(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ) gechoseni@gmail.com
ትዝብት አንድ- ፓርላማችን ሆይ! በአራት ኪሎ የምትኖር፤
ሕዝብን እያስተዳደረ ያለው መንግሥታችን ከጎምቱ ሹማምንቱ እስከ ጭፍራ ካድሬዎቹ ድረስ ደጋግሞ እየነገረን ያለው “ሥልጣኑን የተረከብኩት ከምርጫ ኮሮጆ ውስጥ አብላጫ ድምጽ ስላገኘሁ ኮንትራቱን አሸንፌ ነው” በማለት ጽኑ አቋሙን እየገለጸ ነው። ያልገባን እየመሰለውም እስኪሰለቸን ድረስ “ገብቷችኋል?” እያለ ሲያስጨንቀን ባጅቷል። የእስከ ዛሬውን “የኮንትራት ውል ስምምነት” በተመለከተ ለጊዜው “በሆድ ይፍጀው” አርምሞ ማለፉ ይበጅ ይመስለናል።
ለወደፊቱም እንደ አፋቸው ያድርግልን ከማለት ውጭ “ጀንበሯ እያዘቀዘቀች” ባለችበት አስራ አንደኛው ሰዓት ላይ “የመንግሥትነት ኮንትራት ፊርማው” እርግጠኛነት ይጣራልን ብሎ መወትወቱና አታካራ መግጠሙ ጉንጭ አልፋነት እንደሆነ ይሰማናል።
ለማንኛውም “የኮንትራት አሰጣጡና አቀባበሉን ጉዳይ” በተመለከተ “ዱቢን አቡልቱ” በማለት ኮቪድና እኛ ብዙኃን ዜጎች ድምጻችንን በአንድ አስተባብረን ሥልጣን ላይ ላለው መንግሥታችን የአንድ ዓመት ዕድሜ ጨምረንለት ስድስት ዓመታትን በመንበሩ ላይ እንዲቀመጥ በ“አሜንታችን ማጽደቃችን” ሳይዘነጋ ኮንትራታችንን ስላደስንለት ስለ አራት ኪሎ ፓርላማችን የሚያብከነክኑኝን አንዳንድ ትዝብቶች ላስታውስ።
ከተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤታችን ጋር የተያያዙ ተደጋጋሚ አስተያየቶችን ከአሁን ቀደም በዚሁ አንጋፋ ጋዜጣ ላይ ባስነበብኳቸው ጽሑፎቼ አማካይነት “ይድረስ!” ማለቴ አይዘነጋም። ከአስተያየቶቼ መካከል አንደኛው በፓርላማው ሕንጻ አናት ላይ የተሰቀለው ሰዓት እስከ መቼ “እንደ ተርኪስ ባቡር በድን ሆኖ ተገትሮ ይቀራል?” የሚል እንደነበር አስታውሳለሁ። በዓለም አቀፍ ደረጃ በፓርላማ ሕንጻ አናት ላይ የሚሰቀሉ ሰዓቶች ከሰዓት አስታዋሽነታቸው በሻገር የከበረ ታሪካዊ ዳራ እንዳላቸውም ለመጠቃቀስ ሞክሬያለሁ።
አስተያየቱን ያነበቡት የተወካዮች ምክር ቤት የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለትችቱ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት “ያንቀላፋው” የፓርላማው ሰዓት ተጠግኖ መንቀሳቀሱን በግል ስልኬ ላይ ደውለው የገለጹልኝ የመጀመሪያው ደውል ዳግመኛ ባቃጨለበት ዕለት ሳይሆን አይቀርም። ኃላፊዋ ዶክተር ምስራቅ መኮንን አስተያየቱን ጉዳዬ ብለው በአክብሮት በመቀበል ለተግባራዊነቱም ፈጣን እርምጃ በመውሰድ ላሳዩት አርዓያነት ምሥጋና ብቻ ሳይሆን አድናቆቴም ከፍ ያለ ነው።
ሰዓቱ ተጠግኖ ወደ ሥራ ከተመለሰ በኋላ በሽታው ሳያገረሽበት እስካሁን መስራት ያለመስራቱን ደግሜ ማጣራት ይኖርብኛል። እንደተለመደው ወደ ሽልብታው ተመልሶም ከሆነ ደጋግሞ ሊነቃ እንደሚገባ ማስታወሱ ተገቢነት ይኖረዋል። በርካቶቹ የሀገራችን ሹማምንቶች ለሚሰነዘርባቸው ገንቢ አስተያየቶች “አለርጂክ” መሆናቸውና ሲበረታም “ለክስ” መጣደፋቸው ሥር በሰደደበት ባህል ውስጥ አንድ ተምሳሌት ሹም ማግኘት በግሌ ቀላል ጉዳይ አይመስለኝም።
