የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ያልበገራቸው የሆርቲካልቸር አምራች

የዛሬው የስኬት ዓምድ እንግዳችን ዘመናዊ አርሶአደር የመሆን የልጅነት ሕልማቸውን ለማሳካት ሲሉ ከተፈጥሮና ከሰው ሰራሽ አደጋዎች ጋር በመጋፈጥና እድሜያቸውን ሙሉ የለፉበትን ሃብት ሳይሰስቱ ወጪ በማድረግ ለስኬት የበቁ ናቸው። የጊዳቦ የተቀናጀ ግብርና ድርጅት ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰዒድ ሃሰን ይባላሉ፤ ከእርሻው ባሻገር በብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ስማቸውን መገንባት የቻሉ ጠንካራ የሥራ ሰው ናቸው።

ተወልደው ያደጉት በቀድሞ ጋሞ ጎፋ አውራጃ ሳውላ ቡልቂ ከተማ ነው። ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ 10ኛ ክፍል ትምህርታቸውን ቦትሬና ሳውላ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል። አዲስ አበባ መድሐኒያለም ትምህርት ቤት ገብተው ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል። አዲስ አበባ ንግድ ሥራ ኮሌጅ (ኮሜርስ) ገብተውም በንግድ ሥራ ዲፕሎማቸውን አግኝተዋል ። እንዲሁም በዩኒቲ ዩቨርሲቲ በማርኬቲንግ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኤክስኪዩቲቭ ቢዝነስ ማኔጅመንት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል።

ከዛሬ 23 ዓመት በፊት ዲፕሎማቸውን እንዳገኙ የተቀጠሩት ”ኢኮቴሪያል ቢዝነስ ግሩፕ” በተባለ ድርጅት ውስጥ በ500 ብር ደመወዝ ነበር። በወቅቱ የሚከፈላቸው ደመወዝ ለእሳቸው ባያንስም የተመደቡት ሐዋሳ ከተማ፤ ከቤተሰብ ተለይተው በመሆኑ የቤት ኪራይና አንዳንድ ወጪዎችን ለመሸፈን ከብዷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህ ምክንያት ብዙም ሳይቆዩ ሥራውን ለመልቀቅ ተገደዋል ።

አዲስ አበባ ተመልሰው አብረዋቸው ከተማሩ ጓደኞቻቸው ጋር በመካከር ሆርን ኦፍ አፍሪካ ስቲል ትሬዲንግ (ሃስት) ኢንተርፕራይዝ የተባለ የብረታ ብረት አስመጪ ድርጅት በአስር ሺ ብር ከፈቱ። ድርጅታቸው በሁለት ዓመት ውስጥ በአስገራሚ ፍጥነት ማደግ ቻለ፤ ካፒታላቸውንም ወደ 300 ሺ ብር ከፍ አለ።

ይህም ሆኖ አብረዋቸው ከሚሰሩ አጋሮቻቸው ጋር መስማማት ባለመቻላቸው ሁሉም ቀስ በቀስ የየራሱን ድርጅት እየከፈተ ሲወጡ አቶ ሲኢድ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የብረታ ብረት ማስመጣቱን ሥራ መስራታቸውን ቀጠሉ። በርካታ የብረታ ብረት ምርቶችን ከቻይና እያመጡ በማከፋፈል ገበያውን መቆጣጠር ጀመሩ።

ድርጅታቸው እየሰፋ፤ ካፒታላቸውም ወደ አስር ሚሊዮን ብር አደገ፤ አሁንም ግን በሚሰሩት ሥራ እርካታ ማግኘት አልቻሉም። በዚህ ሁኔታ ሳሉ እንደወትሯቸው ብረት ለማስመጣት ቻይና በሄዱበት አጋጣሚ ንግዳቸውን ሆነ ሕይወታቸውን እስከወዲኛው የሚለውጥ ሁኔታ ተፈጠረ። ይኸውም ዘወትር ብረት የሚገዟት ቻይናዊ ሁልጊዜ ከቻይና እየገዙ ከመሄድ ይልቅ ለምን በምትኩ ከኢትዮጵያ ሌላ ምርት እያመጡ አይሸጡም ስትል ጠየቀቻችው።

