ለምለም መንግሥቱ
ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ የሥርጭት አድማሱን ከማሥፋቱም በላይ ባህሪውን ቀይሮ የሰው ልጅን በመቅጠፍ ይኸው ክንዱን ካፈረጠመ አመት ሊሞላው የሁለት ወር ዕድሜ ነው የቀረው፡፡ከወደ እንግሊዝ የሚሰራጨው መረጃ እንደሚያመለክተው በአዲሱ የቫይረሱ በሽታ በቀን የሚያዘው ሰው ቁጥር 50 ሺ እየደረሰ ነው፡፡በአሜሪካና በሌሎችም ሀገሮች እንዲሁ አሳሳቢነቱ ቀጥሏል፡፡
ወደ ሀገራችን ስንመጣም በየዕለቱ የሚያዘውና የሚሞተው ሰው ቁጥር ሥጋት ፈጥሯል፡፡እስካሁን በሀገሪቷ ባለው የመመርመር አቅም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከ125ሺ በላይ ልቋል፡፡የሞተው ደግሞ ከአንድ ሺ በላይ ሆኗል፡፡ከበሽታው ያገገመው የሚያስደስት ቢሆንም ውጤቱ ግን ሊያዘናጋን አይገባም፡፡
ጤና ሚኒስቴር ምክረሀሳቡን ጨምሮ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማሳወቅ መረጃ መሥጠቱን አላቋረጠም:: ህሙማንን የማሥተናገዱ ሥራም አቅም የሚፈትን እየሆነ መምጣቱንም እያስታወቀ ነው፡፡ነገር ግን ቫይረሱን በመከላከል በኩል ያለው እንቅስቃሴ በአንድ ጆሮ እየሰሙ በሌላው ማፍሰስ እየሆነ በሚፈለገው ያህል የመከላከሉ ሥራ ውጤት አላመጣም፡፡
ርቀትን መጠበቅ፣እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና መታጠብ ወይንም የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታዘር መጠቀም፣አፍና አፍንጫን መሸፈን፣በለቅሶና በተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶች ሥፍራ የህዝብ ቁጥር መቀነሥ እንዳለበት ለመከላከል የሚረዱ መልዕክቶች ቫይረሱ ከተከሰተ ጀምሮ ያለመታከት ሲተላለፍ ቆይቷል፡፡አንዳንዶቹ መልዕክቶችም አስገዳጅነት አላቸው፡፡ለአብነትም በቀብር ሥነሥርዓት የሚታደሙ ሰዎች ቁጥር ተወስኗል፡፡
መልዕክቶቹና በመንግሥት የተላለፉት ውሳኔዎች ተናብበው ውጤት እያስገኙ አይደለም፡፡ማህበረሰቡ ወደቀድሞ እንቅስቃሴው ሙሉ ለሙሉ ገብቷል ማለት ይቻላል፡፡ በቀብር ላይ የሚታደመው ሰው ከቀድሞው አልቀነሰም፡፡ እንደውም በቀብሩ ላይ የተገናኙ ሰዎች በመሳሳም ጭምር ሰላምታ ሲለዋወጡ ነው የሚሥተዋለው::
ከመከላከያ መንገዶቹ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀም የተሻለ ተደርጎ ቢወሰድም በተደጋጋሚ እንደሚባለው ሰዎች ድንገት በመንገድ ላይ በህግ አካል ብንጠየቅ ከሚል የመነጨ እንጂ የቫይይረሱ ስርጭት የሚያመጣውን ጉዳት በመፍራት አይደለም፡፡ በህዝብ ትራንስፖርት ውስጥ ሲጠቀሙ እንዳይከለከሉ መከላከያውን በእጃቸው በመያዝ ወይንም አገጫቸው ላይ በማድረግ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡
ወረርሽኙ በሀገራችን እንደተከሰተ መሸፈኛውን በማያደርጉ ሰዎች ላይ ይወሰድ የነበረው ጥብቅ ቁጥጥርና ከመንገድ ላይም ተወስደው በአንድ ቦታ እንዲቆዩና ግንዛቤ እንዲኖራቸው የተደረገው ጥረት ጥሩ ማስጠንቀቂያ የነበረ ቢሆንም በጉዳዬ ላይ የገፋበት አካል ግን የለም፡፡
ትራንስፖርት ተጠቃሚው፣የዕለት ጉርሱን ለማሟላት ወዲያና ወዲህ የሚለውና ሌላው ማህበረሰብ ጥንቃቄ ማድረጉን እየፈለገ ግን አስገዳጅ በሆነ ሁኔታ እራሱን ለቫይረሱ እያጋለጠ መንቀሳቀሱን ተያይዞታል፡፡
በግለሰቦች ደረጃ የሚደረገው ጥንቃቄም አንዱ ከሌላው ይለያል፡፡ አንዳንዶች ውጭ ውለው ወደቤታቸው ሲመለሱ የለበሱትን ልብስ ቀይረው ከሌላው ልብሳቸው ጋር እንዳይቀላቀል እስከማድረግ እርምጃ ድረስ የደረሰ ጥንቃቄ ሲያደርጉ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡
