ፍሬህይወት አወቀ
መልከ መልካም፣ ተግባቢና ሰው አክባሪ ናቸው። የሰውነት አቋማቸው በአካላዊ እንቅስቃሴና በአመጋገብ የተጠበቀ ለመሆኑ ምስክር አያሻቸውም። ምንም እንኳን ስድስት አሥርት ዓመታትን መሻገር የቻሉ የዕድሜ ባለጸጋ ቢሆኑም፤ የተስተካከለና ቅልጥፍጥፍ ያለው ተክለ ቁመናቸው ግን ገና በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ አፍላ ጎረምሳ አስመስሏቸዋል።
ለሠራተኞቻቸውም ሆነ ለእንግዶቻቸው ጎንበስ ቀና ብለው በሚያቀርቡት ሰላምታ ማንም ሰው በቀላሉ ሊግባባቸው የሚችሉ ዓይነት ሰው ናቸው። በሥራቸው ትጉህ ታታሪና ደግሞም ስኬታማ ናቸው። ከራሳቸው አልፈው ለሀገር ለወገን የሚተርፉ፤ የተረፉ።
እኚህ ሰው ማን ናቸው ካላችሁ፤ ለማስተዋወቅ ከድርጅቶቻቸው መካከል ቀዳሚና ታዋቂ የሆነውን ድርጅት መጥቀስ ብቻ በቂ ነው። ይህ ሥመጥር ድርጅታቸውም በመላው ሀገሪቱ የታወቀ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ምክንያቱም ከህጻን እስከ አዋቂ በሚባል ደረጃ ለሰርግ፣ ለምርቃት ደግሞም ለዝነጣ ሙሉ ልብስ ሲታሰብ አምባሳደር ልብስ ስፌት ቀዳሚ ይሆናል።
አምባሳደር ጋርመንት፣ አምባሳደር ሆቴል፣ አምባሳደር ሪልስቴት እንዲሁም በቅርቡ ግንባታውን አጠናቅቆ ወደ ሥራ ለመግባት እየተንደረደረ ያለው የአምባሳደር ሞል ባለቤት አቶ ሰኢድ መሀመድብርሃን ናቸው የዛሬው የስኬት እንግዳችን።
በወቅቱ አካባቢው የጦርነት ቀጣና ከመሆኑም በላይ የትውልድ ቦታቸው እጅግ ገጠራማ ስለሆነ በሚፈልጉት ልክ መሥራት አልቻሉምና በ1972 ዓ.ም 200 ብር ይዘው ወደ መቀሌ አቀኑ። መቀሌ ላይ በቀላሉ ሥራ ማግኘት ስላልቻሉ ከመቀሌ 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ኩሀ ከምትባል ከተማ ሥራ ፈልገው አገኙ። በወቅቱ የቀይ ኮከብ ዘመቻ ነበርና የወታደር ልብስን ጨምሮ የከተማ፣ የገጠር፣ የሴትና የወንድ ብለው ሳይመርጡ ያገኙትን ልብስ ሁሉ እየሰፉ 11 ወራትን አስቆጠሩ።
የ11 ወራት ቆይታቸውን ባደረጉበት አነስተኛ ክፍል ውስጥ ከቀን እስከ ሌሊት ሲሰፉ ያሳልፋሉ። ብዙም የእንቅልፍ ጊዜ ያልነበራቸው አቶ ሰኢድ፤ መቀመጫ አድርገው የዋሉባትን ትራስ ተንተርሰው ቢበዛ ለአራት ሰዓታት ያሸልባሉ። ለኪራይ የሚከፍሉት ገንዘብ አልነበራቸውምና አንድ ልብስ ሰፍተው የሚያገኙትን ገቢ አከራያቸው ጋር እኩል ያካፍላሉ።
በ1974 ዓ.ም በአንዲት የልብስ ስፌት መኪና የተጀመረው የስኬት ጉዞ ዛሬ ወደ ተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች አድጎ ለበርካታ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። የዚህ ሥራ መነሻቸው አባታቸው እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ ሰኢድ፤ ትውልድና ዕድገታቸው በትግራይ ክልል ሽሬ አካባቢ ነው። ከታላቅ ወንድማቸው ስር ሆነው የተዘጋጁ የገጠር ልብሶችን በመተኮስ፣ በመዘምዘምና ጥብቆ የመስፋት ሥራን ‹‹ሀ›› ብለው ጀምረዋል።
እንዲህ እንዲህ እያሉ በ11 ወራት ቆይታቸው ሦስት ሺህ ብር ማጠራቀም ቻሉ። ያጠራቀሙትን ገንዘብ ይዘው ወደ መቀሌ በማቅናት በአንድ ሺህ ብር ያገለገለ የስፌት መኪና፤ በሁለት ሺህ ብር የቀበሌ ቤት ቁልፍ ገዝተው የግላቸው በሆነ ቤትና የስፌት መኪና የተለመደውን የልብስ ስፌት አስቀጠሉ። በዚህ ጊዜ ታዲያ ነገሮች መሥመር የያዙ በመሆናቸው አንድ ሁለት እያሉ የስፌት መኪና መጨመርና የሥራ ዕድል በመፍጠር ሥራቸውን ማስፋፋት ጀመሩ።