‹‹የዚህች ቻይናዊ ጥያቄ ጭንቅላቴን ነካው፤ ከዚያች ቅስፈት ጀምሮ እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ለሀገሬ ማድረግ የሚገባኝን ነገር ማሰብ ጀመርኩ›› ይላሉ። በተለይም የልጅነት ሕልማቸው የሆነውን የእርሻ ሥራ እውን ለማድረግና ወደ ተለያዩ ሀገራት መላክ የሚችሉበትን መንገድ አሰቡ፤ ከዚያ በፊት ግን የፋይናንስ አቅማቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው አመኑ። በጉዳዩ ዙሪያ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መከሩ፤ እናም ለትልቁ ዓላማቸው አቅም ማጎልበቻ ይሆነኛል ያሉትን ”ፊሪክ ቤልት ሜታል ፕሮሰሲንግ ኤንድ ኢንጅነሪግ ፋብሪካን ” አለም ገና ላይ ከፈቱ።

በዚህም አልተወሰኑ፤ ቀጠሉናም ”አርቲሜታል ኢንጅነሪንግ” የተባለ ሌላ የመሸጫ ድርጅት አቋቁመው የሚያስመጡት ብረት ላይ እሴት በመጨመር፤ አዳዲስና በቴክሎጂ የታገዙ የብረታብረት ውጤቶችን ወደ ማምረትና መሸጥ እንዲሁም የሕንፃ ፊኒሺንግ (ማስዋብ) ሥራ ውስጥ ገቡ። በሪል ስቴት ዘርፍም ተሰማርተው አቅማቸውን ማሳደግ ቻሉ።

ይሁንና በእነዚህ ሥራዎች ብቻ ልባቸው ተረጋግቶ መቀመጥ አልቻለም፤ ይልቁንም የልጅነት ሕልማቸው የሆነውና የዘወትር ቁጭታቸው ወደ ሆነው የእርሻ ዘርፍ ለመግባት ወሰኑ። ሥራውን ለመጀመር የመጀመሪያ ምርጫቸው ያደረጉት ወደ ትውልድ ቀያቸው የጋሞ ጋፋዋን ሳውላ ነበር። ስለሕልማቸው በወቅቱ ለነበሩት የመንግሥት ባለስልጣናት ቢያማክሩም ፤ ቢሮክራሲው ውስብስብ ሆነና እንዳሰቡት ሳውላ ላይ መሬት ለማግኘት ተቸገሩ።

ሌላ አማራጭ አስበው ከአዲስ አበባ ከ800 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ኦሞራቴ ወደ ተባለ ሥፍራ በመሄድ ለማልማት ጥረት አደረጉ፤ ሆኖም ምንም አንኳን የኦሞ ወንዝ ለግብርና ልማት ምቹ ቢሆንም የቦታው ርቀት አዋጭ እንዳልሆነ ተገነዘቡ፤ እናም ሌሎች ሥፍራዎችን ማማተር ያዙ። ከብዙ ጥረት በኋላ የሚያውቁት አመራር ጥቆማና ድጋፍ ሲዳማ ክልል ጊዳቦ ወንዝ አቅራቢያ የሚገኝ 1ሺ 200 ሄክታር ለም መሬት ተረከቡ።

ከዲላ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንዲሁም ከሃዋሳ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ ይኸው የእርሻ ስፍራ ምንም እንኳን ለከተማ ቅርብ ቢሆንም ጥጥቅ ባለ ደንና ጥሻ የተሞላ፣ የሰው እግር ፈፅሞ ረግጦት የማያቅና በርካታ የዱር እንሳስት ያሉበት፤ ምንም አይነት መሰረተ ልማት ያልተዘረጋለት አካባቢ መሆኑ ቶሎ ወደ ልማት ለመግባት በከፍተኛ ሁኔታ ፈተኗቸዋል ።

