በሰው ልጅ ህይወት ውስጥ ማግባት፣ መውለድና መሞት የማይቀሩ ወሳኝ ኩነቶች ተብለው ቢቆጠሩም ማግባት ግን የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ (አለማግባትም ይቻላል) በማህበረሰቡ ውስጥ (በተለይ ደግሞ ማህበረሰባዊ ባህልን በሚከተሉ ማህበረሰቦች) ያገቡ ሰዎች፣ ካላገቡት ይልቅ የኃላፊነት ስሜት አላቸው የሚል እምነት በመኖሩ ነው አብዛኛውን ጊዜ ጋብቻን የሚመርጡት (መውለድና መዋለዱ ዘርን መተካቱ ‹‹ሌላውም›› እንዳለ ሆኖ) በማህበራዊ ግንኙነት ውስጥ የሚገኘውን ደረጃ መጨመር የማግባት ማህበራዊ ጥቅም ነው ልንለው እንችላለን፡፡
ወገን ጉዳዬ ጋብቻን ማስረዳት ሳይሆን ተያያዥ መዘዙን ለመግለጥ ነው፡፡ (በቃ ወቅቱ የሰርግ ስለሆነ አግብተህ መሆን አለበት እያላችሁኝ ይሆን?) አትሸወዱ እኔ እንኳን ግራ ጎኔን በመፈለግ ሥራ እየተጠመድኩ ነው፡፡ አፈቅርሻለሁ እንጂ አፈርጥሻለሁ ሳልል ሴቶች ሁሉ ሲያዩኝ ስለሚሸሹኝ እስካሁን ማግባት አልቻልኩም፡፡
አንድ ጊዜ ስጠራት 99 ጊዜ አቤት የምትለኝን ሚስት ለማግኘት ግን ፈጣሪን ተማጽኖ ላይ ነኝ፡፡ (ታዲያ ለምን ትተረተራለህ አትሉኝም) አትሉም እኮ አይባልም ግድ የለም በሉኝ፡፡ መቼም በአገሬው ብሂል ‹‹ነገርን ከሥሩ ውሃውን ከጥሩ›› ይባል የለ ተንደርድሬ ‹‹ወደ ገደለው›› ከምገባ ላዩን አሳይቼ ስለምን ለማውጋት እንደፈለግኩ በጽሁፍ መግቢያ አንቀጽ ፍጆታዬን ማሳያ ነው፡፡ ከጋብቻ ይልቅ በጋብቻ ምክንያት የሚወጣው የድግስ ወጪን የሀሳቤ ማጠንጠኛ ለማድረግ እንዳሰብኩ ተገንዘቡልኝና አብረን እንዝለቅ፡፡
መቼም በከተሞች የሚደረጉ ጋብቻዎችን በአንክሮ የተመለከተ ሰው ከእኔ በላይ ትዝብት እንደሚኖረው አልጠራጠርም፡፡ በተለያዩ ህብረ ቀለማት አበቦች ያሸበረቁ የሠርገኞች መኪኖች በየመንገዱ የጋብቻ ማስታወቂያ ጩኸት እያሰሙ ቪዲዮ እየተቀረጹ አደባባዮችን ይዞራሉ፡፡ ባለ ሁለት ጎማ (እግረኞች) የሆንን ደግሞ ይህንን የሠርግ ትዕይንት ያለ ክፍያ መመልከት ልማዳችን ነው፡፡ ብዙ ሠርገኞች ከአደባባዩ ቄንጥ በላይ ለሠርጉ የሚያወጡት ወጪ ያናድደኛል፡፡ በተለይ ለአንድ ቀን ታይታ ብለው ዕድሜ ልካቸውን ብድር ሲከፍሉ የሚኖሩ ሰዎች፡፡
ከማን አንሼ የምትለው ኢትዮጵያዊ መፈክራችን ስንቱን ሰው አፈር ድሜ አስበልታዋለች መሰላችሁ፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ቅልጥ ያለ ሠርግ ደግሶ ያገባው የመንደሬ ሰው ‹‹የዕዳ ድሩ›› እስካሁን አልተ በጣጠሰም፡፡ አሁን አሁን የጠዋት ጸሎቱ ቀኝ አውለኝ ሳይሆን ‹‹እባክህ ሸረሪቷን ግደልልኝ!›› ሆኗል፡፡ ሚስጥሩም ዕዳዬን አቅልልኝ ከማለት አበዳሪዬን የሰማይ ቤት ቪዛ ስጥልኝ እንደ ማለት ነው፡፡
