ወርቅነሽ ደምሰው
ዓለም በግሎባላይዜሽን ወደ አንድ መንደር እየጠበበ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የካፒታል፣ የምርቶች፣ የመረጃና ሌሎች ጉዳዮች ዝውውር እያደገ መሆኑን ተከትሎ የሰው ልጆች ፍልሰትም በከፍተኛ ደረጃ ሊያድግ መቻሉ መረጃዎች ያመላክታሉ። በዚህ የተነሳ በርካታ ሰዎች ከሀገራቸው ውጪ በተለያዩ የዓለም ሀገራት እየኖሩ ይገኛሉ።
ከእነዚህ ውስጥ የሚጠቀሱት ኢትዮጵያውያንም በተለያዩ ምክንያቶች ከሀገራቸው ውጪ በሌላ የዓለም ሀገራት እንደሚኖሩ ይታወቃል። እነዚህን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊ በአንድነት አቅፎ የሚይዝ ማህበር ግድ ይላል።
ታዲያ በሀገር ውስጥ ለእነዚህ ዜጎች ውክልና የሚወስደው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ቢኖርም በተጠናከረ መልኩ ሁሉንም በአንድነት አቀናጅቶ ተደራሽ ከመሆን አንፃር ውስንነቶች ያሉበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ በክልሎችም የየራሳቸው የዲያስፖራ ማህበር በማቋቋም በተበታተነ መልኩ የሚስራበት ሁኔታ መኖሩን የሚናገሩት አቶ ያሲን ሀጂ መሀመድ የአፋር ክልል የዲያስፖራ ማህበር ሥራ አስኪያጁ ናቸው።
አቶ ያሲን እንደሚገልጹት፤ የአፋር ክልል የዲያስፖራ ማህበሩ ከተመሰረተ ሁለት ዓመት ሲሆን፤ ከፌዴራል ዲያስፖራ ኤጀንሲ በተሰጠን አቅጣጫ መሠረት ከክልሉ መንግሥት ጋር የሚሰራ ነው።
ማህበሩን ህጋዊ አድርጎ ለማስቀጠል ከክልሉ መንግሥት በኩል የሚሰጠውን ደብዳቤ ያላገኘ መሆኑን ጠቅሰው፤ ማህበሩን አጠናክሮ ለማስቀጠልም ከክልሉ ምክትል ርእስ መስተዳድር ጋር በመገናኘት በጉዳዩ ዙሪያ የተወያዩ ቢሆንም፤ ከክልሉርዕስ መስተዳድር ጋር ለመነጋገር በኮቪድ እና ከሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ያልተቻለ መሆኑን ይናገራሉ።
የማህበሩ ዓላማ ሰፋ ያለና በርካታ ተግባራት ለማከናወን ያለመ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በውጭ የሚኖሩ በርካታ የአፋር ዲያስፖራዎች በክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ይጠቁማሉ።
ማህበሩ የአፋርን ብቻ የሚይዝ ሳይሆን በአፋር ተወላጅ የሆኑትንና ሁሉንም ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በአባልነት ያቀፈ ነው። አሁን ላይ አፋር ክልል ተወልደው ያደጉ፤ ነዋሪነታቸው አፋር ክልል የነበረ፤ ነገር ግን አሁን ውጪ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች በክልሉ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎትና እቅድ ቢኖራቸውም፤ ይህንን ለማድረግ በቅድሚያ ማህበሩ ህጋዊ እውቅና ማግኘት እንዳለበት ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ የአፋር ዲያስፖራ ማህበር አሁን ላይ 22 አባላት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱበት ሲሆን፤ በርካቶች ደግሞ አባል ለመሆን ፍላጎት ያላቸው በውጭ የሚኖሩ መኖራቸውን ይጠቁማሉ። ዋና ወቅታዊ ጉዳዩ የማህበሩን ቢሮና አካውንት መክፈትና ህጋዊ ማድረግ መሆኑን በመጥቀስ፤ አሁን ላይ ህጋዊ ያልሆነ ሥራ እንዳይሰራ ፍራቻ ስላለ ዲያስፖራው ሀገሩ ላይ ኢንቨስት ሲያደርግ በእምነት ቢሆንም፤ የበለጠ እምነት እንዲኖረው እና በስፋት ኢንቨስት እንዲያደርግ ማህበሩ ህጋዊ ሆኖ መቋቋም እና ቢሮው ኖሮት ሊሰራ ይገባል። በመንግሥት ደረጃ ታውቆ የማህበሩ የዲያስፖራው አካውንት በህጋዊ መንገድ መዘጋጀት እንዳለበት ያስረዳሉ።
ማህበሩን ዝግጅቱን በሙሉ ያጠናቀቀ ሲሆን፤ በክልሉ መንግሥት በኩል ለማህበሩ ጽሕፈት ቤት የሚውል ቢሮ በቤተመንግሥት ቅጥር ግቢ ውስጥ የተመቻቸ ቢሆንም፤ በማህበሩ በኩል በዲያስፖራ አባላትእንደልብ እንቅስቃሴን ለማድረግ ከቤተመንግሥት ውጪ የሆነ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠይቀው እንደነበር አስታውሰው፤ ይህንን በክልሉ ፕሬዚዳንት በኩል መፍትሔ ይበጀለታል ብለው በተስፋ እየጠበቁ መሆኑን ያስረዳሉ ።