ቀደም ባሉት እትሞች ለማስታወስ እንደሞከርኩት በታዳጊነት ዘመኔ የንጉሡን ዘመን “ካባ ለባሽ” የፓርላማ አባላት፣ በወጣትነት የደርግ ዘመነ ዕድሜዬ ደግሞ “በዝሆን ምልክት ጀርባ ላይ ተጭነው የተጫኑን” ወንበረተኞችና በጎልማሳነት የዘመነ ኢህአዴግ ዕድሜዬ “የተናዳፊነት ግብር” በምትወክለው “ንቡት” ተመስለው አራት ኪሎ ላይ ስለከተሙት የየዘመናቱ “ፓርላሜንታሪያን” ንባቤንና የሩቅ ተመልካችነቴን በመጠቃቀስ ጽሑፎቼን ለማስነበብ ሞክሬያለሁ።
የንጉሡ ዘመን ፓርላማ መንፈሱ የከበደ፣ የሹማምንቱ ሞገስ የገዘፈ፣ የክርክር ዘይቤያቸውም ፊውዳላዊ ባህርይውን እንደያዘ የተሟሟቀ እንደነበር ዝርዝሩን ያጫወቱኝ ነፍሰ ሄር የቀድሞ ፕሬዚዳንትና ወዳጄ ክቡር አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ነበሩ። “የሰማያዊ ካኪ ዩኒፎርም ለባሾቹ” የኢሕዲሪ (የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ) መንግሥት የፓርላማ አባላት ክራሞት አጀንዳዎች በዋነኛነት “የሰሜን የሀገራችን ተገንጣይ ቡድኖችን እንዴት እናንበርክክ?” የሚሉ ዓይነቶች ስለነበሩ ከዚህ ውጭ ብዙ ማለት የሚቻል አይመስለኝም።
በጦርነት መካከል ይነደፉ የነበሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን ዝርዝር በተመለከተ ዋነኛው የወቅቱ ሹም በመጽሐፍ ሊያስነብቡን ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ ስለሆነ ያኔ የሚባለውን እንላለን። የደርግ ፓርላማ በሶሻሊዝም ፍልስፍና ልቡን መዝጋቱ ብቻ ሳይሆን ወደ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የሚያስገቡ የሕዝብ መመላለሻ ጎዳናዎች ሳይቀሩ ተዘግተው ስለነበር ሕዝበ ምዕመኑ እንደምን “እንባውን ወደ ፀባኦት” ይረጭ እንደነበር የደረስንበት እናስታውሰዋለን። በዚህና በፖለቲካው ድንዳኔ የተነሳ ሕዝቡ ሕንጻውን እንኳን ዞር ብሎ ለማየት ተቀይሞ እንደነበርም የሚዘነጋ አይደለም።
የሩቅ ዘመኑን ጉዳይ ለጊዜው ተወት አድርገን በቅርቡ ላይ እናተኩር። የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለአንድ ሀገራዊ ሴሚናር ለሚያቀርበው የጥናት ጽሑፍ መረጃ ለማግኘት የፓርላማውና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በጋራ ወደሚገለገሉበት የተቋሙ ቤተ መጻሕፍት ጎራ ብሎ ነበር። እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ በመስተንግዶ ጠረጴዛው ላይ የተኮፈሰው በረኛ ጥያቄዬን አዳምጦ እንደጨረሰ “እንዴት በተራ ዜጋ የተከበረው ቤተ መጻሕፍት ለአገልግሎት ይጠየቃል” በሚል ስሜት ያደረሰብኝ ግልምጫና ማመነጫጨቅ በዝርዝር ለንባብ የሚቀርብበት ወቅት ሩቅ አይሆንም።
