አብርሃም ተወልደ
“ይፍቱኝ” የሚለው መጽሐፍ በወጣቱ ደራሲና ዲያቆን ማለደ ዋስይሁን የተደረሰ ነው። መፅሃፉ በአምስት ምዕራፎች፤ በአንድ መቶ አርባ ስድስት ገጾች የተዘጋጀ ሲሆን የ100 ብር የመሸጫ ዋጋ ተቆርጦለት በያዝነው ወር ለንባብ በቅቷል።
ይህ የስነ ፅሁፍ ውጤት መረጃ ሰጪና አስተማሪ የፈጠራ ስራ ሲሆን የአሳታሚነት ሚናውን ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማህበረ ቅዱሳን ወስዶታል፡፡
የስነ ፅሁፍ ባህሪ ውበት፣ ጠብሰቅ ያለ ሃሳብ፣ ለስሜት ቅርብነት፣ በምናብ ሲራቀቅ፣ ደራሲው የራሱ የሆነ ለዛ ሲኖረው፣ በጊዜ ሲፈተን፣ ለህይወት የሚጠቅም ዋጋ ሲኖረው፣ ለብዙ ሰዎች ትርጉም የሚሰጥ ሲሆንና አለም አቀፋዊነት ሲላበስ ነው፡፡
ጋዜጠኛ ዲያቆን ማለደ ዋስይሁን ከሐሳብ ድሮች መካከል አዲስ የሐሳብ ልቃቂት ፈትሎ ሰዎች ያዩትን ርእሰ ጉዳዮችን መርጦ በቀለማማ ቃላት ማሳመር የሚችል ድንቅ ጸሐፊ መሆኑን በዚህ መጽሐፉ መመልከት ችያለሁ፡፡ ለዚህም ነው ከዚህ እንደሚከተለው “የይፍቱኝ”ን ዘርዘር ያሉ ጉዳዮች ለመዳሰስ የምሞክረው።
መጽሐፉ ምን ይዟል?
“ይፍቱኝ” በሚል ቀዳሚ ርእስ የተሰየመው የስነ ፅሁፍ ውጤት በአራት ምዕራፎች ተከፍሎ ወደ ሰላሳ ሶስት የሚሆኑ ንሑስ ምዕራፎችን የያዘ ነው፡፡ እነዚህ ምዕራፎች በዘመናችን ስላለው የትውልድ ተግዳሮቶች እና ለአመፅ ስለሚጋለጡት ሱሶች እና መውጫ መንገዶች ይተርክልናል፡፡
ደራሲው በይፍቱኝ እንደሚያትተው ከርእሰ ጉዳዮቹ መካከል አንዱ የሆነው የሱሰኝነት ጉዳይ ነው። ከዚህ ውስጥም የተነሱት የሱስ አይነቶች በአብዛኛው የሚያጠምዱት ወጣቱን መሆኑን ይጠቁመናል። ይህ ሱስ ወጣቱን አላማ ቢስና እምነት የለሽ ለማድረግ የሚያደረገው ጥቃት ዋናውን ቦታ እንደሚይዝ በተዋቡ ቃላትና በደረጁ መረጃዎች አስደግፎ ይነግረናል፡፡ በጦርነት ከሚያልቀውና ከሚጠፋው ትውልድ በበለጠ በአዕምሮ ላይ በሚደረጉ የዘቀጡ እውነት መሳይ ሀሰቶች የሚመክነው ትውልድ ቁጥሩ ከፍ እያለ መምጣቱን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡
ደራሲ ማለደ በ“ይፍቱኝ” ሰዎች በተለይም ወጣቶች በከፍተኛ የስጋ እና የመንፈስ ጉስቁልና ውስጥ እየገቡ ላለበት ሁኔታ ሱስ እና ዝሙት ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ ሰዎች በእነዚህ ወጥመዶች መጠለፋቸው ስጋቸውን ብቻ ሳይሆን ነፍሳቸውን የሚያጠፉ በመሆኑ ለሀገርም ለቤተ እምነቶችም ሀዘን እንደሆኑም ይገልጻል፡፡ ከዚህ እስራት ለመፈታትም ከሚሰጡ የተለያዩ ምክሮች እና ሌሎች ተግባራት መካከል መጽሐፉ አስፈላጊ እንደሆነም ያትታል።
በአምስቱ የይፍቱኝ ዋና ዋና ክፍሎች ሱስን በተመለከተ፣ ስለምንነቱ፣ ስለሚያስከትለው ጉዳት እና ከእስራቱ አምልጠን ወጥመድን ሰብረን ለመውጣት ማድረግ ስለሚገባን ነገር ያስረዳናል፡፡ ለሱስኝነት እስራት የሚዳርጉ አንዳንድ መድኃኒቶችን እና የአልኮል መጠጥ ሱሰኝነትን በስፋት ለመዳሰስ ጥረት አድርጓል፡፡
ሱሰኝነት በራሱ ከሚመጣው መዘዝ ባሻገር ለሌላ እኩይ ተግባር የሚጋብዝ ነው። በተለይ ደግሞ ለዝሙት ይዳርጋል። ታዲያ እነዚህ ልማድ እና ድርጊቶቹ በጥልቀት በማለደ ብእሮች ተዳስሰዋል፡፡
