ሙለቀን ታደገ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ቤት የወንጀል ህግ መምህር ዶክተር ስሜነህ ኪሮስ አሰፋ እንዳስታወቁት፤ ህወሓት በዓለም ላይ ካሉት አስር ወንጀሎች አራቱን በኢትዮጵያ ላይ ፈፅሟል። በአለም አቀፍ ከባድ ከሚባሉት አስር ወንጀሎች በሰሜኑ ህዝብ ላይ በተፈጠረው ትንኮሳ እና ተያያዥነት ያላቸው እንደሚገኙበት አስታውቀዋል።
ህወሓት አራት ዋና ዋና ወንጀሎችን (top four) የሚባሉትን ፈፅሟል ሲባል፤ አንደኛው ዘር ማጥፋት፣ ሁለተኛው በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች (crimes against humanity)፣ ሶስተኛው ደግሞ የጦር ወንጀል ሲሆን፤ የመጨረሻ እና አራተኛው ደግሞ የትንኮሳ ወንጀል(crime of aggression) ነው።
ነገር ግን እነዚህ በአለም አቀፍ ህግ አራቱ አደገኛ ወንጀሎች ይሁኑ እንጂ ወደ ሃገሪቱ ሲመጣ ከዚህ በፊት በእነ ጌታቸው አሰፋ በቀረበው ክስ በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች (crimes against humanity) መሆን ሲገባው፤ በኢትዮጵያ በወንጀል ህጉ በደንብ ስላልተደነገገ አቃቤ ህግም ክስ መመስረት ስለተቸገረ በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ( crimes against humanity ) በሚል ክስ አልተመሰረተም። በመሆኑም የተከሰሱት ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም በሚል ነው።
አብዛኛዎች ደግሞ የተከሰሱት በሙስና ወንጀል ነው። በጦር ወንጀል የሚለው በወንጀል ህጉ ቢኖርም መንግስት የራሱን ጥቅም ለማስከበር በጦር ወንጀል ከመክሰስ የታቀበ የሚመስላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
‹‹ብዙ ሰዎች ምንም አይነት ቅጣት በህወሓት አመራሮች ላይ ቢወሰድ ፍታዊ ፣ ተመጣጣኝ እና አስተማሪ አይደለም ሲሉ ይሰማል።›› የሚሉት ዶክተር ስሜነህ፤ ይህ ስህተት ነው። የህወሓትን አመራሮች ለህግ ለመቅረብ አሁን መንግስት እየሄደበት ያለው እና የሚያደርገውም ማንኛውም ቅጣት ተመጣጣኝ ይሆናል። የህወሓት ጥፋት ከተጠና በኋላ ሊተላለፍ የሚችለው ውሳኔ የእስራት ወይም የሞት ቅጣት መሆኑ እንደማይቀር ያመለክታሉ ።
ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር እንደ ወንጀል አይነቱ የሚወሰን መሆኑን በማስታወስ፤ በእርግጥ በህወሓት የተፈፀመው ወንጀል በጣም ከባድ እና የተለያዩ አይነት ወንጀሎች በመናቸው፤ መንግስት የትኛው ላይ ተመርኩዞ በዋናነት ክስ እንደሚያቀርብ ፣ ማን ማን ላይ ክስ እንደሚያቀርብ ግን ገና አልተለየም ይላሉ። ምክንያቱም ሂደቱ ገና ስለሆነ እና የተያዙት እና ያልተያዙት እንዲሁም የተሳትፎ ደረጃቸውም ገና አለመታወቁ መዘንጋት እንደሌለበት ይገልፃሉ።
ነገር ግን የተሳተፉ የሰዎችን ብዛት ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለማየት ከተሞከረ መንግስት ክስ መመስረት የሚችለው እና የሚገባው ዋና ወንጀል አድራጊዎች ላይ ነው ይላሉ።
ሌላው በዶክተር ስሜነህ የተገለፀው እና መታየት ያለበት የወንጀሎችን አይነት ነው። ምን ምን ወንጀሎችን የሚያቋቁሙ ፍሬ ነገሮች እንዳሉ ሁሉም ባይታወቁም ህዋሓት የአገር ክዳት ወንጀል ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል እና የሽብር ወንጀል ፈፅሟል የሚሉት ጉዳዮች ሊነሱ ይችላሉ።
