
ትውልድና እድገቱ በአዲስ አበባ ከተማ ነው:: በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዟል:: የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ በኮንስትራክሽን ዘርፍ በግሉ ለመሥራት ብድር ቢጠይቅም፣ ሳይሳካለት ይቀርና ፊቱን ወደ መጽሐፍ ማንበቡ መለሰ::
ካነበባቸው መጻሕፍት መካከል የአንዱ ታሪክ ሳበው:: በዓለም በጣም ሀብታም የሆነው ሰው ከምን ተነስቶ ምን እንደ ደረሰ ከምንባቡ ታሪክ ተረዳ፤ ከዚያም ቆም ብሎ ራሱን መጠየቅ ጀመረ::
የዚህ ሰው ታሪክ እንደሚያስረዳው፤ ቤተሰቦቹ ስኳር ይነግዱ ነበር፤ ከቤተሰቡ ገንዘብ ተቀብሎ ያን ሥራ በመሥራት አትርፎ መልሶ በራሱ ተቋቁሞ ሌሎችንም ሥራዎች እየሠራ ከፍ ያለ ደረጃ ይደርሳል::
ይህንን አንብቦ እንደ ጨረሰ ወደ ራሱና በዙሪያው ወዳሉ ሰዎች ትኩረቱን አደረገ:: ሙያውን ሳይሰስት ሊሰጠው የሚችለው አባቱ መሆኑ በፍጥነት ተከሰተለት:: አባቱን በማገዝ ሥራ ለመልመድ ቆርጦ ተነሳ:: ‹‹ለምን አባቴን እያገዝኩ ሙያውን አልለምድም በሚል ሃሳብ ተነስቼ ሙያውን ሱስ አደርኩት›› የሚለው የማርፌልስ ሌዘር አጠቃላይ የቆዳ ውጤቶች ማምረቻ ድርጅት መስራች ወጣት ሱራፌል ማስረሻ ነው::
ማርፊልስ ሌዘር በ2011 መጨረሻ የተመሠረተ ድርጅት፤ በማንኛውም እድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ጫማ፣ ቀበቶ፣ ጃኬት፣ የኪስ ቦርሳና የመሳሰሉ የቆዳ ውጤቶች ያመርታል::
የአባቱን ጫማ የማምረት ሥራ በማሻሻል ሁሉንም የቆዳ ውጤቶች ማምረት መቻሉን ወጣት ሱራፌል ይናገራል:: አመራረቱን በማሻሻል ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ የቆዳ ውጤቶች በማምረት አሁን ሙሽሮች ጭምር የሚያደርጓቸውን ውብ ጫማዎች ማምረት መቻሉን ይገልጻል::
ሱራፌል ሥራው ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ የቤተሰብ ሥራ መሆኑን በማመን አሁንም ከአባቱ ጋር እየሠራ መሆኑን ይናገራል:: ‹‹አባቴ ከጎኔ ሆኖ እየሠራ ነው፤ ሙያውን ልምዶቹንና ተሞክሮውን እያጋራኝ በአንድ ላይ እንሠራለን:: እኔ ደግሞ ሥራዎቹን እያሻሻልኩ የአባቴን ሙያ ይበልጥ ለማሳደግ አጋዥ ሆኜ እየሠራሁ ነው›› ይላል::
ወደ ሥራው ሲገባ ምንም ዓይነት ገንዘብ ወይም ጥሪት አልነበረውም:: ‹‹ምንም ነገር አልነበረኝም፤ ምንም ዓይነት ገንዘብ የለኝም፣ ሙያውም ጭምር አልነበረኝም›› ሲል ያስታውሳል:: የአባቱን የቆዩ ማሽኖች ተጠቅሞ ለመሥራት በቁርጠኝነት በመነሳት በብድር ባገኛት 500 ብር አንድ ጫማ በመሥራቱን መሥራት እችላለሁ የሚል ሞራል እንዳተረፈም ይናገራል:: ከዚያም ከጓደኛው ብድር ይወስዳል፤ በጣም ትንሽ ቆዳ በመጠቀም ጫማዎችን እየሠራ በመሸጥ ብድሩን እየመለሰ ሥራዎቹን እያሻሻለና እያሳደገ አሁን ላለበት ደረጃ እንደደረሰ ይናገራል::
ሱራፌል እንደሚለው፤ ድርጅቱ ‹‹ማርፌልስ›› የተባለው ከቤተሰብ ስም የመጀመሪያ ፊዳላትን በመውሰድና ወደ አንድ ቃል በማምጣት ነው:: የጫማዎቹን በቀጥታ ለገበያ አያቀርብም:: በቅድሚያ ሞዴሎቹን ራሱና የቤተሰቡ አባላት በሙሉ እንዲሞክሯቸው ያደርጋል፤ በዚህም ምቾት የሚሰጡና የማይሰጡ መሆናቸውን ይመለከታል፤ ከዚያም ለተጠቃሚ በሚሆን መልኩ ወደ መሥራት ይገባል፤ ይህም ጥረቱ ምርቶቹ ከፍተኛ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማድረጉን አስታውቋል::