በክፍል ሁለት የዝሙት “የዋዜማዎቹ ዋዜማ” በሚል ለዚህ እኩይ ተግባር ከሚያመቻቹን ጉዳዮች ወሳኝ ያላቸውን ጉዳዮች ይዳስሳል፡፡ ለዚህ ለእኩይ ተግባር (ኃጢያት) የሚያጋልጡንን ምክንያቶች ነው “የዝሙት ዋዜማዎች” በሚል ርእሰ ጉዳይ ቀንብቦ በዝርዝር ግንዛቤ የሚያስጨብጠን፡፡
በመጨረሻም የግብረ ዝሙት ምንነትና መዘዝን አስዳስሶ ይልቁንም የዘመናችንን ፀያፍ ድርጊት “የግብረ ሰዶምን” ለማብራራት ይጥራል፡፡ በመጨረሻም የመጽሐፉ ክፍልም ከዚህ እስራት ለመውጣት ማድረግ ከሚገቡ ቁልፍ እርምጃዎች ወሳኝ የሚባሉ ነጥቦችን ይጠቁማል፡፡
የደራሲ ማለደ “ይፍቱኝ” አብዛኛው ሰው በግልጽ የማያወራቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የተነተነ የስነ ፅሁፍ ውጤት ነው። በተለይ ትዕይንተ ግብረ ዝሙት “ፖርኖግራፊ” እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ በመጽሐፉ እንዴት ከዚህ ችግር እንደሚወጣ በግልጽ ያስረዳል። ሰዎች በስፋት ስለ መጠጥ እና ሲጋራ ሱሶች ከጓደኞቻቸውም ሆነ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መመካከር ላይከብዳቸው ይችላል።
ስለ ትዕይንተ ግብረ ዝሙት “ፖርኖግራፊ” ግን አብዛኛው በጉዳዩ ላይ ማውራት ስለሚያሳፍረው እርዳታም ለማግኘት ይቸገራል። ይፍቱኝ በሚለው መፅሃፍ ላይ ግን ከዚህ ህይወት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመውጣት ከፈለጋችሁ ሊረዳችሁ ለሚችል ለአንድ ሰው በግልጽ ችግራችሁን መናገር ይኖርባችኋል በማለት ከችግሩ በምን መልኩ እንደምንወጣ ብሩህ መንገድ ያሳየናል።
ሚስጥር ያረጋችሁትን ነገር ወደ ብርሃን በማውጣታችሁ ይህ ድርጊት በእናንተ ላይ ያለውን አቅም ያጣል። ስትደክሙ የሚያማክራችሁ፤ መቆማችሁን ሁሌ የሚከታተል አንድ ሰው ማረድረጋችሁ ፀንታችሁ እንድትቆሙ ብርታት ይሰጣችኋል። እንዲህ ያለ ሰው የማታገኙ ከሆነ ይህች የዲያቆን ማለደ ዋሲሁን መጽሐፍ ጥሩ አማካሪያችሁ መሆን ትችላለች፡፡
እንደ መውጫ
በደራሲ ማለደ ይፍቱኝ መጽሐፍ ውስጥ በዘመናችን እጅግ በስፋት ወጣቶችን አስረው የያዙ ስጋዊ ስራዎችን በመተንተን ሰለባዎቹን ከተበተባቸው እስራት “ይፍቱኝ” ብለው በተጋድሎ እንዲወጡ ሲያበረታታ እንመለከታለን::
በይፍቱኝ ላይ መልካም ምክሮችን ብቻ ሳይሆን ውብ የሆነ የቋንቋ አጠቃቀም፣ ጥልቅ ሃሳብ እና ስሜት የሚነኩ ርእሰ ጉዳዮችን እናገኛለን። ለዘመናችን ችግር መውጫ መንገድ ያበጀ “ሙሉ” ሊባል የሚችል የስነ ፅሁፍ ውጤት ነው። በጥቅሉ ከፍ ብሎ ከቁመታችን በላይ ለሆነው ችግር መፍትሄ የሚያፈልቅ ድንቅ መጽሐፍ ነው፡፡
ለራስ ችግር መፍትሄ ከመፈለግ ባሻገር ለመጥፋት ዳር ዳር የሚለውን ትውልድ ሊታደግ የሚፈልግ ሊያነበው የሚገባ መጽሐፍ መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን። የዝግጅት ክፍላችንም ከይፍቱኝ ላይ በብድግ ብድግ ለማየት የሞከረውን ዳሰሳ እዚህ ላይ በመቋጨት ቀሪውን ሃሳብ ከመፅሃፉ ላይ እንዲያነቡት እንጋብዛለን፡፡ ቸር እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013