የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የጎላ ሚና እንዲኖረው ይጠበቃል፡፡ መንግሥትም ሚናውን በመገንዘብ የማበረታቻና አስፈላጊ ድጋፎች ሲደረግ እንደነበር በተለያየ ጊዜ መግለጹ ይታወሳል፡፡ይሁን እንጂ የግሉ ክፍለኢኮኖሚ ሚናውን እንዲወጣ የሚያስችል በቂ ድጋፍም ሆነ ምቹ ሁኔታ በመንግሥት አለመፍጠሩን አንዳንድ የዘርፉ ተዋናዮችና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡የግሉ ክፍለኢኮኖሚ የነበረበትን ማነቆ እና በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ሚናውን እንዲወጣ መወሰድ ስላለበት እርምጃም አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር አጥላው ዓለሙ እንደሚሉት ባለሀብቱ የሌላ አካል ውሳኔ አይጠብቅም፡፡ቢያተርፍ ተጠቃሚ እንደሚሆን፣ ቢከስር ደግሞ እንደሚጎዳ ስለሚገነዘብ ጠንክሮ ይሰራል፡፡መንግሥት ግን ሠራተኞቹ ካለ እርሱ ትእዛዝ በራሳቸው ስለማይንቀሳቀሱ፣መወሰንም ስለማይችሉ ፣አገልግሎቱም የተቀላጠፈ ባለመሆኑ ውጤታማ አይደለም፡፡በመካከላቸው ያለው የአሰራር ልዩነት ሰፊ ነው፡፡በመሆኑም የግሉ ክፍለኢኮኖሚ ከመንግሥት በተሻለ በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የጎላ ሚና አለው፡፡በሀገሪቷ በመንግሥት ሊከናወኑ የሚገባቸው ዘርፎች ይታወቃሉ፡፡ከእነዚህ ውጭ የሆኑት አብዛኞቹ በግሉ ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው፡
የግሉ ዘርፍ ሰፊ የሥራ ዕድል ቢኖረውም መንግሥት ለሁሉም እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ባለመፍጠሩ በኢኮኖሚው ላይ የሚጠበቅባቸውን ድርሻ አበርክተዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በመንግሥት በኩል ተደረገ የተባለው ድጋፍም እራሱ መንግሥት ለሚሰራቸውና ለሚፈልጋቸው ጥቂት ባለሀብቶች ካልሆነ በስተቀር አብዛኛውን የግል ባለሀብት ማዕከል ያደረገ ድጋፍ አላደረገም፡፡ ለተጠቃሚው የሚቀርቡ አገልግሎቶችም ቢሆኑ ከውጭ መጥተው የሚቀርቡ መሆናቸው እንዲሁም ለዜጎች ሥራ ሊፈጥሩ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ባለሀብቶች እንዲሰማሩ አለመደረጉ እና ሌሎችም ምክንያቶች የግል ዘርፍን እንዳቀጨጨው፣የፈቃድ አሰጣጥ፣ የግብር አሰባሰብ፣አገልግሎት አሰጣጦች የሚያረኩ አለመሆናቸው ባለሀብቱ መስራት ያለበትን ያህል እንዳይሰራ ማነቆ ከሆኑት ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡እንዲህ ያለው አሰራር ኢትዮጵያ ውስጥ የንግድ ስራውን ከባድ አድርጎታል፡፡አብዛኛው ነጋዴም በችርቻሮ ንግድ ውስጥ ነው የቆየው፡፡አምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ መግባት ፈተና ነው የነበረው፡፡
