የግብርና ሥራ እረፍት የለውም። አርሶ አደሩ ከአንዱ የእርሻ ወቅት ወደሌላኛው ይሸጋገራል እንጂ አያርፍም። የ2012 /13 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት አዝመራ በአብዛኛው ማለት በሚያስችል መልኩ ተስብስቧል። ይህም የመኸር እርሻ እንቅስቃሴ መጠናቀቁን ያመለክታል፤ ማነህ ባለሳምንት እንዲሉ የመስኖ እርሻ ተራውን እየተረከበ ነው።
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ሀገሪቱ ከ2012/13 የምርት ዘመን በአጠቃላይ 460 ሚሊየን ኩንታል እህል ለማምረት አቅዳ ስትሠራ ቆይታለች። ከዚህ ብቻም ከ363 ሚሊየን ኩንታል በላይ እንደምታመርት ይጠበቃል። ቀሪውን ደግሞ ከመስኖ እርሻ በተለይም ስንዴ በመስኖ በማልማት ለማግኘት ተቅዶ እየተሠራ ይገኛል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሀገራችን በመስኖ እርሻ የሚለሙት አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲሁም በቆሎን የመሳሰሉ ሰብሎች ብቻ ነበሩ። ይህ ሁኔታ ካለፈው ዓመት አንስቶ መቀየር ጀምሯል። አንደ ሀገር በተያዘ አቅጣጫ መሰረት ሀገሪቱን ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወጪ እየዳረጋት የሚገኘውን ከውጭ የሚገባ ሰንዴ ለማስቀረት ስንዴን በመስኖ ማልማት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበትና አቅጣጫም ተቀምጦ እየተሠራ ነው።
ሀገሪቱ የስንዴ መስኖ ልማትን አሀዱ ብላ በጀመረችበት ባለፈው ዓመት 54 ሚሊየን ኩንታል ስንዴ ማምረት ተችሏል። በዚህም መንግሥት ስንዴን በመስኖ ለማልማት የያዘውን አቅጣጫ ትክክለኛነት የሚያመለክት ውጤት አይተናል፤ 54 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በማግኘትም እሸቱን መቋደስ ችለናል።
በመጀመሪያ ዓመት ብቻ ይህን ያህል ለውጥ ማስመዝገብ ትልቅ ስኬት ነው። ስኬቱ በተገኘው የምርት መጠን ላይ ብቻ አይወሰንም፤ ለቀጣይ ልማት የተገኘው ተሞክሮም ሌላው የአቅጣጫውን አዋጭነት ያመለከተ ተግባር ነው።
ዘንድሮም ከስንዴ የመስኖ እርሻ 60 ሚሊየን ኩንታል ይመረታል ተብሎ ተገምቷል። ዘንድሮ የመስኖ እርሻው በሁለት መቶ ሺ ሄክታር መሬት የሚካሄድ ይሆናል። የስንዴ ምርታማነትን በማሻሻል ከዚህ ቀደም ከተገኘው 10 ሚሊየን ኩንታል ተጨማሪ ለማግኘትም እየተሠራ ነው። እቅዱን ማሳካት ከተቻለ ሀገሪቱ ከውጭ ከምታስገባው ስንዴ 50 በመቶውን በሀገር ውስ ጥ ማምረት እንደሚቻል የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ይጠቁማል።
የተያዘው እቅድ በሀገር ውስጥ የሚመረተው ስንዴ እንዲጨምር እንዲሁም ሀገሪቱ ከውጭ የምታስመጣውን የስንዴ መጠን እንዲቀንስ ያስችላል፤ ለስንዴ ግዥ ከሚውለው የውጭ ምንዛሬ 350 ሚሊየን ዶላሩ ሀገር ውስጥ እንዲቀር እንደሚያስችል መረጃው ይጠቁማል።
የዘንድሮው የመስኖ እርሻ ባለፈው ዓመት የመስኖ እርሻ ተሞክሮ ላይ ጭምር ተመስርቶ የሚካሄድ አንደመሆኑ ስኬታማ እንደሚሆን ይታመናል። ለዚህም የምርጥ ዘር እና ማዳበሪያ አቅርቦትና የግብርና ባለሙያዎች የቅርብ ድጋፍና ክትትል አተኩሮ መሥራት ይኖርባቸዋል። የመስኖ ልማቱ በስፋት የሚካሄደው በቆላማ አካባቢዎች እንደመሆኑ በዚህ አካባቢ ሊከሰት የሚችለውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ሰፊ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።
ሀገሪቱ በመስኖ ሊለማ የሚችል በቂ ለም መሬት ፣ወንዞች እና የአየር ንብረት እያላት ለዳቦ የሚሆን ስንዴ ሀገሪቱ ለበርካታ ልማታዊ ተግባሮች የሚያስፈልጋትን የውጭ ምንዛሬ በማውጣት ስታስገባ ኖራለች። በተለያዩ ምክንያቶች ከውጭ የሚገባው ሰንዴ ሲዘገይ በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የዳቦ ስንዴ እጥረት ሲከሰት ኖሯል። መንግሥት ታሪክ እንዲቀየር አቅጣጫ አስቀምጦ ዝግጅት ተደርጎ ነው ስንዴ በመስኖ ወደ ማልማት የተገባው።
እንደሚታወቀው ፤የግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እየጨመረ ቢሆንም፣የሚፈለገው ደረጃ ላይ ገና አልደረሰም። በሀገሪቱ የእህል ዋጋ አለመረጋጋት እንድም የሚያመለክተው በቂ የግብርና ምርት አለመመረቱን ነው። እነዚህ ሁሉ በግብርናው ዘርፍ ላይ በስፋት መሥራት እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባሉ።
አሁን ወደ መስኖ እርሻ ተገብቶ የተገኘው ውጤትና በቀጣይም ያለው ተስፋ ምርትና ምርታማነቱን ማሳደግ እንዲሁም በእህል ዋጋ ላይ የሚታየውን ጭማሪ ማረጋጋት እንደሚቻልም ያመለክታሉ። በመስኖ እርሻው የተገኘው ስኬት በዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ የቆየውን ግብርናችንን በመስኖ እርሻ መደገፍ ብሎም መለወጥ እንደምንችል ያመላከተ ጥሩ መንደርደሪያ ነው።
የዘንድሮው ስንዴ በመስኖ የማልማት እቅድ እቅዱን ለማሳካት ብቻ የሚከናወን መሆን የለበትም፤ አንደ ሀገር በስንዴ የመስኖ ልማት ለመድረስ የታሰበውን ግብ ለማሳካት የሚረዳ ሌላ ተሞክሮ የሚቀሰምበት ይሆናል። ለዚህ ሥራም ከእስከ አሁኑም በላቀ መልኩ ግብርናውን በምርምር፣ በባለሙያ፣በግብአትና በባለድርሻ አካላት በመደገፍ ወደ ተፈለገበት ደረጃ ማድረስ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2013