
በግለሰብ ፣ በማህበረሰብ ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚደረግ ለውጥ ነገን በተስፋ ከመጠበቅ የሚመነጭ መነሳሳት ነው ። ትናንትን በሁለንተናዊ መልኩ በማጤን ፣ ዛሬን ከትናንት በተሻለ በመግራት ነገን በብዙ ተስፋ የመጠበቅ ሠብዓዊ መነቃቃት ነው ። ከትናንት መሠረት ላይ ቆሞ ዛሬ ላይ ነገዎችን የመሥራት እና ከትናንት ድባቴ የመውጣት ተፈጥሯዊ መንገድ ነው ።
ዓለም በሁለንተናዊ መንገድ ዛሬ ላይ የደረሰችው በተንሰላሰሉ የለውጥ ሂደቶች ውስጥ በማለፍ ነው። ሂደቶቹን ከስሜት በዘለለ በተጨባጭ እውቀት መግራት የቻሉ ግለሰቦች፣ ማህበረሰቦች፣ እና ሀገራት ስኬታማ የሕይወት ተሞክሮዎች ውስጥ በማለፍ ነገዎቻችውን ዛሬ ላይ መሥራት ችለዋል ። በዚህም ትውልዶች ከትናንት ድባቴ ወጥተው የራሳቸውን ዛሬዎች በብዙ ተስፋ እንዲኖሩ እድል ፈጥረዋል ።
ዓለማችን ከራሳቸው አልፈው የዓለምን አሁናዊ ገጽታ የለወጡ ብዛት ያላቸው ለውጦችን አስተናግዳለች ። ለውጦቹ በባህሪያቸው ከተለመዱ / በልምምድ ብዛት ባህል ከሆኑ ግለሰባዊ ማህበራዊ እና ሀገራዊ አሴቶች ጋር ተጣጥመው የሚሄዱበት የአስተሳሰብ መሠረት ስለሌላቸው በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ለማለፍ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል ።
በግለሰቦች ደረጃ ያለውን እውነታ ትተን እንደሀገር ያለውን ለማየት ብንሞክር ፣ በዓለማችን እጅግ ብዙ ሀገራት በለውጥ መነሳሳት ውስጥ አልፈዋል ። አንዳንዶች መነሳሳቱን በእውቀት እና በጥበብ መግራት ባለመቻላቸው ፤ መሠረታዊ የሆነውን የለውጥ ባህሪ ባለመረዳት ለውጡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸው ለከፋ ውድቀት እና ኪሳራ ተዳርገዋል።
ሀገራዊ የለውጥ መነሳሳቶችን በስክነት ፤ በእውቀት እና በጥበብ መግራት የቻሉ ግን ከራሳቸው አልፈው ለዓለም ያበረከቱት እና እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ከግምት ያለፈ ፤ በተጨባጭ የዓለምን አሁናዊ መልክ እና ቅርጽ መቀየር ያስቻለ ነው። ለዚህም የቅርቦቹን የቻይናንን፤ የደቡብ ኮሪያን እና የእስያ ሀገራትን የለውጥ ተሞክሮ ማየት በራሱ በቂ ነው።
ከዚህ በተቃራኒው በስሜታዊነት ተጀምረው በጥፋት የተጠናቀቁትን ፤ እስከዛሬም የሀገራቱን ሕዝቦች ብዙ ዋጋ እያስከፈሉ ያሉ በዓረቡ ዓለም የጸደይ አብዮትን ተከትለው የተፈጠሩ ሀገራዊ የለውጥ መነቃቃቶችን ማሰብ ይቻላል ። እነዚህ ሕዝባዊ የለውጥ መነሳሳቶችን በአግባቡ በእውቀት እና በጥበብ መምራት የሚያስችል ሃይል ባለመፈጠሩ ከሽፈዋል ።
በብዙ የለውጥ ተስፋ ወደ አደባባይ የወጡ የሀገራቱ ሕዝቦች ፍላጎታቸውን በአግባቡ ተረድቶ ከለውጥ ባህሪ አኳያ የሚገራ ፤ ለዚህ እራሱን ያዘጋጀ ሃይል በባለመኖሩ ለውጡ የተለያየ ፍላጎት ባላቸው ሃይሎች ተጠልፎ ሀገራት እንደ ሀገር የጦርነት አውድማ ፤ የግጭት እና የሁከት ማእከል የሆኑበት እውነታ ተፈጥሯል ። በዚህም በለውጥ መነቃቃት ወደፊት ለመራመድ ተስፋ ያደረጉ የሀገራቱ ሕዝቦች ብዙ ዓመታትን ወደኋላ እንዲመለሱ ሆነዋል።
በብዙ ፍላጎቶች በተሞላችው አሁናዊቷ ዓለም ለውጥ እና የለውጥ ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ ከሆነ ውሎ አድሯል። የለውጥ ክሽፈቶች እየፈጠሩት ካለው ያልተገመተ ጥፋት እና ውድመት አኳያም፤ አሁናዊ የለውጥ ንቅናቄዎች ከሁሉም በላይ የለውጥ ሃይሉን ስክነት ፣ እውቀት እና ጥበብ በብዙ የሚጠይቁ ሆነዋል። ከለውጥ ዋዜማ እና ማግስት ያሉ ጩኸቶችን እና ሆይታዎችን ፤ ውዳሴ እና ዝማሪዎችን በአግባቡ ማየት እና ማስተናገድን የሚፈልጉ ሆነዋል ።
እንደሀገር የዛሬ ስድስት ዓመት አደባባዮቻችንን የሞላው የሕዝባችን የለውጥ መነቃቃት ፈተናዎችን ተሻግሮ በብዙ ስኬቶችን እና የለውጥ ተስፋዎች አሁን ላይ መድረስ የቻለው የለውጥ ሃይሉ ለውጡን በስከነ መንፈስ ፣ በእውቀት እና በጥበብ መምራት የሚያስችል ዝግጁነት መፍጠር በመቻሉ ነው ። ይህ ዝግጁነት ተፈጥሮ ባይሆን ኖሮ እንደ ሀገር በከሸፈ ለውጥ ውስጥ መገኘታችን አይቀሬ ነበር ።
በተለይም በለውጡ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ የተቃረኑ ፍላጎቶችን ይዘው የለውጡን አደባባይ በውዳሴ እና ዝማሪዎች የሞሉ ሃይሎች ጅማሯቸው የለውጡ ድምቀት ሆኖ ቢታይም ፣ በሂደት ግን የቱን ያህል ለውጡን እንደፈተኑት ፣ ሀገር እና ሕዝብንም ምን ያህል ያልተገባ ዋጋ እንዳስከፈሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው ። የለውጥ ሃይሉ ዝግጁነት ባይኖር በሀገር ላይ ይዞት የመጣው ውድቀት የቱን ያህል የከፋ እንደነበር ለግምት የሚከብድ አይሆንም ።
አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም