ከጋራዥ ቅጥር ሠራተኛነት ወደ ድርጅት ባለቤትነት

በወላጅ ፍቅርና እንክብካቤ ለማደግ አልታደለም:: ገና በለጋ እድሜው ወላጅ እናቱን ሞት ነጥቆታል:: ከዘመድ ጋር ለመኖር አልፈለገም፤ ራሱን ለመቻል በማሰብ በአስራ አምስት አመቱ ሥራ ለመቀጠር ወሰነ::

ምንም እንኳን እድሜው ለሥራ ባይደርስም በጋራዥ ቤት ውስጥ የደንብ ልብሶች የማጠብና የመላላክ ሥራ ጀመረ:: በጋራዡ ከልብስ ማጠብ ሥራው ጎን ለጎን ኑሮውን ለማሸነፍ ብሎም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም ቀን ከሌት ሳይል እንጀራ ለሆቴል ከማድረስ ጀምሮ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል::

ይህ ሁሉ ጥረቱ ራሱን ችሎ ለመኖር የሚደረግ ትግል እንጂ የሚያስገኘው ገንዘብ ብዙ አልነበረም፤ በክረምት ወቅትም እንዲሁ ጊዜውን በዋዛ በፈዛዛ ማሳለፍ ሳይፈልግ በጋራዥ ውስጥ በመላላክ ሠርቷል::

ትጋቱን የተመለከተው የጋራዡ ባለቤት እየተማረ የጋራዡን ሥራ በትርፍ ጊዜው እንዲሠራ ፈቀደለት:: በዚህና በመሳሰሉት ብዙ ድጋፍ ስላደረገለትም ፊቱን ወደ ትምህርቱም በመመለስ ቀን እየሠራ በማታው መርሃ ግብር የኮሌጅ ትምህርቱን ጨረሰ ::

ትምህርቱን እንደጨረሰም የራሱን ሥራ ለመክፈት በመወሰን በጋራዥ ውስጥ ከሚሰራቸው መደበኛ ሥራዎች በተጨማሪ ልብስ ከማጠብ ጀምሮ እስከ መላላክ ያሉ ሥራዎችን ሳይመርጥ መሥራቱን ቀጠለ:: ገንዘብ ያስገኛል ያለውን የትኛውንም አይነት ሥራ እየሠራ ከዕለት ጉርሱ የሚተርፈውን ገንዘብ እየቆጠበ በራሱ ሥራ የመጀመር ፍላጎቱን ለማሳካት ከማውጣት ማውረዱ አልፎ ወደሥራው ገባ::

ይህ የዛሬ የስኬት እንግዳችን አቶ ገረመው አሕመድ ይባላል:: የገረመው አሕመድ አልሙኒየም ማቅለጫና የብረታብረት ሥራ ኢንተርፕራይዝ መስራችና ባለቤት ነው::

ይህን ሥራውን ለማስተዋወቅ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በአዲስ ኢንተርናሽናል ኮኔክሽን ማእከል ባዘጋጀው የከተማዋ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤግዚቢሽን ያገኘነው አቶ ገረመው፣ ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ ነው::

እሱ እንደሚናገረው፤ በልጅነቱ የጀመረው የጋራዥ ሥራ የራሱን ሥራ እንዲጀምር መነሻ ሆኖታል:: እናቱን ካጣ በኋላ ኑሮውን ለብቻው መጋፈጥ ያልቻለበት ሁኔታ ወደ ሥራ ፍለጋ ያወጣው ገረመው፣ በወቅቱ በጋራዥ ውስጥ ሥራ መጀመሩ የበርካታ ሙያና የካበተ ልምድ ባለቤት እንዲሆን እንዳደረገው አመልክቷል:: ጋራዥ ሥራው ወደ ግል ሥራው በድፍረት እንዲገባና አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ መሠረት እንደሆነው ይናገራል።

‹‹የጋራዡ ባለቤት ምሳ ከማብላት ጀምሮ በቀን እየሰራሁ ማታ እንድማር የሚያስፈልገኝን ክፍያ እየፈጸመ አስተምሮኛል፤ በብዙ መልኩ ድጋፍና እገዛ እያደረገም በደንብ ሙያተኛ እንዲሆን ረድቶኛል›› ሲል ገልጾ፣ እንደ ሠራተኛ ሳይሆን እንደ ልጅ እያየ ለእዚህ ደረጃ አብቅቶኛ፤ ትልቅ ባለውለታዬ ነው፤ መነሻም መሰረትም ሆኖኛል›› ይላል::

