አስመረት ብስራት
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ ይባላሉ። የቀድሞው 102ኛ አየር ወለድ ክፍለ ጦር አባል ናቸው። በስልሳዎቹ መጀመሪያ እድሜ ክልል ላይ የሚገኙት እኚህ ሰው ውትድርና ደሜ ውስጥ ያለ ኢትዮጵያዊነት ደግሞ እስትንፋሴ ነው ይላሉ። ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ነው። ወላጅ አባታቸው የቀድሞው የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ጦር ሰራዊት አባል ነበሩ።
አባታቸውም በሰሜን ጦር ግንባር የተሰዉ ወታደር ናቸው። በደርግ ሥርዓት አባቶቻቸው በውትድርና የሞቱባቸው ታዳጊ ልጆችን የማሳደግና የመንከባከብ ሃላፊነትን የሀገሪቱ መንግስት ይወስድ ነበር።
ያኔ የኩባና የኢትዮጵያ መንግስት ወዳጅነት የጠበቀ ስለነበር ይህ መንግስት ልጆቹን ሊያስተምር ይወስዳቸዋል። ከነዛ ህፃናት መካከልም ሻለቃ ጌትነት
አንዱ ነበሩ። 1200 ህፃናት ወደ ኩባ ለትምህርት ከተላኩ በኋላ ትምህርታቸውን በንቃት መከታተል ጀመሩ። ትምህርቱም እየጠነከረ ህፃናቱም እየጎረመሱ ሲመጡ የውትድርና ትምህርት ፍላጎት ያላቸው ልጆች ወደ ስልጠናው ተቀላቅሎ መሰልጠን እንደሚችል ይነገራቸዋል።
የጀግና ልጅ ጀግና ለመባል የቆረጡት ሻለቃ በውትድርና ሳይንስ ትምህርታቸውን አጠናቀው ለመመረቅ ቻሉ። ገና በአፍላው እድሜ ውትድርናን የተቀላቀሉት እኚህ ሰው ውትድርናን “ሀ” ብለው ከጀመሩበት ጊዜ አንሰቶ ከሰራዊቱ እስከሚገለሉበት ጊዜ ድረስ በመቶ ሁለተኛ ክፍለ ጦር ውስጥ ከተራ ወታደርነት እስከ ብርጌድ አዛዥነት ድረስ በሃላፊነት ሲሰሩ ቆይተዋል።
ሻለቃ ጌትነት በቀደመው ሰራዊት ውስጥ የነበሩና ሌሎች የቀደሙ ታሪኮቻቸውን ያካፍሉን ዘንድ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንግዳ አድርገናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡– በቅድሚያ ለቃለ ምልልሱ ፍቃደኛ ስለሆኑ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ስም ላቅ ያለ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡– እኔም የህይወት ልምዴን እንዳካፍል ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን፡– እንደ መነሻ የኢትዮጵያ ሰራዊት የቀደመ ታሪክ በእርሶ አንደበት እንዴት ይገለፃል?