በወቅቱ የፌደራል መንግሥት በጊዳቦ ወንዝ ላይ የመስኖ ግድብ የጀመረ ቢሆንም ገና ባለመጠናቀቁ እሱን መጠቀም አልቻሉም ። በዚህ ምክንያት ለሰራተኞቻቸው የሚሆን ንፁህ መጠጥ ውሃ እንኳን ለማግኘት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ ይጠይቃቸው ነበር። የጊዳቦ ወንዝ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስ ቢሆንም የአካባቢው ማሕበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ባለመሆኑ ለእርሻውም ሆነ ለማሕበረሰቡ የሚሆን የጉድጓድ ውሃ አስቆፈሩ። መሬቱን ለእርሻ ምቹ ከማድረጉ ሥራ ጎን ለጎን ከ 20 ኪሎ ሜትር በላይ የሚልቅ ከዋና መንገድ ጋር የሚያገናኝ ጥርጊያ መንገድ በራሳቸው ወጪ ዶዘር አስገብተው አሰሩ።

አቶ ሰዒድ አካባቢውን ለእርሻ ምቹ የማድረጉ አጠቃላይ ሥራ አስር ዓመታትን የፈጀባቸው ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ሙሉ ያለምንም ትርፍ ከፍተኛ ምዋለንዋይ የሚጠይቅ ኢንቨስትመንት ለማፍሰስ ተገደውም ነበር። ለእርሻ ካላቸው የተለየ ፍቅር፤ ሀገራቸውን ወገናቸውን ለመጥቀም ካላቸው የተሻገረ ሕልም የተነሳ ለዓመታት በሌሎች ድርጅቶቻቸው ያካበቱትን ሃብት ጊዳቦ ላይ ማዋላቸውንም ይናገራሉ።

በተለይም ደግሞ የወንዞችን ውሃ ለመጥለፍ ከፍተኛ ገንዘብ የጠየቃቸው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሰዒድ፤ የመስኖ ግድብ ሥራ የሚያከናውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ማግኘትም ከባድ ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። በአካባቢው የእርሻ ሥራ እምብዛም የማይታወቅ በመሆኑ፤ ከአየር ንብረቱም ሆነ ስነ-ምህዳሩ ጋር ተስማሚ የሆነ እንዲሁም አዋጭ የሆነውን የሰብል አይነት ማወቅም ሌላው የአቶ ሰዒድ ፈተና ነበር።

ከዚሁ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ በቆሎ ማምረት ሲጀምሩ ደግሞ የአመረቱት ምርት ማሳ ላይ እያለ በወረበሎችና በዝንጀሮ መንጋ የመዘረፍ አደጋ ተጋረጠበት። ይህን ጊዜ እርሻቸውን ከሰብል ወደ ቋሚ ፍራፍሬ ልማት ለመቀየር ወሰኑ። ጎን ለጎንም ከቀበሌው አስተዳደር ጋር በመነጋገር በገዛ ገንዘባቸው ፖሊሲ ጣቢያ ለመገንባት ተገደዱ።

አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት ሲጀምሩ ደግሞ በመንገድ ችግር ምክንያት ለብልሽት ይዳረግባቸው ጀመር። ለዚህም መላ አላጡም፤ ከሌላ አካባቢ የቀሰሙትን ልምድ በመቀመር በበርሜል ታንኳ ሰርተው ለከተማ ቅርብ የሆነውን መንገድ የጊዳቦ ወንዝ በማቋረጥ ምርቶቻቸውን ወደ ዲላና አቅራቢያ ባሉ ከተሞች ማድረስ ቻሉ።

ይህም ግን ዘላቂ መፍትሔ ሊሆናቸው አልቻለም፤ አንድ ቀን እንደተለመደው የጥበቃ ሰራተኛቸው ሌሎቹን ባልደረቦቹንና የአካባቢውን ነዋሪዎች በታንኳይቱ ወደ ሌላኛው የወንዙ ዳርቻ አሻግሮ በሚመለስበት ጊዜ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ደራሽ ውሃ እሱንም ሆነ የተሳፈረበትን ታንኳ ጠራርጎ ወሰዳቸው።

