማሲ ግንኙነት ታሪኳ ግን ከእዚህም የቀደመ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። የኢትዮጵያ የገለልተኝነት፣ ለጋራ ጥቅምና መፍትሔ የመሥራት የዲፕሎማሲ አቋም ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመንግሥታት ልዩነት የትኩረት ለውጦች ሊኖሩት ቢችሉም ለማንም አካል ያልወገነ፣ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን መሠረት በማድረግ እዚህ ደርሷል።

ኢትዮጵያ የራሷን ነጻነት አጥብቃ የመፈለጓን ያክል የሌሎችን ነጻነት እና ክብርም አብዝታ ታከብራለች። በፍትሕ እና ፍትሐዊነት እምነቷ የጠነከረው ኢትዮጵያ ለጭቁኖች መብት ለተገፉት ነጻነት ብርቱ አጋር ናት። ኢትዮጵያ በሽምግልና የምታምን በገለልተኛ አቋም የማታወላውል ዲፕሎማት ናት። ኢትዮጵያ በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ገለልተኛ መሆን ካለባት ገለልተኛ ትሆናለች፤ ዓለም ጎራ ሲለይ ኢትዮጵያ ደግማ ደጋግማ ገለልተኛ አቋም አራምዳ የዓለምን ሚዛን የሳተ የዲፕሎማሲ መስመር ትዝብት ላይ ጥላለች።

በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በዓለም አቀፍ ሁኔታዎች በሚነሱ ግጭቶች ወይም በሁለት አካላት መካከል በሚነሱ ጦርነቶች ላይ ኢትዮጵያ አንድን ወገን መርጣ ከመደገፍ ይልቅ መካከለኛውን ቦታ ይዛ ሁኔታውን ማጤን ላይ እንደምታዘነብል የታሪክ ማስረጃዎች ብዙ ናቸው።

በዛጉዌ ሥርወ መንግሥት ከተከሰቱ ዓለም አቀፋዊ የታሪክ እውነታዎች መካከል ሊጠቀስ የሚገባው ዲፕሎማሲያዊ ጉዳይ የምዕራብ አውሮፓ የክርስቲያኑ ዓለም እና በአፍሮ ኤዥያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና በሰሜን አፍሪካ የኢስላሙ ዓለም መካከል ዓለም አቀፋዊ የበላይነት ለመያዝ ከ1095 እስከ 1365 ዓ.ም ድረስ ለ300 ዓመታት ያክል የመስቀል ጦርነት ሲካሄድ ኢትዮጵያ የነበራት ገለልተኛ አቋም ነው።

“የኢትዮጵያ የሁልጊዜ ውግንና ከብሔራዊ ጥቅሟ ጋር ነው” የሚባለው የገለልተኝነት አካሄድ ለጋራ ጥቅምና መፍትሔ የመሥራት የዲፕሎማሲ አቋሟ ከጥንት እስካሁንም የዘለቀ በመሆኑ ምክንያት ነው።

የኢትዮጵያ የዘመናት የዲፕሎማሲ መስመር ጥሎ ማለፍ ላይ የቆመ ሳይሆን ተደጋግፎ መዝለቅ ላይ የተመሠረተ ነው። የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መስመር ዘርፎ ማደግ ሳይሆን ተደጋግፎ መበልጸግን ያለመ ነው። ኢትዮጵያ የባሕር በር አልባ ሀገር ከመሆኗ በፊት የባሕር በሮቿ ጦር የሚሰበቅባቸው ሳይሆኑ ንግድ የሚጧጧፍባቸው የትብብር እና አብሮ የመኖር ቅን እና ክፍት በሮች ነበሩ። በመንግሥታት ቅብብሎሽ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ከወገንተኝነት ይልቅ ብሔራዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ ነው።

የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መርሕ ማንንም ወገን የማይደግፍ (Non-Aligned) በመሆኑ በተለያዩ ዘመናት በነበሩ ነገሥታትና መሪዎች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ላይ ያተኮረ የዲፕሎማሲ መርሕ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል። አሁንም የቀጠለው ይህ ነው።

