ምህረት ሞገስ
የድጎማ ኩፖን ማብቂያው መቼ ነው?
ወይዘሮ ለይላ አወል ይባላሉ። የአምስት ልጆች እናት ሲሆኑ፤ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ልዩ ስሙ ኮልፌ አካባቢ ነው። አሁንም ልጆቻቸውን በዛው አካባቢ ሲያሳድጉ ችግር የሆነባቸው ዋነኛው ጉዳይ የልጆቻቸው የጠዋት እና የማታ ለሻይ የሚሆን ስኳር ማጣት ነው።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ስኳር እና ዘይት ማግኘት አዳጋች ነው።
‹‹እንኳን ለእንደኔ አይነት ጊዜ የሌለው ባተሌ ቀርቶ ቤት የምትውለዋ የቤት እመቤት ተሰልፋ ስኳር ማግኘት ያዳግታታል።›› የሚሉት ወይዘሮ ለይላ፤ ስኳር በነፃነት ያለኩፖን እና ያለሰልፍ የሚያገኙበት ጊዜ የናፈቃቸው መሆኑን ይናገራሉ።
‹‹በእርግጥ በወረዳው በኩል ብቻ አይደለም። ነዋሪው ላይም ከፍተኛ ችግር አለ። በአንድ ቤተሰብ ስም ተደጋጋሚ ኩፖን የወሰደ ሰው ቁጥር ብዙ ነው። በአንድ ቤት እስከ አምስት ሰው ኩፖን መውሰዳቸው ይነገራል። ስኳርም ወስደው አሳልፈው ለሌላ አካል የሚሸጡ ሰዎችም ቁጥር አነስተኛ አይደለም።›› ካሉ በኋላ፤ የዚህ ሁሉ ችግር መንስኤ ስኳር ያለኩፖን እንደተፈለገ በማንኛውም የሸቀጥ ሱቅ መገኘት አለመቻሉ መሆኑን ያስረዳሉ።
እንደወይዘሮ ለይላ ገለፃ፤ ስኳር ለመግዛት ወረዳም ሆነ ሸማች ማህበራት ሲኬድ ኩፖን የሚሰርቁ አካላት አሉ። ስኳር በቀላሉ ለማዳረስ በሚል አስር ሰው ኩፖን ይሰበሰባል። በመሃል አንዱ ኩፖን ይጠፋል። ኩፖኑ ለአምስት ዓመት በመሆኑ ሽፋኑን አስቀርተው የመሃሉን ወረቀት የሚገነጥሉም አሉ።
‹‹ኩፖን ጠፍቶብኛልም ሆነ ተበላሽቶብኛል ብሎ ወረዳ ኩፖን ማግኘት የሚታሰብ አይደለም›› የሚሉት ወይዘሮ ለይላ፤ እርሳቸውም ኩፖኑ ጠፍቶባቸው ከፖሊስ ጣቢያ ማረጋገጫ ቢያመጡም ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ኩፖን እንደከለከላቸው እና የሚያሳትመው የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ በመሆኑ ምንም ማድረግ አይቻልም የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው በመግለፅ ይህ ጉዳይ ይጠየቅልኝ ሲሉ ለዝግጅት ክፍሉ አሳውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ የህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ እና የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ሚኤሳ በሰጡን ምላሽ፤ በአጠቃላይ የድጎማ ምርቶች ስርጭት የሚካሄደው በኩፖን መሆኑ ይታወቃል።
ኩፖኑ የሚዘጋጀው በዋናነት በንግድ ቢሮ ነው። ከንግድ ቢሮ በኋላ እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ እና ወረዳ ባለው ኮታ ልክ ወይም ይህን አገልግሎት ያገኛሉ ተብሎ በሚታሰቡ የህብረተሰብ ክፍሎች ኮታ ልክ እያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ኩፖኑን ይረከባል። ክፍለ ከተሞቹ ወረዳ ላይ ላለው አካል ያወርዳሉ። በዛ መሰረት ማግኘት አለባቸው የተባሉ የከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ስርጭቱ ይካሄዳል።
ከዛ ውጪ በሚጠፋበት ጊዜ መተካት ይቻላል የሚሉት አቶ ዳንኤል፤ ንግድ ቢሮ ስለሚያሳትመው የለም ወይም እኛ ጋር አይመጣም መባል እንደሌለበት በማመልከት ማንኛውም ሰው ኩፖንም ሆነ መታወቂያ፤ መንጃ ፈቃድም ሆነ ፓስፖርት ቢጠፋ የራሱ የሆነ የመንግስት አሰራር በመኖሩ ይህንን የሚመራ አካልም አስፈላጊውን የማጣራት ሥራ ከሰራ በኋላ ስለመጥፋቱ ከህጋዊ አካል ማረጋገጫ ካገኘ በምትኩ ኩፖን እንዲሰጥ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ይገልፃሉ።