እየተስፋፋ በመጣው ሥራ ጥሪት መቋጠር የቻሉት አቶ ሰኢድ ከልብስ ስፌት ሥራው ጎን ለጎን የጭነት መኪና ከነተሳቢው መግዛት ችለዋል። ይሁን እንጂ በወቅቱ መኪናው በጉዞ ላይ በደረሰበት አደጋ ከረጅም ጊዜ የጋራዥ ቆይታ በኋላ ከተገዛበት ዋጋ በእጥፍ ተቀንሶ በመሸጡ ምክንያት ወደ ኪሳራ መልሷቸውም ነበር።
‹‹ከማያውቁት መልዓክ የሚያውቁት ሰይጣን ›› እንደሚባለው ያለሥራቸው ወደ መኪና ከነተሳቢው ሥራ መግባታቸው ስህተት መሆኑን በማመን የቀደመ የልብስ ስፌት ሥራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል በቁጭት ተነሱ።
በዚህ ወቅት ታዲያ ትውልድና ዕድገቱ ከጉራጌ ብሔረሰብ የሆነ አንድ የልብስ ስፌት ባለሙያን ይዘው ሥራቸው ማስፋፋት ጀመሩ። ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ልብስ ስፌት በማድረግ ጥሩ እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት የደርግ ወታደር ከሥልጣን ወርዶ በ1981 ዓ.ም ህወሓት መቀሌን ተቆጣጠረ።
በዚህ ጊዜ በአካባቢው የነበረው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ ሁሉም ነገር ጸጥ ረጭ በማለቱ የነበሯቸውን በርካታ የስፌት መኪኖች እና ብዛት ያላቸውን ጨርቆች ጭነው ወደ አዲግራት አቀኑ። ከአዲግራትም ወደ ዛላንበሳ እንዲሁም አሥመራ ተጓዙ።
ቀጥሎም በርካታ የወንድ ልብስ ጨርቆችን ሸጠው አራት የልብስ ስፌት መኪኖችን እና 21 ሺህ ብር ይዘው ጉዞ ወደ አዲስ አበባ አደረጉ። አዲስ አበባም አላሳፈረቻቸውም እጆቿን ዘርግታ ተቀብላቸዋለች። ለሥራ አመቺ በሆነው መርካቶ አካባቢ በወር 800 ብር የሚከፈልበትን ሱቅ ተከራይተው ሥራቸውንም ኑሯቸውንም በሱቁ በማድረግ ሕይወትን በለውጥ ጎዳና ማስቀጠል ጀመሩ።
የተከራዩት ሱቅ አምባሳደር ልብስ ስፌት የሚባል መጠሪያ የነበረው በመሆኑ መጠሪያው በዛው እንዲቀጥል የፈቀዱት አቶ ሰኢድ፤ ይኸው ዛሬም ድረስ አምባሳደር አምባሳደርነቱን ይዞ ቀጥሏል። ቀን ቀን ልብስ ሲሰፉ በሚውሉባት ጠባብ ሱቅ ውስጥ ማታ ማታ ደግሞ ታጣፊ ሽቦ አልጋቸውን እየዘረጉ ይተኛሉ።
እንዲህ እንዲህ እያሉ አንድ ዓመት አስቆጠሩ። ከዓመት በኋላ አቅማቸውን ስላሳደጉ ሁለት ልጆቻቸውን እና ባለቤታቸውን ከመቀሌ ወደ አዲስ አበባ አስመጥተው መሥመር መያዝ የጀመረውን ኑሮ አስቀጠሉ።
ባለቤታቸውን እና ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው በሥራ ቦታ ላይ መዋልና ማደር የማይሆን ነውና ጎጃም በረንዳ አካባቢ በ150 ብር መኖሪያ ቤት ተከራዩ። በዚህ ሁኔታ ለሁለት ዓመታት ከሠሩ በኋላ አቅም እያደረጁ የመጡት ታታሪው አቶ ሰኢድ፤ በርካታ ደንበኞችን ማፍራት ቻሉ።
ይሁን እንጂ ሥራው ሲሰፋ ያግዙኛል ብለው የቀጠሯቸው ሰራተኞች የልብ የማያደርሱና በሰዓት የማይንቀሳቀሱ በመሆናቸው ከደንበኞቻቸው ጋር ቅሬታ በመፈጠሩ ደስተኛ አልሆኑም። በዚህም ምክንያት ሥራቸውን ለመቀየር ወስነው ወደ ኤሌክትሮኒክስ ንግድ ገቡ።
