ከገብረክርስቶ
ለማሟሻ
እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
የትህነግን ታሪክ መሆን ተከትሎ የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ባለፉት ጥቂት ወራት የዚያን የዘራፊ ቡድን ሀብትና ንብረቶችን በማደን ላይ ይገኛል፡፡ትህነግ ከፈጸማቸው ወንጀሎች ውስጥ አንደኛው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል (Money Laundering) መሆኑን ነው፡፡ እኛም በዚህ ጽሁፍ ስለ መኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ንቃተ-ሕግ የሚያዳብሩ ሃሳቦችን ሰንቀንላችኋል፡፡
የአራጣው ወንጀል
ባሳለፍነው ዓመት የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአንድ የወንጀል መዝገብ ላይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የፌስቡክ ገጽ ለንባብ የበቃው የችሎት ዘገባ እንዲህ ይላል- ንጉሴ ይርጋና ሰብለ ተረፈ የተባሉ ባለትዳሮች የገንዘብ እጦት ገጥሟቸው “እጅ ሲያጥራቸው” አበዳሪ ፍለጋ ከላይ ከታች ሲሉ ይበልጣል ታሪኩን ያገኛሉ፡፡
ይበልጣል ደግሞ ምናለ ዘውዴና ኤልሳ ምናለ የተባሉትን አባትና ልጅ ለባለትዳሮቹ ያገናኛቸዋል፡፡ ምናለም ለጥንዶቹ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በ12 ፐርሰንት ወርሃዊ ወለድ አራጣ ያበድራቸዋል፤ ይበልጣልም የአገናኝነቱን ድርሻ ይቀበላል፡፡
ባልና ሚስት ግምቱ 15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሆነውን በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘውንና በ500 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈውን የጋራ ንብረታቸው የሆነውን ባለሁለት ፎቅ መኖሪያ ቤት ለአራጣው መያዣነት አደረጉ፡፡
በአራጣ ብድር ውሉ መሰረት ተበዳሪዎቹ የብድር ገንዘቡን ከነወለዱ ከሶስት ወር በኋላ ለመመለስ ባለመቻላቸው አራጣ አበዳሪው ምናለና ልጁ ኤልሳ ለአራጣ ብድር ውሉ ሽፋን ለመስጠት “አስደናቂ” ተግባር ይፈጽማሉ፡፡
የተበዳሪዎቹን የ15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር መኖሪያ ቤት በብድሩ ገንዘብ እና በሶስት ወሩ ወለድ በድምሩ በ3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ኤልሳ የገዛችው በማስመሰል በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽህፈት ቤት ከጥንዶቹ ተበዳሪዎች ጋር በመቅረብ የሽያጭ ውል ይፈራረማሉ፡፡
የኋላ ኋላ ተበዳሪዎች በነበራቸው በዕምነት ላይ የተመሰረተ የቃል ስምምነት መሰረት ብድሩን ከነወለዱ መልሰው ቤታቸውን እንዲመልሱላቸው አበዳሪዎቹን ቢጠይቁም “አፍንጫችሁን ላሱ” ይሏቸዋል፡፡ ተበዳሪዎቹም መብታቸውን በሕግ ለማስከበር ወደ ፍትህ አካላት ያመራሉ፡፡
በፍጻሜውም ዓቃቤ ሕግ በአበዳሪዎቹና በደላላው ላይ በአራጣና በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀሎች ክስ መሰረተባቸው፡፡ ፍርድ ቤትም ጥፋተኝነታቸውን በማስረጃ አረጋግጦ የጽኑ እስራትና የገንዘብ ቅጣት ውሳኔን አስተላልፎባቸዋል፡፡
እኛም ይህንን ጉዳይ እንደመነሻ ይዘን በዚህ ጽሁፋችን በወንጀል የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ከማቅረብ ወንጀል ጋር በተያያዘ ንቃተ-ሕግን የሚያዳብሩና የወንጀሉን አስከፊ ገጽታ የሚያሳዩ መሰረታዊ ጉዳዮችን እናብራራለን፡፡
በወንጀል የተገኘን ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ወንጀል በጥቅሉ