በፖለቲካው የሚደገፉና የማይደገፉ ተለይተው የሚሰሩበት አሰራር እንደነበርና ድጋፉ የተደረገላ ቸውም የፖለቲካና የመንግሥት ከለላን በመጠቀም ከወሰዱት ፈቃድ ውጭ ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር አጥላው፤ የግሉ ዘርፍ በተለያዩ ተጽእኖዎች ውስጥ በመሆኑ ሥራ የመፍጠር አቅሙ ደካማ እንዳደረገው፣በልዩ ድጋፍ መንቀሳቀሱ ተወዳዳሪ እንዳላደረገውና ይህ ደግሞ ጥራት ያለው ነገር ለመስራት እንዳላስቻለው አስረድተዋል፡፡ የነበረው አሰራር ባለሀብቱ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ እንዲንቀሳቀስና በጊዜያዊ ሥራ ላይ እንዲያተኩርና የንግድ ልምዱን እንዳያዳብር በማድረጉ ውጤታማነቱን ጥያቄ ውስጥ እንደከተተው ይገልጻሉ፡፡ኢኮኖሚው ውስጥ ሚናቸውን ለመወጣት ጥረት የሚያደርጉ ቢኖሩም ፖለቲካው ወደ አንድ ወገን ያጋደለ በመሆኑ በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ አስተዋጽኦ ለማበርከት እንዳላስቻላቸው አመልክተዋል፡፡
ዶክተር አጥላው ባለፉት ዓመታት ሀገሪቷ በሁለት አሃዝ እድገት ማስመዝገቧ ሲነገር በነበረው አይስማሙም፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፤ እድገቱ በብድርና በውጭ እርዳታ ጊዜያዊ ዕድገት ያመጣ እንጂ በሀገር ውስጥ ተሰርቶ በመነጨ ኢኮኖሚ የተገኘ አይደለም፡፡ዘላቂ ባለመሆኑም ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል አልፈጠረም፡፡ፍትሐዊ የኢኮኖሚ እድገትም አልነበረም፡፡ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ የተመሰረተው በግብርና ላይ ነው፡፡ግብርናው ከኋላቀር አመራረት ባለመላቀቁ ልማቱም አላደገም፡፡
መንግሥት ካለአድሎ አስፈላጊውን ድጋፍና ማበረታቻ አድርጎ ቢሆን ኖሮ ከተወቃሽነት ይድን እንደነበርና የግሉ ዘርፍም ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣የኑሮ ውድነትን በመቀነስ፣በአጠቃላይ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ላይ የጎላ ሚና ይኖራቸው እንደነበር የሚገልጹት ዶክተር አጥላው፤ባለፉት ጊዜያቶች የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በሁለት አሃዝ አድጓል እየተባለ ሲገለጽ የነበረውን አይደግፉም ፡፡እድገቱ የሥራ ዕድል የፈጠረና ዘላቂ አይደለም ይላሉ፡፡
በሌላው ዓለም መንግሥት በረዳትነት እንጂ ዋና አምራች ሆኖ እንደማይንቀሳቀስ ይገልጻሉ፡፡ ከፍተኛ መዋዕለነዋይ ያላቸውና በሀብታቸው የሚጠቀሱ ሰዎችን ማፍራት የተቻለው ሀገሮቻቸው በፈጠሩላቸው ምቹ ሁኔታና ባደረጉላቸው ማበረታቻ እንደሆነና ድጋፋቸውም ለስኬት እንዳበቃቸው ይናገራሉ፡፡ መንግሥት በዘርፉ ምርምር በማድረግ ችግሮችን የሚጠቁሙ ተመራማሪዎችን አለማ ሳተፉንም ይወቅሳሉ፡፡ በእርሳቸው በኩልም በኢንዱስትሪ ዘርፉ አጽንኦት እንዲሰጥ ፣ግብርናው ሊያድግ የሚችለውም ግብዓቶች በዘመናዊ በሀገር ውስጥ ተመርተው ሲቀርቡ እንደሆነ የሚያሳይ ጥናት ማቅረባቸውንም አመልክተዋል፡፡
የግሉ ክፍለኢኮኖሚ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሚና እንዲኖረው ከተፈለገ የኢትዮጵያ መንግሥት አድሎአዊ ከሆነ የብድር አገልግሎት፣ጎሳን መሰረት ካደረገ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወጥቶ መሰረተ ልማት ሥራ ላይ የጀመራቸውን እንቅስቃሴዎች በማጠናከር፣ እንደ ሀገርም የተበላሸውን አሰራር ማስተካከልና መልካም አስተዳደር ማስፈን ይኖርበታል ብለዋል፡፡
የብሉ ሙን የወጣቶች ኢንኩቤተር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር እሌኒ ዘውዴ‹‹አንድ ባለሀብት ከሚያየው ችግር ተነስቶ እራሱንም ሀገሩንም ለመጥቀም መነሳሳት ያለበት፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አይስተዋልም፡፡ይሄ አንዱ ችግር ነው፡፡ሌላው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለሀብቱ ለግሉ እንደሚጠቀም ተደርጎ ስለሚታሰብ በጥርጣሬ ነው የሚታየው፡፡ጥርጣሬው የበዛ በመሆኑ በራሱ ሰርቶ ውጤታማ ቢሆንም እንኳን አይታመንም፡፡ቁጥጥርና ክትትሉ ከመጠን በላይ መሆኑም ባለሀብቱን በስጋት እንዲንቀሳቀስ ነው ያደረገው››ሲሉ ባለሀብቱ ላይ ያለውን ጫና ያስረዳሉ፡፡
አመለካከቱ ጎጂ መሆኑ ደግሞ ከእራሱ አልፎ ሀገርን ለመጥቀም ጥረት የሚያደርገው ባለሀብት በአስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ እንዲሰራ ማድረጉን ይገልጻሉ፡፡ጉዳቱ ደግሞ ሀገር ሊጠቅም ቀርቶ ከስራውም እንዲወጣ እያደረገው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ትክክለኛና አስፈላጊ የሆነ ቁጥጥር ግን በጥረቱ ውጤታማ የሆነውንና መንግሥትን ተጠግቶ ወይንም በሙስና ለመክበር የተንቀሳቀሰውን ለይቶ ያወጣል፡፡ ባለሀብቱ ለሀገር የሚጠቅም ተደርጎ እን ዳይወሰድ ተጽዕኖ መፍጠሩንም አመልክተዋል፡፡ኢትዮጵያ ውስጥ በባለሀብቱ ላይ የሚደረገው ጫና እንደ ኬንያ ባሉ ጎረቤት ሀገሮች እንደማይስተዋልም ይናገራሉ፡፡
እንደ ዶክተር እሌኒ ገለጻ፤የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው መንግሥት ሀብት አይፈጥርም ፡፡ብቻውንም ሀገር አይገነባም፡፡ካነስተኛ ሥራ ፈጠራ ጀምሮ እስከ ከፍተኛው ድረስ የግሉ ባለሀብት ነው የሚሳተፈው፡፡ባለሀብቱ ከአንድ ሀኪምና መሀንዲስ እኩል የተከበረ ነው፡፡በኢትዮጵያ ግን ገና ነው፡፡አክብሮቱም ድጋፉም ይቀራል፡፡መንግሥት ለብቻው ለመስራት ጥረት ሲያደርግ ነው የሚስተዋለው፡፡ባለሀብቱን ተስፋ የሚያስቆርጥ እንጂ የሚያበረታታ ነገር የለም፡፡ባለሀብቱ የግብር ግዴታውን ለመወጣት፣ የስራ ቦታና ከባንክ ብድር ለማግኘት፣ ይጉላላል፡፡በሥራ ላይ ያለውም ቢሆን ባለው ሁኔታ እድሜውን ማራዘም እንጂ ለተሻለ ውጤት የሚንቀሳቀስ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለንግዱ ማህበረሰብ ያለውን መጥፎ አመለካከት ከመቀየር ጀምሮ የአገልግሎት አሰጣጥን ማስተካከል ካልተቻለ ውጤት ይመጣል ብሎ መጠበቅ የዋህነት እንደሆነ ዶክተር እሌኒ ያስረዳሉ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የሚሰራ ሥራ እያለ ምግብቤት እና ፀጉርቤት ከፍቶ መስራት፣ ቤት አከራይቶ መጠቀም ላይ ነው ያለነው፡፡ትክክለኛው ባለሀብት አልተፈጠረም ማለት ይቻላል፡፡የግሉ ዘርፍ ከጥርጣሬ ውስጥ ሲወጣ ለሀገር ያስባል፡፡ይነሳሳል፡፡ ለእራሱ ብሎ ስለሚንቀሳቀስም ፈጠራዎች ይዳብራሉ፡፡በየዓመቱ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመቶሺ የሚመረቁ ተማሪዎች የሥራ ዕድል ማግኘት የሚችሉት የግሉ ዘርፍ ሲስፋፋ ነው፡፡ በመሆኑም የፈጠራ ስራዎች ወደመሬት ይወርዳሉ›› በማለት የግሉ ክፍለኢኮኖሚ ሚና የጎላ እንደሆነ ያስረዱት ዶክተር እሌኒ ያለፉ ስህተቶችን አርሞ ለውጤት