የቀድሞ ሰራዊት ታሪክ መለያው የኢትዮጵያዊነትን ስሜት ነው። የኢትዮጵያዊነት ማሳያ፤ የአንድ የመሆን ማመላከቻ ነው። ምንም አይነት የብሄር ልዩነት የማይታይበት ስለ አንደ ሀገር ብቻ የቆመ ሰራዊት ነበር። በኢትጵያዊነቱ ያመነ፤ ለባንዲራው ክብር የቆመ፤ ለሀገር ክብር የሚሞት ሰራዊት ነበር።
ውስጡ ደሙ የሚንተከተከው የሀገሩን ጥቃት ሲሰማ ነበር። በአንድ ቃል ብሄራዊ ጦር ሰራዊት ነው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– በተለይ እርሶ በሰራዊቱ ውስጥ በነበሩበት ወቅት የነበሩበት የ102ኛ ክፍለ ጦር የሰራዊት ቁመና ምን ይመስል ነበር?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡– እኔ የነበርኩበት የመቶ ሁለተኛ ክፍለ ጦር አውደ ውጊያው ለመመልከት ብንሞክር ከስልጠና ጀምሮ ሰራዊቱ ለዳር ድንበሩ የቆመ፤ ለሀገሩ ተቆርቋሪ የነበረ ነው። በሰሜን የነበረው አውደ ውጊያ ላይ የሚሰራቸው ተጋድሎዎች ሁሉ ሀገሩን በትክክለኛ አካሄድ ውስጥ ለመክተት ግንባሩን ለጦር የሰጠ ነው።
በተለይም አየር ወለድ ክፍለ ጦር ጦርነት የተፋፋመበት አካባቢ ገብቶ ድል ለመቀዳጀት የሚሰራ በመሆኑ በፓራሹት ከጠላት ጀርባ በመውረድ ድባቅ የሚመታ ስሙ ሲነሳ ጠላት የሚርበደበድበት አየር ሃይል ነው።
አዲስ ዘመን፡– በደርግ ጊዜ የነበረው የሀገሪቱ ሰራዊት ለሽንፈት የተዳረገው በብዙ ውስብሰብ ሴራዎች ነው ይባላል በእርሶ አንደበት ይሄን እንዴት ይገልፁታል?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡– ሰራዊቱ በራሱ ሙሉ ለሙሉ የአንድነት መንፈስ የነበረው፤ ሀገር ወዳድ ሰራዊት ነበር። ይህ ሰራዊትን ለማፍረክረክ ውስጡ የክፋት ሀሳብ ያላቸው ሰዎች በመሰግሰግ ነበር ሊረታ የቻለው እንጂ በምንም መስፈርት ይህ ሰራዊት ከጎኑ በተኛ ጓዱ ላይ አልተነሳም ነበር።
ተንኮል ያደጉበት መሆኑን እናንተም የዚህ ትውልድ አባላት ለመመልከት ችላችኋል። በተንኮልና በሸር የሚደርስባቸው ስላልነበረ በዛ ሴራ የተፍረከረከው ይህ ሰራዊት ጦርነቱ በሁለት በመክፈል፤ የሃያላን ሀገራት ጣልቃ ገብነትና ህዝቡ በደርግ መንግስት የአስተዳደር በደል በመማረሩ የተነሳ ድሉ የጠላት እንዲሆን አስቻለ እንጂ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት በቀላሉ የሚበገር አይነት አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡– ያ ለረጅም ዓመታት በበረሃ ለሀገሩ ሲዋደቅ የኖረ ትልቅ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሲበተን ምን ተሰማዎት?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- በጣም ነበር ያዘንኩንት። በወቅቱ የመስራት አቅም የነበረው በርካታ የወታደራዊ ታክቲክን የሚያወቅ ሰራዊት ሲበተን እጅግ በጣም ነበር ያዘነኩት። ሰራዊቱን ለማሰልጠን በርካታ የሀገር ሀብትና ንብረት ባክኗል።
ሀገር ተችግራ አሰልጥና ብቁ ያደረገችውን ሊያውም ሀገር ወዳድ የሆነውን ሰራዊት ሜዳ ላይ እንደ አልባሌ እቃ ሲጣል ከማዘን በስተቀር ምን አቅም ኖሮን መናገር አንችል ነበር?