የአሜሪካውን የኮንግረስ ላይብረሪ በጎበኘሁበት አንድ አጋጣሚ የተደረገልኝን የልብ አድርስ መስተንግዶና በራሴ ሀገር ያጋጠመኝን ውርደት እያነጻጸርኩ ባሰብኩት ቁጥር “ይብላኝልን ኮንትራት ሰጭውን ተራ ዜጋ ለማያምን ፓርላማ” ከማለት ውጭ እጅግም የምለው የለኝም።
ክልዔቱ። እኔው ራሴ የዝግጅቱ ኮሚቴ አንዱ አባል በነበርኩበት አንድ ጉባዔ ላይ እንድቀመጥ ተመድቦ በተሰጠኝ ወንበር ላይ “ሀገር ሰላም ብዬ” መርሃ ግብሩን በጥሞና እየተከታተልኩ እያለ “የተከበሩ አንድ የፓርላማ ሰውዬ” አርፍደው በመምጣት በብጤዎቻቸው ግራና ቀኝ መካከል መቀመጤን አስተውለው “ቦታው ለእሳቸው መሰል እንጂ ለእኔ እንደማይገባ” በማመናቸው ግብረ ገብነት በጎደለው ትዕዛዝ ወንበሩን እንድለቅላቸው ማስገደዳቸውን ባሰብኩ ቁጥር አሁንም “ይብላኝልሽ አንቺ ሀገሬ የውክልና ወንበር ለሰጠሻቸው መሰሎች” በማለት የምብከነከነው “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን” በሚሉት ብሂል ማለፉ ይሻላል በማለት ነው።
ምስክር እንዳቀርብ የምገደድ ከሆነ በዚያ ጉባዔ ውስጥ ድርጊቱን በጽሞና ሲከታተሉ የነበሩትን የፌዴራል የፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥራ ኃላፊዎች መጠየቅ ይቻላል። እኒህን መሰል መሪር አጋጣሚዎች ቀደም ሲል ለጠቀስኳቸው አርአያ ሰብ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ በእግረ መንገድ ጭውውት መሃል አንስቼባቸው ከልብ ማዘናቸውን በመግለጽ “ከስሜት ህመሜ ፈውሰውኛል።” በዚህም ምክንያት ነው ሰሚ ያገኘሁ ስለመሰለኝ ዛሬም ስለተከበረው የፓርላማ ወንበረተኞች ገንቢ ትዝብቴን ለማካፈል የሞከርኩት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩና አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች በፓርላማው ፊት ቀርበው ስለ ሀገራዊ ዕቅዶች አተገባበርና ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጡና ጥያቄዎችን እንዲመልሱ የሚያስገድድ አሰራር መኖሩ ይታወቃል። መልካም ነው። ነገር ግን ጥያቄዎቹና አስተያየቶቹ በንባብ የሚቀርቡበት ሁኔታ በእጅጉ አሸማቃቂ መሆኑን “ኮንትራት የሰጠናቸው እኛ ዜጎች” በየጓዳችን ብቻ ሳይሆን በየአደባባዩም ጭምር ብንገልጽም እስካሁን ሰሚ አላገኘንም።
ለመሆኑ እንደ እኛ ሀገር የሌሎች ሀገራት ተወካዮች ለአስፈጻሚው አካል ጥያቄዎችንና አስተያየታቸውን የሚያቀርቡት የግድ በጽሑፍ ነውን? ከሆነስ እንደ አብዛኞቹ የእኛ ተወካዮች ጥያቄዎችን፣ አስተያየቶችንና የግል ሃሳባቸውን እያደበላለቁና የግድ እንደ መጫኛ እያረዘሙ ይሆንን? በአንድ ዐረፍተ ነገር መጠየቅ የሚገባው ጥያቄ አላግባብ እንዳይተነተንስ ለምን አይሞከርም? በአንዱ ተወካይ የተጠየቀው ጥያቄስ በሌላ ሰው እየተብራራ ደግሞ ደጋግሞ የሚቀርበው ሃይ ባይ ጠፍቶ ወይንስ ስብሰባውን ለማራዘም ተፈልጎ? አንዳንዴ ጠያቂዎቹ ራሳቸው የሚጠይቋቸውን ጥያቄዎች በተመለከተ እንኳን ለመላሹና ለእኛ “ለወካዮች” ቀርቶ ለጠያቂዎቹ ለራሳቸውስ ግልጽ ይሆንላቸዋልን?