‹‹ማምረት ያለብን ለራሳችን ብለን መሆን አለበት›› ሲል የገለጸው ሱራፌል፣ ‹‹እኔ ሁሉንም ምርቶቼን ሥሠራ መጀመሪያ እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ የምንጠቀምባቸው ዓይነት መሆን አለባቸው በሚል አመለካከት ነው›› ይላል::
እሱ እንዳለው፤ የሚሠራውን የመጀመሪያ ጫማ በቅድሚያ ራሱ ከዚያም አባቱ፣ እናቱ፣ ወንድሞቹ ሁሉ እንዲሞክሩት ያደርጋል:: ከዚያ በኋላ ነው ለገበያ የሚያመርተው:: በዚህ መንገድ በማምረት ለእሱ ቤተሰብ የተመቸውን ምርት ለሌላ ቤት እንደሚደግም አስታውቋል::
የቤተሰቡን አስተያየት አዳምጦ መሥራቱ ምርቱን እንዲያሻሽል እንዳደረገው ይገልጻል:: እኔ ካደረኩትና ከተመቸኝ ለሌላው የማይመችበት ምንም ምክንያት አይኖርም፤ ማንኛውም ሰው ሊያደርገው ይችላል›› ሲል ያብራራል::
ለሽያጭ የሚወጣው ምርት እና እነሱ ለራሳቸው የሚያመርቱት የተለያየ መሆን እንደሌለበትም ያስገነዝባል:: ‹‹ይህንን ስናደርግ ደግሞ ምርታችን ተቀባይነት ላይኖረው የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም›› ብሏል::
ድርጅቱ ዘወትር አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ጫማዎችን፣ ቦርሳዎችን፣ ቀበቶዎችን ለሁሉም ሰው በሚስማማ መልኩ በመሥራት ለገበያ እንዲውሉ ያደርጋል:: ምርቶቹ ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ የሚቀርቡ አይደሉም፤ ወደ ተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ኤክስፖርት እንደሚደረጉም ይገልጻል::
ሱራፌል እንደሚለው፤ ድርጅቱ ምርቱን በየጊዜው እያሻሻለ ለውጭ ገበያም እያቀረበ ነው:: በዚህ የተነሳም ከአፍሪካ ሀገራት በኬንያ የምርቶቹ ከፍተኛ ፍላጎት አለ፤ ይህንንም በተደጋጋሚ መመልከት ችሏል:: በአሜሪካና በአውሮፓም እንዲሁ ምርቶቹ ጥቅም ላይ እየዋሉ ስለመሆናቸው መረጃው አለው::
ምርቶቹን በተለያዩ አውደ ርዕዮች ላይ በሚቀርቡበት ጊዜ ሰዎች ገዝተው ወደ ተለያዩ ዓለም ሀገራት ይዘው የሚሄዱበት ሁኔታ እንዳለ መረዳቱን ጠቅሶ፣ በይበልጥ ግን በሀገር ውስጥ ገበያ በቡቲኮችና በተለያዩ ቦታዎች እየተሸጡ እንደሚገኙ አስታውቋል:: በተለምዶ ከዚያ ወደዚህ እንደሚመጣ ብቻ ነው የሚታወቀው ሲል ገልጾ፣ ወደ ውጭ ለመውሰድ ምርቶቹን ሲገዙና ሲያዙም እንመለከታለን ሲልም ያብራራል::
ድርጅቱ ማምረቻ ቦታ ቤቴል ፖስታ ቤት አካባቢ ነው:: ምርቶቹ ተሠርተው ብቻ የሚቀመጡ ሳይሆን በትዕዛዝም የሚሠሩ አሉ:: የድርጅቱ ማምረቻ፣ ምርቶች ማሳያና መሸጫ ቦታ አንድ ላይ ናቸው::
አሁን ላይ ዘጠኝ ቋሚ ሠራተኞች አሉት፤ ብዛት ያለው ሥራ ሲኖር ደግሞ በርካታ ሠራተኞች በጊዜያዊነት ቀጥሮ ያሠራል:: በተለይ ብዙ ትዕዛዞች በሚኖሩበት ወቅት ብዛት ያለው የሰው ኃይል ስለሚፈልጉ እንደ ሥራው ብዛትና እንደተሰጠበት የጊዜ ፍጥነት ታይቶ የሰው ኃይሉ ከፍም ዝቅም ሊል ይችላል::
