መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ ኢትዮጵያ ካላት የታዳሽ ሃብት ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው 10 በመቶ ብቻ ነው። ይህ ማለት ገና ነገሮች ሁሉ በጅማሮ ላይ ናቸው፡፡ ብዙ ሊገኝበት፤ ብዙ ሊታፈስበት በሚገባው ዘርፍ ላይ ወደ ኋላ ቀርታለች፡፡ ይህ የሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ቢሆንም ችግሩን ውስጣዊ እና ውጫዊ መሆናቸውን በማሳያዎች ማስረዳት ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ በታዳሽ ኢነርጂ ላይ በሰፊው ወደ ልማት ለመግባት በምታደርገው ጥረት በርካታ ውጫዊ ፈታኝ ሁኔታዎች ተደቅነውባታል፡፡ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ይህን እውን እንዲሆን መፍቀድ ቀርቶ ዓላማውን በሐሳብ ደረጃ መኖሩ በራሱ የማያባራ የራስ ምታታቸውን ይቀሰቅስባቸዋል፡፡ ይህን መሰል ሀሳብ ሲሰሙም መፈጠራቸውን ይጠላሉ፤ ከውስጣቸው ያንዘረዝራቸዋል፡፡
ለአብነትም ኢትዮጵያ ካላት ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል ውስጥ አንዱ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ (ከውሃ የምታመነጨው) ኃይል እጅግ ግዙፍ አቅም ያላት መሆኑ ነው፡፡ ይህን እውን እንዳይሆን በርካታ የኢትዮጵያ ጠላቶች በእያንዳንዱ ሥራ እግር በእግር እየተከታተሉ የማደናቀፍ ሙከራዎችን እያደረጉ ነው። ለዚህ ማሳያ ጥቂት ምሳሌዎችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ሁኔታው ያልተዋጠላቸው አካላት ኢትዮጵያን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የማወክ ሥራ ላይ ተጠምደዋል፡፡ ወሣኝ በሚባሉ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ መድረኮች ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ጀምሮ በስውር ዲፕሎማሲ ጫና ብሎም ጂኦ-ፖለቲክስ በማወክ እጃቸውን ያስረዘሙ ሀገራት በርካቶች ናቸው፡፡ አሁናዊ የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ትኩሳት በተለይም የግብፅ በሞቃዲሾ አምባ ዙሪያ መሽከርከር ዋነኛ ምክንያት ይኸው ነው ፡፡
በአሁኑ ወቅትም ምሥራቅ አፍሪካን ማወክ እና በአብዛኛው ደግሞ ኢትዮጵያን ከጉዞዋ መግታት የሚለው እሳቤ የዚሁ አኩይ ተግባር አካል ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ በግልገል በለስ ላይ ሲካሄድ የነበረውም ልማት ለማደናቀፍ ሲደረግ የነበረው ሙከራም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ በተመሳሳይ ጊቤ እና ሌሎች የኃይድሮ ኤሌክትሪክ የኃይል ማመንጫ ግንባታዎች ሂደት ላይ ኢትዮጵያን በከፋ ሁኔታ እንድትፈተን አድርገዋታል፡፡
ዓለም አቀፍ የገንዘብ አበዳሪ ተቋማትን በር በማንኳኳት ብድር ከማስከልከል እስከ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ያልሞከሩት አማራጭ፤ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ ይህ የታሪካዊ ጠላቶች አካሄድ በቀጣይም ይበልጥ በእልህ የሚገፉበት እንጂ አሜን ብለው የሚቀበሉት አለመሆኑን ብዙ አስረጂዎችን በመጥቀስና ቢሆኖችን በማስቀመጥ ሁኔታዎችን ከዚህ በላይ መተንተን ይቻላል፡፡
ውጫዊ ጫናዎች እንደተጠበቁ ሆነው ውስጣዊ ችግሮችን መመልከትም አስፈላጊ ነው፡፡ ኢነርጂውን ወደ ቢዝነስ በመቀየር ብሎም ማኔጅ ማድረግና ሥርዓት መገንባት ላይ እንደ ሀገር ብዙ አልተሠራበትም፡፡ ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ኢነርጂ ትልቅ ዲፕሎማሲ መሥራት ትችላለች፡፡ የቀጣናው ሀገራትን ጨምሮ በርካታ አፍሪካ ሀገራት በታዳሽ ኃይል አቅም ከኢትዮጵያ አይስተካከሉም፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች ሀገራትም የኤሌክትሪክ ኃይል አሻግሮ ለመሸጥ ስትራቴጂክ ቦታ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስመጥር የሆኑ ምሑራንና እና ጥናቶችም የሚያመለክቱት ኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ቋት መሆኗ ነው፡፡ ዳሩ ግን ይህን ሀብት አውጥቶ ለመጠቀም በመጀመሪያ ደረጃ ዕውቀትና ቴክኖሎጂ በሀገሪቱ በስፋት ሥራ ላይ እየዋለ አይደለም፡፡