ኢትዮጵያ በምትከተለው የውጭ ግንኙነት የማንም ሀገር ብቸኛ ወዳጅ አይደለችም፡፡ ከሁሉም ሀገራት ጋር ወዳጅነትን ትሻለች። ኢትዮጵያ የምትጎዳው የአንድ ኃያል ሀገር ብቻ ወዳጅ ስትሆን ነው።

ወደ አንድ ወገን ብቻ መግባት ከሌላኛው የሚመጣውን ጫና ለመቋቋም ዕድል አይሰጥም። የተናጠል ወዳጅነት መመሥረት ከባድ አጫ ያስከትላል። ኢትዮጵያ ደግሞ ሙሉ ትኩረቷ በልማትና ከድህነት መውጣት በመሆኑ ከሁሉም የሚገኘውን ጥቅም ማግኘት ይገባታል። ድሃ ሀገር እንደ መሆኗ ከድህነት ለመውጣት ከሁሉም በኩል የሚገኘውን ድጋፍ ማግኘት ትክክለኛው መንገድ ነው።

ኢትዮጵያ የተለያዩ ፖለቲካ ቡድኖች አባል ብትሆንም በአንድ የኢኮኖሚ ቡድን ብቻ ተወስና ከሌሎች ጋር ያላትን ዲፕሎማሲ አታቋርጥም። ለአብነት ኢትዮጵያ ወደብሪክስ ቡድን ከገባች በኋላ ከምዕራቡ ዓለም ጋር በዲፕሎማሲው መንገድ ትገነጠላለች የሚል እሳቤ ሳይሆን ሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅሟን በማስቀደም ከሁሉም ወገኖች ጋር እየሠራች ትቀጥላለች።

ይህ የባለብዙ ወገን ገለልተኛ አቋም ያለው ዲፕሎማሲ ከጉዳቱ ይልቅ ጥቅሙ እንደሚያመዝን ሳይታለም የተፈታ መሆኑ፤ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባጋጠሙን ፈተናዎች ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴያችን ውጤታማ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው።

ኢትዮጵያ በዘመናት ቅብብሎሽ ዲፕሎማሲዋን ከወገንተኝነት በራቀ መልኩ ያከናወነችበትን መንገድ የቀጣዩ ዘመን ዲፕሎማቶች በሰፊው ሊማሩበት የሚገባ ነው።

ዲፕሎማሲ አስቀድሞ ሊመጡ የሚችሉ ፈተናዎችን መገመት የመቻል ጥበብ፣ የስለላና የመረጃ አቅምን ማጎልበት፣ ሊከሰት የሚችለውን ፈተና የመቋቋም ብልሀት ጭምር ነው።

ኢትዮጵያ የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ፖሊሲዋ በመስኩ የምትታወቅበትና በጉልህ የምትጠቀስበትም ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል በራሷ ችግር ውስጥም ሆና በቻለችው አቅም ሁሉ በዓለም የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ የማይጠፋ ዐሻራ ማኖሯን ትቀጥላለች። የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ድንገት በቀልና ትናንት የተከሰተ አይደለም። ዲፕሎማሲው የትናንት መነሻ እርሾ ያለው የጋራ መተላለፊያ መንገድ ሆኖ ያገለገለና የነገውን የተሳሰረ ዕጣ ፈንታ በውስጡ የያዘ ነው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዘመኑን በዋጀ መልኩ በሰጥቶ መቀበል መርህ ስትራቴጂካዊ አቅሞችን ይበልጥ ለዓለም ማሳየት ግን ይጠበቅባታል። ኢትዮጵያ ለቀጣናው፣ ለአፍሪካና ዓለም ሰላም መጠበቅ እንዲሁም ለጋራ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ያላትን መሻት ይበልጥ በዲፕሎማሲው አማራጮች ማስተዋወቅ ይገባታል። በተለይም ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የፈጠረችውን ስትራቴጂክ አጋርነት ይበልጥ ማስፋትና አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል።

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ብሌን ከ6ኪሎ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You