ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ በሌሎች ክለቦች ከአሁን በፊት አስመዝግቦት የነበረውን ገድል ‹‹በቀያይ ሰይጣኖቹ›› ቤት ይደግሙታል ተብሎ ቢጠበቅም፤ ክለቡ ውጤት እየራቀው በመሄዱና የቀድሞ የጨዋታ ፍልስፍናውን እያጣ በመሄዱ፤ እኝህን በቅጽል ስማቸው «ዘስፔሻል ዋን» በመባል የሚታወቁትን የክለቡ አሰልጣኝ የነበሩትን ጆዜ ሞሪኒሆን ዩናይትድ ከወራት በፊት እንደሸኘ ይታወሳል።
የአሰልጣኙን መባረር ተከትሎ ሳይታሰብ በጊዜያዊ አሰልጣኝነት ኦልትራፎርድ የደረሰው በቅጽል ስሙ ‹‹ቤቢ ፌስ›› በመባል የሚታወቀው የቀድሞው የቀያዮቹ ሰይጣኖች አጥቂ የነበረው ኖሮዊያዊው ኦሊ ገነር ሶልሻየር ነው፡፡ ሶልሻየር በአሰልጣኝነት እግሩ ኦልትራፎርድን ከረገጠበት ማግስት ጀምሮ የክለቡ አመራርም ሆነ የስፖርት ቤተሰቡ ያልጠበቀውን ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ታሪክ እየሰራ ይገኛል። ከዘጠኝ የፕሪሚርሊግ ጨዋታዎች ስምንቱን በበላይነት ሲያሸንፍ በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል። በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ የዓለምን ቀልብ መግዛት ችሏል፡፡
‹‹ጥሩ ውጤት ብናስመዘግብም ክለቡ ወደ ቀድሞው አስፈሪነቱ፣ የዋንጫ ክብሩ እና በያዝነው የውድድር አመት በደረጃ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አራት ይዘን ለሚቀጥለው አመት በሻምፒዮንስ ሊጉ መሳተፍ የሚያስችለንን ውጤት በጃችን እስክናስገባ ድረስ በየጨዋታው ሶስት ነጥብ ብቻ መሰብሰብ በቂ አይደለም፡፡ እስከመጨረሻው ድረስ የማሸነፍ ስነልቦናችን ጠብቀን በደረጃ ሰንጠረዡ አናት ከተቀመጡት ክለቦችጋር አንገት ለአንገት በመተናነቅ በደረጃ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አራት ይዘን ማጠናቀቅ አለብን›› በማለት የቀያይ ሰይጣኖቹ ምህታታዊው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴህያ ለስካይ ስፖርት ተናግሯል።
ተጫዋቹ ከስካይ ስፖርትጋር በነበረው ቆይታው እንደተናገረው፤ ‹‹ክለቡ ባለፉት ሁለት ዓመታት ካስመዘገባቸው ውጤት በተሻለ ሶልሻየር በአሠልጣኝነት ወደ ክለቡ በመጣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። አሰልጣኙም ከክለቡ ተጫዋቾች ጋር ተግባብቶ በመስራት ተጫዋቾች በክለቡ ጥሩ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እያደረገ ይገኛል። በዚህም ባሳለፍነው ሳምንት አርብ በኢምሬትስ እስታዲየም ከአርሰናል ጋር በአደረግነው አምስተኛ ዙር የኤፍ.ኤ ካፕ ጨዋታ ‹‹መድፈኞቹን›› ሶስት ለአንድ በሜዳቸው በማሸነፍ ታሪክ መስራት ችለናል›› በማለት ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