አቶ ገረመው በ2007 ዓ.ም ‹‹የገረመው አሕመድ አልሙኒየም ማቅለጫና የብረታብረት ሥራ ኢንተርፕራይዝ›› የተሰኘ ድርጅትን በመመስረት ነው ወደ ራሱ ሥራ አሃዱ ብሎ የገባው:: ድርጅቱ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማራ ኢንተርፕራይዝ መሆኑን አመልክቶ፣ የማሽን መለዋወጫና የመኪና እቃዎችን እንደሚያምርትም ተናግሯል::

ድርጅቱ የተለያዩ ተረፈ ምርቶች (ቁርጥራጭ አልሙኒየም፣ ነሀስና ካስትአየረን (የብረት ዘር ሆኖ በተለመዶ ሸክላ የሚባለውን) መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ሥራዎችን ይሰራል:: አገልግሎት የጨረሱ ቁርጥራጮች ብረቶችን በማቅለጥ የመኪና መለዋወጫዎችን ያመርታል፤ ሞልዶችን እንዲሁም ቅርጻቅርጾች በመሥራት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ ይሠራል::

ገረመው ሥራውን ከጀመረ በኋላ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አማካኝነት ከቀድሞ አዲስ ብድርና ቁጣባ ከአሁን ስኬት ባንክ የ50ሺ ብር ብድር እንደተመቻቸለት አስታውሶ፣ ክፍለ ከተማው ከዓመት በኋላ የሥራውን ጠቀሜታ በመረዳት ሰፊ የመስሪያ ቦታ ድጋፍ እንዳደረገለት ይገልጻል:: የጥሬ እቃ አቅርቦት ድጋፍ የሚያገኝበትን መንገድ በማመቻቸትም ከንብረት ማስወገድ አገልግሎት አልሙኒየሞችን በስፋት ማግኘት የሚያስችል የገበያ ትስስር እንደተፈጠረለትም ይገልጻል::

እሱ እንደሚለው፤ ኢንተርፕራይዙ በአሁኑ ወቅት ለስራው የሚያስፈልጉትን ማሽነሪዎች አሟልቶ ይሰራል:: የማሽን መለዋወጫና የመኪና እቃዎችን በተሻለ ጥራት እየሰራ ለገበያም ያቀርባል:: ከውጭ የሚመጡት ምርቶች ማስቀረት የሚያስችሉ ተኪ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እያመረተ ይገኛል::

ኢንተርፕራይዙ በ2016 ዓ.ም በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን 500 ኪሎግራም ብረት ማቅለጥ የሚችል የብረት ማቅለጫ ፈጠራ በመሥራት ሥራ ላይ አውሏል:: ለመንገድ ልማት የሚሆኑ ዲሽከበሮችን፣ ከውጭ የሚመጡ በአልሙኒየም የማይሰሩ በካስትአየረን የሚሰሩትን ያመርታል::

የብረት ማቅለጫው ትልቅ አገልግሎት የሚሰጥና ከ1700 እስከ 2000ዲግሪ ሴንቲግሬድ አካባቢ ብረት ያቀልጣል:: ይህንን ፈጠራ ለመሥራት ሦስት ዓመታት ወስዶበታል:: ከውጪ የሚመጣው ይህን አይነቱ የብረት ማቅለጫ ማሽን ዋጋው ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት አስታውቆ፣ በእሱ በሀገር ውስጥ የተሰራው ማሽን ግን በሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ዋጋ እንደተሰራ አስታውቋል::

የማሽኑ ምርቶች ከህንድ፣ ከፓክስታን፣ ከሩሲያ እና ከቻይና የሚመጡ መለዋጫዎችን እንደሚተኩ ገልጾ፣ ጥራታቸውን የጠበቁና የተሻሉ ምርቶች መሆናቸውም አስታውቋል:: ከባድ ማሽነሪዎች ሊረግጧቸው የሚችሉና የማይሰበሩ የመንገድ ላይ ዲሽከበር መሸጋገሪያዎች፣ የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃ መስኮቶች ላይ የሚገጠሙ ምርቶችን እያመረተ መሆኑን ተናግረዋል:: ለማኑፋክቸሪንግ አገልግሎት የሚውሉ ማሽነሪዎችና መለዋወጫዎችንም እንደሚያመርት አስታውቋል::

አቶ ገረመው እንዳብራራው፤ እነዚህን ማሽነሪዎችና መለዋወጫዎች ማምረት ከጀምረ ዘጠኝ ዓመት ገደማ ሆኖታል፤ የምርቶቹን ጥራት በየጊዜው እያሻሻለና እያሳደገም ይገኛል:: የምርቶቹ የጥራት ደረጃ ላቅ ያለ ሲሆን፣ ይህም የገበያ ትስስር በመፍጠር ብዙ ደንበኞችን ማፍራት አስችሎታል::