እንደእርሳቸው ገለፃ፤ የጦር ወንጀል የሚለው ትንሽ አነጋገሪ ቢሆንም፤ በህወሓት ተፈፅሟል ባይ ናቸው። በአጠቃላይ ሲገለፁ ወንጀሎቹ ትልልቅ ናቸው። ነገር ግን እነኝህ ሁለት ሶስቱ ብቻ እንኳን ቢወሰዱ የፈፀሙት ብዙ ወንጀሎችን የሚያቋቁም መሆናቸውን ይገልፃሉ። ነገር ግን ተዘውትረው በሚሰሙት ወንጀሎች እንኳን ይከሰሱ ቢባል ሊኖር የሚችለው ቅጣት አብዛኛዎቹ የእድሜ ልክ እስራት የሚያስቀጡ አንዳንዶቹ ደግሞ በሞትም የሚያስቀጡ ናቸው።
የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስቀጣው ከአምስት አመት እስከ ሃያ አምስት አመት ነው። ነገር ግን የጦር ወንጀል የተባሉት የአፈፃፀም ሁኔታቸው እየታየ በሞትም የሚያስቀጡ አሉ ካሉ በኋላ፤ የሙስና ወንጀሎች ግን ሁሉም የሚያስቀጡት በእስራት ብቻ መሆኑን ይጠቁማሉ።
ሌላው እንደዶክተር ስሜነህ ገለፃ፤ በህወሓት የተፈፀመው የሽብር ወንጀል ነው። ይህ ወንጀል በሞት ቅጣት ያስጣቀል። አዲሱ የሽብር ወንጀል አዋጅ ቁጠር 11/ 76 ሞት ቅጣት እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል። ከዚያ በተረፈ ቅጣት ሲወሰዱ ማክበጃ የሚባሉ ጉዳዮች ስላሉ ቅጣቱ እንደዚሁ እየጨመረ ይሄዳል። ነገር ግን በዋናነት የሚታየው የሞት ቅጣት አይደለም ። በመርህ ደረጃ የሞት ቅጣት ሊኖርም አይገባውም ካሉ በኋላ፤ ከሙያቸው አንፃር የሞት ቅጣትን እንደማይደግፉ ይናገራሉ።
የቅጣት አላማ በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ መሰረት በቀል አይደለም። የቅጣት አላማ ተቀጭው እንዲማር ሌላው ህዝብንም ለማስተማር ነው። ተቀጭው ጥፋቱን አውቆ ተፀፅቶ መልካም ዜጋ እንዲሆን ማድረግ እና ተቀጭው እንደገና ተመልሶ ሌላ ወንጀል እንዳይፈፅም ማድረግ ነው የሚሉት ዶክተር ስሜነህ፤ የኢትየጰያ የወንጀል ህግ ውስጥ ያሉ የቅጣት ዋና ዋና አላማዎች የተለያዩ መሆናቸውን እና ቅጣት ማለት ግን በቀል አለመሆኑን ይናገራሉ።
‹‹አስተማሪ እርምጃ በህወሓት ላይ ካልተወሰደ የሚቀጥለው ትውልድ ስለህግ የሚኖረው አመለካከትስ ምን ሊሆን ይችላል? የሚሉ ወገኖች በብዛት ይሰማሉ።››
የሚሉት ዶክተር ስሜነህ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ቅጣት ያስተምራል ብለው እንደማያምኑ ያስረዳሉ ። የወንጀል ህግ ሲያጠኑ እና ሲያስጠኑ መኖራቸውን በማስታወስ፤ ቅጣት ስለማስተማሩ በወንጀል ህግ ፍልስፍና ውስጥ የተረጋገጠ አለመሆኑን ይናገራሉ።
ነገር ግን እነኝህን ሰዎች ከማህበረሰቡ ዘወር አድርጎ ማቆየት የግድ መሆንን ገልፀው፤ ሌላውን ማህበረሰብ ሊያስተምር የሚችለው ቅጣት ከህብረተሰቡ ዘወር ማድረግ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደእርሳቸው እምነት፤ 10 አመት ማሰር በራሱ እጅግ ጥሩ አስተማሪ ነው። ምክንያቱም ከአንድ ሰው ላይ አስር አመት በመቀነስ የሚቀጣው ሰው አምራች ዜጋ በሆነበት የህይወቱ ወርቃማ ጊዜ መቀጣቱም አነስተኛ ቅጣት የሚባል አለመሆኑን ያመላክታሉ።
የወንጀል ህግ መጀመሪያ የሚያስገድደው፣ የሚመክረውም ሆነ የሚያስጠነቅቀው ወንጀል እንዳፈፀም ነው። ከዚያ በተረፈ ደግሞ በጁንታው እንደተሰሩት አይነት አፀያፊ ወንጀሎች ደግሞ የሚያስፈልጋቸው የግድ የወንጀል ህግ አይደለም። ከኢትዮጵያ የስነ ምግባር ደንቦች ጋር ሁሉ አያይዞ መመልከት ያስፈልጋል።
ህወሓትን የመሰለ አረመኔ ከተወገደ እንደእነርሱ አይነት አጸያፊ ተግባር በኢትዮጽያ መቼም ይደገማል የሚል እምነት እንደሌላቸው አመልክተው፤ ነገር ግን ስለማይደገም ደግሞ ዝም ተብሎ መታለፍ እንደሌለበት እና ይህን ማድረግ አስነዋሪ እና አስፀያፊ ወንጀላቸው በአገሪቱ እንዳይኖር አረንጓዴ መብራት እንደማብራት ስለሆነ በህግ በቃል ኪዳኑ መሰረት ቅጣት መኖር እንዳለበት አመላክተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013