በእንግሊዝኛ ቋንቋ Money Laundering የተሰኘው ድርጊት ሰፊ ጉዳዮችን የያዘ ነው፡፡ በአገራችን የመኒ ላውንደሪንግ ድርጊት ወንጀል ተደርጎ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕግ የተደነገገው በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ ነው፤ በአንድ አንቀጽ ብቻ ማለት ነው፡፡
ይሁንና ድርጊቱ እየተወሳሰበና የአስጊነቱ ጥላ እየከበደ በመምጣቱ በ2005 ዓ.ም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያለመ አዋጅ ቁጥር 780/2005 ወጥቷል፡፡
በአዋጁ መግቢያ ላይ ሰፍሮ እንደምናነበው ይህ ወንጀል የደህንነት ሥጋት ከመሆኑም በላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ የተረጋጋ፣ ግልጽነት ያለው፣ ጤናማና ቀልጣፋ እንዳይሆን የሚያደርግ ከባድ ወንጀል ነው፡፡
በዚሁ መነሻ ነው እንግዲህ የተለያዩ አካላትን ድርሻና ኃላፊነት ባካተተ መልኩ የተሟላና ሁሉን አቀፍ የህግ ማዕቀፍ በአዋጅ መልክ ሊዘጋጅ የቻለው፡፡
በአዋጁ መሰረት በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ሥር ከሚካተቱት ድርጊቶች ውስጥ የመጀመሪያው ንብረቱ የወንጀል ፍሬ መሆኑን በማወቅ ወይም ማወቅ እየተገባ በቸልተኝነት የንብረቱን ሕገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን ወይም አመንጪውን ወንጀል የፈጸመውን ሰው ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ለማድረግ ንብረቱን መለወጥ ወይም ማስተላለፍ ነው፡፡
ከላይ በተገለጸው የአራጣ ጉዳይ ምናለ የተባለው ግለሰብ በአራጣ ምክንያት የተገኘውን ቤት ይህንን ሕገ-ወጥ ምንጩን ለመደበቅ ወይም ለመሸፈን በሚል ልጁ ኤልሳ ምናለ ቤቱን ከተበዳዮቹ የገዛች እንዲመስል በማድረግ የሽያጭ ውል እንዲፈራረሙ አድርጓል፡፡
ኤልሳ የተባለችው ልጁ በበኩሏ የመኖሪያ ቤቱ ከአራጣው ጋር በተያያዘ የተገኘ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀች ይህንኑ ሕገ ወጥ ምንጭ ለመደበቅ ወይም አመንጪ የሆነውን የአራጣ ወንጀል የፈጸመውን አባቷን ከሕግ ተጠያቂነት ለማስመለጥ የቤቱ ገዥ በመምሰል በሽያጭ ውል ላይ በመፈራረም የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ፈጽማለች፡፡
ሌላው በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ሥር የሚመደብ ድርጊት ንብረቱን መረከብ፣ በይዞታ ሥር ማድረግ ወይም መጠቀም ነው። እነዚህን ተግባራት በመፈጸም መሳተፍ፣ ለመፈጸም ማደም፣ መሞከር፣ መርዳት፣ ማመቻቸት ወይም እንዲፈጸም ማማከርም እንዲሁ ወንጀል ነው፡፡
በአጠቃላይ ከእነዚህ የአዋጁ ድንጋጌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ታዲያ የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል በቁሙ ትርጓሜ የተሰጠው ባይሆንም ቅሉ፤ የተጠቀሱት አድራጎቶች የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀሎች ተብለው እንደሚያስቀጡ ነው፡፡
የአመንጪው ወንጀል ፍርድ ማግኘት ወይም ያለማግኘት እሰጥ አገባ
ከላይ በተብራሩት የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል አድራጎቶች ውስጥ “የወንጀል ፍሬ” እና “አመንጪ ወንጀል” የሚሉ ሁለት ፍሬ ነጥቦችን እናገኛለን፡፡
በአዋጁ በተሰጠው እንድምታ መሰረት የወንጀል ፍሬ ማለት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከአመንጪ ወንጀል የተገኘ ማንኛውም ገንዘብ ወይም ንብረት ማለት ነው፡፡ አመንጪ ወንጀል ማለት ደግሞ ማንኛውም ለወንጀል ፍሬ ምንጭ የሆነና ቢያንስ አንድ ዓመት ቀላል እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡
