ጀግንነት ብዙ መገለጫዎች አሉት፡፡ ስለጀግንነት ሲነሳ በአሁኑ ወቅት በቅድሚያ በአእምሯችን የሚመጣው የሃገር መከላከያ ሰራዊት ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ሰራዊት ሃገርን ከመፍረስ ያዳነና ሁላችንም በሰላም ወጥተን እንድንገባ ያስቻለን የምንጊዜም ባለውለታችን ነውና፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ግን ጀግና በየፈርጁ ይፈጠራል፡፡ ከራስ አልፎ ለሌሎች አርአያ ሊሆን የሚችል፣ ሃገርና ህዝብን በሚጠቅሙ ተግባራት ላይ ተሰማርቶ የራሱን በጎ አሻራ ያኖረ ሁሉ በየሙያው ጀግና ነው፡፡ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል ለሽልማት የበቁት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችም የዘርፉ ጀግኖች ናቸውና ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሃገራችን በአሁኑ ወቅት እየታገለች ያለችው ከጁንታው ጋር ብቻ ሳይሆን ከድህነት ጋርም ጭምር ነውና፡፡
ድህነት የሰው ልጅ ሁሉ ጠላት ነው፡፡ በተለይ በሃገራችን ይህ ጠላት ላለፈው ግማሽ ምዕተ ዓመት አንገታችንን አስደፍቶን ቆይቷል፡፡ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ደራሽ የነበረችው አገራችን ቀስ በቀስ ድህነት ባደረሰብን ጥቃት የምዕራባዊያን መዘባበቻ እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ከዚህ ጠላት ጋር የሚደረገው ትግል ደግሞ የእያንዳንዱን ዜጋ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡
ድህነት በቀላሉ በጦርነት የምታሸንፈው ሳይሆን ጠንካራ መዳፍ፣ የሰላ አእምሮና ትጋት የሚጠይቅ የመሸገ ጠላት ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ጠላት ሊሸነፍ የሚችለው ዛሬ ለሽልማት እንደበቁት አርሶ አደሮቻችን በተሰማሩበት የስራ መስክ ቀን ከሌሊት ሰርተው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ እድል የፈጠሩ ወይም ለሃገራዊ እድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ያበረከቱ ጀግኖች ሲኖሩን ነው፡፡
በእርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በስራ ወዳድነቱም ሆነ በጀግንነቱ የሚታማ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህንን ህዝብ አስተባበሮ ለስኬት የሚያበቃ በየደረጃው ያለ አመራር፣ የአስተዳደር በደሎችና ችግሮችን እየፈታ እና የስኬት መንገዶችን የሚያሳይ መሪ ከሌለ ግን ይህንን ማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
በሃገራችን የነበረው ነባራዊ ሁኔታ ግን ከዚህ በተቃራኒው ነበር፡፡ በየጊዜው በተከሰቱ ሆዳሞች የተነሳ ለልማት ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ይልቅ ለራስ ብልጽግና ብቻ የሚሯሯጡ መሪዎችና የአመራር አካላት በመፈጠራቸው ድህነትን ማሸነፍ ሳንችል ቆይተናል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ በተለይ በግብርና ራሷን ከመቻል አልፋ የተሻለ ስኬታማ የምትሆንበት ምቹ ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች አላት፡፡ አገራችን ለእርሻ ምቹ የሆነ ሰፊ የመሬት ሃብት አላት፤ ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያ የአየር ፀባይም ለግብርና ስራ ምቹ ነው፡፡
ለመስኖ ስራ የሚያመች የመሬት አቀማመጥና በርካታ ያለምንም ጥቅም የሚፈሱ ወንዞችም የሃገራችን የተፈጥሮ ሃብቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሲደማመሩ ኢትዮጵያ በግብርና ዘርፍ ራሷን ከመቻል አልፋ ለሌሎች አገራት ሊተርፍ የሚችል ምቹ ሁኔታ እንዳላት ያሳያል፡፡
ይሁን እንጂ ግብርናን ለማሳደግና በዘርፉ ስኬታማ ለመሆን ከባህላዊ አሰራር ወጥተን ዘመናዊ ቴክሎኖጂን ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአገራችን በግብርና ስራ ላይ ትምህርት የሚሰጡ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆችና የምርምር ተቋማት አሉ፡፡ እነዚህ ተቋማት ለዘርፉ እድገት በመረባረብ የዘርፉን እድገት እውን ለማድረግ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል አርሶ አደሩም ቢሆን በተቻለው መጠን ምርቱን ለማሳደግ በየጊዜው ዘመናዊ አሰራሮችን ተከትሎ በመስራት ከራሱ አልፎ ለሌሎች የሚተርፍ ምርት ለማምረት ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡ በተለይ በአገራችን ከ80 ከመቶ በላይ የሚሆነው ህዝብ በዚህ ዘርፍ ላይ የተሰማራ በመሆኑ እያንዳንዱ አርሶ አደር የሚጠበቅበትን ከተወጣና ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችና የተሻሻሉ የግብርና ዘዴዎችን በመጠቀም የግብርና ምርቱን ማሳደግ ከቻለ ከራሱም አልፎ ሃገሪቱን ለማሳደግ ትልቅ አቅም ነውና ሁሉም አርሶ አደር ከዚህ አንጻር የራሱን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል፡፡
ዛሬ የሚካሄደው የኦሮሚያ አርሶ አደሮች ሽልማትም በዘርፉ ተሰማርተው ስኬታማ የሆኑና ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የስራ እድል የፈጠሩ፣ በግብርና ምርትም ለሃገራቸው ትልቅ ስራ የሰሩ አርሶ አደሮች እውቅና የሚሰጥ መድረክ በመሆኑ ሌሎችም ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ራሳቸውን ለማሳደግ ሊሰሩ ይገባል፡፡ የግብርና እድገት የሃገር እድገት ነውና እንዲህ ስኬታማ የሆኑ አርሶ አደሮች የዘመኑ የዘርፉ ጀግኖች ናቸውና ሊበረታቱ ይገባል፡፡
በተለይ በአሁኑ ወቅት ሃገራችን በዘርፉ ትልቅ አቅም እያለ በሚሊየን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ከውጭ የግብርና ምርት ታስገባለች፡፡ ይህ ደግሞ እንደአገር ሲታይ ኪሳራ በመሆኑ ይህንን ማስቀረት ይጠበቃል፡፡
ከዚህ አንፃር የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ የቆላ ስንዴ ፍላጎትን በሃገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን በሚደረገው ጥረት ውስጥ የራሱን አስተዋፅኦ ለማበርከት ከፍተኛ ስራ እየሰራ በመሆኑ ይህንን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል፡፡
ዛሬ ለሽልማት እንደበቁት አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ሁሉም የራሱን ድርሻ የሚወጣ ከሆነም በቀጣይ በርካታ ተሸላሚ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮችን እናፈራለን፤ ከሽልማቱም በላይ ደግሞ እንደ አገር በግብርና ዘርፍ ራሳችንን ከመቻል አልፈን ለሌሎችም የምንተርፍ እንሆናለን፡፡ ይህ ደግሞ በሃገራችን ብልጽግና እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም ነውና ሊበረታታ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2013