ከቤተሰባቸው ውጭ እንግዳ ላለመቀበልም የወሰኑ ሰዎች መኖራቸውን ሰምተናል፡፡ ጉንፋን ሲይዛቸውና ጥርጣሬ ሲኖራቸው ያለሀኪም ትዕዛዝ እራሳቸውን ከሌላው በማራቅና በመገለል ውጤቱን የሚከታተሉ በጥርጣሬም ምርመራ በማድረግ ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋገጡም ሰዎች ነበሩ፡፡
አሁን ያለው ሁኔታ ግን እንዲህ አይደለም፡፡ በተቃራኒው አብዝተው የሚጠነቀቁትን ሳይተቹ አይቀርም:: ቫይረሱ በሌሎች የዓለም ሀገራት እያደረሰ ካለው ጉዳት ጋር እራስን በማወዳደር በኢትዮጵያ የለም ወደሚል ድምዳሜ የደረሰ መዘናጋት ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል፡፡
የሚገርመው ደግሞ መዘናጋቱ ጥሩ ግንዛቤ ይኖራቸዋል በሚባሉ ተቋማት ውስጥም ተመሳሳይ ችግር መኖሩ ነው:: የንጽህና መጠበቂያ ከማዘጋጀት ጀምሮ ርቀትን በመጠበቅ ይሰጥ የነበረው መሥተንግዶ ተቀዛቅዟል ብቻ ሳይሆን በአብዛኞቹ ቀርቷል ማለት ይቻላል፡፡
በየተቋሞቻቸው ለሰራተኞቻቸው የትራንሥፖርት አገልግሎት ያመቻቹ ተቋማት ሠራተኞቻቸው የሚጓጓዙበት ትራንስፖርት የህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ እንጂ የአንድ ተቋም ሰራተኛ የሚያጓጉዙ አይመሥሉም፡፡ ከዚህ የትራንስፖርት አገልግሎት የወረደው ሰራተኛ ከሌላው ሰራተኛ ጋር ይቀላቀላል፡፡
የሚገርመው ተቋማቱ በውስጥ የአገልግሎት መሥጫ ክፍሎቻቸው የቅድመጥንቃቄ ማስታወቂያ ለጥፈው ከሌላው ለመከላከል ጥረት ሲያደርጉ እነርሱ ለሰራተኞቻቸው የሚያደርጉት ጥንቃቄ አናሳ መሆኑ ነው፡፡
መንግሥት ያጋጠመውን ውስጣዊ ችግሮች ለመቅረፍ በህግ ማሥከበር ላይ የተጠመደ ቢሆንም የመከላከሉን ሥራ ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላት ወቅቱ ከሚጠይቀው ጋር ተከታትለው ቫይረሱን የመከላከሉ ሥራ ቸል ሊሉት እንደማይገባ ግንዛቤ መያዝ አለበት፡፡ቫይረሱ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ዜጎችን ከጎዳ ህግ ከማስከበሩም በላይ ፈተና እንዳይሆን መጠንቀቁ ለነገ የሚባል መሆን የለበትም፡፡
ቫይረሱ ከተከሰተ ጀምሮ ለቅድመ መከላከያዎች በግለሰብና በተቋማት የወጣውን ወጭ ቀመር የሚያዘጋጁ የሂሳብ ባለሙያዎች አስልተው ባያሳውቁንም ከፍተኛ መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡
በቀላሉ ሥሌት እንኳን አምስት ቤተሰብ ለንጽህና መጠበቂያ ከሚውለው ሳኒታይዘር ውጭ ለአፍና አፍንጫ መሸፈኛ የሚያወጣው ወጭ ለቤተሰቡ ቁርሥ የሚገዛውን ዳቦ ቀንሶበታል፡፡እንዲህ እያሰላን ቫይረሱን ብንከላከል ለውጥ ልናመጣ እንችላለን ብሎ መንቀሳቀሱ የሚበጅ ይመሥለኛል፡፡
ኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረሥ ወረርሽኝ እንዳደረሰው አይነት ጉዳት እስኪያጋጥምና የእያንዳንዱን ቤት እስኪያንኳኳ የምንጠብቅ ከሆነ ጉዳቱ ከግለሰብ አልፎ ሀገራዊ እንዳይሆን መጠንቀቁ የተሻለ ነው፡፡
ምንም እንኳን ጥንቃቄው ከእያንዳንዱ ዜጋ የሚጠበቅ ቢሆንም በመንግሥት የመከላከያ ሥትራተጅ ተዘርግቶ በተቋም፣ በማህበራትና በተለያዩ አካላት የመከላከሉ ሥራ ተደራሽ የሚሆንበትን አሰራር መከተል የግድ የሚል ነው፡፡
ኮቪድ 19 ቫይረሥ ወረርሽኝ በጤና፣በገንዘብ ወጭ፣የሥነልቦና ጫና በማሳደር ጥይት የሌለው ቃታውን እየሳበብን ስለሆነ ለአፍታም ቢሆን ለቃታው እንዳንዘጋጅ፡፡ እኛም ሌላውም እንዲኖር ከተሳበብን ቃታ እናምልጥ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013