አሸብር ኃይሉ
በአንድ ሃገር ጥሩ እንዳለ ሁሉ መጥፎም አይጣፍም። ጥሩ ነገር ታሪክ ሆኖ እንደምንኮፈስበት ሁሉ በመጥፎ ነገር ደግሞ ታሪክ ሆኖ ሲያልፍ አንገት የሚያስደፋ ይሆናል። በመካከለኛው እና በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ የታየው ታሪክ ሆነው ሲታዩ እንደ ሃገር የምንኮራባቸው እና የሚያሳፍሩ ታሪኮች ተሰርተዋል። አሁንም ይሰራል ወደፊትም ይጠበቃል።
እነአሉላ እና እነ አፄ ዮሃንስ በተፈጠሩባት ትግራይ ከሰብል መሃል አረም እንደሚበቅል ሁሉ ከሰው መካከልም እንክርዳድ በቅሎ ሃገር ለማፍረስ ጫፍ እስከ መድረስ የዳረጉ ታይተዋል። በጎጃም እነ በላይ ዘለቀን የመሰለ ሀገር ወዳድ ባሉበት እነ ራስ ሃይሉ የሰሩት የሚታወቅ ነው። በሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶችም በተመሳሳይ ለሃገር የሚፋለሙ እንዳሉ ሁሉ አገር ሻጮችም ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ወደፊትም የሚጠበቅ ነው።
ከምሁራን ብንመለከት እነ ክቡር ዶክተር ሃዲስ አለማየሁ እስከ ጦር ግንባር ዘምተው ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው ትውልድ የሚያኮራ ታሪክ ሲሰሩ እነ ክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ደግሞ ለጣሊያን አድረው ኢጣሎ የሚል ጋዜጣ እያዘጋጁ ጣሊያን ነጭ ነው እግዜርም ነጭ ነው ለጣሊያን ተገዙ በማለት የሃገራቸው ህዝብ ቀና ብሎ ደረቱን ነፍቶ እንዳያወራ ጥቁር ታሪክ ሰርተዋል ።
ይህን በተመለከትኩ ጊዜ ህወሓት የሰራው ኢሰባዊ እና ኢ-ኢትዮጵያዊ የሆነ ድርጊት በመካከለኛው ዘመን የነበረውን ራስ ሚካኤል ስሁልን አስታወሰኝ። ራስ ሚካኤል ስሁል ከአፄ እያሱ መጀመሪያ እስከ ጎንደር ዘመን በኢትዮጵያ የመጨረሻው መንግስት ድረስ የነበረ ኢትዮጵያን በመከፋፈል ለዘመነ መሳፍንት የዳረገ በአረመኔአዊ ተግባር የሚደሰት ሰው አይነት ሰው ነበር።
ህወሓትም የአያቴን ብለቅ ያለ ይመስላል። ሴረኛው ህወሓት መከላከያን በመግደል ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ያደረገው እንቅስቃሴ ቆም ብሎ ላሰበው ከእንቅልፉ እንደ ነቃ ሰው የሚወራጭ እና የሚያስደነግጥ እና በታሪክነቱ በጥቁር መዝገብ ውስጥ በቀዳሚ ደረጃ የሚሰፍር ይመስለኛል።
ህወሓት ያደረገው ድርጊት በመከላከያ ጥንካሬ ብቻ ኢትዮጵያ ከመፈራረስ እና ለማሰብ ከሚዘገንን እልቂት የዳነች አይመስለኝም፤ ይልቁኑ በኢትዮጵያ በማይታይ አምላኳ ተጋድሎ ጭምር የተረፈች ይመስለኛል።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ራስ ሚካኤል ስሁል ከታላቁ አፄ እያሱ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በትግራይ ክፍለ ሃገር የነበረ የነጋሲ ዝርያ የሌለው አርሰቶክራት ነበር። ታላቁ አፄ እያሱ ሶስት ወንድ ልጆች ይወልዳሉ። አንደኛውን ከትግራይ እናት ይወልዳሉ። ስሙንም ተክለሃይማኖት ይሉታል። ሁለተኛውን ደግሞ ከጎንደር እናት ይወልዳል። ስሙንም ዮሃንስ ይሉታል። ሶስተኛ ልጃቸውን ደግሞ ከጎጃም እናት ይወልዳሉ። ስሙንም ባካፋ ይሉታል።
በዚህ ጊዜ ራስ ሚካኤል ስሁል ከትግራይ እናት የተወለደውን ተክለሃይማኖትን ተንኮል ይመክሩታል። በልቡም ክፉ እሾህ ይተክሉበታል። የተንኮል ምክራቸውም እንደሚከተለው ነበር። አንተ እኮ አባትህን እና ወንድሞችህን ብትገድል በብቸኝነት ያለምንም ተቀናቃኝ ኢትዮጵያን ትገዛለህ ይሉታል።
ተክለሃይማኖትም በራስ ሚካኤል ስሁል ምክር በመታለል ከጎንደር እናት የተወለደውን ዮሃንስን እጁን ይቆርጠዋል። ለምን ቢሉ አካሉ የጎደለ ሰው በክብረ ነገስት የኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት ኢትዮጵያን ማስተዳደር ስለማይችል። በመቀጠልም ከጎጃም እናት የተወለደውን ባካፋን ሊገድለው ሞክሯል።
