ግርማ መንግሥቴ
ልጆች ባጠቃላይ “ልጆች” ይባሉ እንጂ እንደማንኛውም ሰው ይለያያሉ። ይህ ልዩነታቸው ደግሞ መገለጫው ብዙ ነው።
እየተነጋገርን ያለነው ከትምህርትና እውቀት ጋር በተያያዘ ስለሆነ ሌሎች ሰዋዊ ልዩነቶችን አይመለከትም። እንደውም ጽሑፋችን በጥቅል የሚመለከት በመሆኑ ከሌሎች ለየት ይላል። ወላጆችም ከዚሁ ከአጠቃላይ ሁኔታ በመነሳት ወደ እራሳቸው በማምጣትና ልጆቻቸውን ለይተው በማወቅ፤ ፍላጎታቸውን በመረዳት፤ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ በማድረግ ልጆቻቸውን እፈለጉበት ደረጃ ማድረስ ይችላሉ።
ልጆችም አስፈላጊውን የቤተሰብ፣ ትምህርት ቤት ማህበረሰብና መምህራን፣ የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ ድጋፍ ካገኙና ያላቸውን ተሰጥኦ በማውጣት ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ የሚፈልጉት የህይወት እርከን ላይ መድረስ ይችላሉ።
ለመግቢያ ያህል ይህን ካልን ወደ ተነሳንበት እንሂድና ልዩ ተሰጥኦ ስላላቸው ልጆች አንዳንድ ምልክቶችን በመፈንጠቅ ለወላጆች ማሳሰቢያ ቢጤ እናቅርብ።
ለመሆኑ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ልጆች በምን በምን ጉዳዮች ተለይተው ይታወቃሉ? ምንስ የተለየ ባህሪይና እንቅስቃሴ ይታይባቸዋል? እና የመሳሰሉት መሰረታዊ ጉዳዮች የሁልጊዜ የመስኩ ተመራማሪዎች የጥናትና ምርምር ርእሰ ጉዳዮች ናቸው። ለዛሬ የጋራ ግንዛቤ የተያዘባቸውን ይዘን ቀርበናል።
በጠቀስነው ተቋም እንደተረጋገጠው ተሰጥኦ ወጥ አይደለም። ከልጅ ልጅ ይለያያል። የአንዱ ተሰጥኦ ለአንደኛው ፍፁም የተጠላ ሊሆን ይችላል። አንደኛው ልጅ ላይ የሚታየው ብቃት በሌላኛው ላይ ላይታይ ይችላል። በመሆኑም ተሰጥኦ በግለሰብ ዝንባሌ፣ ፍላጎትና ብቃት ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ነው።
ይህ በወላጆች ዘንድ በሚገባ መታወቅ አለበት። አንዱ በሂሳብ 100 ካመጣ ሌላኛውም 100 ማምጣት አለበት የሚባል ማጠቃለያ የለም። ይህ የግድ መሆን አለበት ካልን ደግሞ ያኛው በኬሚስትሪ 100 አምጥቷልና ይሄኛውም 100ዋን ቁጭ ሊያደርጋት የግድ ነው እያልን ነው።
ይህ ደግሞ አያስኬድም፤ አንድ ልጅ 10 የትምህርት አይነቶችን ቢከታተል ለአስሩም እኩል ፍላጎትና ፍቅር ይኖረዋል፤ ወይም ሊኖረው ይገባል (ቢኖረው ጥሩ ሆኖ ሳለ) ማለት ነውና ስህተት ነው። ይህን ስንል ግን ባለ ተሰጥኦ ልጆች የጋራ የሆኑ ባህርያት የሏቸውም ማለት እንዳልሆነ ግን ተግባብተን ማለፍ ይገባናል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ተሰጥኦ በባህርይው አዝጋሚ ሳይሆን ፈጣን፤ ባለበት ረግቶ የሚቆም ሳይሆን ተንቀሳቃሽና በተወሰነ ደረጃም ተለዋዋጭ ነው። ባለ ተሰጥኦነት ምንም አይነት የፆታም ሆነ የቀለም ወይም ሌሎች ልዩነቶች አይገድቡትም። ባለ ተሰጥኦነት በአንድ ዘርፍ ብቻ የሚወሰን አይደለም፤ አንድ ልጅ በተለያዩና ከአንድ በላይ በሆኑ ዘርፎች ልዩ ተሰጥኦ ሊኖረው ይችላል።
ተሰጥኦ አቅጣጫው ወይም ሂደቱ ወደ እውቀትና ጥልቅ አስተሳሰብ መሆኑን ማወቅ የግድ ነው። ተሰጥኦ እንደ ሁኔታው የሚታይና የሚለካ ሊሆን እንደሚችለው ሁሉ በባለቤቱ ብቻ የሚታወቅና ቤተሰብ በሂደት እየተረዳለት ሊመጣ የሚችል መሆኑንም ከወዲሁ መገንዘብ ከወላጆች የሚጠበቅ ተግባርና ሀላፊነት ነው። ተሰጥኦ በትምህርት ቤት ውስጥ ብቻ ሊገለፅ ይችላልና ከመምህራን ጋር ጥብቅ ግንኙነት መፍጠር ከወላጆች የእለት ተእለት ተግባራት አንዱ መሆኑንም መቀበል ያስፈልጋል።
ሌላው የልጆችን የተሰጥኦ ባለቤትነት ከማጎልበት አኳያ ያለው ችግር የልየታ ችግር ነው። ይህን ችግር ለመፍታትና የልጆቹን ልዩ ተሰጥኦ ፈልጎ በማወቅ ማብቃት ተገቢ ሲሆን ለዚህም የተለያዩ ዘዴዎችን (በፈተና፣ በቃል ጥያቄና መልስ፣ በቅርብ ክትትል፣ በውይይት ወዘተ) መጠቀም ተገቢ ነው። ምን ላይ እንደሚያተኩሩ፣ በምን በምን ነገሮች ላይ ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ ወዘተ የሚሉትን በቅጡ ለይቶ ማወቅ በተለይ የቤተሰብ ሀላፊነት መሆኑ ላይ መስማማት ያስፈልጋል።
ልጅዎ ፈጣን፣ ለማወቅ ጉጉና ጥያቄ የሚያበዛ፣ ለማድረግ የሚደፍር፣ በአንድ ነገር (ጉዳይ) ላይ የሚያተኩር፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚሞክርና የራሱ የሆነ ፈጠራ እንዲኖረው የሚጥር፣ ለተፈጥሮ ልዩ ፍቅር ያላቸው ወዘተ ከሆኑ እነሱ የልዩ ተሰጥኦ ባለቤት ለመሆናቸው ከወዲሁ አመላካች ነውና ወላጅም ሆነ መምህራን ሊንከባከቧቸው፣ ሊረዷቸውና የነገ ፍሬ ይሆኑ ዘንድ ሊያበቋቸው ይገባል ማለት ነው። አርፈህ ተቀመጥ፣ እንዲህ አድርጊ፣ ያን አድርግ፣ ልጅ ነሽ ወዘተ እዚህ ጋር እንደማይሰራ መረዳትም ከቤተሰብ የሚጠበቅ ቀዳሚው ሃላፊነት ነው። ይህ ከሆነ አባባ ተስፋዬ “ልጆች የዛሬ አበባዎች፤ የነገ ፍሬዎች” ያሉት እውን ሆነ ማለት ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013