ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሚያስደምም ለውጥና ሀገራዊ መነቃቃት ውስጥ በመግባት ማንም ሊክደው የማይቻል በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችላለች። ከተመዘገቡት ስኬቶች መካከል አንዱ ዜጎች የሃሳብ ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህም ለጀመርነው ሰላምና ዘላቂ ልማት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው፡፡
ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ቡድኖች የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት የወጣቶችን ስሜት በመኮርኮር አመፅና ረብሻ ለማስነሳት በርካታ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ይታያሉ። እነዚህ ኃላፊነት የጎደላቸው ቡድኖች የሕዝቡን ሰላም ለማደናቀፍ ትንንሽ ጉዳዮች መልካቸውን እንዲቀይሩ በማድረግ እና የተሳሳቱ የፈጠራ መረጃዎችን በማሰራጨት ወጣቱን ወደ ብጥብጥና ሁከት በመቀየር የሰዎች ህይወት እንዲጠፋና ንብረት እንዲወድም ምክንያት እየሆኑ ይገኛሉ።
ይህን ተከትሎ መንግስት ጸጥታ የማስጠበቅ፣ የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ስራን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ እነዚህ ህይወት የሚያጠፉና ንብረት የሚያወድሙ ኃይሎች ፊታቸውን ወደ ሰላም አዙረው ለሀገር እድገት እንዲሰሩም በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። ይህንን ለማሳካት መንግስት በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል ወጣቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ሥራ መስራት አንዱና ዋነኛው ነው።
የሰላም ሚኒስቴር በኢትዮጵያዊ አብሮነትና አንድነት ዙሪያ በመጀመሪያ ዙር ለ35 ሺህ ወጣቶች ስልጠና ያዘጋጀ ሲሆን በአጠቃላይ በስልጠናው 50 ሺህ ወጣቶች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተሰምቷል፡፡ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ እነዚህ ወጣቶችም “ሰላም፣ መተሳሰብና ፍቅር” የሞላባት ኢትዮጵያን የማየት ራዕይን በመሰነቅ በ22 ዩኒቨርሲቲዎች ወደ ተዘጋጁ የማሰልጠኛ ማዕከላት ገብተው ለ45 ቀናት ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ለአሥር ወራት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመሰማራት ለማህበረሰቡ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ይሰጣሉ።
ሰልጣኞች ከመላው የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጡና በፈቃደኝነት የተመዘገቡ፣ የከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው ስራ ላይ ያልተሰማሩ ሲሆኑ፣ ስልጠናው አገር ወዳድና ምክንያታዊ የሆኑ ወጣቶችን በመገንባት የሰላም ዘር መዝራት እንደሚያስችል የታመነበት ነው።
በርግጥ መንግስት ከባለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት፣ ሀገራዊ መግባባትና አብሮነትን ለማጎልበት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን አከናውኗል። ማሕበራዊ መስተጋብሯ የተሟላ፣ ሰላሟ የተጠበቀና አንድነቷ የተጠናከረ ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት ወጣቶችን ማሳተፍ የማይተካ ሚና አለው።
ለብሔራዊ አንድነትና ዘላቂ ሰላም መከበር ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይም ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ እንደነዚህ ያሉ አሳታፊ ፕሮግራሞች ተቀርጸው ሲተገበሩ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ይቻላል።
ይህን ለማሳደግም የሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ የወጣቶች በጎ ፈቃድ ማህበራዊ አገልግሎት ፕሮግራም ቀርፆ ወጣቱን በስብዕና፣ በአመለካከት እና በሥራ ባህል ዙሪያ ስልጠና መስጠት መጀመሩ ይቀጥል የሚያስብል ነው። በዚህም ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ እጅግ ከፍተኛ እንደሚሆንም እሙን ነው።
ለነውጥ የሚያነሳሳ ስሜት ኮርኳሪ ነገሮችን በመጨማመር ወጣቱን ወዳልተፈለገ መንገድ እንዲያመራ ከሚሰሩ የጥፋት ኃይሎች ወጣቶችን ቀድሞ ማንቃት አስፈላጊ ነው።
በርግጥ ወጣት ለልማትም ሆነ ለጥፋት ትልቅ ድርሻ ያለው አካል ነው። ወጣቶች ነገሮችን በትኩረት ተመልክተው መልካሙን ከመጥፎው መለየት ካልቻሉ በቀላሉ ለጥፋት ኃይሎች መገልገያ መሆናቸው አይቀርም። በስሜታዊነት የሚቀሰቀስ አመጻና ነውጥ መነሻውም መድረሻውም አይታወቅም።
አሁን በአገራችን ልዩነትን ማስተናገድ የሚችል ሥርዓት እውን ሆኗል። እንዲህ ያለ ስርዓት እውን እየሆነበት ባለው አገር ነውጥንና ሁከትን መፈለግ አግባብነት የለውም። አንዱ የስልጣኔ መለኪያ ልዩነትን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ ነውና።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ሀገራችንን ያስቸገራት የአመላካከት ችግር ነው። ኢትዮጵያ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መብታቸው የሚከበርባትና ወጣቶች ህልማቸውን እውን የሚያደርጉባት ሀገር እንድትሆን ሁሉም በቀና አስተሳሰብ ሃሳቡን በሰላማዊ መንገድ ማራመድ መቻል ይኖርበታል። ለዚህም ግጭቶች ሲፈጠሩ በጉልበት ሳይሆን በማስተዋል የሚንቀሳቀስ፣ በምክክርና በምክንያት የሚያምን ዜጋ መፍጠር ያስፈልጋል።
መንግስት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታት በአትኩሮት እየሰራ ሲሆን ለተፈናቀሉ፣ ከትምህርት ለተስተጓጎሉና ወላጆቻቸውን ላጡ ህጻናት፣ ሴቶችና አቅመ ደካሞች አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ እንዲያገኙ ጥረት ማድረጉን ሊቀጥልበት ይገባል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ህብረተሰቡ ከጸጥታ አባላት ጋር በመተባበርና በመተጋገዝ ለሰላም መስራት ይኖርበታል።
የሁሉም ነገር መሰረት ሰላም ነው። በአገራችን የተጀመረውን የብልፅግና መስመር ቀጣይነት ማረጋገጥ የሚቻለው እስካሁን ያስመዘገብናቸውን ድሎች በመጠበቅ የቀሩንን ለማሳካት ጠንክረን መስራት ስንችል ብቻ ነው።
በአጠቃላይ በሊቢያና በሶሪያ ከሚታየው ቀውስ በመማር አንድነትንና አብሮነትን ያጎለበተ ትውልድ በመፍጠር ሰላሟ የተጠበቀና የበለፀገች ኢትዮጵያን የመገንባት ሂደት መቀጠል አለበት። ይህም ሊሳካ የሚችለው በወጣቶች ላይ ሰላምን መዝራትና ማጨድ ስንችል መሆኑን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሊገነዘብ የሚገባው ጉዳይ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 27/2013