በማክሮ ኢኮኖሚ የእድገት መለኪያዎች ውጤት የታየባቸው አፈፃፀሞች

ኢትዮጵያ በተለይም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሙሉ ትግበራ ውስጥ ከገባ ወዲህ በሁሉም ዘርፎች ከፍተኛ የሚባል ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች፡፡ በ2017 በጀት ዓመት ባለፉት ወራት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በዲጂታል፣ በቱሪዝምና በማዕድን ዘርፍ እመርታዎች እየተመዘገቡ ስለመሆናቸው ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በቅርቡ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅትም ይህንኑ ማመላከታቸው ይታወቃል፡፡

ሰሞኑን ደግሞ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የ2017 በጀት ዓመት የሦስተኛው ሩብ ዓመት የ100 ቀን አፈፃፀም እና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ትግበራ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በተገመገመበት ወቅት በሰጡት ማብራሪያ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተለያዩ ዘርፎች ስኬቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡ የዘንድሮ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ኢትዮጵያ የተሟላ ማክሮ ማሻሻያ በገባችበት ወቅት የሚከናወን መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው አስታውቀዋል፡፡

በዛሬው የስኬት ዓምዳችንም በስኬታቸው ከተጠቀሱት ዘርፎች የተወሰኑትን ይዘን ቀርበናል። እንደሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ ዓመቱ የሀገሪቱ የገቢ አቅም ያደገበት፣ የዋጋ ግሽበት የቀነሰበትና በሌሎች የማክሮ ኢኮኖሚና የእድገት መለኪያዎችም ጥሩ ውጤት የተመዘገበበት ነው፡፡ በተለይም የዋጋ ግሽበቱ ካለፉት ወራት አሁን ላይ የቀነሰበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ ይህም የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የተወሰደው ርምጃ ውጤታማ መሆን መጀመሩን ያመላክታል፡፡ በአጠቃላይ የሀገሪቱ የገቢ አቅምን በማሳደግ ረገድ ጥሩ ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡ ይህንንም ከዚህም በላይ አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ ኢንዱስትሪው 12 ነጥብ 8 በመቶ እንዲሁም ማኑፋክቸሪንግም 12 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት፤ ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት /በጂዲፒ/ ላይ ለሚያመጣው ለውጥ አንዱ ዓለም አቀፍ አመላካች ኢነርጂ ነው፡፡ ኢንዱስትሪዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተጠቀሙት ኢነርጂ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ29 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ኢንዱስትሪዎቹ አምና ከተጠቀሙት ኢነርጂ በላይ ተጠቅመዋል ማለት አምና ካመረቱትም በላይ አምርተዋል ማለትም ነው፡፡ ኢነርጂም በአጠቃላይ ከ60 በመቶ በላይ ጨምሯል ሲሉ አብራርተዋል፡፡ ሌላው በኢንዱስትሪ ውስጥ ወሳኙ ዘርፍ የኮንስትራክሽን ዘርፍ መሆኑንም አመልክተው፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ወሳኝ ዓለም አቀፍ አመላካች ደግሞ የሲሚንቶና ብረት ምርት ናቸው ይላሉ፡፡

ለእዚህም ብረትንና ሲሚንቶን ጠቅሰው ሲያብራሩ ካለፈው ዓመት ስምንት ወር ጋር ሲወዳደር የዘንድሮው የ25 በመቶ ብልጫ እንዳለው ጠቅሰው፣ ሲሚንቶ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር የ11 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው የኢንዱስትሪ ካውንስል ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በግብዓት፣ በአቅም ግንባታ፣ በመሠረተ ልማት፣ በፋይናንስና ታክስ፣ በጉምሩክ በሎጂስቲክስ፣ በንግድ ፋሲሊቴሽን በኩል ያደረገውን ከፍተኛ ድጋፍ ጠቅሰዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ የ50 ኢንዱስትሪዎች /በስም የሚታወቁ ኢንዱስትሪዎች ናቸው/ የኃይል አቅርቦት ችግር ተፈቷል፤ ለአግሮ ኢንዱስትሪዎችና ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች የተሻለ የግብዓት አቅርቦት እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ከጉምሩክም አንጻር ለአግሮ ኢንዱስትሪዎች ለብቻቸው የአንድ መስኮት አገልግሎት ለመስጠት ተሠርቶ፣ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣትም ተችሏል፡፡

