ክፍለዮሐንስ አንበርብር
እንደ መግቢያ
ሕይወት በየፈርጁ የራሷ ቀለም፣ የራሷን ጣዕምና የራሷን መዓዛ ይዛ ትጠብቃለች። አሊያም ደግሞ ሕይወትን እንደአመጣጧ ተቀብለን የራሳችን መዓዛ እንጨምርባታለን። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሕይወት በተደላደለ መስመር ላይ ሆና የሰው ልጆችን ፍጥረት ትቀበላለች። ሌሎች ደግሞ መደላድል ፈጥረው ያጣጥሟታል።
የሆነው ሆኖ ሕይወት እኛን ትመስላለች። እኛም ሕይወትን እንመስላለን። የሰጠናትን የምትሰጠን፤ የነፈግናትን የምትነሳን ናት ሕይወት። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሕይወት በአሸናፊዎች እና ተሸናፊዎች መካከል ሆና ልክ እንደ ክብ ቀለበት ሽክርክሪት እየሰራች ከፍም ዝቅም ሳትል፤ ሳትሞላም ሳትጎድልም እንዲያው በድርበቡ እዚያው በዛው አለሁ እንዳለሁ፤ እንዳለሁ አለሁ ትላለች።
ወዳጄ ሕይወትን፤ ማሳመርም፣ ማማረርም በእጅህ ናት። በዛሬው ‹‹እንዲህም ይኖራል›› የተለያዩ የተክል ዓይነቶችን እየፈለጉና ረጅም ሰዓታትን በእግራቸው ተጉዘው የጥርስ መፋቂያ በማበጀት ለዓመታት ሲሸጡ የነበሩትንና በአሁኑ ወቅትም በዚሁ መንገድ ኑሯቸውን እየመሩ የሚገኙትን የ80 ዓመት አዛውንት ሕይወት እናስቃኛችኋለን።
ውልደት
በጉራጌ ዞን በአበሽ ወረዳ በገራባ ቀበሌ አንገዶ መንደር ተወልደው ያደጉ ሲሆን ለቤተሰቦቻቸው ብቸኛ ልጅ ናቸው። በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዘመን አዲስ አበባ ላይ ሊስትሮ ጠርገው ነው ሦስት ጉልቻ የመሰረቱት። እኚህ አባት በወልቂጤ ከተማ በአራቱም ማዕዘናት እየተንቀሳቀሱ ከተለያዩ እፅዋት አሳምረው የሰሩትን የጥርስ መፋቂያ አዙረው የሚሸጡ አባት ባርህኒ ዘብሬ ይባላሉ።
ወላጅ አባታቸው በጣሊያን ጊዜ ከሞቱ በኋላ ያቆዩላቸው የእርሻ መሬት በሰው ተወስዶባቸው እርሳቸው የበይ ተመልካች እንዲሆኑ ተፈረደባቸው። ታዲያ ብቸኛ በመሆናቸውና አይዞህ የሚል ወንድም ወይም እህት አጠገባቸው ባለመኖሩ የአባታቸውን ርስት ተከራክረው አሊያም ደግሞ ህጋዊ አካሄድን ተከትለው መርታት አልቻሉም። በዚህ ሁኔታ ኑሮን መምራት አልተቻላቸውም።
ሌሎች የሥራ አማራጮችንና የገቢ ማፈላለጊያ መንገዶች ላይ ማማተር ጀመሩ። ወጣት እያሉም አዲስ አበባ በመሄድ ጫማ በማሳመር ሥራ (ሊስትሮ) በመሥራት ህይወታቸውን መምራት ጀመሩ። በሂደትም ትዳር ይዘው መኖር ጀመሩ።
ዳሩ ግን አዲስ አበባ ከትመው መቅረት አልሆነላቸውም። የትውልድ መንደራቸው ናፈቃቸው። ከዚያም ወደ ጉራጌ መመለስ ፈለጉ። ልባቸው ያለውን አደረጉ። ከአዲስ አበባ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው በመመለስ መሬት ገዝተው ቤት ሰርተው ኑሯቸውን ‹‹ሀ›› ብለው መምራት ጀመሩ።