አንዳንዱ ተወካይ ጭርሱኑ የተሰጠውን ጥያቄ ማንበብ እየተሳነው ሲጨነቅ ስናስተውል በቴሌቪዥናችን ፊት እንዳፈጠጥን ስሜታችን እንደሚኮማተር አይገባቸው ይሆን? ይበልጥ የሚያበሳጨውና ትዝብቱን መሪር የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ተወካዮቹ በሙሉ የታደሉትን የጥያቄዎች ወረቀት ልክ እንደ ብሔራዊ ፈተና አንድ ላይ እየገለጹ ማስተዋልስ አይሰቀጥጥም? ወረቀቱ አንዳንዴ ቀይ፣ አንዳንዴም ነጭ ወይንም ሌላ ቀለም መሆኑ ልዩ ትርጉም ይኖረው ይሆን ወይንስ የተመልካችን ዓይን ለመሳብ? ምናለ አንድ ተወካይ የሚሰጠውን ጥያቄ በሚገባ አብላልቶና ሃሳቡን ጨብጦ በቃሉ እንዲያቀርብ ቢፈቀድለት? የፓርላማው አሰራር የሚያስገድድ ከሆነስ ጥያቄዎቹ በሙሉ ለታሪካዊ ሪከርድ ተሰንደው እንዲቀመጡ ተደርጎ ጠያቂዎች በቃላቸው እንዲጠይቁ ቢደረግ አይሻልም? ይህን መሰሉ የፓርላማ ውሎ “እኛን ኮንትራት ሰጭ” ዜጎችን ብቻ ሳይሆን ውሎውን ለመታዘብ በልዩ ሁኔታ የሚጋበዙ የዲፕሎማቲክ ኮሚዩኒቲ አባላትንም ለትዝብት ስለሚዳርግ በጥብቅ ሊታሰብበት ይገባል።
መሪር አስተያየቴን ለማቅረብ የተደፋፈርኩት የሰለጠንኩበትና ዓመታት ፈጅቼ ያጠናሁት የኮሙዩኒኬሽንና የባህል ጥናት ትምህርቴ ግድ ብሎኝ ስለሚሞግተኝ መሆኑ ይታወቅልኝ። ዝርዝሩን አቅርብ ከተባልኩም ዝግጁነቴን አረጋግጣለሁ።
ትዝብት ሁለት – የቦርድ ሹመትና ሹመኞች፤
ኢህአዴግ እንዳይነቃነቅ አድርጎ ተክሎ ከሄደብን ሀገራዊ በሽታዎች መካከል አንዱ አንድን ሹም አሥርና ሃያ ቦርድ ውስጥ አባል አድርጎ የመሾም አባዜ ነው። መቼም ተሸሽጎ መታዘብ ብቻ ሳይሆን ሃሳባችንን በነፃነትና በፀሐይ ፊት ለማስጣት ጭምር “ዲሞክራቱ ሕገ መንግሥታችን” የማይገሰስ ሥልጣን ስለሰጠን “ከምን ይሉኝና ምን ያደርጉኝ ስጋት ነፃ ስላወጣን” ልናደንቅ ይገባል።
በዘመነ ኢህአዴግ አሥራ ምናምን ቦርዶች ውስጥ ሰብሳቢና አባል ስለነበሩ አንድ “ፊታውራሪ ፖለቲከኛ” በተደጋጋሚ ሲወራ እንደነበር እናስታውሳለን። አንዳንዶች “ገመናቸው” በይፋ ስላልተገለፀ እንጂ ከተባለው ቁጥር ከፍ ባሉ ቦርዶች ውስጥ “ይተከሉ” እንደነበር በሹክሹክታም ቢሆን ውስጥ ለውስጥ እየተወራ ስንታዘብ መክረማችን አይዘነጋም።
