በለዉ አንለይ batlast@gmail.com
ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም በሃርመኒ ሆቴል ፀረ ሙስና ላይ ያተኮረ አንድ ወርክሾፕ ተካሂዶ ነበር።“መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነትን በማስፈን ሙስናን በግልጽነትና በተጠያቂነት የሚታገሉ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጎልበት” በሚል ርዕስ በትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ አማካኝነት የተዘጋጀዉ ይህ ፕሮጀክት ለሶስት ዓመት የሚቆይ ሲሆን የአውሮፓ ሕብረት (Civil Society Fund III) የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ነው።
ፕሮጀክቱ ባለድርሻ አካላት ብሎ ከለያቸው መካከል አንዱና ዋናው መገናኛ ብዙኋን ናቸው።መገናኛ ብዙኋንን እንደ አንድ ሁነኛ ሙስናን መከላከያና መመርመሪያ መሳሪያ አድርጎ በመውሰድ ከመገናኛ ብዙኋን ጋር አብሮ ለመስራት ያሳየው ተነሳሽነት የሚደነቅ ነው።በእርግጥም መገናኛ ብዙኋን ሙስናን በመከላከል፣ በማጋለጥና የህዝብን ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወቱ የዲሞክራሲ ተቋማት ናቸው።
የአገራችን መገናኛ ብዙኋን ሙስናን በመከላከል ረገድ ሚናቸው ዝቅተኛ እንደሆነ በዕለቱ የመክፈቻ ጥናት ያቀረቡት አቶ ሰለሞን ጎሹ ጠቅሰዋል።አቶ ሰለሞን እንዳሉት መገናኛ ብዙሃን ያሉበት ሁኔታ (ከህግ፣ ከመዋቅርና አደረጃጀት አንጻር) ሙስናን ከመከላከል ይልቅ የራሳቸውን ህልውና ጠብቀው ለመቆየት የሚታገሉ ናቸው።
ሙስና በአገርና ህዝብ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ ለማጤን የግድ የጥናት ማህደር ማገላበጥ አያስፈልግም።አገራችን ኢትዮጵያ አሁን የገባችበትን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውጥንቅጥ በማየት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።ሙስና ብዙ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትል ሲሆን በተለያዩ መስኮች ሊገለጽ ይችላል።ጉቦን ጨምሮ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ የመንግስት ግዥ፣ ግብርና ታክስ፣ የኮንስትራክሽን ስራዎችና የመሳሰሉት ዋና ዋና የሙስና መንስኤዎች ናቸው።
ሙስና የልማትና የፖለቲካ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ በመንገዳችን ላይ የወቀደ ትልቅ እንቅፋት ነው።የአሁኑ ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትና የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በአንድ ወቅት እንዳሉት ሙስና የዜጎችን እምነት የሚገድል፣ ስራ ፈጠራን የሚያዳክምና የሚያጠፋ ካንሰር ነው።
አገራችን አስቸጋሪ ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ እንድትገባ ሙስና የነበረው አስተዋጽኦ በጣም ከፍተኛ ነው።ሙስናን ለመከላከል መወሰድ ያለበት እርምጃ ሁሉ መወሰድ አለበት።ለአብነት ያህል አሁን ላይ በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን ህግን የማስከበር ዘመቻ ሙስናና ዘረፋን የመከላከል አንዱ አካል ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
ሙስናን ለመከላከል ዋናው መንገድ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሆነ ተደጋግሞ ይነሳል።ግልጽነት ሲነሳ ደግሞ የመገናኛ ብዙኋን ነጻነት የማይረሳ ጉዳይ ነው።የፀረ ሙስና ትግሉ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ መገናኛ ብዙኋን የማይተካ ሚና አላቸው።
መገናኛ ብዙኋን የህዝብን አስተያየት፣ አመለካከትና ስሜት የሚለኩ ባሮሜትር እንደመሆናቸው መጠን፣ በነጻነትና በኃላፊነት ስሜት መስራት የሚችሉበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ለነገ የሚባል ስራ አይደለም።ሙስናንና ብልሹ አሰራርን የመከላከሉ ጥረት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው የተጠናከረ የፕሬስ ነጻነት ሲኖር፣ ሲጎለብትና ሲስፋፋ ብቻ ነው።
በአንጻሩ የመናገርና የፕሬስ ነጻነት መብት ሲገደብ ሙስና በእጅጉ ይንሰራፋል።ነጻ ሚዲያ የነጻ ሀሳብ መድረክ ከመሆኑም በላይ ዜጎች በመንግስት አሰራርና አመራር ላይ ሀሳብ እንዲያቀርቡ በማስቻል ጉልህ የሆነ ሚና ይጫወታል።“የነጻነቶች እናት” በመባል የሚታወቀው የአመለካከትና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት እስካልጎለበተና እስካልተስፋፋ ድረስ፣ ሙስና ለአገራችን ዕድገት እንቅፋት ከሆኑት ችግሮች መካከል አንዱና ዋነኛው ሆኖ ይቀጥላል።
በተለይ ሙስናን ለመዋጋት የሚያስችሉ ሥራዎች ተብለው ከሚታወቁት ሶስት ስልቶች (የመከላከል፣ የመመርመርና የመክሰስ) ውስጥ መገናኛ ብዙኋን የሙስና ወንጀሎችን በመመርመር ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።ለዚህም የምርመራ ጋዜጠኝነት (investigative journalism) ላይ ትኩረት በማድረግ ሙስናንና ሙሰኞችን ለህዝብ ማጋለጥ ይጠበቅባቸዋል።
የፀረ ሙስና ትግሉ ጠንካራ አለት ላይ እንዲገነባ የመንግስት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው።መገናኛ ብዙኋን የተጣለባቸውን ህዝባዊ ኃላፊነት በአግባቡ ይወጡ ዘንድ ከመንግስት ባለስልጣናትና ፖለቲከኞች ቀጥተኛ ተጽዕኖ ነጻና ለመረጃ ተደራሽ መሆን አለባቸው።
ሁሉም የመንግስት ባለስልጣን፣ ህዝቡ የመንግስትን ስራ ለማወቅ ያለውን መብትና የመንግስት ባለስልጣናት ያለባቸውን የተጠያቂነት መርህ በመከተል ከመገናኛ ብዙኋን ጋር የመተባበር ግዴታ እንዳለባቸው ህጉ ይደነግጋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013