በሌላ በኩል በፌዴራል ደረጃ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ለማቋቋም ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑን የሚናገሩት ሥራአስኪያጁ፤ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ የመንግሥት አካል በመሆኑ የሚቋቋመው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር በዲያስፖራው የሚመራ ሆኖ ከኤጀንሲ ጋር በመሆኑ ለኢትዮጵያና ለትውልደ ኢትዮጵያን መስራት የሚችል ማህበር ነው ይላሉ።
ይህ ማህበር ሁሉንም ያቀፈ ኢትዮጵያዊ ማህበር ሲሆን ፤ የኢትዮጵያ አፋር ዲያስፖራ፤ የኢትዮጵያ የአማራ ዲያስፖራ ፤ የኢትዮጵያ ኦሮሚያ የሚለው በአንድ ላይ በማካተት ዋናውን ማህበር በማጠናከር የክልል ዲያስፖራ ማህበራት ለዋና ተጠሪ የሚሆኑበት ሁኔታ የሚፈጠር መሆኑን ይጠቅሳሉ። እስካሁን ያለው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ሁሉን ያቀፈ ስላልሆነ ሁሉን ያቀፈ ማህበር ለመመስረት በተጠየቀው መሠረት ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ሂደት ላይ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደሥራአስኪያጁ ገለጻ፤ አንድ ሰው ብሔሩ አማራ ቢሆን አፋር ክልል ተወልዶ ካደገ ብሔሩ አማራ ይሆን እንጂ እሱ የሚያውቀው የተወለደበት አፋር ክልል ነው። ስለዚህ የአፋርም ሆነ ተወላጁ ወይም አማራ ሆነ ተወላጁ እየተባለ በክልል የዲያስፖራ ማህበር የሚቋቋመው ዋና የኢትዮጵያዊነት ስሜት ለመመለስ መሆኑን ይናገራሉ ።
‹‹የአፋር ብሔር ወደ አፋር ክልል ብቻ ፤ የአማራ ብሔር ወደ አማራ ክልል ብቻ ኢንቨስት ያደርግ›› የሚባል ከሆነ ልዩነት ፈጠረ ማለት ነው። ለምሳሌ አንድ ዲያስፖራእኔ አፋር ክልል ነው የተወለድኩት ብሎ ከአማራ ወይም ከኦሮሚያ መጥቶ አፋር ክልል ላይ ኢንቨስት ማድረግ ቢፈልግ ወይም ሌላ ቦታ የተወለደ አፋር ክልል ኢንቨስት ማድረግ ከተፈለገ የሰውዬን ፍላጎት ተከትሎ የሚፈፀም መሆኑን እና የሚቋቋመው ዋና የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበር ከክልሉ የዲያስፖራ ማህበር ጋር በመነጋገር ሁኔታዎች ያመቻቻል። ይህ ሲሆን ሰው በፈለገበት አካባቢ መሥራት የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩ የኢትዮጵያዊነት ስሜትን በተሻለ መልኩ ያሳድገዋል።
ማህበሩ እውነተኛ የኢትዮጵያውያን ማህበር ሆኖ መመስረት ይኖርበታል ካሉ በኋላ፤ አንዱ ክልል ተቀጣይ አንዱ አስቀጣይ መሆን ሳይኖርበት ሁሉንም በጋራ ያቀፈ መሆን አለበት ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ማህበር ከፌዴራል የሚተላለፈውን አቅጣጫ በየክልሉ ላሉት ቅርንጫፎቹ በማስተላለፍ በትክክለኛው መንገድ እየተመራ ችግሩን በመቅረፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
ክልሉ ብዙ ተፈጥሯዊ ስጦታዎች ያሉት ቢሆንም በኢንቨስትመንት ሆነ በማንኛውም ነገር ወደ ኋላ የቀረ ነው የሚሉት ሥራአስኪያጁ፤ ይህንን ወደፊት ለማምጣት በመንግሥት እርዳታና ውጭ በሚኖሩት የአፋር አካባቢ ተወላጅ ዲያስፖራው አባላት ወደ ሀገሩ በመምጣት ኢንቨስት በማድረግ በሀገሪቱም ለውጥ ማምጣት እንዳለባቸው ያመላክታሉ።
የአፋር ዲያስፖራው ሀገሩን ጠቅሞ፤ እራሱም ተጠቃሚ ሆኖ ከክልል አልፎ እስከ ፌዴራል እንዲደረስ ዓላማ አድርጎ የሚሰራ ማህበር እንዲሆን ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ጠቁመው፤ የማህበሩ ፍላጎት በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ ዲያስፖራው ኢንቨስት እንዲያደርግበት ሁኔታው የሚያበረታታ መሆኑን አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 28/2013