በሌላኛው በኩል ደግሞ በሀገሪቱ ውስጥ ቀጣይነት ያለው የተረጋጋ ሠላም አለመስፈን ባለሀብቶች በዘርፉ በስፋት እንዳይሳተፉ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በተጨማሪም የፖለቲካው ፍኖተ ካርታ እና የማኅበረሰቡ እሳቤ ብሎም የምጣኔ ሃብት ዕድገት እየተጓዘበት ያለው ሐዲድ የተራራቀ መሆን ሁኔታዎችን የበለጠ አስቸጋሪ አድርገውታል፡፡
ኢትዮጵያ ከኃይድሮ ኤሌክትሪክ ባለፈም በሶላር ኢነርጂው በሰፊው አቅም ያላት ሲሆን ወደ ምርት በአግባቡ አልተገባም፡፡ በዘርፉ ላይም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመርቂ ጥናትና ምርምር ሥራዎችን በበቂ ሁኔታ አከናውነዋል ማለት አያስደፍርም፡፡ በባሕሪው የኢነርጂ ዘርፍ ቅንጅታዊ አሠራር ይፈልጋል፡፡ በዚህ ላይም በበቂ ሁኔታ አመሠራቱን ከሁኔታዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ በታዳሽ ኃይል ላይ ለመሥራት፤ ካላት ሃብት በላይ ያላት የአየር ንብረት በጣም ምቹ የሚባል እና ሌሎች አልሚዎችን ለመሳብ የሚያስችል ነው፡፡ በዘርፉ ላይ በትክክል የተቀመጡ እና የተቀናጁ ብሎም ምሑራዊ እሳቤዎችንና ትንታኔዎችን ያካተቱ ዶክመንቶች በቀላሉ አይገኙም፤ ቢገኙም በጣም በተቆራረጠ እና ቅንጅት በጎደለው መልኩ ነው፡፡
በተለይም ደግሞ የግል ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ እንዲሰማሩ ሰፋ ያለ መግቢያ እና ዕድል ሊመቻች ይገባል፡፡ ይህ አንድም ባለሀብቶች ሀገራዊ አቅሙን ተጠቅመው በብዛት ኢነርጂ እንዲያመርቱ ያስችላል፤ ኃይሉ ታዳሽ በመሆኑ በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ቢውልም ታዳሽ ካልሆኑ የኢነርጂ ምንጮች አኳያ አዋጭ መሆኑም ዘላቂ ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል፡፡ ዘርፉ ልዩ ትኩረት ከተሰጠው ሚሊዮን ዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርም ይታመናል፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ ታዳሽ ያልሆኑ ኃይሎች ጥቅም ላይ ውለው ወይንም የአገልግሎት ዘመናቸው ሲያበቃ ብሎም ተረፈ ምርቶችን ለማስወገድ ከፍተኛ ወጪ መጠየቁ፤ ታዳሽ ያልሆኑ ኃይሎች መጠቀም ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ወይንም ገንዘብ የሚጠይቅ መሆኑ በቋሚነት ሀብት እንዲመደብለት ያስገድዳል፡፡
ለአብነት ኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶች ለማስገባት በዓመት በአማካይ 6ነጥብ4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች፡፡ ይህ እጅግ ከፍተኛ የሚባለው ነው፡፡ ይህንን ሀገራዊ ወጪ ለመቀነስ ሆነ ለማስቀረት በታዳሽ ኃይል ላይ በሰፊ መሥራት እና በቀጣናው የኢነርጂ ተደራሽነት ላይ ማተኮር አዋጭ ነው፡፡ በተለይም አጀንዳ 2063 ለማሳካት በዋናነት ከጠቀመጡ ግቦች አንዱ አፍሪካ በኢነርጂ መሠረተ ልማት ማስተሳሰር መሆኑም እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ የሚታይ ነው፡፡
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ አንጻር፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ካላት እምቅ አቅም አኳያ ብዙ መሥራት የሚጠበቅባት ቢሆንም ጎን ለጎን የዘርፉ ተጠቃሚ እንዳትሆን ጠላት የሚሸርባቸውን ማለቂያ የሌላቸው ሴራዎች አውቅ ተዘጋጅቶ የመመከት ሥራዎችን በስፋት መሥራት ይጠበቅባታል ።
ለዚህ ደግሞ ለኢነርጂ ዲፕሎማሲ ትኩረት በመስጠት የቀጣናውን ሀገራት ስስ ብልት ማወቅና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ወዳጅን በሁሉም መስክ ማፍራት እጅግ አስፈላጊው ነው፡፡ ዲፕሎማሲው በየዘርፉ አስረጂ ሁኔታዎችን ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ የኢነርጂ ዲፕሎማሲ የኢትዮጵያ ትልቅ የቤት ሥራ መሆን አለበት ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን መስከረም 10/2017 ዓ.ም