የኮሮና ቫይረስ ከተከሰተ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በዓለም ላይ የሚገኙ ሁሉንም ሀገራት ከማካለሉም አልፎ 90 ሚሊዮን የሚጠጋ የኣለም ህዝብ በቫይይረሱ ተይዟል፤ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችንም ህይወት ቀጥፏል፡፡ በሀገራችንም ከ1ሺ በላይ ሰዎች በዚሁ ቫይረስ ምክንያት ላይመለሱ አሸልበዋል፡፡
ይህንን ቫይረስ እጅግ በጣም ዘመናዊ የሕክምና ተቋማት፣ ዘመኑ ያፈራቸው የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች፣ የሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች፣ እንዲሁም የተሟላ የሳይንስና የቴክኖሎጂ አቅም ያላቸው የበለፀጉ አገራት ጭምር ሊቋቋሙት አልቻሉም፡፡
አንዳንዶቹ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚስችል ክትባት አገኘን ቢሉም ፈዋሽነቱ ምን ያህል አስተማማኝ ነው ከሚለው ጥያቄ አንስቶ በተለይም ቫይረሱ መልኩን ቀይሮ ለሁለተኛ ዙር ጥት መዘጋጀቱ ቫይረሱ አሁንም የዓለም ስጋት ሆኖ እንዲቀጥ አስችሎታል፡፡በዚሁ ምክንያትም የኣለም ሀገራት አሁንም የመከላከያ ጥንቃቄዎችን በመተግበር ቫይረሱን ከመከላከል ውጪ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ እየተናገሩ ነው፡፡
ቫይረሱ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎም ህብረተሰቡ ሊወስዳቸው ስለሚገቡ የጥንቃቄ እርምጃዎች በጤና ባለሙያዎችና በመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎች ጭምር በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን እነዚህ ጥረቶች ለውጥ ያመጡ ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እነዚህ የጥንቃቄ እርምጃዎች እየተዘነጉ መጥተው ጭራሽ ቫይረሱ የሌለ እስኪመስል ድረስ መዘናጋቱ ጫፍ ደርሷል፡፡
ኮሮና ቫይረስን መከላከል የሚቻለው በተቻለ መጠን እንቅስቃሴን በመገደብ፣ ሰዎች የሚበዙባቸው ሥፍራዎች ባለመገኘት፣ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅና እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና በመታጠብ ወይም በፀረ ተዋህስያን በማፅዳት እንደሆነ በሚመለከታቸው የጤና አካላት እየተነገረ ቢሆንም አሁንም ያልታረሙ ተግባራትእዚህም እዚያም ይስተዋላሉ፡፡
በታክሲዎች ላይ ከተቀመጠው ገደብ በላይ ደርቦ መጫን፤ወደ ተለያዩ ክልሎች በሚኒባሶችና በዶልፊኖች በተፋፈገ እና ጥንቃቄ በጎደለው መልኩ የምሽት ጉዞዎችን ማድረግ፤ያለ ጥንቃቄ በየገበያ ቦታው ተጨናንቆ መገበያየት፤ መጠጥ ቤቶች ማስክ ባላደረጉ ሰዎች መጥለቅለቅ ፣ በጫት መቃሚያዎችና በሺሻ ማጨሻዎች መታደም ያልተቀረፉ አሳሳቢ ችግሮች ናቸው፡፡
እነዚህ ችግሮች በፍጥነት ካልተፈቱ ጦሱ የሚተርፈው ለአገርና ለሕዝብ ነው፡፡ በሌሎች ሀገራት እንዳየነውና እንደሰማነው አስከፊ ዕልቂት የመፈጠሩ ዕድልም ሰፊ ነው፡፡
ጥንቃቄ በመጓደሉ ምክንያት በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት የጽኑ ሕክምና አገልገሎት የሚፈልጉ የህሙማን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡በርካታ የህክምና መስጫ ተቋማት የታማሚው ቁጥር ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ አዳዲስ ህሙማንን ከማይቀበሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡
በየቀኑ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ለሕክምና ክትትል ወደ ሕክምና ማዕከል ከሚገቡት ታማሚዎች ውስጥ በአማካይ 305 የሚሆኑት ጽኑ ህሙማን ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፥ ከነዚህ ውስጥም ከ40 እስከ 45 የሚሆኑት ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ የሚጠቀሙ ናቸው ።እስካሁን ባለው ሁኔታ የጽኑ ሕክምና ክፍል ከገቡት ውስጥ 59 በመቶ ያህሉ ህይወታቸው እንዳለፈም መረጃዎች እያሳዩ ነው፡፡
በሕብረተሰቡ ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ከፍተኛ ቸልተኝነትና መዘናጋት፤ በሽታው ጠፍቷል ወይም በሽታው በኔና በቤተሰቤ ብሎም በማሕበረሰቤ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል ብሎ ካለመረዳትና እና እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የሚጠበቅበትና ሚና አለመወጣቱ አሁን ላይ ለሚስተዋለው ችግር እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚጠቀሱ ስለመሆናቸውም የጤና ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ።
ይህ ሁኔታም በዚህ ከቀጠለ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ እንደ ሀገር ካለው ውስን የጽኑ ህሙማን እንክብካቤ አቅም በላይ ሊሆን እንደሚችልም ጭምር የጤና ሚኒስተር ዶክተር ሊያ ታደሰ ከፍተኛ ስጋታቸውን አስታውቀዋል።
በመሆኑም መዘናጋቱ ይብቃ ፡፡የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እያደረሰ ያለው እና ሊያስከትል የሚችለውን አሉታዊ ተጽዕኖዎችን የመከላከል ስራ ለአፍታም ቢሆን ጊዜ የማይሰጠው እና ለተወሰኑ ተቋማት የማይተው በመሆኑ እንያንዳንዱ ሰው እያንዳንዷን ደቂቃ በጥንቃቄ ሊያሳልፍ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2013