መነሳሳት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ዶክተር እሌኒ ተቋማቸውም በኢኮኖሚ ውስጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡እርሳቸው እንዳሉት ተቋማቸው ትልልቅ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውንና ፈጠራ በመስራት ላይ ያሉ ወጣቶችን የክህሎት ስልጠናና የመነሻ ካፒታል በመስጠት ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ከኩባንያዎች ጋር በማገናኘት እየሰራ ይገኛል፡፡ ትላልቅ የፈጠራ ስራዎች እየመነጩ በሀገር እድገት ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያግዝ ሥራ እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
የፓንአፍሪካ ንግድ ምክርቤት ዋና ኃላፊ አቶ ክቡርገና ደስታ‹‹የግሉ ዘርፍ ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ግብር በመክፈልና የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ኢኮኖሚውን የሚያንቀሳቅስ ኃይል ነው››ይላሉ፡፡ የግሉዘርፍ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሚናውን መወጣት የሚችለው መንግሥት የሚጠበቅበትን መሰረተልማት ሲያሟላ፣የግብርና የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማመቻቸት ሲችል እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ ክቡርገና በሀገሪቷ ውስጥ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋጋት በንግድ እንቅስቀቃሴ ላይ ጫና ያሳድራል፡፡ ይሄ ደግሞ የኢኮኖሚ አቅምን ያዳክማል፡፡ የኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት ያስመዘገበችው ባለሁለት አሀዝ ዕድገት በመንግሥት ብቻ የተመዘገበ አይደለም፡፡የግሉ ዘርፍ ሚናም ነበረበት፡፡በዓለም ላይ ለውጦች ሲኖሩም ኢትዮጵያንም በተዘዋዋሪ ይነካታል፡፡የንግድ ልውውጥ ይስተጓጎላል፡፡የግሉ ዘርፍ በሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የጎላ ሚና እንዲኖረው ከተፈለገ አሰራሩን መፈተሽ ይገባል፡፡ስለ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ሲታሰብ ቆዳና ሌጦ ወይንም ቡና ብቻ መታየት የለበትም፡፡በትራንስፖርት ዘርፉም ሊቃኝ ይገባል፡፡
አሁን ያለውን የኢትዮጵያ አየርመንገድ ሁለትና ከዛ በላይ እንዲሆን መስራት ይጠበቃል፡፡ቴክኖሎጂ እና ኢንዱስትሪው መስፋፋት አለበት፡፡የውጭው ባለሀብት ግብር ላይ ብዙ ተደራድሮ የሚመጣ በመሆኑ የሚጠቅመው የሀገር ወስጥ ባለሀብቱን ማበረታታት ነው፡፡ነፃ የንግድ ቀጠናን ለማስፋፋት ተቋማቸው እየሰራ መሆኑን የሚናገሩት ክቡርገና የገበያ ዕድል እንዲሰፋና እንዲበረታታ እንዲሁም ምርቶች ወደ አፍሪካ እንዲላኩ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
እንደ አስተያየት ሰጭዎቹ ማብራሪያ ያለፉትን በማስተካከል ውጤታማ መሆን የሚቻልበትን መንገድ መያዝ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው፡፡
ጥር 24/2011
ለምለም መንግሥቱ