በወቅቱ ከኩባ በአፍላ እድሜዬ ነበር ወታደራዊ ስልጠና በአግባቡ ወስጄ የመጣሁት። ገና ወጣት እያለሁ ነበር በአመራርነት ስሰራ የነበረው። ከጦር ሰራዊቱ ከተገለልኩ በኋላ ለዓመታት ውስጤ በከባድ ቁጭት እየተንገበገብኩ ነበር የኖርኩት። አሁን ግን እነዚህ ተገንጣይ አስገንጣዮች የእጃቸውን ስላገኙ በጣም ነው ደስ ያለኝ።
አሁንም ቀጣይና ተከተታይ ስራ የሚኖር ከሆነ ባለኝ አቅም ለማገልገል መንግስት እንዲጠራኝ እየተጠባበኩኝ እገኛለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በወጣትነትዎ ነበር ከሰራዊቱ የተገለሉትና ላለፉት 27 ዓመታት ምን እየሰሩ ነበር የኖሩት?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- ያለፉት ዓመታት የተለያዩ ተባራሪ ሰራዎችን ስሰራ ነው የኖርኩት። አሁን በአንድ የግል ባንክ ውስጥ የጥበቃ ስራ ነው የምሰራው። ሰው የሚያደርገው ሲያጣ የትናንት ማንነቱን በይደር አስቀምጦ የእለት ጉርሱን ለማግኘት ከመጣጣር ያለፈ ምን ማድረግ ይችላል።
ቀን ቀና ያረገኝ እለት ማእረጌንም ታሪኬንም አወራለሁ ብዬ ያለ ምንም ቅሬታ ያገኘሁትን ስራ በመስራት ክፉ ቀንን ለመሻገር ችያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ችግሩ ከፖለቲካ በላይ የአገር ጉዳይ ነው ብለው ብዛት ያላቸው ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ወደ ጦሩ ተመልሰዋል። ይህንን ውሳኔ እንዴት አገኙት?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- እኔ ጥሪ ሲደረግ አልተዋጠልኝም ነበር። ̋ሌባ ሲሰርቅ ይስማማል ሲካፈል ይጣላል” አይነት ነገር ሆኖ እነሱ የጥቅም ሽኩቻ በሚያደርጉበት ወቅት የጣሉትን ሰራዊት መጥራታቸው በጣም ነው የገረመኝ።
የኤርትራ መንግስት ብለው ሊወጉት የተነሱት እኮ ሻቢያና ወያኔ ብለው በግራና በቀኝ የኢትዮጵያን ጦር ሰራዊት ሲያጣደፉት የነበሩት እኮ ናቸው። እኔ በበኩሌ ጥሪ ቢደረግም ሄዶ የመዋጋት ተነሳሽነት አልነበረኝም።
ሌሎች የወሰኑትን ውሳኔው ትክክል ነው፤ ትክክል አይደለም ለማለት ግን ይከብደኛል። እንደየ ሰው አመለካከት ነው። ለኔ ሀገር ወራሪ የውጭ ሃይል ቢመጣ ያለ ምንም ማንገራገር ሊሄድ እችላለሁ። ለእንደዚህ አይነቱ ጥሪ ግን እንጃ …. ። ሰራዊት ማለት አገር ነው። አገርን የሚያገለግል። ወታደር ወደ ውትድርና በየዘመኑ የሚገባው የዘመኑን መሪ ለማገልገል ሳይሆን አገርን ለማገልገል ነው።
የኛ ሰራዊት ቁመና ሀገርን ያስቀደመ ስለነበር ውሳኔው አያስደንቅም። ትክክልም ነበር። ነገር ግን የጦርነቱ አስፈላጊነት ላይ ስላላመንኩ የሁለቱ ሌቦች ድግስ ማድመቂያ ላለመሆን ጥሪውን አልተቀበልኩም።