በክፍለ ከተማ እና ወረዳ ስለማይታተም የለም ማለት ተገቢ አለመሆኑን በማስታወስ፤ የጠፋውን ለይተው እና አረጋግጠው በደብዳቤ ማዕከሉን መጠየቅ እንደሚችሉ፤ የኩፖን እጥረት ካለም እጥረት መኖሩን ጠቅሰው እና የጠፋባቸው ሰዎች መኖራቸውን ያም በህጋዊ አካል መረጋገጡን አካተው ለንግድ ቢሮ የመጠየቅ ኃላፊነታቸውን ቢወጡ ቢሮ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ይገልፃሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ በተጠየቀው ልክ ምላሽ የሚሰጥበት ሁኔታ መኖሩን በማመልከት፤ ኩፖን ላይ ጠንከር የሚባልበት ምክንያት የድጎማ ምርቶቹን መጠቀም ካለባቸው ሰዎች ውጪ የሚጠቀሙ መኖራቸው እና አንዳንዶችም ከኮታቸው በላይ የመጠቀም እና የመሸጥ አዝማሚያዎች በመታየታቸው መሆኑን ያመለክታሉ።
እዚህ ላይ ለአብነት የድጎማ ዘይትን በመጥቀስ ብዙ ሰዎች በድጎማ ዘይቱ ከመጠቀም ይልቅ የድጎማ ዘይቱን ከገዙ በኋላ የሚሸጡበት ሁኔታ መኖሩን በማብራራት፤ ይህንን እና ተመሳሳይ ሌሎች ችግሮችን ለማቃለል በኩፖን አሰጣጥ ላይ ጥብቅ መመሪያ ተዘጋጅቶ እየተሰራበት ነው ይላሉ። እንደአቶ ዳንኤል ገለፃ፤ በእርግጥ የንግድ ስርዓቱ ቀጣና እና ወረዳ ድረስ በብሎክ ማኔጅመንት እየተመራ ይገኛል።
ይህ ብሎክ ማኔጅመንት ወረዳን፣ ቀበሌን እና መንደርን ሳይቀር በተደራጁ መልኩ ቁጥጥር ለማድረግ ያግዛል። አሁን ላይ ማን ደረሰው ማን አልደረሰውም የሚለው ጉዳይ ላይ የማጣራት ሥራ ይሰራል። በዚህ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ካሉ እና አላስፈላጊ ጥቅም የሚጠቀሙ ከሆነ እየተጣራ እርምጃ ይወሰዳል።
አሁን ላይ የሚታተመው በብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ሲሆን፤ በብዛት ታትሞ የተዘጋጀ በመሆኑ ችግር የለም። ስለዚህ አሁን ላይ ምንም አይነት የኩፖን እጥረት አላጋጠመም።
የታተመው ቢያልቅም በማንኛውም ጊዜ መታተም የሚችልበት ሁኔታ በመኖሩ የሚያሳስብ አይደለም ካሉ በኋላ፤ በድጎማ ምርቶች ላይ ማለትም ስኳር እና ዘይትም በበቂ መጠን መኖራቸውን በተወሰነ መልኩ የዱቄት እጥረት መኖሩ ግን የሚካድ አለመሆኑን ያመለክታሉ። ዱቄቱም ቢሆን በድጎማ ከሚገኘው ውጪ ገበያ ላይ በስፋት መኖሩን እና ሸማች ማህበራትም ያላቸው መሆኑን ያመለክታሉ።
በቀጣይ ዓመታት ያለው ዕድገት እየታየ ከኩፖን አሰራር ውጪ የሚታይበት ሁኔታ ይኖራል። አሁን ግን ባለው ሁኔታ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥርዓት እየተዘረጋ የሚገኝ መሆኑን በመጠቆም፤ እያንዳንዱ ግለሰብ ከሸማችም ሆነ ከነጋዴ ላይ ሲወስድ የድጎማ ምርቱን እንደወሰደ መልዕክት ይደርሰዋል። በዚህ ላይም ለሶስት ወር የቆየ የሙከራ ስራ ሲሰራ የነበረ ሲሆን፤ ይህ አሰራር ሲተገበር የድጎማ ምርቱ በአስተማማኝ መልኩ ለሚፈለገው አካል እንዲደርስ ያደርገዋል ብለዋል።
ስለዚህ በቀጣይ ስኳሩ ከፋብሪካ ሲወጣ መረጃ ይደርሳል። ከክፍለ ከተማ ሲወጣም መረጃው ለቢሮ ይደርሰዋል። ግለሰቡ ምርቱ እንደደረሰውም ንግድ ቢሮ መረጃ ስለሚያገኝ የሥርጭት ሂደቱ አስተማማኝ ይሆናል ይላሉ። በቀጣይ ይህ በዘመናዊ መንገድ የታገዘ የሥርጭት ሂደት በሁሉም ወረዳ እና ክፍለ ከተሞች በሸማች ተቋማት ተግባራዊ ይደረጋል።
ምንም እንኳ ኩፖን ለአምስት ዓመት እንዲያገለግል የተደረገ ቢሆንም፤ አገሪቱ እየተሻሻለች የስኳር አቅርቦት እያደገ ሲመጣ መንግስት ከድጎማ ስለሚወጣ ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ይቃለላል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013