ሌላው ወሳኝ አመላካች በማክሮ ኢኮኖሚው ትልቅ ውጤት ተደርጎ የሚወሰደው ቁጠባና ኢንቨስትመንት ነው፡፡ ቁጠባና ኢንቨስትመንት ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት እድገት አኳያ ያላቸው ድርሻ ከ2015 በጀት ዓመት በፊት መቀዘቀዝ ይታይበት እንደነበር አስታውሰው፣ ከ2015 በጀት ዓመት ወዲህ ግን በተለይ በ2016 በጀት ዓመት 20 በመቶ ነበር ይላሉ፤ በ2017 ግን 23 ነጥብ 2 በመቶ ኢንቨስትመንቱ ተሻሽሏል ብለዋል፡፡

ቁጠባም ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርት እድገት አንጻር ሲታይ የተሻለ አፈፃፀም እንደታየበት ተናግረው፤ ‹‹በ2016 በጀት ዓመት 14 ነጥብ ሦስት በመቶ እድገት ማስመዝገቡን፣ በ2017 በጀት ዓመት ደግሞ 19 ነጥብ አራት በመቶ እንደሚሆን ነባራዊ ሁኔታው እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡

በመቶ ቀናት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ በትኩረት የታየው ሌላው ዘርፍ ቱሪዝም ነው፡፡ የሀገርን ገፅታ የሚገነባው የቱሪዝም ዘርፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት በኮንፍረንስ ቱሪዝም ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቦበታል ሲሉ ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ60 በላይ ዓለም አቀፍ እና አሕጉር አቀፍ ጉባኤዎችን ማስተናገዷን ጠቅሰው፣ አፈፃፀሙ በዘርፉ በተሻለ መልኩ ከሠራች ከፍተኛ ውጤት እንደምታስመዘገብ የታየበት ነው ብለዋል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ነባር የቱሪዝም ሀብቶችን የማላቅና የማደስ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ የነባር የቱሪዝም መዳረሻዎች እድሳት እንዲሁም በአዳዲስ መዳረሻዎች ላይም በስፋት ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

በቀጣይ ደግሞ እስከአሁን የተሠሩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና የሀገር ማስተዋወቅ ሥራዎች የበለጠ የሚጠናከሩበት፤ የእሱን ደግሞ ውጤት መመንዘር የሚጀመርበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት ከ10 ሚሊዮን በላይ ተጓዦችን በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ አድርጎ እንደሚያጓጉዝ አመልክተው፤ ይህም ኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ማዕከል ከመሆኗ ጋር ተዳምሮ የብዙ ባለድርሻ አካላትንና ተቋማትን እገዛ በማከል በዘርፉ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተጠባቂ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ለግብርናው ዘርፍ በሰጠችው ትኩረት በዘርፉ ከፍተኛ እድገት እያስመዘገበች ስለመሆኑንም ሚኒስትሯ አመልክተዋል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 20 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመኸር መሸፈኑን በመግለፅ፤ ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የሦስት ሚሊዮን ብልጫ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡ ይህም ከፍተኛ እመርታ እንደታየበት ተብራርቷል፡፡

በምርትም ጭምር አበረታች ውጤት መታየቱን ተናግረው፣ በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ ለአብነት ሲጠቅሱም፤ ዘንድሮ 610 ሚሊዮን ኩንታል፣ ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት 505 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

እንደእርሳቸው ማብራሪያ፤ በስንዴ ልማት ካለፈው ዓመት የተሻለ ምርት ማግኘት ተችሏል፡፡ አምና በመኸር ወቅት 122 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ የተመረተ ሲሆን፤ ዘንድሮ ወደ 152 ሚሊዮን ኩንታል ተመርቷል፡፡ ይህም የ30 ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ያሳያል፡፡

ስለዚህ በመኸር እቅድ ለግብርናው ዘርፍ ከተሰጠው ሀገራዊ እድገት ማሳካት አንፃር ከእቅድ በላይ የተሠራበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰው፣ በአፈፃፀሙም ለሰብል ምርት የተያዙ ግቦች ሙሉ ለሙሉ የሚሳኩና ከግቡ በላይ የሚሄዱ መሆኑ መታየቱን ገልጸዋል፡፡ ከሌማት ትሩፋት ጋር በተያያዘም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከፍተኛ እድገት መመዝገቡን ጠቅሰው፣ በዚህም ከታቀደው በላይ ውጤት ተመዝግቧል ነው ያሉት፡፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የዲጂታል አሠራር ሥርዓት በመዘርጋትና ብዙ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ የተሻለ ሥራ ማከናወን መቻሉንም ሚኒስትሯ አመላክተዋል፡፡ በተለይም በዲጂታል ገንዘብ ዝውውር 800 ቢሊዮን ብር በቴሌ ብርና በመሰል ዲጂታል አገልግሎቶች ተዘዋውሯል ሲሉ ጠቅሰው፣ ይህም አንዱ የሪፎርም ውጤት ነው ብለዋል፡፡ ውጤቱ ሀገሪቱ በዘርፉ ያላትን ልምድ ይበልጥ ለማጎልበት የሚያንደረድራት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ሰባት ነጥብ ሰባት ሦስት ቢሊዮን ብር በዲጂታል መልክ ቁጠባ መሰብሰቡን ጠቅሰው፣ በዚህ ውስጥ ቴሌብር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ብለዋል፡፡ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር የ38 በመቶ ጭማሪ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ባለፉት ዘጠኝ ወራት 26ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ማይክሮ ብድር በዲጂታል መሰጠቱን አስታውቀዋል። በዚህም ቴሌ ብር ትልቁን ሚና መጫወቱን ጠቅሰው፣ አምና በዚህ ሰዓት አምስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ብቻ ነበር ማይክሮ ቁጠባ በዲጂታል የተሰጠው ብለዋል፡፡

ዘንድሮ ይህ አኅዝ በ369 በመቶ አድጓል ማለት ነው ሲሉ አብራርተው፣ ስለዚህ የፋይናንስ አካታችነታችንንም በዚሁ መጠን ተሻሽሏል የሚለውን ያሳያል ሲሉ አመልክተዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ በዲጂታል የተከናወነ ግብይት በአጠቃላይ 12 ነጥብ 51 ትሪሊየን ብር ነው፡፡ አምና በተመሳሳይ ወቅት ስድስት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህ በአጠቃላይ በዲጂታል ኢኮኖሚው የታየው እመርታ የአገልግሎት ዘርፉ ለአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት /ለጂዲፒው/ የሚያደርገው እሴት ጭመራ ከተጠበቀው በላይ እንዲሆን ለማድረጉ እንደ ማሳያ ይወሰዳል፡፡

ከወጪ ንግድ በዘጠኝ ወሩ 5 ነጥብ ሦስት ቢሊየን ዶላር መገኘቱን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡ ይህም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር በ108 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ሁሉም ዘርፎች ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደሩ ጭማሪ አሳይተዋል። ግብርና በ34 በመቶ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ በ18 በመቶ ማዕድን በከፍተኛ ሁኔታ ከአምናው ጭማሪ አሳይቷል፤ ኤሌክትሪክም እንዲሁ 188 በመቶ ተጨማሪ አሳይቷል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ሌላው አመላካች ገቢ ንግድ (ኢምፖርት) መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ እሳቸው እንዳብራሩት፤ ባለፉት ስምንት ወራት ለገቢ ንግድ (ኢምፖርት) 11 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ተከፍሏል፤ ይህም ከአምናው የአንድ ነጥብ ሁለት በመቶ ጭማሪ አለው፡፡ ኢምፖርቱን በግርድፉ ከመመልከት ይልቅ ምን ኢምፖርት አደረግን የሚለው ለኢኮኖሚው ያለውን አንድምታ ያሳያል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት በተለይ ከኮቪድ በኋላ የዓለም የምግብና የሸቀጥ ዋጋ በጨመረ ጊዜ መድኃኒትን ጨምሮ አብዛኛውን ለኢምፖርት ከሚመደበው አብዛኛው ይወጣ የነበረው ለፍጆታ እቃ ነበር ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

ሚኒስትሯ እንዳሉት፤ ላለፉት ስምንት ወራት የካፒታል እቃዎች ኢምፖርት በ15 በመቶ ጨምሯል። ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲወዳደር ለግብርና የመጣ የካፒታል እቃ (ለሜካናይዜሽን የሚውል) በ52 በመቶ ጨምሯል፤ ለኢንዱስትሪ የመጣ የካፒታል እቃ በ24 በመቶ ጨምሯል፡፡ ጥሬ እቃም በተወሰነ ደረጃ ጨምሯል፡፡