አዲስ ዘመን፡– ከለውጡ በፊት የነበረው የሰራዊቱ ሁኔታ ብሔራዊ ጦር የሚያስብለው ቁመና፤ የስልጠና ሥርዓቱ ለግዳጅ ውጤታማ የሚያደርገው ነበር?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- በደንብ ነበር። የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ብሄራዊ ጦር ነው። ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጵያዊነትን ተቀብሎ ለሀገሩ የሚሞት ነው። በትልቁ የቀድሞ ሰራዊት ስልጠና ዘሩን የሚጠራ አንድም ወታደር አልነበረም። ስለ ሀገሩ ስለ አንድነቱ ስለ ኢትዮጵያዊነቱ እየዘመረ የሚሰለጥን ሰራዊት ነበር። ይህ የስልጠናው አካል ነው።
ስልጠናው ነው ኢትዮጵያዊነቱን እየዘመረ እንዲዋጋ ያደረገው እንጂ ማንም ዘር ሳይኖረው ቀርቶ አይደለም።
ሁሉም የተወለደበትን አካባቢ ብሄር ሳይሆን የሚያስበው ኢትዮጵያዊነትን፤ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ነበር። ነፍሱም ስጋውም የሀገር ፍቅር ስሜት ላይ ነው የነበረው። ስለ ሀገር ኖሮ ስለ ሀገር መሞትን ብቻ የሚያስብ ሰራዊት ነበር።
በወታደር ቤት ̋ላብ ደምን ያድናል” የሚል አባባል አለ። ይህ ማለት በስልጠና የሚፈሰው ላብ፣ በስልጠና የሚገኘው ውጤት ደምን የማዳን፣ የህይወት ዋጋ ሳይከፈል ድል ሊያደርግ የሚችልበት አቅም የሚፈጥርበት ሁኔታ ስላለ ነው። ይህ ሰራዊት በፍፁም ስልጠና የታሸ፤ በእሳት ተፈትኖ እንደ ወርቅ የነጠረ ሰራዊት ሊሆነ በቅቷል።
ስልጠናውም ምልመላውም ፍፁም ሀገር ወዳድ ብሄራዊ ጦር ሰራዊት እንዲኖር እንዳደረገው ነው የሚታየው። ከነስሙም የኢትዮጵያ የጦር ሰራዊት ነው የሚባለው። የሀገርን ስም የተሸከመ ብሄራዊ ጦር ነበር።
አዲስ ዘመን፡– ከቀድሞ ሰራዊት አንጻር አሁን በሰራዊቱ ውስጥ የሚካሄደውን የሪፎርም ሥራ እንዴት አገኙት?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- ሰራዊቱ ሪፎረም መደረጉ የእውነት ሰራዊቱ መካከል የአንድነት ስሜት ከፈጠረ ሪፎርሙ ድንቅ ነው። ወታደር ሲቀጠር የእከሌ ዘር ተብሎ ሳይሆን ውትድርናን የሚፈልግ በውድድር ሰራዊቱ ውስጥ መግባት ነው ያለበት። ውትድርና ውስጥ የብሄር ተዋፅኦ እንደ አንድ መስፈርት መቀመጥ የለበትም።
ውትድርና ገንዘብ ከፍለህ የምታልፈው ነገር አይደለም፤ ክቡርን የሰው ልጅ ህይወት የሚያስከፍል ነው እንጂ። ይህን ክቡር የሰው ልጅ ህይወት የሚያስከፍል ስራ በፍላጎትና በፍቅር ብሎም በብቃት ተወዳድሮ ከፊት የሚሆኑበት እንጂ በሹመት የሚገባበት ባለመሆኑ ሪፎርሙ ኢትዮጵያዊነትን ማእከል ያደረገ ወታደር እንዲኖረን መስራት አለበት።
ጠንካራ ሀገር ወዳድ ሰራዊት ለመፍጠር ከስልጠናው ጀምሮ የሀገር ፍቅር ስሜት ለመገንባት ያስቻለ የስልጠና ስራ መሰራት ይኖርበታል። ሪፎርሙ በዚህ መልኩ ቢሆን መልካም ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ የአየር ወለድ ሰራዊት ምረቃ ላይ በእንግድነት ሲገኙ ምን ተሰማዎት?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡– በእለቱ በራሴ ምክንያት አልተገኘሁም። ጥሪው ግን ቀርቦልኝ ነበር። በእለቱ ግን በቴሌቪዥን ስመለከት እንባ ነው የተናነቀኝ። የጥንቱን ሰራዊት በአካል ያየሁ ነው የመሰለኝ። እኛም መታወሳችን የሚያስደስት ተግባር ሆኖ ነው ያገኘሁት። አንገታችንን ከደፋንበት ቀና የምንልበት ቀን ደርሶ በማየቴ ክብር ተሰምቶኛል። ላስታወሱንም ምስጋና ይድረሳቸው ብያለሁ።