ምርቶቹ በማሽንና በእጅ የሚሠሩ መሆናቸውም ለሚሰጠው ትዕዛዝ የሚያስፈልገው የሰው ኃይል ከዚህ አኳያ እንደሚወሰን የሚያደርግበት ሁኔታ እንዳለም ያመለክታል:: ለአብነት ሲጠቅስም የአንድ ሺ ጫማ ትዕዛዝ ቢኖረን እንደተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ያለንን የሰው ኃይል ከፍ አድርገን እናመርታለን ሲል አብራርቷል::
በተለይ በብዛት ማሠራት የሚፈልጉ ተቋማት ካሉ በተባለው ጊዜ ውስጥ ሠርቶ ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ተናግሮ፣ ይህንንም ብዙ የሰው ኃይል በመጠቀም እንደሚሠራ ያመላክታል:: ከዚያ ውጭ ላለው ገበያ ግን በየዕለቱ እየተመረተና እየተዘጋጀ የሚቀመጥበት ሁኔታ እንዳለ ይናገራል::
ለጫማ መሥሪያ የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ከውጭ የሚመጡበት ሁኔታ እንዳለ ሆኖ በሀገር ውስጥ የሚመረቱበት ሁኔታ እንዳለም ተናግሯል:: ማራኪና ሳቢ አድርጎ ለመሥራት የሚያስችሉ ግብዓቶች በቀላሉ እንደሚገኙም ነው የተናገረው::
‹‹እነዚህን የቆዳ ምርቶች በሀገር ውስጥ ገበያ ስናቀርባቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ የሀገር ውስጥ ጫማ ጥሩ አይደለም የሚል የቆየ አመለካከት አለ›› የሚለው ሱራፌል፤ ይህንን አመለካከት ለመቀየር የሚያስችሉ ሥራዎች እየሠራ እንደሆነም ይገልጻል::
የሀገር ውስጥ ምርት ጫማ በአብዛኛው ባለበት ቅርጽ አይቆይም ቅርጹን ይቀይራል፤ ይጨማደዳል፤ የማስቲሽ ይዞታቸው ቶሎ የሚለቅ ይሆናል በማለት የሚነሱ ቅሬታዎች እንዳሉ የሚገልጸው ሱራፌል፤ ሶላቸውም ቶሎ የመቆረጥ ባሕሪና አጨራረሳቸው የወረደና ምቾት የሌላቸው ናቸው በሚል የሚነሱ ቅሬታዎች እንዳሉም ተናግሯል::
‹‹ይህ እንዳይሆን ባደረግነው ጥረት የኛ ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁ የሀገር ውስጥ ምርቶች ብቻ ሳይሆኑ ከውጭ የሚመጡ ምርቶች እንዲመስሉ ማድረግ ችለናል፤ ምቾት ያለው ብራንድ ምርት በማምረት ችለናል›› ይላል::
ማርፌልስ ሌዘር አጠቃላይ የቆዳ ምርቶች አምራች ድርጅት እንደ ቴሌ ግራም፣ ቲክቶክ ባሉት ማህበራዊ ሚዲያዎች ምርቶቹን እያስተዋወቀ መሆኑን ተናግሯል:: ድርጅቱ በማንኛውም እድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ለሁለቱም ጾታዎች የሚያገለግሉ የቆዳ ውጤቶችን እያመረተ መሆኑን ጠቅሶ፤ ምርቶቹ ለረጅም ጊዜ ሊያገለግሉ የሚችሉ መሆናቸውንም ጠቁሟል::
ድርጅቱ በምርቶቹ የተሻለ መሆን ከብዙ አምራቾች ተመርጦ በቅርቡ ወደ ሥራ በገባው አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከል በተዘጋጀው ኤግዚቢሽን እንዲሳተፍ መደረጉንም ጠቅሶ፣ ለኢግዚቢሽኑ ያስመረጠው ዋና ምክንያት የምርቶቹ ኤክስፖርት ስታንዳርድነት መሆኑንም ሱራፌል ተናግሯል::
ድርጅቱ አውደ ርዕዩ ላይ መሳተፉ ከብዙ ሰዎች ጋር ለመገናኘት እንዳስቻለውም ሱራፌል ይገልጻል፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ጎብኚዎች የተሳተፉበት ኢግዚቢሽን መሆኑን ጠቅሶ፣ ምርቶቻችንን በማስተዋወቅ የራሳችንን ብራንድ ለመገንባት እድሉን ፈጥሮልናል ይላል:: ምርቶቹን ወደ ውጭ ሀገራት ለመውሰድ ፍላጎት ያላቸው አጋሮችን ማግኘት መቻሉን ገልጿል::