ይህ ያልሞላለት ልታይ ባይ ከአቅም በላይ ደጋሽ በሁለት ዓመት የትዳር ኑሮው ትዝታው ውስጥ የቀረው የግድግዳው ፎቶ ብቻ ነው፡፡ የዛኔ አብረውት ሠርጉን ያደመቁ የበሉና የጠጡ ሰዎች የአንድ ቀን አድናቆት ሰጥተውታል እንጂ የቤቱን ጎዶሎና ገበና መች አዩለት፡፡ እርሱ ግን ከዚህ ሁሉ ምጥ መገላገል አቅም አጥቶ በቀን አምስት ጊዜ ከንፈሩን እየነከሰ ይገኛል፡፡ አጋጣሚውን አግኝታችሁ ይህንን ሰው ‹‹እንዴት ነው ኑሮ?››ብትሉት ‹‹ተመስገን ነው የሞላልኝ የስልኬ ባትሪ ብቻ ነው›› ማለቱ አይቀርም፡፡ ታዲያ እርሱንና መሰሎቹን ያየ ሰው ሠርግ መደገስ ያምረው ይሆን? (ልጥጦችን አይመለከትም)
ያለውማ ከአንድ በላይ ቢደግስስ ምንችግር አለው፡፡ (ታዲያ ሌላ ሚስት ያግባ ማለቴ አይደለም) በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ላይ ብዙ የሚወራለት አንድ ቅንጡ ባለ ሀብት አራት ጊዜ እኔ ነኝ ያለ ሠርግ ደግሶ ብዙ ሀብታሞችን በወይን ማራጨቱን ታውቁ ይሆን? እንግዲህ ሰርጉን ይሁን ሚስት መቀያየሩን የወደደው ባይታወቅም አራት ጊዜ ጋብቻ ማከናወኑ ቅንጣት እንዳላጎደለበት እንኳን አሁንም ለማግባት ሽር ጉድ እያለ መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ የሚገርመው ለአራተኛ ጊዜ ያገባትን ሴት ‹‹ባንቺይርጋ›› የሚል የዳቦ ስም አውጥቶላት ነበር መባሉንም ሰምቻለሁ፡፡ ልማድ ነውና ቀጣይ የማግባት ዓላማ ካለው ደግሞ አምስተኛዋን የመጀመሪያዬ ይላት ይሆናል ማን ያውቃል፡፡
እንደኔ ዓይነቱ ኪሱ ከሲታ የሆነ ሰው ደግሞ እነዚህን ሰዎች እያየ ነው እኩል ካልሆንን እያለ ለመደገስ የሚሯሯጠው፡፡ የማይመጥነንን ህይወት በማየት አጓጉል ቅናት ማሳደር ተገቢ አይመስለኝም፡፡ በብዙ ርቀት ላይ ያሉ ሰዎችን ኑሮ ማየትና ከኛ ህይወት ጋር ማነጻጸሩ መጨረሻ ላይ የራሳችንን ኑሮ እንድንጠላ ያደርጋል፡፡
ወዳጄ ከሌለህ የለህም ነው፡፡ ዛሬ ከአቅም በላይ ደግሰህ ያበላኸው ሰው ነገ ዞር ብሎ አያይህም፡፡ ከአቅም በላይ መንጠራራት ትርፉ ለመውደቅ ነው፡፡ በዚህ ዘመን አትውደቅ ‹‹ከወደቅክ ይህ ህዝብ የሚያነሳህ በካሜራ ብቻ ነው›› የሚለው ተረት እንዳይደርስብህ ደግሰህ ግራ ከምትጋባ ተግባብተህ ግባ!
ጥር 24/2011
አዲሱ ገረመው