በዚህ ጊዜ ባካፋ ከወንድሙ ግድያ ለመዳን ወደ መተማ ይሰደዳል። በዚህ ጊዜ ባካፋ በማያውቀው ሃገር ወባ ስለነደፈችው በማየውቀው ቤት ይተኛል። በዚህ ጊዜ ነው የውሃ አጣጩን እቴጌ ምንተዋብን ያገኛት።
ታላቁ እያሱ ሲሞቱ አፄ ባካፋ በአባታቸው ዙፋን ተቀመጡ። አፄ ባካፋም የመተማዋን ወይዘሮ እቴጌ ምንትዋብን አግብተው እያሱ ሁለተኛውን ወለዱ። አፄ ባካፋ በሞቱ ጊዜ እያሱ ሁለተኛ በአባታቸው ዙፋን ተተኩ።
በዚህ ጊዜ ዳግማዊ አፄ እያሱ ልጅ ስለነበሩ እናታቸው እቴጌ ምንትዋብ የልጃቸው አማካሪ በመሆን አዛዥ አናዛዥ ሆኑ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ማደግ አይቀርም እና ዳግማዊ እያሱ ስላደጉ ከየጁ ተወላጅ የሆኑትን ወይዘሮ ዋቢን ያገባሉ። ከወይዘሮ ዋቢም አፄ እዮዋስ ተወለዱ። አፄ እዮዋስም አባታቸው ዳግማዊ እያሱ በሞቱ ጊዜ በአባታቸው ዙፋን ተተኩ።
ይሁን እንጂ ራስ ሚካኤል ስሁል የሃሰት ክስ በመመስረት ራሱ ራስ ሚካኤል ስሁል በሰየሟቸው ዳኞች አፄ እዮዋስም ሞት ፍርድ ስለተፈረደባቸው ታንቀው ተገደሉ። ከዚያም ራስ ሚካኤል የኢትዮጵያ ንጉስ አንጋሽ ሆነው አረፉት።
በዚህም በክብረ ነገስት ክልክል የሆነውን አካሉ የጎደለ ሰው አይነግስም የሚለውን ህግ በመጣስ እጅ የሌላቸውን ዮሃንስን አነገሱ። በዚህ የራስ ሚካኤል ስሁል ስራ ክፉኛ የተበሳጩ ኢትዮጵያዊያን ከራስ ሚካኤል ጋር ተፋልመው ራስ ሚካኤልን ድል አድርገው ማረኳቸው። በዚህም ኢትዮጵያ ያለምንም ንጉስ እንድትቀር ተፈረደባት።
በዚህም ኢትዮጵያን ለብዙ ችግር የዳረገው ዘመነ መሳፍንት አዘቅት ውስጥ ወረወራት። በዘመነ መሳፍንት ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት በመጥፋቱ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለውጭ ወረራ ተዳረገች። የአካባቢ ገዢዎች እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በማለት በሚያደርጉት የእርስ በእርስ ጦርነት የዜጎች ህይወት አደጋ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል።
የሚገርመው ራስ ሚካኤል ስሁል ሲማረኩ እድሜያቸው ከ120 ዓመት በላይ እንደነበር አንዳንድ የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ። ይህን ያህል ዓመት ሲቀመጡ ኢትዮጵያን ሲበጠብጡ እና በጎጥ በመካፋፈል የኢትዮጵያን አንድነት ሲፈታተኑ ኖረዋል።
ህወሓትም እንደ ራስ ሚካኤል ስሁል ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። የሃገር ሁለንተናዊ ንብረቶች ማለትም መንፈሳዊ እና ቁሳዊ ሀብቶችን ለማጥፋት ያልረገጠው ቦታ የለም። የህወሓት የመጀመሪያው ትልቁ ጥፋቱ የታቦተ ፅዮን እና የአል ነጃሽ መስጂድ መቀመጫ የሆነውን እና በሃገራዊ አንድነቱ ለማይደራደረው የትግራይ ህዝብ ጠላት መግዛቱን የሌት ተቀን ስራው አድርጎ መያያዙ ነው።
በዚህም የትግራይን ህዝብ እንደ ሽፋን በመጠቀም ስርቆቱን እና ግድያውን አጧጧፈው። በዚህ አድራጎቱ የሃገራቸው ወደፊት እጣ ፋንታ ያሰጋቸው የትግራይ ብሎም የመላው ኢትዮጵያ ህዝብ የህወሓትን ሰይጣናዊ ስራ ግንባር ለግንባር በማፋለም ህወሓትን ከማዕከላዊ መንግስቱ ስልጣን አባረሩት።
ከማዕከላዊ መንግስቱ የተባረረው አረመኔው ህወሓት አሁንም በዕምነት ታንጾ በዕምነት ላደገው የትግራይ ህዝብ ጠላት ለመግዛት መቀሌ ላይ ቁጭ ብሎ ያልሸረበው ተንኮል አልነበረም። ግን ሊሳካ አልቻለም።
ይህ አልበቃው ብሎ እንደ ራስ ሚካኤል ስሁል ኢትዮጵያን ያለ ማዕከላዊ መንግስት ለማስቀረት በመከላከያ ላይ የወሰደው እርምጃ በኢትዮጵያ ታሪክ ኢትዮጵያዊያን አንገታቸውን ቀና አድርገው እናዳይናገሩ የሚያደርግ፤ የሚያሳፈር ታሪክ ሆኗል።
በመጨረሻም እንደ ራስ ሚካኤል ስሁል እና እንደ ህወሓት ያሉ ባንዳዎችን ከመላው ኢትዮጵያዊያን ጉያ እየነጠሉ በማውጣት የኢትዮጵያን መፃይ እድል በአበባ ምንጣፍ ላይ እናስቀምጠው መልዕክቴ ነው ። ሰ ላም !!!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013