ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ ወደ ስልጣን የመጡበት ወቅት እንደ አገር በሁሉም ረገድ እጅግ ፈታኝ የሆኑ ጉዳዮች ችግር ውስጥ ሊከቱን በቋፍ ላይ በነበሩበት ወቅት ነው። ወቅቱ መንግስት ውስጣዊ መረጋጋትን ማስፈን ተስኖት ሁለት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የተገደደበት፣ እዚህም እዚያም ግጭቶችና ትርምሶች የሚፈሉበት፣ በማንኛውም ቅፅበት አዲስ አበባ በሁከት ልትናጥ እንደምትችል የምታስፈራበት፣ ተረጋግቶ መስራትና መኖር አዳጋች የሆነበት፣ ኢኮኖሚው ተንገጫግጮ የነበረውን ፍጥነት ለማስቀጠል የተቸገረበት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ጫፍ የደረሰበት፣ ኢህአዴግና መንግስት በየጊዜው መግለጫ ቢያወጡም ተሰሚነታቸው እጅጉኑ የቀነሰበት ነበር።
በዚህ ውጥረት ውስጥ ተገብቶ ነው የኢህአዴግ ምክር ቤት ከመጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄደው ስብሰባ መጋቢት 19 ቀን 2010 ዓ/ም ዶክተር አብይ አህመድን የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሊቀመንበር አድርጎ የመረጣቸው።-
መጋቢት 24/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቀርበው አገር የመምራት ስልጣን ሲረከቡ «ኢትዮጵያ ማህጸነ ለምለም ናት። ከፍ ባለ የአገር ፍቅር መንፈስ ሰርክ የሚተጉ ልጆችን አፍርታለች። ልጆቿም ወደቀድሞ ክብሯ እንድትመለስ፣ የሕዝቧ ሰላምና ፍትህ እንዲጠበቅ፣ ብልጽግና ያለ አድልኦ ለመላው ዜጎች ይደርስ ዘንድ አጥብቀው ይመኛሉ፤ ይደክማሉ» በማለት የኢትዮጵያን ዝናና ክብር ከፍ የሚያደርጉ፣ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ፣ ፍቅርና ስምምነትን የሚሰብኩ ሀገር ወዳዱ ኢትዮጵያዊ መስማት የናፈቀውን አባባል ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ንግግር ባልተሰማበት ፓርላማ ውስጥ ያቀረቡት።
«አባቶቻችን በመተማ፣ በማይጨውና በካራማራ አጥንታቸውን ከስክሰው የከበረ ደማቸውን አፍስሰው በክብርና በአንድነት ያቆይዋት አገር አለችን። እኛ እድለኞች ነን። ውብ አገር አኩሪ ታሪክ አለን። እኛ መነሻችንን እናውቃለን። በርካታ ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው ታላቅ ህዝብ ነን » ሲሉ የኢትዮጵያን የረዥም ጊዜ አኩሪ ታሪክ አስታውሰዋል፤ በአገራችን ውስጥ ያለውን በጎ የማኅበረሰብ ትስስር ምሳሌዎችን በማንሳትም አወድሰዋል።
«ኢትዮጵያ የሁላችን ሀገር፤ የሁላችን ቤት ናት!” በማለትም ቀደም ሲል ኢትዮጵያውያን የናፈቁትን የዴሞክራሲ መብት እንደሚከበርና ፍትሃዊነት እንደሚሰፍን ፍንጭ ሰጥተዋል። ከዚህም በላይ የሀሳብ ልዩነቶች መኖር ለቁልፍ ችግሮቻችን የተሻሉ የመትፍሄ ሀሳቦች መገኘት መሠረት ሊሆኑ እንደሚችሉና ይህም እውን የሚሆነው በመደመር ፍልስፍና መሆኑን በመግለጽ « በመተባበር ውስጥ ኃይል አለ። ስንደመር እንጠነክራለን» የሚል አዎንታዊ ኃይለ ቃል ተናግረዋል። ዲሞክራሲን በሚመለከትም «እኛ ኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲና ነጻነት ያስፈልገናል፣ ይገባናልም !” ብለዋል።
እነዚህን ተስፋ ሰጪ ንግግሮች ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት መስማት አጅግ በጣም የሚያበረታታ ነበር። መልዕክቶቹ በንግግር ብቻ እንደሰማናቸው ሳይቀሩ በቶሎ በተግባርም መተርጎም ችለው ለማየት በቅተናል። ያለፉት 300 ቀናትም ቃል ተግባር እንደሆነ አፍ አውጥተው የሚናገሩ ህያው ምስክሮች ናቸው።
ዶ/ር አቢይ ባለፉት ያለመረጋጋት ዓመታት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ሲታገሉ በፀጥታ ኃይሎች ሕይወታቸው ለተቀጠፉ፣ አካላቸው ለጎደለና ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን ገልፀዋል፤ለጠፋው ጥፋትም ይቅርታም ጠይቀዋል። ለወደፊቱም ተመሳሳይ የመብት ጥሰት እንዳይፈፀም ስለእርቅ ተናግረዋል፤ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አድርገዋል፡፡ በህገመንግሥቱ ውስጥ ተጽፈው የሚገኙ መብቶች ሁሉ መከበር እንደሚኖርባቸውም አጽንኦት ሰጥተው የሚመሩት መንግስት ተግባራዊ ለማድረግ ቀንና ሌሊት እንደሚተጋ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነትን ተረክበው አገር መምራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በአገራዊ፣ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ተግባራትን አከናውነዋል። በአገር ውስጥ በሶማሌ፣ በደቡብ፣ በአማራ፣ በትግራይ፣ በጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር የውይይት መድረክ ፈጥረው ህዝብን አዳምጠዋል። በውይይታቸውም ህብረተሰቡ በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ዘርፎች ላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት መንግስት ህብረተሰቡ ለሚያነሳው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በትጋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎረቤት አገሮች ያደረጉት የስራ ጉብኝት ኢትዮጵያ ለክፍለ አህጉሩ ሰላምና የኢኮኖሚ ትስስር መጠናከር ሚናዋን ለማሳየት ታሳቢ ያደረገና መተባበርን የሚያጎላ ተግባራትን አከናውነዋል። በጂቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ኬንያ እንዲሁም አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ቻይና፣ኡጋንዳ ወዘተ… ያደረጉት ጉብኝት ውጤታማና የአገሮቹን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ከፍ ያደረገ መሆኑ ይጠቀሳል።
ከአገሮቹ ጋር በተደረጉ ውይይቶች በወደብ አጠቃቀም፣ በዜጎች ደህንነት፣ በመሰረተ ልማት ትስስርና በአፍሪካ ቀንድ የሰላም ሁኔታ ላይ በመወያየት በርካታ ስምምነቶችን ፈፅመዋል። በኢኮኖሚና በመልካም ትብብር የአገሮቹን የመንግሥታትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስሩን የበለጠ ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ጠቃሚ ምክክር ለማድረግም ችለዋል። የኬንያ መንግስት ኢትዮጵያ በላሙ ወደብ መሬት የምታገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የገባው ቃል በዋናነት ተጠቃሽ ነው።
በአገሮቹ የሚኖሩ ዜጎች ደህንነታቸውና ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ያደረጉት ስምምነትና የተወሰዱ እርምጃዎችም የጉብኝቱ ውጤት ስለነበሩ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን እስረኞችን የማስፈታት ተግባር አከናውነዋል። በዚህም ከሱዳን፣ ከግብጽ፣ ከኬንያና ሳዑዲ አረቢያ ታስረው የነበሩ ዜጎች ተፈትተው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ሲያደርጉ በግብጽ በእስር ላይ ይገኙ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን አስፈትተው ይዘው በመመለስ ለዜጎች ያላቸውን የላቀ ክብርም አሳይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ለአገሪቱ መንግስት ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት እስረኞችን ለመፍታት ስምምነት ላይ መደረሱም ይታወሳል። ከዚህም በላቀ የቀጥታ በጀት ድጋፍን ጨምሮ ታላላቅ የኢንቨስትመንት ስምምነቶችን በማድረግ ሀገራዊ ተጠቃሚነታችንን የሚያጎሉ ተግባራትን ፈጽመዋል።
በግብፅ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲ ጋር ተወያይተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ታላቁን የህዳሴ ግድብ የምትገነባው ግብጽንና ሌሎች የተፋሰሱ ሀገራትን በማይጎዳ መልኩ እንደሆነና እንዲያውም ይበልጥ ተጠቃሚ በሚያደርጋቸው ሁኔታ መሆኑን አስረድተው በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት በመተማማን ላይ ተመስርቶ የሚቀጥልበትን ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል። በሊቢያ በስደት እያሉ በአሸባሪዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያንን አጽም ከተቀበረበት በማውጣት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የመጨረሻ እረፍት እንዲያገኝ ለማድረግ ስምምነት ላይ መደረሱም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲፕሎማሲ ስኬት አንዱ ነበር።
በሳዑዲ አረቢያ በህክምና ስህተት የአልጋ ቁራኛ ሆኖ ለዓመታት የቆየው ኢትዮጵያዊው ታዳጊ መሀመድ አብዱላዚዝን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሳዑዲ አረቢያ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ለሳዑዲ መንግስት ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የ21 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ካሳ እንዲከፈለውና ወደ አገሩ መጥቶ የህክምና ክትትል እንዲያደርግ መደረጉም ይታወቃል።
