ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደስልጣን ከመጡ 300 የሥራ ቀናት አሳልፈዋል፡፡ በነዚህ ቀናት ስኬቶች አስመዝ ግበዋል፡፡ ተግዳሮቶችም አጋጥመዋቸዋል፡፡ ባሳለ ፏቸው የስራ ቀናት ላይ ያነጋገርናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የነበሯቸውን ስኬቶችና በቀጣይ መስራት የሚጠበቅባቸውን እንደሚከተለው አስተያየታቸውን ሰጥተውናል፡፡
በቅድሚያ ያነጋገርናቸውና ሀሳባቸውን የሰጡን የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራተጂያዊ ጥናት ኢንስቲትዩት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ሙሉዓለም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያስመዘገቧቸውን ስኬቶች እንዳስረዱት በየክልሉ በመሄድ ከህዝብ ጋር ያደረጉት ምክክር በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ወደስራ ሲገቡ ከሚመሩት ህዝብ ጋር ለመወያየት መወሰናቸው እንደ አንድ መሪ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ያላቸውን ዝግጁነት ያሳያል፡፡
የፖለቲካ ስነምህዳሩን ለማስፋት ያደረጉት እንቅስቃሴም ከስኬቶቻቸው መካከል ይጠቀሳል፡፡በፖለቲካው የሚስተዋለውን ችግር በውይይት ለመፍታት በውጭ ሀገር ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሀገርቤት እንዲገቡ ማድረጋቸው ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል፡፡
ቀደም ሲል የነበሩት ባለስልጣናት በተለያዩ ሀገራት ቀ ኢትጵያውያን ዘለፋ እና ተቃውሞ ይደርስባቸውና ብዙዎቹ ባለስ ልጣናትም ተሸማቅቀው ይመለሱ እንደነበር ያወሱት አቶ መላኩ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሆድና ጀርባ ሆነው ከመንግሥት ጋር እንደጠላት ይተያዩ የነበሩ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን አመለካከት መቀየር መቻላቸው ለስኬት እንዳበቃቸው ይገልጻሉ፡፡
በሀገራቸው ጉዳይ የማይሳተፉ የነበሩ ምሁራን አሁን ተንታኝ ሆነው በዙ ማለት እስከሚችሉ ድረስ ተሳትፎአቸው መጨመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጥረት የተገኘ መሆኑን መናገር እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡
ብዙ ሴቶች ወደ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት መምጣት የቻሉት በእርሳቸው ጊዜ መሆኑ፣ በየአጋጣሚው በሚያደርጉት ንግግር ከልጅ እስከአዋቂ ተደማጭነት ማትረፍ መቻላቸው ፣የመገናኛ ብዙሃን ለሚያቀርቡት ዘገባ ነጻነት እንዲኖራቸው ማድረጋቸውና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ያደረጉት ጥረት ከስኬቶቻቸው መካከል መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአጠቃላይ ለችግሮች መፍቻ ኃይል የበዛበት አካሄድ አለመጠቀማቸው እንደስኬት የሚታይና ቀደም ሲል የነበረውን ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድር የነበረ አካሄድ የሰበረ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አቶ መላኩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ተግዳሮቶች ብለው ከጠቀሷቸው መካከል የሥራአጥነት መስፋፋት፣የወጣቱ በሁከት ተሳታፊ መሆን፣የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣በብሄርና በመንደር ያለው ክፍፍል፣ በራሱ በገዥው ፓርቲ መካከል ክፍፍል መኖሩ፣ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው በሀገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ አለመ ቻላቸው፣በየጊዜው በሚፈጠር ሁከትና ግርግር በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመንደራቸው መፈናቀላቸው፣ኢትዮጵያ የሌሎችን ዜጎች ስደተኞች የምትቀበል ሀገር ሆና ነገር ግን እርሷ ችግር ውስጥ መሆኗ፣የብሄር ጉዳይ በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ በተለይ በተማሪዎች ላይ የፈጠረው ጫና እና የሚረብሹት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ፣ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣የውጭ ምንዛሪን ማሸሽ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀጣይ የሚጠበቅባቸውንም አቶ መላኩ እንደገለጹት በፓርቲያቸው ውስጥ የሚታ የውን ክፍተት መስመር የማስያዝ፣በአንዳንድ ክልሎች የሚስተዋለውን ክልል አበጅቶ የመንቀሳቀስና ለፌዴራል መንግሥትም ለመታዘዝ ፈቃደኛ ያለመሆን አዝማሚያ እንዲሁም በክልሎች መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ስልጣኑም መጠቀም መቻል አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሆደሰፊነት የሚያልፏቸው ነገሮች ‹‹ህዝብ ለምን ውሳኔ አይወስንም›› የሚል ጥያቄ እንዳያነሳባቸው ከወዲሁ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስኬቶች በአብዛኛው በፖለቲካው ዘርፍ እንደሚታይ ይገልጻሉ፡፡ እርሳቸው እንዳሉት የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው፣ ተገድበው የነበሩ የመገናኛ ብዙሃን ስራቸውን እንዲሰሩ መደረጉ፣የኢትዮጵያን ክብር ከፍ ለማድረግ በተለይም ለሥራ ሄደው ሰብአዊ ክብራቸው ተደፍሮ የነበሩ ዜጎችን ጉዳይ ላይ ያከናወኑት ተግባር የሀገር ክብርን ያስመለሰ ስኬት ነው፡፡ ለዴሞክራሲ ወሳኝ ናቸው የተባሉ እንደ ምርጫ ቦርድ ያሉ ተቋማት የሀገር መከላከያ ላይ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ለማድረግና የህግ ማሻሻያዎችንም ለማድረግ እየተሰራ ያለው ሥራ አበረታች ነው፡፡ ሥራዎች ቢሰሩም በሀገሪቷ ውስጥ ያሉት ውስብስብ ችግሮች በፖለቲካው ዘርፍ ብቻ እጅግ ሰፊ ናቸው፡፡
ተግዳሮቶቹ ብዙ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አንዳርጋቸው፤ዘር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አመለካከትና አደረጃጀት አስከፊ ሁኔታ ላይ መድረሱን ይናገራሉ፡፡ በዘር ላይ የተደራጀ ፖለቲካና ክልል በዋናነት ማዕከላዊ መንግሥቱን ለመፈታተን የሚያስችላቸው የራሳቸው ሚሊሻ፣የፖሊስና የደህንነት ኃይል ያላቸው እንዲሁም በስራቸው የተደራጀ የመገናኛ ብዙሃን መኖሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ፈጽሞ ሊታሰብ እንዳይችል እያደረገ መሆኑ ከፍተኛ ተጋዳሮት ነው፡፡
የወረዳዎቹ እንቅስቃሴ በየክልሎቹ እጅ ነው ያለው፡፡ በየወረዳው ነጻ ምርጫ ማካሄድ አይደለም በየአካባቢው መንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ችግሩ ከድሮ በበለጠ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡የፌዴራል መንግሥቱ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የሚያደርጋቸው ጥረቶች ዘር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ፓርቲዎች የኢሕአዴግ መዋቅር የያዙትንም ያልያዙትንም ጭምር ከዘራቸው ውጭ ያሉት በቀጠናቸው እንዳይንቀሳቀሱ የፖለቲካ ስራ እየሰሩ መሆናቸው የፖለቲካ ምህዳሩን እያጠበበው መሆኑ ሌላው ተግዳሮት ነው፡፡ ‹‹የፌዴራል መንግሥቱ እንዴት አድርጎ ነው በክልሎች እጅ ያለን ፀረ ዴሞክራሲ ተቋምና በዘር ከተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች እጅ አውጥቶ የፌዴራል መንግሥቱን ፍላጎት እና እምነቶች ለሁሉም በእኩልነት ቱርፋቱ እንዲደርሳቸው ማድረግ የሚቻለው የሚለው ጥያቄ ከፍተኛ ተግዳሮት ነው›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በኢኮኖሚ በኩልም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በብድርና በተለያየ መንገድ የወጣው አራት ቢሊዮን ብር ማንም መክፈል የማይችለው መሆኑ ትልቅ ተግዳሮት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የፖለቲካ እስረኞችን መፍታታቸው፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ለውጥ መጀመራቸው በራሱ ስኬት እንደሆነ በመጠቆም ተግዳሮቶቹ ላይ ማተኮር እንደሚገባ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በተደጋጋሚ እንደምለው ትልቁ ተግዳሮት መቶ ሚሊዮን ህዝብ ለለውጥ ከመምራት ይልቅ ትልቁ ችግር ኢህአዴግን ለለውጥ መምራት ነው›› ይላሉ፡፡
ዶክተር መረራ እንዳሉት ለውጡ ተጀመረ እንጂ ወደ ሥራ አልተለወጠም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ስነምህዳሩን ለማስፋት፣ ህጎችን ለማሻሻልና ሌሎችም የገቧቸው ቃሎች በስራ ላይ ካልዋሉ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ስለዚህ የተጀመረው ለውጥ ወደኋላ እንዳይቀለበስና የተሳካ እንዲሆን በሚገባው ፍጥነት ወደፊት መምራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ለውጡ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንና በሚፈለገው ፍጥነት ለውጡ ካልተተገበረ ወዳልተገባ አቅጣጫ ሊያመራ እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከተለያዩ አካላትና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የተጀመሩ ውይይቶችና በፍኖተ ካርታዎች አቅጣጫ ለማስያዝ የተጀመሩት ስራዎች ክፍተቶች እንዳይፈጥሩ መስራት ይጠበቃል፡፡
የፓንአፍሪካ ንግድ ምክርቤት ዋና ኃላፊ አቶ ክቡር ገና ደስታ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ300 የሥራ ቀናት በከፍተኛ ሁኔታ የተንቀሳቀሱት በፖለቲካ ለውጡ ላይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከኤርትራ ጋር የፈጠሩት የሰላም ግንኙነት፣ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራቸው እንዲንቀሳቀሱ፣ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ፣የመናገር፣የመሰብሰብና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች የሰሯቸውን በመጠቆም፤በ ኢኮኖሚው ላይ በተለይም የመንግሥትን ሚና በመቀነስ የግሉን ክፍለኢኮኖሚ በማጉላት በኩል ገና እንዳልተነካ ገልጸዋል፡፡ እንደ አየርመንገድና ቴሌኮሙኒኬሽን ያሉ ትላልቅ ኩባንያዎች ውስጥ የግሉ ዘርፍ በተለይም በውጭዎች እንዲያዝ የቀረበው ሀሳብ እንደማይደግፉና በነጠላ መታየት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡
በቀጣይ የተጀመሩት ለውጦች በፖሊሲም በአሰራርም መደገፍ እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ ክቡር ገና በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የንግድና የተለያዩ ግንኙነቶች መስመር እንዲይዙ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመል ክተዋል፡፡ ‹‹ምርጫው ከተካሄደ በኃላ አንድ ኢትዮጵያ ነው የምትሆነው ወይንስ የተከፋፈለች ኢትዮጵያ ነው የምትሆነው የሚያስብል ሁኔታ ስላለ በዚህ ላይም ቢሰራ›› ጥሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከአስተያየት ሰጭዎቹ መረዳት እንደተቻለው የተሰሩት ስራዎች ብዙ ቢሆኑም የሚስተዋሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ረጅም ርቀት መጓዝ ይጠይቃል፡፡
ለምለም መንግሥቱ
ጥር 24/2011