ዛሬ የገና በዓል ነው። በክርስትና ሃይማኖት አስተምህሮ በዓሉ ዓለምን በሞቱ ሊያድን ከሰማይ የወረደው የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት ቀን ነው። በዚህ የልደት ቀን በቀጣይ ሕይወታችን ራሳችንን ለእግዚአብሔር በማቅረብ በልጅነት መንፈስ ተቀድሰን በጽድቅና በሕይወት መንገድ ለመጓዝ የተሻለ ዝግጅት የምናደርግበት ነው፡፡
እኛ ሰዎች በክርስቶስ ልደት ለሰዎች የምንከፍለው ዕዳ አለብን፡፡ ይህም ዕዳ ለሰው ልጆች ሁሉ የፍቅር ሥራ የሆነውን መልካም ምግባር መፈፀም ነው፡፡ ከዚህ መልካም ምግባር አንዱ “የተቸገሩትን መርዳት” ነው።
በተለይ በአሁኑ ጊዜ በስደት፣ በመፈናቀልና በመከራ ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ማገዝ፣ መደገፍና አይዟችሁ ማለት ያስፈልጋል። ይህ ክርስቲያናዊ ግዴታችን ነው። ይህንን ግዴታ መወጣት የአንድ ወቅት ወይም ለነገ የሚባል ሳይሆን በየዕለቱ ልንከውነው የሚገባ ተግባር ነው፡፡
ሁሉም ሰው ለበዓሉ ዝግጅት በሚያደርገው ዝግጅት መጠን በዕለቱ በተለያዩ ሰው ሰራሽ ችግሮች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ፤ በቀደሙ የበዓል ትዝታዎች ቆዝመው በዓሉን ለማክበር የተገደዱ ወገኖች መኖራችውን እያሰበ ሊሆን ይገባል።
የክርስቶስ ልደት የተለያዩት የተገናኙበት፣ የተራራቁት የተቀራረቡበት፣ ሰማያውያንና ምድራውያን ስለ እግዚአብሔር ክብርና ስለ ሰላም በኅብረት የዘመሩበት ታላቅ በዓል ነው። ስለሰላም ስለአንድነት ጠቀሜታም ከልደተ ክርስቶስ የበለጠ ትምህርትና አስተማሪ ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡
በመላ አገራችን በየጊዜው የምናየውና የምንሰማው የሰው ልጆች ለቅሶና ሰቆቃ እንዲሁም መፈናቀል ክቡር የሆኑትንና ቅዱስ እግዚአብሔር በአርዓያውና በአምሳሉ የፈጠራቸውን ሰዎች ሕይወት መቅጠፉ የመላው ህዝባችንን ልብ እያሳዘነ ያለ መራራ እውነታ ነው።
ይህን እውነታ ሁላችንም የሰላም ሰዎች በመሆን በወንድማማችነትና በእህትማማችነት መንፈስ የጎሳ፣ የዘር፣ የቀለም፣ የጾታና የዕድሜ ልዩነት ሳይለያየን እንደ አንድ ቤተሰብ በመሆን በመተባበር፣ በመረዳዳትና በመተጋገዝ፤ አንድ ሆነን በመቆም ልንቀይረው ይገባል፡፡ በዓሉ በፍቅር ተሳስረን ለመኖር የተሻለ ዝግጅት እንድናደርግ የሚረዳን የማንቂያ ደወል ጭምር አድርገን ልንወስደው ይገባል፡፡
ቀዳሚው የበዓል ዕለት ተግባራችንም የታመሙትንና፣ የታሠሩትን መጠየቅ፣ የተራቡትንና የተጠሙትን ማብላትና ማጠጣት እንዲሁም የታረዙትን በማልበስ ለቅዱስ እግዚአብሔር ያለንን ክብርና፣ ለወገን ያለንን ፍቅር መግለፅ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡ የነገ የበዓል ትዝታችንም ይሄው ሊሆን ይገባል። መልካም የልደት በዓል!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2013