የመፋቂያ ሽያጭ አጀማመር
እኚህ አባት ከእናት አባታቸው ያገኙት ቤት ንብረት የለም። የተደላደለ ኑሮ ላይ ባለመድረሳቸው በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ገንዘብ ለማግኘት የሚቻላ ቸውን ሁሉ ይሞክራሉ። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አገሪቱን እንደተቆጣጠረ አካባቢ ዋቤ ላይ ለዓመት በዓል የሚሆናቸው እንጨት ቆርጠው ለማጠራቀም በተንቀሳቀሱበት ወቅት በጫካው ውስጥ ለመፋቂያ የሚሆን እንጨት በብዛት መኖሩን አስተዋሉ።
ይህንን አጋጣሚም ወደ ቢዝነስ መቀየር እንዳለባቸው አሰቡ። ከዚያም የጥርስ መፋቂያውን ቆርጠው እና አስተካክለው በወልቂጤ ከተማ እያዞሩ መሸጥ ጀመሩ። ታዲያ ይህ ሥራ በድንገት ይጀመር እንጂ የመፋቂያው ሥራ አሁንም ድረስ ኑሯቸውን እየመሩበት፣ እየደጎሙበት መለያቸው እየሆነ መጣ።
በ80 ዓመት 8 ሰዓት የእግር ጉዞ
መፋቂያውን ለመቁረጥ ዋቤ ድረስ በእግራቸው አራት ሰዓት ለመሄድ እንዲሁም ሲመለሱ አራት ሰአት ያህል ይጓዛሉ። ይህም ብቻ አይደለም እኚህ እርጅና ያልበገራቸው አባት ከሚኖሩበትና ከወልቂጤ ከተማ ወጣ ብላ ከምትገኘው ገራባ ቀበሌ በየቀኑ ወደ ወልቂጤ ከተማ እየተመላለሱ ይሰራሉ። ታዲያ ለድካምና እርጅና እጅ ለመስጠት ከቶውንም አልፈቀዱም።
አዛውንቱ መፋቂያ በመሸጥ ራሳቸውን ብቻ መደጎም ሳይሆን በረከቱ ለልጃቸውም ተርፏል። በወልቂጤ ከተማ ላይ መፋቂያ አዙረው ሸጠው ባገኙት ገንዘብ ለመጀመሪያ ልጃቸው 60 ቆርቆሮ ቤት ሰርተው ሰጥተዋል። በዚህም ለትውልድ ትልቅ አርዓያ ስለመሆናቸው በርካቶች ይመሰክሩላቸዋል።
ለአሁኑ ወጣት ደግሞ ከምንም በላይ የመልካምነት እና የልፋት ዋጋን በሚገባ የተረዱና የሚያስረዱ ትልቅ ተምሳሌት ይሏቸዋል የአገሬው ሰው። ወልቂጤ ከተማ እየተዟዟሩ መፋቂያ በመሸጥ ኑሯቸውን መምራት መደበኛ የህይወት አካላቸው አድርገውታል። ሌላው ቀርቶ የመሬት ግብር የሚከፍሉት እንኳን ይህንን መፋቂያ ሸጠው ነው።
አሁን አሁን በሀገራችን ላይ የመስራት አቅም ያላቸው ውጣቶች ለልመና ውደ ጎዳና ሲወጡና ሲለምኑ ይታያል። እኚህ አባት ግን ለልመና ሳይሆን ለስራ፣ ቁጭ ብለው መጦር ሳይሆን ለፍቶ ማግኘትን መርጠው ሲንቀሳቀሱ ይስተዋላሉ። ማታ ማታ የኩራዝ ጭስ ተቋቁመው ቀን ቆርጠው ያመጡትን የመፋቂያ እንጨት ያስተካክላሉ። እኚህ የ80 ዓመት አዛውንት ለበርካታ ዓመታት መፋቂያ እየሸጡ ቤተሰብ እያስተዳደሩ ይገኛሉ። ለአሁን ወጣት የሥራ ፈጠራን የይቻላልን መንገድ አስተማሪ ሆነዋል።
እምቢኝ ለጡረታ!