በሁኔታው የተደናገጡት እንግዳችን ሌላ አማራጭ መፈለግ እንዳለባቸው አመኑ፤ ከባልደረቦቻቸው እንዲሁም ወንዙን ከሚያዋሰኑ የጉጂና ሲዳማ ሕዝብ ጋር ተማከሩና ከፍተኛ በጀት በመመደብ ለእርሻው ሰራተኞችም ሆነ ለአካባቢው ማሕበረሰብ የሚያገለግል 40 ሜትር ርዝመት ያለው የብረት ድልድይ ገነቡ። የድልድዩን ስም በጊዳቦ ወንዝ ሰምጦ በቀረው የጥበቃ ሰራተኛቸው ስም ‘’ታሪኩ ድልድይ’’ አሉት። ለዘመናት በተለይ ክረምት በመጣ ቁጥር በጊዳቦ ወንዝ ይፈተን የነበረው ማሕበረሰብ ያለስጋት ከብቶቹን ሳይቀር በቀላሉ ማሻገር፤ እንዳሻው ከቦታ ወደቦታ መንቀሳቀስ ቻለ።

ከዚህ ቀደም በስም ብቻ ይታወቅ ለነበረው ሃንጠጤ ቀበሌ ፅህፈት ቤት ቢሮ ዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብለው ፊደል ከመቁጠር የዘለለ ዘመናዊ ትምህርት ለማያውቁት የአካባቢው ህፃናት እስከ አራተኛ ክፍል የሚማሩበት ትምህርት ቤት ከእነ ሙሉ መማሪያ መሳሪያው ገንብተው አስረክበዋል። እንዲሁም መለስተኛ የሕክምና አገልግሎት መስጠት የሚችል ክሊኒክም ያለማንም አጋዥ ገንብተው ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ችለዋል። በውሃ እጥረት ምክንያት በተለያየ ጊዜ ፀብ ውስጥ ይገባ የነበረው የጊዳቦ አካባቢ ነዋሪ በአቶ ሰዒድ እርሻ የመሰኖ ግድብ ከተገነባ ወዲህ እንዳሻቸው ለራሳቸውም ሆነ ለከብቶቸቸው መጠቀም ችለዋል።

የዛሬው የስኬት እንግዳችን የማሕበረሰቡን ችግር ለመፍተት በሚያደርጉት ጥረት በአካባቢው ማሕበረሰብ ከፍተኛ የሆነ ተቀባይነትንና ከበሬታ ማግኘታቸውን ይገልፃሉ። የሚሰሩት ሥራ ጠቃሚ መሆኑን በመገንዘቡም ማሕበረሰቡ እርሻውን ከታጣቂና ከወንበዴዎች ጭምር ዘብ ሆኖ የሚጠብቀውና የሚንከባከበው መሆኑን ያስረዳሉ።

ከዚህ ቀደም ለም መሬትና ዓመቱን ሙሉ የሚፈስ ወንዝ እያለው በችግር ውስጥ የሚኖረውን የአካባቢን ማሕረሰብ የሥራ ባሕል በመቀየር ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማድረጋቸውንም ይገልፃሉ። ‹‹የእኛን እርሻ በማየታቸውና እኛ ጋር ተቀጥለው በመስራታቸው በፊት አርሶ መብላትም የማያውቀውና እኛ ስንሰራ ቆሞ ይመለከተን የነበረው የአካባቢው ነዋሪ ለዘመናት ያለ ሥራ ያስቀመጠውን መሬቱን ማልማት ጀምሯል›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡

አቶ ሰዒድ በጊዳቦ እርሻቸው ብቻ ከ400 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ፈጥረዋል። መኖሪያ ካምፕና የምግብ ወጪያቸውን ጭምር በመሸፈን ተጠቃሚ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በተለይ ሴት ሰራተኞቻቸው በየቀኑ ከማሳቸው በየቀኑ አንድ አንድ ኪሎ በቆሎ በነፃ እንዲያገኙ አድርገዋል። ከዚህ ባሻገርም በሌሎች እህት ድርጅቶቻቸው ቁጥራቸው ከአንድ ሺ የሚልቁ ዜጎች ተቀጥረው እያገለገሉ ይገኛሉ።