በዚሁ መነሻ አንድ ሰው በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል የሚጠየቀው በአንድ በኩል አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ እስራት የሚያስቀጣ አመንጪ ወንጀል ሲፈጽምና ከዚሁ ወንጀልም የገንዘብ ወይም የንብረት ጥቅም ሲያገኝ ነው፡፡
ከላይ በመግቢያችን በጠቀስነው የወንጀል ጉዳይ አመንጪ ወንጀል የሚባለው አራጣው ሲሆን፤ የወንጀሉ ፍሬ ደግሞ የመኖሪያ ቤቱ ነው፡፡ የአራጣ ወንጀል በወንጀል ሕጉ እስከ አምስት ዓመት እስራት የሚያስቀጣ በመሆኑ እና የወንጀል ፍሬ ለሆነው ቤት የመገኛ ምንጭ በመሆኑ ተከሳሾቹ ከአራጣው በተደራቢነት በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀልም ተቀጥተዋል ፡፡
እዚህ ላይ አከራካሪው ጉዳይ የንብረቱ ምንጭ ሕገ-ወጥ መሆኑን ለማስረዳት በተከሳሹ ላይ በአመንጪው ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ መሰጠቱ የግድ እንደማያስፈልግ በአዋጁ መደንገጉ ነው፡፡ ይህ ማለት ለማሳያነት በተነሳንበት ጉዳይ በመኒ ላውንደሪንግ ክስ ምንጩ የተደበቀውን መኖሪያ ቤት ሕገ-ወጥ ምንጭ ለማስረዳት በተከሳሾቹ ላይ በአራጣው ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ እንዲሰጥ አይጠበቅም እንደማለት ነው፡፡
ሕግ አውጪው ይህንን ድንጋጌ በሚያካትትበት ወቅት በአመንጪው ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ የማይሰጥባቸውን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት እና ፍርድ ባለመሰጠቱ ምክንያትም በወንጀል ፍሬው ምክንያት በግለሰቦች መብትና በኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡
ለማሳያነት አመንጪው ወንጀል በይርጋ ቢታገድና ክስ መስርቶ የጥፋተኝነት ፍርድ ማሰጠት ባይቻል የመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ክስና ቅጣት ባይርጋ የማይታገድ ወንጀል በመሆኑ ክሱ ራሱን ችሎ ተመስርቶ እንዲቀጥል እድል የሚሰጥ ድንጋጌ ነው፡፡ በተጨማሪም በአመንጪው ወንጀል የተከሰሰ ሰው ቢሞትና ክሱ ቢቋረጥ በግብረ-አበሩ ላይ የቀረበው የመኒ ላውንደሪንግ ክስ ግን ራሱን ችሎ እንዲቀጥል ይደረጋል፡፡
በመኒ ላውንደሪንግ ክስ የንብረቱ ምንጭ ሕገ-ወጥ መሆኑን ለማስረዳት በተከሳሹ ላይ በአመንጪው ወንጀል የጥፋተኝነት ፍርድ መሰጠቱ የግድ አይደለም ሲባል ግን የንብረቱ ምንጭ ሕገ-ወጥ ስለመሆኑ ማስረጃ አይቀርብም ማለት እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ማስረጃ በማቅረብና የንብረቱ ምንጭ ሕገ-ወጥ መሆኑን በማሳየት በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ጥፋተኛ ማስባል ይገባል እንጂ፡፡
ነገር ግን አንድ ሰው በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብ ወንጀል ሲከሰስ የክሱ መነሻ ሆኖ የሚቀርበው አመንጪ ወንጀል መኖሩና ከዚህም ወንጀል ገንዘብ መገኘቱ ተጠቅሶ ይህ የተገኘው ሕገ-ወጥ ገንዘብም ሕጋዊ እንዲመስል በአዋጁ የተጠቀሱት እነዚህ ድርጊቶች ተፈጽመዋል በሚል ነው፡፡
እናም በአመንጪው ወንጀል ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ሳይሰጥ እንዴት በመኒ ላውንደሪንግ ወንጀል ሊከሰስ ይችላል የሚል ክርክር መነሳቱ አይቀርም፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2013