አዲስ አበባ፡- ዶክተር አብይ አህመድ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የዛሬ አሥር ወር የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ፡፡ ልክ ዛሬ 300 ቀናት ሞላቸው፡፡ በበዓለ ሲመታቸው «ዕለቱ ለሀገራችን ታሪካዊ ቀን ነው፤ በታሪካችን በተለያዩ አጋጣሚዎች አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ የመጀመር እድሎችን አግኝተን ብዙዎቹን በወጉ ሳንጠቀምባቸው አምልጠውናል፡፡ አሁንም ይህ የስልጣን ሽግግር አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ሌላ ታሪካዊ እድል ነው፤ በመሆኑም በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ልንጠቀምበት ይገባል» ሲሉ የአገሪቱን የወደፊት ተስፋና በእርሳቸው ሊከናወኑ የሚገቡ አንኳር ጉዳዮችን ዘረዘሩ፡፡ በርግጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃልና ተግባር ገጥሞ ይሆን?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አገሪቱን የመምራት ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ በፖለቲካ፣በማኅበራዊና በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ በመልካም አስተዳደር፣ በህግ የበላይነት፣ በሠላምና ፀጥታ ዘርፎች ሰፊ ተግባራቶች ማከናወናቸውና በቀጣይ ምን እንደሚጠበቁባቸው በልዩ ልዩ የሥራ መስክ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን የ300 የሥራ ቀናትን በተመለከተ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ኢኒስቲትዩት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ሙሉዓለም እንደገለጹት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየክልሉ በመሄድ ከህዝብ ጋር ያደረጉት ምክክር በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ወደሥራ ሲገቡ ከሚመሩት ህዝብ ጋር ለመወያየት መወሰናቸው፣ የፖለቲካ ስነምህዳሩን ለማስፋት ያደረጉት እንቅስቃሴ፣ በውጭ ሀገር ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሀገርቤት እንዲገቡ ማድረጋቸው፣ሆድና ጀርባ ሆነው ከመንግሥት ጋር እንደጠላት ይተያዩ የነበሩ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን አመለካከት መቀየር መቻላቸው፣በሀገራቸው ጉዳይ የማይሳተፉ የነበሩ ምሁራን ተሳትፎአቸው መጨመሩ፣ ብዙ ሴቶች ወደ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት መምጣታቸው፣ የመገናኛ ብዙኃን ለሚያቀርቡት ዘገባ ነጻነት እንዲኖራቸው ማድረጋቸውና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት መቻላቸው ከስኬቶቻቸው መካከል መሆናቸውን ያስታውሳሉ፡፡
አቶ መላኩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ተግዳሮቶች ብለው ከጠቀሷቸው መካከል የሥራአጥነት መስፋፋት፣ የወጣቱ በሁከት ተሳታፊ መሆን፣የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣በብሄርና በመንደር ያለው ክፍፍል፣ በራሱ በገዥው ፓርቲ መካከል ክፍፍል መኖሩ፣ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሰጣቸውን ዕድል ተጠቅመው በሀገሪቷ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ አለመቻላቸው፣በየጊዜው በሚፈጠር ሁከትና ግርግር በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከመንደራቸው መፈናቀላቸው፣ኢትዮጵያ የሌሎችን ዜጎች ስደተኞች የምትቀበል ሀገር ሆና ነገር ግን እርሷ ችግር ውስጥ መሆኗ፣የብሄር ጉዳይ በከፍተኛ ትምህርት ውስጥ በተለይ በተማሪዎች ላይ የፈጠረው ጫና እና የሚረብሹት ቁጥር ከፍተኛ መሆኑ፣ህገወጥ የመሳሪያ ዝውውር፣የውጭ ምንዛሪን ማሸሽ የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀጣይ የሚጠበቅባቸውንም አቶ መላኩ እንደገለጹት በፓርቲያቸው ውስጥ የሚታየውን ክፍተት መስመር የማስያዝ፣በአንዳንድ ክልሎች የሚስተዋለውን ክልል አበጅቶ የመንቀሳቀስና ለፌዴራል መንግሥትም ለመታዘዝ ፈቃደኛ ያለመሆን አዝማሚያ እንዲሁም በክልሎች መካከል ያለውን ችግር ለመፍታት ጠንክረው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡የፌዴራል መንግሥቱ ስልጣኑም መጠቀም መቻል አለበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሆደሰፊነት የሚያልፏቸው ነገሮች ‹‹ህዝብ ለምን ውሳኔ አይወስንም›› የሚል ጥያቄ እንዳያነሳባቸው ከወዲሁ መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
የአርበኞች ግንቦት ሰባት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ስኬቶች የሚሉዋቸው፤ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው፣ተገድበው የነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ስራቸውን እንዲሰሩ መደረጉና የኢትዮጵያን ክብር ከፍ ለማድረግ በተለይም ለሥራ ሄደው ሰብዓዊ ክብራቸው ተደፍሮ የነበሩ ዜጎችን ጉዳይ ላይ ያከናወኑት ተግባር፣የምርጫ ቦርድ መቋቋም፣ መከላከያ ላይ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ለማድረግና የህግ ማሻሻያዎችን ለማድረግ እየተሰራ ያለው ሥራ አበረታች ነው፡፡
ተግዳሮቶቹ ብዙ እንደሆኑ የሚናገሩት አቶ አንዳርጋቸው፤ዘር ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አመለካከትና አደረጃጀት፣ማዕከላዊ መንግሥቱን ለመፈታተን የሚያስችል የክልሎች የራሳቸው ሚሊሻ፣የፖሊስና የደህንነት ኃይል ያላቸው መሆን ተጋዳሮቶች ናቸው፡፡
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የፖለቲካ እስረኞችን መፍታታቸው፣በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችም ለውጥ መጀመራቸው በራሱ ስኬት እንደሆነ በመጠቆም ተግዳሮቶቹ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ለለውጥ ከመምራት ይልቅ ኢህአዴግን ለለውጥ መምራት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ዶክተር መረራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ስነምህዳሩን ለማስፋት ህጎችን ለማሻሻልና ሌሎችም የገቧቸው ቃሎች በስራ ላይ ካልዋሉ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ለውጡ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውንና በሚፈለገው ፍጥነት ለውጡ ካልተተገበረ ወዳልተገባ አቅጣጫ ሊያመራ እንደሚችል ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡
የፓንአፍሪካ ንግድ ምክርቤት ዋና ኃላፊ አቶ ክቡርገና ደስታ በበኩላቸው ከኤርትራ ጋር የፈጠሩት የሰላም ግንኙነት፣ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራቸው እንዲንቀሳቀሱ፣ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣የመናገር፣የመሰብሰብና ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች የሰሯቸውን በመጠቆም፤ በኢኮኖሚው ላይ በተለይም የመንግሥትን ሚና በመቀነስ የግሉን ክፍለኢኮኖሚ በማጉላት በኩል ገና እንዳልተነካ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ከምክር ቤቱ ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጡ ሲሆን፤ የዛሬ አሥር ወር በዚሁ ምክርቤት ተገኝተው ነበር በበዓለ ሲመታቸው ላይ ንግግር ያሰሙት፡፡
ጥር 24/2011
ለምለም መንግሥቱ