‹‹ኢትዮጵያ ፈጣሪ የተፈጥሮ ሃብት ያደላት ሃገር ሆና ሳለ፤ በተለይ ዓመቱን ሙሉ የሚፈስ ውሃና ለም መሬት እያለን ከሃብታም ሀገራት ስንዴ መለመናችን ወላሂ ሃጥያት ነው! ነውርም ነው!›› የሚሉት አቶ ሰዒድ፤ አሁን እያለሙ ያሉትን መሬት ከማስፋት በዘለለ የሚያመርቱትን ፓፓያ፣ አባኮዶ፣ ሙዝና ሌሎችንም የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ለሀገር ኢኮኖሚ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ያመለክታሉ።

በአሁኑ ወቅት ከ600 ሄክታር ባላነሰ መሬታቸው ላይ ሄክታር ሙዝ፣ ሄክታር ፓፓያና አቦካዶ እያለሙ ሲሆን እስከ አዲስ አበባና ባህርዳር ድረስ ምርቶቻቸውን ያከፋፍላሉ። በተለይም ከኢትዮጵያ ምርት እነሰ ገበያ ልማት ድርጅት ጋር የረዥም ጊዜ ውል በመፈፀም ምርታቸውን እያቀረቡ ሲሆን በዚህም የሀገር ውስጥ ገበያን በማረጋጋት ረገድ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። ከዚህም ባሻገር በዓለም አቀፍ ገበያ ለመግባትና ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችላቸውን ‘ግሎባል ጋፕ’ የተሰኘውን የጥራት ሰርተክፌት ለማግኘት ጥረት እያደደረጉን መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በተጨማሪም በጠብታ ውሃ (ድሪፕ ኢሪጌሽን) መስኖ ልማት በመጠቀም ጥራታቸውን የጠበቁ የብርቱካን፣ መንደሪን ሎሚ፣ ማጎ እና አናናስ በስፋት ለማልማት አቅደዋል። ጎን ጎን አግሮ ኢንዱስትሪ በማቋቋም ምርቱን በማቀነባበርና እሴት በመጨመር ለሀገር እድገት ወሳኝ ሚና የመጫወት እቅድ አላቸው።

በተለይም በይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ የመግባት የአባካዶ ዘይት፣ የሙዝ ችብስና መሰል ምርቶችን በማምረት ለሀገር የውጭ ምንዛሬ ግኝት እድገት ሚናቸውን ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። እነዚህ እቅዶቻቸውን እውን ማድረግ ከቻሉ ከሁለትና ሶስት ሺ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር እንደሚችሉ ይናገራሉ ።

‹‹ለአስር ዓመታት በኪሳራ ሳለማ የነበረው ለሀገር ካለኝ ፍቅር የተነሳ ነው›› የሚሉት አቶ ሰዒድ ኢትዮጵያ በተለይም ሰፊ የተፈጥሮ ሃብት እያለ የሌሎች ጠባቂ የመሆንዋ ጉዳይ የዘማናት ቁጭታቸው ከመሆን በዘለለ ይህንን የተበላሸ ትርክት ለመለወጥ ቆራጥ አቋም ስላላቸው መሆኑን ያምናሉ። ትውልዱ በተለይም በገጠር ያለው ወጣት የማሕበረሰብ ክፍል በአካባቢው ያለውን ምቹ እድል አይኑን ከፍቶ ማየትና ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባው ይመክራሉ።

ሀገር በዜጎቿ እንድትለወጥ ከተፈለገ የመንግሥት አካላትም ከመድረክ ግብዓት በዘለለ በተጨባጭ መሬት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ ሊሆኑ እንደሚገባ፤ በተለይም ሥራ ፈጣሪዎችን አላሰራ ያሉ ቢሮክራሲዎችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ሳያሳድሩ መፍታት የሚጠበቅባቸው መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።

ማህሌት አብዱል

አቶ ሰይድ ሀሰን አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You