ስፖርትን ከስፖርታዊ እንቅስቃሴው በተጨማሪ ለሌሎች መልካም ተግባራት የመጠቀሙ አዝማሚያ በሀገራችንም ሆነ በመላው ዓለም የተለመደ ነው፡፡ ለአብነትም በሀገራችን በስፖርት ዘርፍ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦች የሚታወሱባቸው የመታሰቢያ ውድድሮች እና የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል ታሳቢ ተደርገው የሚዘጋጁ ውድድሮች ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በቅርቡ አንድ ኢትዮጵዊ የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ስፖርትን እንደ አይነተኛ መሳሪያ በመጠቀም የአየር ንብረት ብክለትን ችግር ለዓለም ማህበረሰብ ማስገንዘብ በሚል ተነሳሽነት ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የጎዳና ላይ ሩጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
የአትሌቲክስ አሰልጣኝ ሙሉየ ዕያዩ ይባላል፡፡ ተወልዶ ያደገው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር በደንቢያ ወረዳ ውስጥ በምትገኝ ሰቀልት አምባጓሊት በምትባል ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ እንደብዙዎቹ የሀገራችን አትሌቶች ከቤት ወደ ትምህርት ቤት እንዲሁም ከትምህርት ቤት ወደ ቤት በሚጓጓዝበት ወቅት እስከ ሀምሳ ደቂቃ በሚወስድ የእግር መንገድ በሩጫ ይመላለስበት ስለነበር አጋጣሚው ለአትሌቲክስ ስፖርት መነሻ እንደሆነው ይናገራል፡፡
ወጣቱ አሠልጣኝ ሙሉየ እያዩ በአሁኑ ወቅት የዓለም አንገብጋቢና ትልቅ የራስ ምታት የሆነውን የአየር ንብረት ብክለትና የሙቀት መጨመርን ለመከላከል ብሎም ለመቀነስ እንዲቻል ስፖርትን እንደ ግብዓት በመጠቀም የሚተገበር ዓለም አቀፋዊ የሆነ አዲስ የፈጠራ ሀሳብ አመንጭቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የፈጠራ ሥራው ደግሞ ስፖርትን እንደ ትልቅ መሳሪያ በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ በአየር ፀባይ ለውጥ ላይ የሚሰራ ሲሆን፤ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግም 17 ዓመታትን ፈጅቶበታል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከኢትዮጵያ የአእምሯዊ ንብረት የፈጠራ ሥራ ባለቤትነት ማረጋገጫ አግኝቶ ‹‹ኢንተርናሽናል ክላይሜት ቼንጅ ኤንድ ስፖርት ኦክስጅንን ተጠቅመን ኃይላችንን እናድስ (ኦ.ተኃ)›› በሚል ተቋማዊ ሥም ተደራሽነቱን ለማስፋት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
አሠልጣኙ እንደሚለው፤ ተቋሙ የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ ካሰናዳቸው 306 የመፍትሄ ሀሳቦች ውስጥ ስፖርት አንዱ ሲሆን፣ ይህንኑ ግንዛቤ ለአጠቃላይ የዓለም ማኅበረሰብ ለመስጠት መነሻና መድረሻውን አዲስ አበባ ሰሚት አደባባይ ላይ ያደረገ የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር የካቲት 10 ቀን 2011 ዓ.ም ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡ የውድድሩ ስያሜ ‹‹ኢንተርና ሽናል ስፖርት ፎር ክላይሜት ቼንጅ – ኦተሃ›› (International Sport for Climate Change) ሲሆን፤ ስፖርትና ተፈጥሮ የማይለያዩ የሰው ልጅ የህይወቱ መድህን አለኝታውና እስትንፋሱ በመሆናቸው፤ ስፖርታዊ መድረኩን በመጠቀም የዓለማችን አሳሳቢ ችግር እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ብክለትንና የሙቀት መጨመርን ለመከላከል የሚያስችል የመፍትሄ ሀሳቦችን ለማመላከት፤ ተሳታፊዎች የውድድሩ ተቋዳሽ በመሆን ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄ በጋራ እንዲሰሩ ለማስቻል የሚል ዓላማን ያነገበ የውድድር መድረክ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በውድድሩ ላይ የውጭ አገራት ተሳታፊዎችን ጨምሮ አንጋፋና ታዋቂ ስፖርተኞች፤ ዕድሜያቸው ከ11 ዓመት በላይ የሆናቸው በርካታ አትሌቶች ይሳተፋሉ፡፡ ከክልሎች፣ ከከተማ አስተዳደሮች፣ ከክለቦች፣ ከተቋማትና ዓላማውን ከሚደግፉ አካላት የተወጣጡ ግለሰቦች የሚሳተፉበት ውድድር በመሆኑ አጠቃላይ ተሳታፊዎችም እስከ 40ሺህ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዋና ሳጂን አትሌት አሰፋ መዝገቡም የዚህ ውድድር አምባሳደር እንደሆነ አሠልጣኙ ጠቁሟል፡፡
እንደ አሰልጣኙ ገለጻ፤ በውድድሩ ከአንደኛ እስከ 20ኛ ለሚወጡ ተሳታፊዎች ሜዳሊያን ጨምሮ ልዩ የሆነ ሽልማትና ከማግኘታቸውም በተጨማሪ የውጭ አገር እድሎችን ጥረት ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ለሚወጡ ተወዳደሪዎች በዓይነቱ የተለየና እስካሁን በአገር ውስጥ ውድድር ሲሰጥ ከነበረው የአትሌቲክስ ሽልማት በእጅጉ የተሻለ የገንዘብ ሽልማት እንዲያገኙና ‹‹International Climate Change and Sport- ኦተሃ››ን ወክለው አምባሳደር በመሆን በውጭ አገራት የስፖርት ሁነቶች ላይ እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ በዕለቱ ከውድድር መልስ ሁሉም ተሳታፊዎች በመጪው ክረምት በስማቸው ችግኝ የተከሉበትን ቁስ የመረካከብ ሥነ-ስርዓት ይኖራል፡፡ በውድደሩ የታዋቂ ስፖርተኞችና የሌሎች ተሳታፊዎች የመነሻ ሰዓትም የተለያየ እንዲሆን ይደረጋል፡፡
ጥር 24/2011
አዲሱ ገረመው