ሰርተው ለመለወጥ እጅግ ጉጉ የሆኑት አቶ ሰኢድ፤ የስፌት መኪኖቻቸውን ሸጠው ወደ ኤሌክትሮኒክስ ንግድ ቢገቡም ሥራው ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑና በመስኩም የነበራቸው ልምድ አናሳ ስለነበር እንዳሰቡት ውጤታማ መሆን ሳይችሉ ቀሩ። ይሁንና ተስፋ ባለመቁረጥ ተመልሰው ወደ ቀደመው የልብስ ስፌት ሥራቸው ለመመለስ ተውተረተሩ። የገዟቸውን የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች በሙሉ በንግዱ ተሰማርተው ለነበሩ ጎረቤታቸው ሸጠው ወደ ቀደመ ሥራቸው ተመለሱ።
ዛሬ ባለሀብት ለመባል ያበቃቸው ልብስ ስፌት ለሁለት ጊዜያት ያህል ያዝ ለቀቅ ያደረጉት ቢሆንም አጠንክረው በመያዝ መርካቶ ላይ 70 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል በመፍጠር በከፍተኛ ቁጭትና ተነሳሽነት መሥራት ቀጠሉ።
ልብስ ስፌት የኖሩበት ሥራቸው ነውና በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሆኑ። የልብስ ስፌት ሥራን ወደ ፋብሪካ ለማሳደግ በነበራቸው ብርቱ ፍላጎት በ1990 ዓ.ም ገርጂ አካባቢ 9500 ካሬ ሜትር ቦታ በጨረታ ገዙ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ፋብሪካ በመገንባት በሰው ጉልበት ይዘጋጅ የነበረው ሙሉ ልብስ ሙሉ ለሙሉ ወደ ተዘጋጀ ልብስ ተቀየረ። በመሆኑም 1974 ዓ.ም የተጀመረው የልክ ልብስ ስፌት በፋብሪካ ደረጃ ተቋቁሞ ከህጻን እስከ አዋቂ አምባሳደር ሙሉ ልብስን እያመረተ ለገበያ ያቀርባል።
በሀገሪቱ በስፋት የሚታወቀው አምባሳደር ሙሉ ልብስን ወደ ገበያ ለማድረስም በርካታ ሱቆችን በመክፈት፤ ወኪሎችን በማምጣት ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የቻሉት አቶ ሰኢድ፤ ለሥራ ባላቸው ጥልቅ ፍቅርና ገና በልጅነት የሰነቁትን ትልቅ ራዕይ ለማሳካትም ከላይ ታች ማለታቸውን አላቆሙም።
ጥረታቸውም ፍሬ እያፈራ መጣና ሥራቸውን ወደ ተለያዩ ኢንቨስትመንቶች አሰፉ። በአሁኑ ወቅትም የአምባሳደር እህት ኩባንያ የሆኑትን አምባሳደር ሪልስቴት፣ አምባሳደር ሆቴልና አምባሳደር ሞል ገንብተው ለዜጎቻቸው ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ አስተዋጽዖ እያበረከቱ ይገኛሉ።
አምባሳደር በአሁኑ ወቅት በአዳማ ከተማ ከሚገኝ ትልቅ የቻይና ፋብሪካ ጋር በጋራ ሙሉ ልብስ እያመረተ ነው። ይህም ማለት ድርጅቱ ለኢትዮጵያውያን ምቹ የሆነውን ዲዛይን በሚፈልገው መጠንና ቅርጽ ያመርታል። የተመረተውንም ሙሉ ልብስ በሀገሪቱ በሁሉም ክልሎች ተደራሽ በማድረግ ለገበያ እያቀረበ ይገኛል። በተለይም በአሁኑ ወቅት አምባሳደር ሙሉ ልብስ ትልቁን የጥራት ደረጃ ያሟላና 80 በመቶ ትክክለኛ ሱፍ ልብስ እያመረተ ይገኛል።
የሀገሪቱን የዕድገት ደረጃ በመከተል ለዕድገቷ ተመጣጣኝ የሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በመገንባት የድርሻቸውን እየተወጡ ያሉት አቶ ሰኢድ፤ በሆቴል ዘርፍ ተሰማርተው አምባሳደር ሆቴልን መገንባት ችለዋል። ሆቴሉ 198 ክፍሎችንና አምሥት መሰብሰቢያ አዳራሾች ያለውና አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለ ነው።
በሪልስቴት ዘርፍ የተሳተፉት አቶ ሰኢድ፤ ደረጃቸውን የጠበቁ 101 ቪላ ቤቶችን ገንብተዋል። የአምባሳደር ሪልስቴት መኖሪያ ቤትን የገዙ ባለንብረቶች እጅጉን ደስተኞች ናቸው። ምክንያቱም ግንባታውን በጥራት ከመገንባታቸው ባለፈ ውሃ፣ መብራትና የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን አስፓልት በማድረግ መሰረተ ልማቶችን አሟልተው ለደንበኞቻቸው ያስረከቡ ሲሆን በቀጣይነት በዘርፉ ለመሳተፍ ሃሳብ አንዳላቸው ይናገራሉ።