በሚኒስትርም ሆነ በዴኤታ ወይንም በኮሚሽነርነት ማዕረግ ላይ ያሉ ግለሰቦች ፈታኝ መደበኛ ሥራቸውን በሚያደናቅፍ መልኩ ያለ ትምህርት ዝግጅታቸውና ያለ መሠረታዊ ዕውቀት ድጋፍ የቦርድ ሹመት ሲቀርብላቸው አንድም በዝቶብኛል፣ ካልሆነም ሙያዬ ከምሾምበት ተቋም ባህርይ ጋር አይመጣጠንም ማለት ለምን እንደሚሳናቸው በግሌ አይገባኝም።
በእርግጠኝነት ለመናገር ግን በእንደነዚህ ዓይነት የሹመት አካሄዶች ወንበር የሚይዙ የቦርድ አባላት ተፈላጊውን ውጤት ያመጣሉ ተብሎ አይጠበቅም። በሙያቸው የበቁ፣ ለውጤታማነት የማይታሙ፣ ሀገራቸውን ለማገልገል በጎ ፈቃድና ዝግጁነት ያላቸውን ዜጎች ለማየት ለምን የመንግሥት ዓይን ሊጨፈን ቻለ? ወይንስ የንጉሣዊያን ቤተሰብ የነበሩ አንዲት ልዕልት “የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ምን ያህል ይሆናል?” ተብለው ሲጠየቁ “እኛ እኛ ተቆጥረን ሃምሳ አንሞላም” እንዳሉት ይሆንን።
ለማንኛውም አንድ ዓመት ምራቂ ተደርጎለት ስድስት ዓመታትን በመጓዝ “ኮንትራቱን ሊጨርስ አምስት ወራት ብቻ እንደቀረው መንግሥታችን” ቀጣዩም “ኮንትራት ተቀባይ ፓርቲ” ፈለጉን የሚከተል ከሆነ የሀገሬ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ መገመት አይከብድም። የእኛ “ወካይ ዜጎች” መብከንከን ለጊዜው ይዘግይና ፈጣሪ ጸሎታችንን ወደ ጎን እንዳይገፋውና መፃኢው መንግሥትም ይህን መሰሉን ልማድ እንዳይቀጥል እንዲያስብበት ፈጣሪን ራሱን “በእግዚሃር አንተ እግዚሃር” እያልን እንማጠነዋለን።
የትዝብት አንድ ማሳረጊያ – የሕዝብን ልብ ልባቸው ያደረጉ፣ የዜጎችን ድምጽ ድምጻቸው ያደረጉ ሞጋችና ኅሊና አደር ብቁ ተወካዮችን “ጌታው ዲሞክራሲ” ለሥልጣን ያብቃልን። ተጽፎ የሚሰጣቸውን ብቻ የሚያነቡ ሳይሆኑ ከሕዝብ የስሜት ሰሌዳ ላይ የተጻፈውን እንባና ስብራት የሚያነቡ ልበ ስሱ ተወካዮችን ፈጣሪ ይስጠን። ልመናም ምኞትም ነው።
የትዝብት ሁለት መሸብለያ – የፖለቲካ ዘብ አደሮችን ሳይሆን ለሕዝብ ክብር ኖረው በኅሊናቸው የሚሸለሙ ተወካዮችን ያብዛልን። “ሲልኳቸው ወዴት፣ ሲጠሯው አቤት” የሚሉ ሳይሆኑ ሹመታቸውን በብቃታቸው መዝነው የሚቀበሉ፣ የፓርቲ ተልዕኳቸውን በዕውቀት የሚከውኑ፣ ሀገራቸውን እንጂ ማጀታቸውን የማያበለጽጉ አለቆችን ሳይሆን አገልጋዮችን ያትረፍርፍልን። አሜን! ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013