‹‹እኛ በደንብ ካመረትን ሰዎች እነዚህ ምርቶች ከውጭ የማምጣት ሱስ የለባቸውም:: ባለሀብቱ አሁን በተሻለ መልኩ ለሀገር ውስጥ ምርቶች ትኩረት አድርጎ የመግዛት ፍላጎት አለው›› ሲልም ተናግሯል::

ኢንተርፕራይዙ የመኪና ሰስፔንሽኖች፣ ማሽኖችን እና ሌሎች የብረታ ብረቶች ውጤቶችን ያመርታል፤ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎቻቸውን የሚያሰለጥኑባቸው እንደአልሙኒየም፣ ነሐስ፣ ካስትአየርን እና የመሳሰሉትን ለማሰልጠኛ ግብዓትነት የሚውሉ ምርቶችን ያመርታል:: ቶርኖ ቤቶች፣ ጋራዦች፣ መካኒካል ኢንጂነሪንጎች፣ ቴክኒክና ሙያ ተቋማት፣ የግል የፈጠራ ባለሙያዎችና ሌሎች ኢንተርፕራይዞች ደንበኞቹ መሆናቸውን ይገልጻል::

ሥራ ፈጥሮ ኢንተርፕራይዝ መስርቶ ከትንሽ ተነስቶ እያደገ እዚህ ደረጃ የደረሰው አቶ ገረመው፣ አሁን ለ13 ቋሚ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል:: በብረት ማቅለጫ ማሽኑ ብቻ 10 ሚሊዮን ብር ሀብት ያካበተ ሲሆን፤ አጠቃላይ ካፒታሉም 20 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ ተናግሯል::

አቶ ገረመው የኢንተርፕራይዙ ምርቶች ለእሱ ጥቅም የሚያስገኙ ብቻ እንዳልሆኑም ጠቅሶ፤ ለሀገርም ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግሯል:: ይህን የማምረት ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጧል:: በሰዎች ትዕዛዝ ላይ እየተመሰረተ የሚሠራውን ይህን ስራ የበለጠ ለማሳደግና ለማስፋት ተጨማሪ ሥራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ መገንዘቡን አስታውቋል::

እሱ እንዳለው፤ ለዚህም ለሆስፒታል፣ ለመኖሪያ ቤት፣ ለሆቴል፣ የማይዝጉ የአልሙኒየም ድስቶችንና የኬሚካል ቁሳቁስን እንዲሁም ከአክንባሎ ጀምሮ ያሉ እንደ ድስት፣ መጥበሻ እና የመሳሳሉ መገልገያ እቃዎችን ለማምረት ፕሮጀክት ቀርጾ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚመለከተው አካል አቅርቧል፤ የሆስፒታል የኬሚካል ማስቀመጫዎች፣ የኪችን ካቢኒት ማሠሪያ ምርቶችንም ለማምረት አቅዷል::

ለእዚህም ከተማ አስተዳደሩ የመሥሪያ ቦታ ድጋፍ እንዲያደርግልን እየጠየቅን ነው፤ ጥያቄያችንም በጎ ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ አለን ያለው አቶ ገረመው፣ ይህን አሟልቶ ወደሥራ በመግባት በኢንዱስትሪው ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ ኢንቨስት ለማድረግ ማቀዱን አስታውቋል::

‹‹የአዲስ አበባ አስተዳደር ባዘጋጀው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አውደ ርዕይ ላይ መሳተፋችን ይህንኑ የሚያረጋግጡልንን እድሎች አግኝተናል›› ሲል ጠቅሶ፣ ‹‹ከንቲባዋና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ኃላፊዎች አውደርዕዩ በጎበኙ ወቅት የኢንተርፕራይዙን ስራ አይተዋል፤ በተለይ ብረት የሚያቀልጠው ማሽን በተግባር ስላሳየናቸው ድጋፍ እንደሚያደርጉል ቃል ገብተውልናል›› ብሏል:: በተጨማሪ የገበያ ትስስር እንደሚፈጠርላቸው ተስፋ እንደተሰጣቸውም ጠቅሶ፣ በኮሪደሩ ልማት ለመሳተፍ የሚቻልበትን አቅጣጫ እንዳመላከቷቸውም ተናግሯል:: እነዚህን እድሎች በመጠቀም ስራችንን አጠናክረን ወደተሻለ ኢንዱስትሪ ለማደግ ፍላጎት አለን ብሏል::

እሱ እንዳለው፤ በቀጣይ በሚሠራው ፕሮጀክት የመሬት ድጋፍ አግኝቶ ወደ ትግበራ ከገባ በማምረቻ ቦታ ብቻ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ዜጎችም የሥራ እድል መፍጠር ይችላል:: በሽያጭ፣ ቁርጥራጭ ብረት በመሰብሰብ፣ በትራንስፖርት አገልግሎት፣ በኮሚሽን ኤጀንትነትና ሌሎች የሥራ መስኮች ለሚሰማሩ በርካታ ዜጎችም የሥራ እድል ይፈጥራል::