አራት ኪሎ ከፓርላማ ፊት ለፊት የሚገኘውና በመጠናቀቅ ላይ ያለው አምባሳደር ሞል በአንድ ጊዜ 140 መኪኖችን መያዝ የሚችል ቦታን ጨምሮ በርካታ ሱቆች፣ ሱፐርማርኬቶችና የመዝናኛ ስፍራዎችን የያዘና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ነው። በቅርቡም ይህ ሞል ሥራ የሚጀምር ሲሆን ከ100 በላይ ለሆኑ ዜጎችም የሥራ ዕድል መፍጠር እንደሚችል ይናገራሉ።
በርካታ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ወደ ሥራ ማምጣት የቻሉት አምባሳደር ልብስ ስፌት 170፣ አምባሳደር ሆቴል 168፣ አምባሳደር ሞል 125 በድምሩ ለ463 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል።
ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር በትውልድ አካባቢያቸው ትምህርት ቤት እና ቤተ ዕምነትን የሰሩት አቶ ሰኢድ፤ ለሕዝባቸው ያደረጉትንና እያደረጉ ያለውን ተሳትፎ በዝርዝር ለመግለጽ ፈቃዳቸው ባይሆንም አሁንም ወደፊትም ከሕዝብና ከመንግሥት ጎን በመሆን በቻሉት አቅም ሁሉ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ በሚፈልጋቸው ጊዜ ምላሽ በመስጠት አጋርነታቸውን ለማሳየት ዝግጁ መሆናቸውን አጫውተውናል።
አቶ ሰኢድ ዛሬ ላይ ለደረሱበት ስኬት በዋናነት የሚያነሱት ሥራን ሳይንቁና በቁርጠኝነት መንቀሳቀሳቸው ቢሆንም፤ እርሳቸው ባስመዘገቡት ስኬት ውስጥ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሚና እንደነበራቸው ያነሳሉ። የስኬታቸው ምስጢር መንግሥትን ጨምሮ ደንበኞች፣ የተለያዩ ግብዓት አቅራቢዎችና አጠቃላይ አስተዳደሩና ሠራተኛው በጋራ ባበረከቱት አስተዋጽኦ እንደሆነም ይጠቅሳሉ። እነዚህ ሁሉ ባለድርሻ አካላት ተጠናክረው መሥራት በመቻላቸው ውጤታማ መሆን ችለዋል።
ወጣቱ ሥራ ለመፍጠር በራሱ ተነሳሽነት ሊኖረው እንደሚገባና ቤተሰብና መንግሥትን ብቻ መጠበቅ እንደሌለበት የሚያነሱት አቶ ሰኢድ፤ በተለይም በትምህርት ሥርዓት ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተካትቶ ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን ስለ ኢንተርፕሪነር እየተማረና እያወቀ መምጣት አለበት። ያኔ በቀላሉ እራሱን የሚችልበት ምቹ ሁኔታን በመፍጠር ከድህነት መውጣት እንደሚቻል ያምናሉ።
የአፍላ ወጣትን ያህል ሞራል ሰንቀው ራዕዮቻቸውን ዕውን እያደረጉ የሚገኙት አቶ ሰኢድ፤ በቀጣይም ወጣቶች ላይ የመሥራት ሰፊ ዕቅድ አላቸው። በተለይም በሀገሪቱ እጅግ ገጠራማ በሆኑ ጠረፍ አካባቢዎች ላይ በመንቀሳቀስ ወጣቱ እንዲቀየር የኢንተርፕሪነር ሺፕ ልምዳቸውን የማካፈልና በዘርፉ ዕውቀት ባላቸው ሞያተኞችም ሥልጠና እንዲያገኙ የማድረግና ወጣቱን ለለውጥ የማነሳሳት ሥራ ላይ የመሳተፍ ዕቅድ አላቸው።
በዚህም በሽሬ ከተማ ለአራት ተከታታይ ጊዜ ወጣቱን ሰብስበው ማወያየት የጀመሩና በቀጣይም ይህንኑ ሀሳባቸውን በተለያዩ ክልሎች ለማስፋት ሃሳብ አንዳላቸው ይናገራሉ። እኛም ይህን ታላቅ ሃሳብ አስፍተው ውጤታማ ይሆኑ ዘንድ ተመኘን።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013