ምርቶቹ ከቤተሰብ ተነስቶ ጎረቤት፣ ወረዳ፣ ክፍለ ከተማና ከተማ እያለ አሁን ለደረሰበት ደረጃ መብቃቱን ጠቅሶ፣ ሁሉም ሰው በሚባል ደረጃ የምርቶቹን ጥራትና ምቾት እየተጠቀመ አረጋግጧል ብሎ እንደሚያምን ይገልጻል::
ሱራፌል እንዳብራራው፤ አሁንም የገበያ ፍላጎቱ ስላለ የድርጅቱ የማምረት አቅም ከፍተኛ ነው:: በተለይ በየቀኑ አምስት ደርዘንና ከዚያ በላይ ጫማዎችን ማምረት ለምዷል:: ትዕዛዝ ካለ ደግሞ ከዚህም በላይ ሊሠራ ይችላል:: ትዕዛዝ ከሌለ ግን ብዙ ጫማ አይሠራም:: ድርጅቱ በጣም ትልቅ የሚባል ባይሆንም ሥራው ግን ከፍ ያለ ነው::
የድርጅቱን ምርቶች ሰዎች መርጠው ለመግዛት ሲፈልጉ ካሉበት ቦታ ማድረስ የሚያስችል አገልግሎት እንደሚሰጥም ጠቁሞ፣ ትዕዛዙ አንድ ፍሬም ቢሆን ደንበኛው የሚገኙበት ቦታ በማድረስ አገልግሎት እንደሚሰጥ ይገልጻል:: ደንበኞች የሞተረኛውን ሂሳብ ብቻ ከፍለው የሚፈልጉትን የቆዳ ምርት ማግኘት የሚችሉበት አሠራር ዘርግቷል::
‹‹እኔ የምጠቀመው አንድ ሰው ጫማውን አጥልቆ ብዙ ሰው የሚሠራበት ቦታ መታየቱ ነው፤ በዚህ ወቅት ይህ ጫማ ተመችቶኛል፤ በጣም ጥሩ ነው ብሎ ሊነገርና ይህን ተከትሎም የጫማ ትዕዛዝ ፍላጎቶች ሊመጣ ይችላል:: ይሄኔ እኔ ተጠቃሚ እሆናለሁ ብዬ አምናለሁ:: ትንሽ ነገር ተጠቅሜ ኅብረተሰቡ ሳይጎዳ መሸጥ እፈልጋለሁ›› ሲል ያብራራል::
ድርጅቱ ብዙ ትርፍ እንደማይፈልግ ጠቅሶ፣ የኅብረተሰቡን ኪስ በማይጎዳ ተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ብዙ ምርቶች እንዲሸጡና ምርቶቹን እንዲታወቁ ማድረግን አልሞ እንደሚሠራ ተናግሯል::
በቀጣይ ድርጅቱ የምርቶቹን ጥራት በየጊዜው በማሻሻል አዳዲስ ብራንዶች በማውጣት ለመሥራት ሃሳቡ እንዳለው ጠቅሶ፤ ይሄ በሀገር ውስጥ ይሠራል እንዴ ብለው ሰዎች ገርሟቸው በደንብ ተመችቷቸው የሚያጠልቁት ጫማ ለመሥራት አቅዷል:: ምርቱ በደንብ ተደራሽ እንዲሆን እንደሚሠራም አስታውቋል::
ወጣት ሱራፌል ገና ሌላም ህልም እንዳለው ጠቁሟል:: ኮንስትራክሽን ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ኮንትራክተር የመሆን ህልም አለው:: ሁለቱንም ሥራዎች ጎን ለጎን መሥራት እፈልጋለሁ፤ ይህን ህልሜን አሳካለሁ ብዬ አምናለሁ›› ብሏል::
‹‹ወጣቱ በተማረው ሙያ ብቻ ሥራ ለመፈለግና ለመቀጠር መሯሯጥ የለበትም›› የሚለው ሱራፌል፤ በቻለው መጠን አጠገቡ ሙያ ሊያስተምረው የሚችል ሰው ካለ ጠጋ ብሎ እንዲማርም መክሯል:: እንዲህ ያለው ሰው ለተወሰኑ ጊዜያት ገንዘብ እጁ ላይ ላይኖርና የፈለገውንም ላያደርግ እንደሚችል ገልጾ፣ ሙያ ከለመደ እንደፈለገ መኖር እንደሚችል አመልክቷል:: ብዙ ጥረት አድርጎ ባለሙያ ሊሆንና ጥሩ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንዲሁም ህልሙን በሂደት ሊያሳካ እንደሚችልም አስታውቋል::
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን መጋቢት 20 ቀን 2017 ዓ.ም