ከኤርትራ ጋር በተካሄደው ጦርነት ተቋርጦ የነበረው የሃያ ዓመታት ግንኙነት እንዲያበቃ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወሰዱት ቁርጠኝነት የአገራቱ መሪዎች እንዲገናኙ ቅድሚያውን በመውሰድና የሰላም ጥሪ በማስተላለፍ እንዲሁም ወደኤርትራ በማምራት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጋር በመገናኘት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር፣ መልካምና ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር አድርገዋል፡፡ በዚህም ታላቅ ዓለምአቀፋዊ ዕውቅናና አድናቆትን ለማጎናጸፍ ተችሏል። ከኤርትራ ጋር የተደረገው ስምምነትን መሰረት በማድረግም የምስራቅ አፍሪካ አገራት ወደ ትብብር እንዲመጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ጥረትም ጅምር ፍሬ በማፍራት ላይ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ፣ በጀርመን ወዘተ…ያከናወኗቸው ተግባራት አገሪቱ በለውጡ ያስመዘገበችውን ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች ተቀባይነት እንዲያገኙ ያደረገና በርካታ ድጋፎችን ያስገኘ ውጤታማ ተግባር ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ አሸንፎ የለውጥ ኃይሎች ወደ ስልጣን ካመጡ ጀምሮ በርካታ ችግሮች ቢስተዋሉም ሙሉ በሙሉ አሊያም በአብዛኛው ተቀርፈዋል። በዚህም አገሪቱ በታሪኳ ለመደመሪያ ጊዜ እስረኞች በብዛት የተፈቱበትና ማዕከላዊ እስር ቤት በይፋ የተዘጋባት እንድትሆን አስችሏል ።
ተዘግተው የነበሩ ድረ ገፆች ተከፍተው በነፃነት እንዲነበቡ፣ ዜጎች የፈለጉትን ሃሳብ በሰላማዊ ሰልፍና በጽሁፍ እንዲገልጹ፣ የህዝብ መገናኛ ብዙኃን የህዝብ ልሳን እንዲሆኑ፣ የመከላከያ ሰራዊቱና የመንግስት ተቋማት የአንድ ብሄር መገልገያ ከመሆን ፀድተው የብሄር ተዋፅኦው እንዲመጣጠን፣ የህዝብና የአገር አገልጋይ እንዲሆኑ ተደርጓል ።
የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል። ከእነዚህም መካከል በዋነኝነት የፖለቲካ አመራር እስረኞችን ከመፍታት ባሻገር በሽብርተኝነት ተፈርጀው የነበሩ የአገር ውስጥ ድርጅቶችን ከሽብርተኛነት መሰረዝ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን «ተፎካካሪ» እያሉ መጥራትና አብረው እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረብ (በቤተመንግስት ተገናኝቶ መወያየት)፣ እንዲታፈኑ በርካታ ገንዘብ ይፈስባቸው የነበሩ ሚዲያዎችን ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረብ፣ ታግተው የነበሩ በርካታ ድረገፆችንና ጦማሮችን ነጻ መልቀቅ፣ …. ይጠቀሳሉ። እነዚህ ውሳኔዎች ለውጡ የምር መሆኑን በማሳየት መንግስትን በመቃወም ለበርካታ ዘመናት በውጭ አገራት የኖሩ ግለሰቦችና ድርጅቶችም ሳይቀር ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከለውጡ ጎን እንዲቆሙ አድርጓቸዋል። የይቅርታ ምህረት አሰጣጥ ሂደቱ ወጥ እንዲሆን የምህረት አዋጅ ረቂቅ ተዘጋጅቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ጸድቋል። በዚህም ከ17 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል።
በዚሁ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሦስት መቶ የሥራ ቀናት የካቢኔ አባላት ሹመት የተከናወነበት፣ በውጭ የሚገኙ ዜጎች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሃገር እንደፈለጉ እንዲገቡና እንዲወጡ፣ ለዘመናት የታፈኑ የዲያስፖራ ድምጾች እንዲደመጡ፣ ታላቅ የመንግስት ኩባንያዎች በከፊል ወደ ግል እንዲዘዋወሩ፣ የፍትህ ስርዓቱ ላይ ማስተካከያ በማድረግ ፍርድ ቤቶችን በአዲስ መልክ የማዋቀርና የአገርንና የሕዝብን ሀብት የዘረፉ ሌቦችና ወንጀል የሰሩ ባለ ስልጣናትን ወደ ፍትህ የማምጣቱ ስራ በከፊል የተጀመረበት፣ እንደ አብዲ ኢሌ አይነት ፀረ ህዝብ አመራሮች ከስልጣን ወርደው ወደ ህግ እንዲቀርቡ፣ የማህበረሰቡ ግማሽ አካል የሆኑት ሴቶች በሚኒስትር ደረጃ ሹመት ያገኙበት፣ የምርጫ ሂደቱን ለሁሉም ተፎካካሪ ኃይሎች ምቹ ለማድረግ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን በአዲስ የመሾም ሥራ የተከናወነበት ተግባር ተፈፅሟል፡፡ ይሁንና አሁንም ቦግ ድርግም የሚለው ግጭትና የጸጥታ መደፍረስ፣ የዜጎች መፈናቀል፣ የወጪ ንግድ ማሽቆልቆል፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የሥራ አጥነት ቸግር ወዘተ… የጠቅላይ ሚኒስትሩና የአገር ፈተና ሆነው የቀጠሉበት ሁኔታ መኖሩ ቀጣዩ ጊዜ የበለጠ ውጤት ለማምጣት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት አገርና ህዝብ ወገባቸውን አሰር አድርገው ሊሰሩ ግድ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።
ጥር 24/2011
አያሌው ንጉሴ