ኢንተርፕራይዙ በማህበረሰብ ውስጥ እንደሚገኝ ጠቅሶ፣ ማህበራዊ ኃላፊነቱንም ከመወጣት አንጻር ብዙ እንደሚሠራ አስታውቋል:: ቀደም ሲል በሚሠራቸው ሥራዎች ያገኘውን ትርፍ ለራሱ ብቻ ሲጠቀም እንደነበር አስታውሶ፤ በተለይ የከተማዋ ኢንዱስትሪ ቢሮ አምራቾችን በአንድ በማስተባበር የደሃ ደሃ ቤቶች ሲገነባ፣ ሲያድስ፣ ማዕድ ሲያጋራ እንድንሳተፍ በተጠየቅን ቁጥር በገንዘብና በሙያችን ድጋፍ እያደረግን እንደ በርና መስኮት ያሉትን እንስራለን›› ብሏል::

መንግስት ስልጠና እንድንሰጥ ወጣቶችን ወደ ተቋማችን ሲልክ በወርክሾኑ በተግባር የተደገፈ ስልጠና በመስጠት ልምምድ እንዲያደርጉ ይተባበራል ሲል አስታውቆ፣ ከቴክኒክና ሙያ ለተግባር ላይ ልምምድ የሚላኩ ሰልጣኞችንም እንዲሁ በመቀበል በሙያ የተደገፈ የተግባር ስልጠና እንዲያገኙ እንደሚያደርግም አመልክቷል:: ስልጠናና ልምምዱ በነጻ እንደሚሰጥም ተናግሯል::

በወጣትነት እድሜ ከሚገጠሙ ፈታኝ ነገሮች የመጀመሪያው ሥራ የመምረጥ ጉዳይ ነው የሚለው ገረመው፤ ‹‹የሥራ ችግር የለም፤ ሥራ መምረጥ ግን ትልቅ ችግር ነው፤ እኔ እዚህ ልደርስ የቻልኩት ሥራ ሳልመርጥ ያገኘሁትን ሁሉ በመስራቴ ነው›› ብሏል:: እነዚህን ስራዎች የሚደፍሩት ከክልል የሚመጡ ወጣቶች መሆናቸውን አመልክቶ፣ የከተማው ወጣቶች ደፍረው መስራት እንደማይፈልጉም አስታውቋል:: ብዙ ጥረትና ልፋት ቢጠይቅም ገቢ እስካስገኘ ድረስ ሥራ ነው›› ይላል::

ሥራ ሳይመርጡ መስራት ዞሮ ጥቅሙ ለራስ መሆኑንም አስታውቆ፣ የፈለጉትን ገዝቶ መጠቀም የሚቻለው የራስ ሥራ ሲኖር መሆኑን ተናግሯል:: ስራ በተመረጠ ቁጥር ብዙ እንደሚታጣም አመልክቷል::

‹‹እኛ የምንሰራው ስራ ቀላል የሚባል ሥራ አይደለም፤ እሳት ውስጥ ነው የምውለው፤ ከተቃጠለ ዘይት ጋር እየተጨማለቅን፤ አፈር ስናቦካ እንውላለን፤ በጣም ከባድ፣ አሰልቺና አድካሚ ሥራ ነው የምንሰራው፤ ሁሉ ነገር የተመቻቸለት አልጋ ባልጋ የሆነ ሥራ አይደለም›› ሲል አብራርቷል:: አጋዥ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ማሽነሪዎች በመግዛት ሥራውን በማሻሻል ድርጅቱን ማዘመን እንደሚያስፈልግ ገልጾ፣ ሥራውን መተው ግን መፍትሔ እንዳልሆነ አስታውቋል::

አቶ ገረመው እንዳስታወቀው፤ ወጣቱ ሥራ ሳይመርጥ መስራት ከቻለ ይለወጣል:: ይህን ካደረገ መለውጥ እንዲሁም የተሻለ ሥራ መፍጠርም ይቻላል:: ወጣቱ ለሥራ ቀና ከሆነ አሰሪው እውቀትና ገንዘብ ሳይሰስት እንዲሰጠው ማድረግ ይችላል:: ከስራ ጋር በተያያዘ ብዙ ሰዎች መተዋወቅ፣ ብዙ ቤተሰቦችን ማፍራትም ይቻላል:: ደስታም የሚገኘው በሥራ ነው:: ወጣቱ በሚቻለው ሁሉ ሥራ ሳይመርጥ መስራት ቢችል የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናል ሲል ምክረ ሀሳቡን ይለግሳል:፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You