አዲስ ዘመን፡– በአንድ አገር የመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የአየር ወለድ ሰራዊት ሚና እንዴት ይገለጻል?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- አየር ወለድ ማለት የስራ ክፍሉ በየትኛውም ቦታ ፈጥኖ የሚደርስ የሰራዊቱ ክፍል ነው። አየር ወለድ የእግረኛ ሰራዊት ደጋፊ ከጠላት ጀርባ ወርዶ ጠላት የሚመታ ነው።
ይህ ሰራዊት የተፋፋመ ጦርነት መካከል ገብቶ ድል የሚያጎናፅፍ ነው። እኛ የነበረንበት ክፍለ ጦር በጦር አውድማ ተሰልፎበት ያላሸነፈበት አውደ ውጊያ ኖሮ አያውቅም።
አየር ወለድ በቁጥር አነስተኛና ከባድ ስልጠናዎችን የወሰደ በመሆኑ ማንኛውም ግዳጅ ላይ የሚላክ አይደለም። እንደማንኛውም እግረኛ ሰራዊትም ሁሉም ቦታ መጠቀም የማይችሉት አይነት ነው።
አስፈላጊና ፈጣን ምላሽ በሚያስፈልግበት ቦታ ላይ ብቻ የሚላክ ሰራዊት ነው፤ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ፤ ቆራጥነት የሞላበት ግዳጅ ላይ የሚሳተፍ ጦርና ለአገር የሚዋደቅ ሰራዊት ነው።
በአጠቃላይ አየር ወለድ የአንድ የጦር ሰራዊት የጀርባ አጥነት ነው ማለት ነው። ያለ አየር ወለድ ጦር ሰራዊት ሙሉ መሆን አይችልም።
አዲስ ዘመን፡– የትግራይ ልዩ ሃይልና የሚሊሻ ጦር በሰሜን እዝ ላይ የፈጠረውን ትንኮሳ እንዴት አዩት?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፥ በእውነቱ ይህን የጭካኔ ተግባር ስሰማ በጣም ነው የተናደድኩት። ደሜ ነው የፈላው። ነገር ግን ይሄ ከነዚህ ሰዎች የሚጠበቅ ነው። እኔም እጠብቅ ነበር። የሚታወቁ ናቸው።
እዚህ የሚናገሩትና እዛ የሚያደርጉት የተለያየ ነው። የማዘናጋት ባህሪ አላቸው። ጦርነቱ እንደ ተጀመረ አካባቢ እንኳን እንደራደር እያሉ ከህግ የማስከበር ስራ መንግሰትን በማዘናጋት ጊዜና ጉልበት የመግዛት እስትራቴጂ ሊጠቀሙ ሞክረው ነበር። ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ ውስጥ ለውስጥ ተንኮል ሲሰሩ የቆዩ ናቸው። ለዚህ ነው ይሄን ስራ የሰሩት።
የቀደመ ባህሪያቸው የሀገርን ታሪክ ለማጥፋት በዘር በጎሳ በሃይማኖት እየከፋፈሉ የነበሩ ናቸው። የእነሱ የስልጣን እድሜ ከተራዘመ የማንም ህይወት ቢጠፋ ግድ የሌላቸው መሆኑንም በተከታታይነት እያሳዩን ይገኛሉ።
በጣም ከሞራል በታች የወደቁ ሰብአዊነታቸውን ያጡ መሆናቸው በዚህ ህግ የማስከበር ስራ ውስጥ ተመልክተናል። ተግባራቸውንም ነውረኛና ፀያፍ ብለነዋል።
አዲስ ዘመን፡– በሰራዊቱ ላይ የተፈጸመውን ኢ ሰብአዊ ተግባር ከምን የመነጨ ነው ብለው ያስባሉ?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፥ ይህ የከሰረ ፖለቲካ የፈጠረው የበቀል ስሜት ነው። ለአንድ ክፍለ ዘመን ሀገራችንን ለመቦጥቦጥ፤ የማይሞላ ሆዳቸውን ለመሙላት ከመፈለግ የመነጨ ነው።