‹‹ይህ ድል ይበልጥ በልምምድ ሜዳ ጠንክረን እንድንሰራና የማሸነፍ ስነልቦናችን ከፍ እንዲል አስችሎናል። በዚህም ከድሉ ማግስት ከበርንሌይ ጋር ያደረግነውን ጨዋታ ወደ ሜዳ ስንገባ በሙሉ ልብ እንደምናሸንፍ ተስፋ ሰንቀን ነበር ። ነገርግን ኳስ ነውና ነጥብ ተጋርተን ለመውጣት ተገደናል። በሜዳችንም የሽንፈትን ጽዋ ከመጎንጨት ኮከባችን ፖል ፖግባና ቪክቶር ሊንድሎፍ ታድገውናል። ሁለት ለባዶ ከመመራት ተነስተን አቻ መውጣት ችለናል። በዚህም በያዝነው የውድድር ዓመት ህዳር 18 ቀን አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪኒሆ ክለቡን ሲለቁ ከቼልሲ ጋር የነበረን የነጥብ ልዩነት 11 ነበር። ኖሮዊያዊው አሰልጣኝ ወደክለቡ ከመጣ ወዲህ ይህን ከፍተኛ የነጥብ ልዩነት ወደ ሶስት ዝቅ እንዲል አድርገን ነበር፤ ከአርሰናል ጋር የነበረውንም ከፍተኛ የነጥብ ልዩነት በማጥበብ እኩል ነጥብ ላይ መቀመጥ ችለን ነበር። ነገርግን ከበርንሌይ ጋር ባደረግነው ጨዋታ ነጥብ በመጣላችን ከአርሰናል ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ከፍ ሊል ችሏል። በሌላ በኩል ቼልሲ በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ምሽት ከቦርንማውዝ ጋር ባደረገው ግጥሚያ አራት ለባዶ በመሸነፉ ምንም እንኳን በበርኒሌይ ነጥብ ብንጥልም ከሰማያዊዎቹ ጋር ያለን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ሊል ችሏል›› ብሏል የቀያይ ሰይጣኖቹ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ ዴህያ።
ሶልሻየር ክለቡን ከተረከበ ወዲህ የሚገርም ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ የአደባባይ ሚስጥር መሆኑን የሚናገረው ዴህያ፤ አሁንም ገና በሻምፒዎንስ ሊግ ለመሳተፍ ከሚያስችላቸው የደረጃ ሰንጠረዥ ውጭ መሆናቸውን ውጤቱ አጥጋቢ እንዳልሆነ ይጠቅሳል፡፡ ‹‹አራተኛና አምስተኛ ደረጃ ከሚገኙት መድፈኞቹና ከሰማያዊዎቹ ጋር ገና የሁለት ነጥብ ልዩነት አለን። እንዲሁም የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ከመሪዎቹ ሊቨርፑልና ማንችስተር ሲቲ ጋር ያለን የነጥብ ልዩነት በጣም ሰፊ ነው። ኖሮዊያዊው አሰልጣኝ ከመጣ ወዲህ በተፈጠረው ምቹ ሁኔታና ባስመዘገብነው ተከታታይ ድል እጅጉን ደስተኛ ነን። ነገርግን ክለቡ ወደ ቀድሞው የዋንጫ ክብሩና ለሚቀጥለው ዓመት በሻምፒዎንስ ሊግ መሳተፍ የሚያስችለውን ደረጃ በደረጃ ሰንጠረዡ ባለመያዙ ደስተኞች አይደለንም›› በማለት ውጤቱ አሁንም እርካታ እንዳልሰጠው ተናግሯል፡፡
ዴህያ ምክንያቱን ሲገልጽ፤ ‹‹ቀያይ ሰይጣኖቹ የምንታወቀው ለዋንጫ ስንፋለም ነበር እንጅ በደረጃ ሰንጠረዡ ከአንድ እስከ አራት ይዞ ለማጠናቀቅ አልነበረም። ነገርግን አሁን ላይ በኖሮዊያዊው አሰልጣኝ እየታገዝን ወደቀድሞው አስፈሪነታችንና የማሸነፍ ስነልቦናችን በመመለስ ላይ ነን። ቀሪዎቹን ጨዋታዎች ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን በመጫወት በሻምፒዎንስ ሊጉ መሳተፍ የሚያስችለንን ቦታ ለማግኝት እድሉ በእጃችን ነው። ይህንንም ለማድረግ ጠንክረን እንሰራለን›› ብሏል፡፡
ዴህያ፤ የምንጊዜውም የቀያይ ሰይጣኖቹ ምርጡ አሰልጣኝ የነበሩት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ክለቡን ከለቀቁ ወዲህ ክለቡ የተለያዩ አሰልጣኞችን ቢቀጥርም የሊጉን ዋንጫ ማንሳት እንደተሳነው በመጠቆም፤ ዩናይትድ ከረዥም ዓመታት ወዲህ በያዝነው የውድድር አመት የሊጉን ዋንጫ የማንሳት ተስፋ እንዳለውና ወጥ አቋም በማሳየት እስከመጨረሻው ድረስ ማሸነፍ እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡
‹‹በሻምፒዎንስ ሊጉ ለመሳተፍ በሚያስችለን የሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ መቀመጥ እንፈልጋለን። ይህ ከባድ እቅድ እንደሆነ ይገባኛል። አሁን ላይ ያለውን የቡድን አንድነትና የማሸነፍ ስነልቦና በመጠበቅና ጨዋታዎችን ቀጣይነት ባለው መንገድ በማሸነፍ እቅዳችንን ለማሳካት እስከመጨረሻው ድረስ ለመፋለም ቆርጠን ተነስተናል›› በማለት አሞራው ግብ ጠባቂ ለስካይስ ስፖርት ተናግሯል፡፡
እንደ ዴህያ ማብራሪያ፤ ማንቸስተር ዩናይትድ በተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፍ መቻሉ በሌሎች ክለቦች ላይ ስነልቦናዊ ጫና ለማሳደር ጠቅሞታል፡፡ በዚህም በሚቀጥለው ዓመት በሻምፒዎንስ ሊግ ለመሳተፍ የሚያስችለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡
‹‹በመከላከሉ በኩል በጣም ደካማ ስለነበርን በፕሪሚርሊጉ የመጀመሪያ የውድድር ዘመን አጋማሽ ብዙ ጎሎችን አስተናግደናል። አሁን ላይ ጨዋታዎችን በተሻለ መንገድ በመቆጣጠር ወደ አሸናፊነት ተመልሰናል። በመከላከሉ በኩል በጣም ተሻሽለናል። የደርቢ ጨዋታዎችን በበላይነት በማሸነፍ ባላንጣዎቻችንን ማሸነፍ ችለናል። ይህም ለኛ ከፍተኛ የራስ መተማመን እንዲኖረን አስችሎናል። ስለዚህ ዋናው ነገር የማሸነፍ ስነልቦናችን ጠብቀን እስከመጨረሻው መዝለቅና መፋለም ነው›› ሲል እስፔናዊው ግብ ጠባቂ ተናግሯል።
አንድ ሜትር ከዘጠና ሁለት ሴንቲ ሜትር የሚረዝመው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴህያ ላይ ጆዜ ሞሪኒሆ በክለቡ አሰልጣኝ በነበሩበት ወቅት ከነበረበት ድብርት ተላቆ በአሁኑ ወቅት ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል። በወሳኝ ጨዋታዎችም ጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማዳን ቀያይ ሰይጣኖቹ በውጤት ጎዳና እንዲጓዙ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ባለፉት አራት ጨዋታዎች ግብ ጠባቂው ከአጥቂዎች ጋር ብቻ ለብቻ ተገናኝቶ ሶስት ጎል የሚሆኑ ኳሶችን ማዳን ችሏል። በዚህም ባለፉት አራት ጨዋታዎች የተጋጣሚ ቡድንን ጎል የማግባት እድል በማጥበብ ክለቡ ጨዋታዎቹን በበላይነት አሸንፎ እንዲወጣ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። በተለይም ቀያይ ሰይጣኖቹ ከስፐርሶች ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ሲያሸንፉ ዴህያ ትልቅ ድርሻ ነበረው። በአጠቃላይ ሶልሻየር ለተጫዋቾቹ ነፃነት በመስጠቱና ጥሩ ግንኙነት በመካከላቸው በመኖሩ ተጫዋቾቹ ዳግም ምርጥ ብቃታቸውን ማሳየት ችለዋል፡፡
ጥር 24/2011
ሶሎሞን በየነ