በቃ ለማለት በቂ ጊዜ አለ !

የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሕዝቦች ከመጡበት እና አሁን ካሉበት ተጨባጭ እውነታ አኳያ ተመሳሳይ እጣ ፈንታ የሚጋሩ ሕዝቦች፤ በአንድ ይሁን በሌላ አንዳቸው ከአንዳቸው ጋር በባሕል፤ በቋንቋ እና በሀይማኖት የሚተሳሰሩ ናቸው። የቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብ ከፈጠረው መከፋፋል ውጪ በሁለንተናቸው የአንድ ቤተሰብ አባል የሆኑም ይገኙባቸዋል።

ቅኝ ገዥዎች በአካባቢው ያላቸውን ፍላጎት ለማስቀጠል ከነበራቸው ፍላጎት እና አፍሪካን በመቀረማማት ሂደት በተጣጣሉት የባለቤትነት እጣ፤ አፍሪካውያን ሳይወዱ በግድ ከወንድሞቻቸው ተለይተው እንዲኖሩ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ባልተገባ የቅኝ ገዥዎች ትርክት መለያየትን እንደ አማራጭ ወስደው በአንድነታቸው ውስጥ የነበረውን አቅም እንዲያጡ ሆነዋል።

ከሁሉም በላይ አካባቢው በልዩነት እና በጠላትነት ትርክት ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ የግጭት እና የጦርነት ቀጠና ሆኗል። የጽንፈና እና አክራሪ ቡድኖች መሸሸጊያ እና መፈልፈያ ማእከል ሆኗል፤ ችግሩ ከአካባቢው አልፎ የዓለም አቀፍ ሰላም እና መረጋጋት ስጋት ምንጭ የሆነበት ሁኔታም ተስተውሏል።

በቀጠናው በአንድም ይሁን በሌላ በሚከሰቱ ጦርነቶች እና ግጭቶች የአካባቢው ሕዝብ ለከፍተኛ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድነት ተዳርጓል። በየወቅቱ ድህነትን አሸንፎ ለመውጣት የሚያስችል መነሳሳት ቢኖርም ልማት ማካሄድ የሚያስችል ሰላም በአካባቢው ማስፈን ባለመቻሉ፤ የድህነት እና የኋላቀርነት ማሳያ ከሆነም ውሎ አድሯል።

ፀረ-ቅኝ ግዛት ትግሉ በብዙ መስዋእትነት በድል ከመጠናቀቁ ማግስት ጀምሮ በአካባቢው የተፈጠረው የመከፋፈል ትርክት በትግሉ ዋዜማ የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች በጋራ የተመኙትን የተሟላ ነጻነት በእጃቸው እንዲያስገቡ አድርጓቸዋል። እራሳቸውን ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ አሳልፎ ለሰጡበት የቁልቁለት ጉዞ ጅምሮ ሆኗል።

የአካባቢውን ሕዝብ የትናንት አብሮ የመኖር ታሪኩን በማይመጥኑ፤ የሕዝቡን ሆኖ የመገኘት ተስፋ በማይሸከሙ የፖለቲካ አመለካከቶች እና አመለካከቶቹ በወለዷቸው ግራ መጋባት እና ውዥንብሮች ከአንድ የፈተና ምእራፍ ወደ ሌላ የከፋ የፈተና ምእራፍ እየተሸጋገረ እዚህ ደርሷል። ዛሬም በተመሳሳይ የልዩነት እና የጠላትነት ትርክት ያልተገባ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል።

የአካባቢውን ሕዝባች ማኅበራዊ፣ መንፈሳዊ እና ባሕላዊ እሴቶችን መሰረት ባላደረጉ፤ የሌሎችን አጀንዳ ተሸካሚ በሆኑ የፖለቲካ ሊህቃን እና በመፈንቅለ መንግሥት እና በነጻ አውጪ ስም ወደ ሥልጣን በመጡ ኃይሎች ቀጣናው ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በላይ መረጋጋት ተስኖት ቆይቷል።