ስግብግብነት ከልክ በላይ አይናቸውን እንዳሳወራቸውኮ ለማየት ሌላ ምሳሌ አያስፈልግም። የወለዳቸው ህብረተሰብን እንኳን አንድ ቀን ዞር ብሎ ሊያዩት አልፈለጉም። የነሱ ራስን መውደድ ሰው መሆን የሚለውን ማንነት አጥፍቶታል።
ለዚህም ማሳያ ገና ወደ ጫካ ሲገቡ የትግራይ ህዝብ አልቀበል ሲላቸው እኮ ነው የሀውዜን ህዝብ ገበያ ላይ ባለበት ምንም የማያውቀውን ንፁህ ህዝብ በመፍጀት የግዱን ወደ ጦርነት እንዲገባ ያደረጉት።
ከጫካም በኋላ ለስልጣናቸው ያልተመቻቸውን ከበረሃ ጀምሮ አብሯቸው የታገለን ወታደር ሲገሉና ሲያስገድሉ የኖሩ ናቸው። ይህ ስግብግብ ጁንታ ለስልጣኑ መቆየት የሚጠቅመው ከመሰለው ህፃን ልጁንም ከመሰዋት የማይቆጠብ፣ ሰብአዊነት የሌለው ቡድን ነው።
አዲስ ዘመን፡– በመከላከያው ላይ ክህደት የፈጸሙ የሰራዊት አባላት ከወታደራዊ ዲስፕሊን አንጻር እንዴት ይታያል፤ የችግሩስ መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው ብለው ያስባሉ?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- ይህ ተግባር የሚነጨው ከጎጠኝነት አስተሳሰብ ነው። በኛ ጊዜ ቋንቋ፤ ብሄር፤ ጎሳ የማይታወቅበት ጊዜ ነበር። አንድ ወታደር በምንም ምክንያት አብሮ የኖረውን ጓድ ይገላል የሚል አስተሳሰብ በማንም ሀገር ታይቶ የማይታወቅ ከወታደራዊ ዲሲፒሊን አንፃርም የማይታሰብ ነው።
አብሮ የተኛን እንቅልፍ ላይ የነበረን ሰራዊት ከጎኑ በሰላም እደር ብሎት የተኛው ወንድሙ ይሄንን ተግባር ይፈጽምብኛል ብሎ ማሰብ የማይቻል ነው። ይህም ታላቅ የውትድርና ወንጀል ነው።
አዲስ ዘመን፡– በአገር ላይ የመከላከያ ሃይልና በትግራይ የሚገኙ ታጣቂዎች መካከል ያለው የሃይል አሰላለፍ እንዴት ነው?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- ወታደር ብዙ ቁመና አለው። እነሱ ሚኒሻ ናቸው። ወታደር የሚባለው ሎጀስቲክ ያለው ከጀርባው የሚደግፈው፤ ምግብ ውሃ ትራንስፖርት አልባሳት የሚያቀርብለት አካል ያለው ነው።
በምንም የሃይል ሚዛን የትግራይ ሚኒሻና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ሊወዳደሩ የሚችሉበት ቁመና አይኖራቸወም።
የህዝብ ድጋፍ ያለው ሎጀስቲክ የሚቀርብለትና በጥቂት ግለሰቦች የሚዘወር ሃይል በምንም ሚዛን እንደማይወዳደር በሰላም ማስከበሩ ስራ ላይ እየተመለከትነው ነው። የሀገራችን የመከላከያ ሰራዊት በየጉደጓዱ ሲያሯሩጣቸው ተመልክተናል። ለጥቂት ጊዜ ቢፍጨረጨርም ግን ምን ማድረግ አይችልም።
ይልቅስ የፈሪ ዱላ አይነት ተግባር ትንንሽ አደጋዎች ህዝቡ መካከል እንዳይፈጥር መንግስት ህግ የማስከበሩን ስራ በአጠቃላይ በሀገሪቱ አጠቃሎ መቀጠል ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡- እንዲህ አይነት ችግሮች ሲያጋጥሙ እንዴት ሊፈቱ ይገባል ይላሉ፤ በቀጣይስ እንዳያጋጥሙ ምን መደረግ አለበት ብለው ይመክራሉ?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- ይህ ችግር በቀጣይነት እንዳይቀጥል የኢትዮጵያዊነት ስሜት ህዝቡ ውስጥ መስረፅ አለበት። ከታች ጀምሮ የሀገር ፍቅር ስሜት ህዝቡም ውስጥ ሆነ ሰራዊቱ ውስጥ መስርፅ አለበት። ሀገር ለማስተዳደር የተቀመጠው አካልም የእውነት የኢትዮጵያ ፍቅር ያለው ሀገሩን ወዶ ህዝብን ማስተዳደር አለበት።