እኚህ አንጋፋና እርጅና ያልበገራቸው አባት ለጡረታ እጅ አልሰጥም በማለት ተንቀሳቅሰው የዕለት ተዕለት ገቢያቸውን ይሰራሉ። አሁንም ድረስ ቤተሰቦቻቸውን ጭምር በዚሁ የሥራ መስክ ላይ አሰማርተው ራሳቸውን እና በዙሪያቸው ያሉትን ቤተሰባቸውን በመርዳት ላይ ይገኛሉ። ቁር፣ ግለት፣ ዝናብና ውርጭ ሳይገድባቸውና ሁሉንም ነገር ተቋቁመው ኑሮን ለማሸነፍ ረጅም መንገድ ተጉዘዋል።
የመፋቂያ እንጨት ካለበት ፈልገው ሰብረው ለወልቂጤ ከተማ እየተሽከረከሩ ይሸጣሉ። እኚህ አንድ መፋቂያ በአንድ ብር እየሸጡ የሚተዳደሩት አባባ ባርህኒ ዘብሬ ሁሌም ልባም፣ ሁሌም እጅ የማይሰጡ፣ ሁሌም የማይረቱ ሆነው ዛሬም ደፋ ቀና ብለው ከሕይወት ጋር ትግል ገጥመዋል። በአጭሩ መፋቂያ አዟሪው በዚህ ዕድሜም መጦርን አልፈልግም ሰርቼ ማግኘት ነው የሚል ህልም አንግበው ከሥራ ጋር ተዋህደዋል።
አሁን ያለው ወጣት
አሁን አሁን በሀገሪቱ ወጣቱ ትውልድ የቤተሰብ እጅ ጠባቂነት የሚታይበት ሲሆን ዝቅ ብለው እራሳቸውን አሳንሰው የመስራቱ ባህል አልተለመደም። ረጅም መንገድ ተጉዘው ያመጡትን እኚህ ጀግና አባትን ጫት ቤት ቁጭ ብለው እየቃሙ ለሚውሉ ለአሁን ትውልዶች፣ ከረንቦላ ቤት ለሚውሉት ውጣቶች ትምህርት የሚሆኑ ናቸው። እኚህ አባት ትምህርት ሳይማሩ በጉልበታቸው ለፍተውና ደክመው ገንዘብ ማግኘትን መርጠው ከሊስትሮ እስከ መፋቂያ አዙሮ መሸጥ ሥራ ላይ በመሰማራት የራሳቸውና የቤተሰቦቻቸውን ህይወት መስመር አስይዘዋል።
አባት ባርህኒ ዘብሬ በወጣትነት ጊዜያቸው አዲስ አበባ ላይ በኃይለስላሴ መንግስት ዘመን ሊስትሮ በመጥረግ ገንዘብ ቆጥበው ለወግ ለማዕረግ በቅተው የሁለት ውንድ ልጆችና የሦስት ሴት ልጆች ወላጅ አባት ሆነዋል። ታዲያ እኝህ አባት ልጆቻቸውን በሂደት የህይወት መስመር እንዲይዙ የራሳቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡
ሰዎች ምን ይላሉ?
አቶ ኑሬ ረጋሣ የጉራጌ ዞን ኮሙኒኬሽን ባለሙያ ሲሆኑ፤ ከእኚህ አዛውንት መፋቂያ ገዝተው ጥርሳቸውን ፋቅ! ፋቅ! አድርገዋል። ከዚያም አለፍ ብለው የእኚህን አዛውንት ልፋትና የማያልቅ ትዕግስት በአንክሮ ተከታትለው በጥንካሬያቸው ተደምመዋል። ሁሉ ነገራቸውን ተመልክተው ወቸ ጉድ! ብለው እጃቸው ከአፋቸው ጭነው ተገርመዋል።
በርካቶችም በእኚህ ሰው ሥራ እየተደመሙ እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል። በተለይም በዚህ የእርጅና ዘመን በርካቶች በልጅ እጅ ጡረተኛ በሚሆኑበት ዘመን እርሳቸው ልጆቻቸውን ለመርዳትና ቤታቸውን ለመደጎም የሚያደርጉት ጥረትና መውተርተር በእውነቱ አግራሞትን እየፈጠረብኝ ነው ይላሉ።
ዕድሜና እርጅና ሳይበግራቸው የሰው እጅ አላይም ብለው ወልቂጤ ከተማን እያካለሉ መፋቂያ እያዞሩ ይሸጣሉ። ታዲያ እኚህ አባት አርበኛ አይደሉምን ሲሉ አግራሞታቸውን በጥያቄ ያስቀምጣሉ።
‹‹የሰው ልጅ በምድር ላይ ሲኖር ህይወቱን ለማቆየት ሲል በተለያዩ የሥራ አማራጮች ውስጥ ተሰማርቶ ሲንቀሳቀስ ይስተዋላል። በዚህም የዕለት ገቢውን በማግኘት ህይወት ከመምራቱ ባለፈ ትዳር ይዞ ልጆች ወልዶ አሳድጎ፣ አስተምሮ በእርጅናው ወቅት ለቁም ነገር ያደረሳቸው ልጆች ሲጦሩት እና ሲንከባከቡት ታያለህ። ከእኚህ አዛውንት ጋር ያለው ልምድ ደግሞ የተለየ›› ነው።
የዝግጅት ክፍላችንም መሰል ሰዎች የሥራ ውዳድነትና የሀገር ፍቅር ስሜታቸው የላቀ ስለመሆኑ ይረዳል። በአጋጣሚውም ጎዳና ላይ በልመና የተሰማሩ ሰዎችም ሆኑ ሥራ የሚያማርጡ ወጣቶች ከእኚህ አባት አንዳች ነገር እንደሚማሩ ተስፋ ያደርጋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013