አንዳንዶቹ አንድ አይነት ቋንቋ እና ባሕል ሀይማኖት ሳይቀር እየተጋሩ፤ የፖለቲካ ሊሂቃኑ በሚፈጥሯቸው የጠላትነት እና የልዩነት የፖለቲካ ትርክቶች አንዳቸው ለሌላኛው የሰላም እና መረጋጋት ምንጭ መሆን አቅቷቸው፤ እስከዛሬዋ ቀን ድረስ የአካባቢው ሕዝቦች ያልተገባ ዋጋ እያስከፈሉ ይገኛሉ።

የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ሕዝቦች ከታሪክ፣ ከባሕል እና ከማሕበረሰባዊ ማንነታቸው አኳያ እጣ ፈንታቸው ተመሳሳይ ስለመሆኑ በብዙዎች ዘንድ በስፋት የሚነገር ነው። ሀገራቱ ያላቸውን አቅም አቀናጅተው ለጋራ ተጠቃሚነት መንቀሳቀስ ከቻሉ፤ አካባቢው አዲስ የኢኮኖሚ አቅም ሆኖ እንደሚወጣ የብዙዎች እምነት ነው።

አካባቢው ካለው ስትራቴጂክ አቀማመጥ ፤ ገና ያልተነካ /ያለማ ከፍተኛ የተፈጥሮ ሀብት ፣ ለመልማት ከፍተኛ ፍላጎት እና ለዚህ የሚሆን አቅም እና መነሳሳት ያለው ሕዝብ መኖሪያ አካባቢ ከመሆኑ አኳያ የሕዝቡን ከድህነት እና ከኋላ ቀርነት የመውጣት መሻት ተጨባጭ ማድረግ እንደሚባለው ብዙ የሚያሳስብ አይደለም ።

የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ከሁሉም በላይ ከሰላም እጦት ጋር በተያያዘ ከከፈሉት ያለተገባ ዋጋ አንጻር ለሰላም እና ከሰላም ለሚመነጭ ልማት እና ብልጽግና እራሳቸው ያስገዙ፤ በእያንዳንዱ የእለት ተእለት እንቅስቃሴው ውስጥ ሰላም እና ልማትን አጀንዳ አድርጎ የሚንቀሳቀስ ሕዝቦች ናቸው። ይህ ደግሞ የመልማት እድላቸውን የበለጠ ተጨባጭ ያደርገዋል።

ለዚህ ደግሞ የሕዝብ ፍላጎት እና የአካባቢውን የመልማት አቅም ተሳቢ ያደረገ፤ አካባቢያዊ አቅሞችን አሟጦ ለጋራ ተጠቃሚነት የሚሰራ፤ ከልዩነት እና ከጠላትነት ትርክት ወጥቶ ለሰላም እና ልማት የሚያዜም አዲስ የፖለቲካ እሳቤ የተሸከመ ቀጠናዊ የአመራር አቅም መፍጠር ያስፈልጋል።

ይህን ተጨባጭ በማድረግ ሂደት የአካባቢው ሀገራት ሕዝቦች ቀጣይ እጣ ፈንታቸው ተመሳሳይ መሆኑን አምነው እና ተቀብለው በጋራ ሊንቀሳቀሱ ይገባል። በተለይም በልዩነት ትርክት እና በጠላትነት መፈላላግ አካባቢውን የግጭት እና የጦርነት ቀጠና እያደረጉ ያሉ፤ በንጹሀን ደም እና ተስፋ የጀግና ጀግና ጨዋታ የሚጫወቱ፤ ከትናንት ጥፋቶቻቸው ተምረው ለመመለስ ፈቃደኛ ያልሆኑ የፖለቲካ ኃይሎችን በቃ ሊሏቸው ይገባል። ለዚህ ደግሞ በቂ ጊዜ አለ።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You