የሀገር ፍቅር ስሜት ከላይ እስከታች በህብረተሰቡ ውስጥ በማስረፅ ለድህነት እጅ የማይሰጥ የውጭ ወራሪም ቢመጣ የሚመክት ህዝብ፣ መንግስትና የሀገር መከላከያ ሰራዊት መፈጠር ይኖርበታል።
አዲስ ዘመን፡– በሰራዊት ውስጥ በነበሩበት ወቅት ፈታኝ ነበር ብለው የሚያስታውሱት ግዳጅ ነበር፤ እንዴትስ ተወጡት ?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- በኤርትራ ውስጥ ብዙ አውደ ውጊያ ላይ ተሳተፌያለሁ። በጣም ከባድና ፈታኝ የሆኑ ግዳጆችንም በድል ተወጥቻለሁ።
ወደ ጦርነቱ ማብቂያ አካባቢ ነበር ናሚዶ የሚባል ቦታን ለማስለቀቅ በምፅዋ በኩል በጀርባ ጠላትን ለማጥቃት ገብተን እያለ ከጀርባችን ተከትሎ መምጣት የነበረበት ጦር ሰራዊት ቀረ። ከበስተኋላችን ይከተለን የነበረውን ሰራዊት እየጠበቀን ቀለብ አለቀ። ሰራዊቱ ተዳከመ። ያን ጊዜ የጠላት ጦር ገጠመንና በርካታ የሰራዊቱ አባላትን የሰዋንበት ቦታ መሆኑ እጅግ በጣም ከባድ እንደ ነበረ አስታውሳለሁ።
የአየር ወለድ በባህሪው ከባባድ ውጊያዎች ስለሚመራ የተሰለፈበት ሜዳ ሁሉ ፈታኝና አስቸጋሪ ጊዜዎችን አሳልፈናል በርካታ ወታደሮችንም ሰውተናል።
አዲስ ዘመን፡- ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚሉት ነገር ካለ እድል ልስጦት?
ሻለቃ ጌትነት ማስረሻ፡- መከላከያ ሰራዊታችን የተቀዳጀው ድል በጣም የሚያኮራ ነው። ነገር ግን አሁንም ቀሪ ስራዎች አሉ። በትግራይ እንዳየናቸው አይነት አፈንጋጭ ቡድኖች በሌሎቹም የሀገራችን ክልሎች እንዳይፈጠሩ ይሄንን ልዩ ሃይል የተባለውን መዋቅር መገምገም ግድ ይላል። በአንድ ሀገር የሀገር መከላከያ ሰራዊት መጠናከር ነው ያለበት።
ይሄ በየክልሉ የሚሰለጥነው የክልሉ ሚኒሻ ወይም የክልል ፖሊስ የሚባል ስም ነው ሊሰጠው የሚገባው። የየክልሉን ሰላምና ፀጥታ የሚያስከብር ግን ከመከላከያ ሰራዊት በታች የሆነ ሃይል ነው ሊሆን የሚገባው።
ሌላው ደግሞ የሰላም ማስከበር ተግባር የተከናወነበት አካባቢ ያለው የትግራይ ብሄር ተወላጅ ያለጭንቀት እንዲኖር በርካታ ስራዎች መሰራት ይኖርባቸዋል።
ህዝብ ከህዝብ ቂም እንዳይኖረው ውስጡ የፀዳ ስራ መሰራት ይኖርበታል። አዲሱ ትውልድም ሙሉ ለሙሉ የአንድነት መንፈስ ይዞ ሀገርን ለማሳደግ ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ መስራት ይኖርበታል።
አዲሱ ትውልድ ዘመናዊ አስተሳሰብና አመለካከትን በመያዝ ሀገራችን ያላትን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት አውጥቶ ኢትዮጵያ ካደጉት ሀገራት ተርታ የምትሰለፍበትን ስራ መስራት ይኖርበታል የሚል መልእክት አስተላልፋለሁ።
አዲስ ዘመን፡– አመሰግናለሁ፤
ሻለቃ ጌትነት፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 26 2013