አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም በድንገት መገደሉን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ የሰዎች ሕይወት በአሰቃቂ መንገድ ጠፍቷል፤ የአካልና የሥነ-ልቦና ጉዳት ደርሷል፤ ንብረት ወድሟል፤ ሰዎች ከቤታቸው እና ከኑሯቸው በመፈናቀል ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል። ይሄ የጭካኔ ሂደት በሀገራችን ይሆናል ብለን የማንጠብቀው፤ ነገር ግን ሆኖ በዓይናችን ያየነው አሳዛኝ ክስተት ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ ባደረገባቸው 40 የኦሮሚያ አካባቢዎች ባሰባሰበው መረጃ መሰረት በሦስት ቀናት ውስጥ የ123 ሰዎች ሕይወት አልፏል፤ በ500 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል። በግለሰቦች፣ በንግድ ድርጅቶችና የመንግሥት ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ዘረፋ መፈጸሙንም አስታውቋል።
ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች መካከል 35ቱ በሁከቱ በተሳተፉ ግለሰቦችና ቡድኖች የተገደሉ መሆኗቸውን አስታውቋል። እነዚሁ አካላት በ306 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት አድርሰዋል። በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተወሰደ ዕርምጃ ደግሞ ቢያንስ 76 ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ190 በላይ ሰዎች የአካል ጉዳት መድረሱን በሪፖርቱ አካቷል።
እንዲሁም በፀጥታ መደፍረሱ ወቅት በተከሰተ ፍንዳታ፣ ቃጠሎ እና መሰል አደጋዎች 12 ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ተጠቅሷል። ይህንን ጥቃት ያደረሱት ብዙ ቁጥር ያላቸው ከቦታ ቦታ በቡድን ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች ሲሆኑ፤ በጩቤ፣ በድንጋይ፣ በእሳት፣ በኤሌክትሪክ ገመድ፣ በዱላ፣ በዶማ፣ በገጀራ እና በመጥረቢያ ተጠቅመው ሰዎችን ደብድበዋል፤ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ ፍጹም ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በማሰቃየት ጭምር ሰዎችን ገድለዋል። የከፋ የጭካኔ ተግባራት ፈጽመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ 6 ሺህ 468 ሰዎች በቤት እና ንብረታቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት ለደኅንነታቸው በመስጋት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በቤተክርስቲያን እና በመንግሥት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ለመሸሽ ተገደዋል። እንዲሁም የመንግሥት ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ ከ900 በላይ በሚሆኑ ንብረቶች ላይ ቃጠሎ፣ ዝርፊያና ውድመት መፈጸሙን የኮሚሽን ሪፖርት አመላክቷል።
ይሄ ሪፖርት የወጣው መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት አይደለም። ከራሳችን የመንግሥት ከሆነው የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ነው።
ሪፖርቱ በመንግሥት ደረጃ ግልጽ ብሎ ሀቁ መውጣቱ አንድም የዴሞክራሲ ተቋሞቻችንን ሪፎርም ለማድረግ የተሠራው ሥራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ያሳያል፤ ሁለትም ከዚህ ቀደም እንደምናውቀውና እንደምነሰማው የተድበሰበሰና የተደበቀ ሳይሆን ግልጽ ሪፖርት መውጣቱ መንግሥት ለሚወስደው የህግ ማስከበር ሥራ ችግሩን ከመሰረቱ ለማወቅና ለማረም ይረዳል።
ለውጡን ተከትሎ የተጀመሩ የዴሞክራሲ ተቋማትን እንደስማቸው የማድረጉ ጅማሮ አበረታች መሆኑን ያሳያል። ሀገር ሀገር ናት፤ ፖለቲካም ፖለቲካ ነው። የዴሞክራሲ ተቋማትም እንደስማቸው መሆን አለባቸው የሚለውን በተግባር ለማየት ያስቻለ ሪፖርት ነው።
ሪፖርት በዚህ ደረጃ መውጣቱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ሪፖርት ማውጣትና ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ብቻውን ግብ አይደለም። በመሆኑም ሪፖርቱ የቀረበለት የመንግሥት አስፈጻሚ አካል ተጠያቂውን አካል ተጠያቂ በማድረግ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይጠበቅበታል።
በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የተጠረጠሩ ሰዎች ተለይተው ለፍትሐዊ የዳኝነት ሂደት እንዲያቀርቡና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ፤ እንዲሁም አሰቃቂ ወንጀሎች እንዳይፈጸሙ የስጋት ምንጮችን እና አመላካቾችን በመለየት መከላከል የሚያስችል ጠንካራ እና የተቀናጀ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና የመከላከያ ሥርዓት መዘርጋት ይገባል።
የአጥፊዎችን ተጠያቂነት ከማረጋገጥና የተጎዱ ሰዎችን መልሶ ከማቋቋም በተጨማሪ፤ መንግሥት ከባለድርሻ አካላትጋር በመተባበር፤ የተሟላ የግፍና ጭካኔ ወንጀል መከላከያ ስትራቴጂ ተነድፎ በአፋጣኝ በሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ ተገቢ ነው።
በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች መሰረት በሕይወት የመኖር መብት ላይ ያንዣበቡ ተጨባጭ ስጋቶችን ለማስወገድ ተገቢ እና ተጨባጭ ዕርምጃዎችን እንዲወሰዱ፤ በተለይም ብሔር እና ኃይማኖትን መሰረት በማድረግ ለሚፈጸም ጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የበለጠ ጥበቃ ማድረግ ይገባል።
ኮሚሽኑ እውነታውን በሪፖርቱ ፍንትው አድርጎ እንዳወጣው ሁሉ አስፈፃሚ አካላትም የሚጠበቅባቸውን ሥራ ሠርተው ውጤቱን ለህዝብ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል። ሁሉም አካል በሚጠበቅበት ልክ የሚሠራው የታሰበውን ያህልም የዴሞክራሲ ግንባታ መደላድል የሚፈጠረው ጋን በጠጠር ይደገፋል እንደሚለው የአበው አባባል የኮሚሽኑ የሥራ ውጤትም በአስፈፃሚው አካል መድገምና ውጤቱን በተጨባጭ ማሳየት ሲቻል ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2013