ጥሬ ዕቃና በከፊል የተሰናዱ በፖሊሲው እየቀነሱ መምጣት አለባቸው ሲሉም አመልክተው፣ ሌሎች ግን እኛ ለማምረት ገና ያልደረስንባቸው ካፒታል እቃዎች ማሽነሪዎች የማስገባት ምጣኔ የተሻለ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ ይህም በግብርናና አምራች ኢንዱስትሪው ባለው አፈፃፀም ላይ ትልቅ አንድምታ እንዳለው አመልክተዋል፡፡

ሌላው የማክሮ ኢኮኖሚው አመላካች የፋይናንስ ዘርፍ አፈጸጸም መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ በ24 በመቶ ጨምሯል ሲሉ አመልክተው፣ በዚህ ስምንት ወር ባንኮች 473 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ብድር ሰጥተዋል ብለዋል፡፡ አምና በዚህ ሰዓት የተሰጠው ብድር 292 ቢሊዮን ብር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ይህ ብድር የት ነበር የሄደው? ሲባል የግል ዘርፍ 76 በመቶውን፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች 23 በመቶውን ወስደዋል ብለዋል፡፡

እንደ ሚኒስትሯ ማብራሪያ፤ በዘርፎች የተለቀቀ ብድር መታየት አለበት፡፡ ከግሉ ዘርፍ እየተለቀቀ ካለው ብድር ግብርና 23 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ 13 በመቶ ወስደዋል። ትልቁን ብድር አሁንም እየወሰደ ያለው የንግዱ ዘርፍ ነው። ይህም ማኑፋክቸሪንግና ግብርና ከትራንስፎርሜሽን አኳያ ያላቸውን ሚና ታሳቢ ያደረገ ብድር ባንኮቹ ማድረግ እንዳለባቸው ያመላክታል፡፡

ባንኮች ማሻሻያዎችን ማድረግ አለባቸው፡፡ ፋይናንስ በማቅረብ በኩል ከፍተኛ መሻሻል ታይቶባቸዋል፤ ይሁንና የሚሰጡት ብድር ወደ አገልግሎት ዘርፍ ያደላ መሆኑን መረጃው ጠቁሟል፡፡

የዓለም የታሪፍ ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ሊኖረው የሚችለው ውጤት እየተፈተሸ ስለመሆኑ የጠቀሱት ፍፁም (ዶ/ር)፤ ያለንበት ሁኔታ የተጣለው ታሪፍ በዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ላይ የሚፈጥረው መናጋት በኢትዮጵያ ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ መጤን አለበት ብለዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን እንዲህ ያለው ሁኔታ ዕድል ተደርጎ መውሰዱ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

‹‹ከተጣለው ታሪፍ ውስጥ ከእኛ በጣም የበለጠ፤ ግን የእኛ ዓይነት ሸቀጦችን የሚያቀርቡ ሀገራት የተጣለባቸው ታሪፍ ተወዳዳሪነታቸውን የሚጎዳ በመሆኑ ያንን ዕድል ለመጠቀም መሥራት ያስፈልጋል›› ይላሉ፡፡

የተፈጠረውን አጋጣሚ ለመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ባሉት ፋብሪካዎች የገበያ ዕድሉን መጠቀም እንደሚያስፈልግም ይመክራሉ። በጥቅሉ በግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ አገልግሎትና ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡ በቀጣይ ምርታማነት፣ የንግድ ሥርዓቱን የበለጠ ማዘመን፣ የወጪ ምርቱን ማሳደግ፣ ገቢን በተሻለ ደረጃ መጨመር፣ የወጪ ቁጠባና ውጤታማነት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን አፈፃፀም ማሳደግንና ሌሎችም ትኩረት የሚሹ ተብለው የተለዩ ናቸው፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በሪፎርም ላይ እንደመቆየቷ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች የዚሁ አካል ናቸው፡፡ ይህንን ውጤት በማስቀጠል ረገድ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያለው የኢኮኖሚ መዋዠቅ እድገቱን እንዳይፈትነው መሥራት ተገቢ እንደሆነም መክረዋል፡፡

ማሕሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You