አዲስ አበባ፤ 1 ሚሊዮን 55ሽህ 286 ብር በላይ ግብይት ይካሄድበታል ተብሎ የሚጠበቀው ሀገር አቀፍ አነስተኛና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ኤግዚቢሽንና ባዛር ትናንት በባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ተመርቆ ተከፈተ፡፡ 129 አቅራቢዎች ይሳተፉበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ እንደገለጹት፤ በባለሥልጣኑ ቅጥር ግቢ የተከፈተው የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ዙር ሀገር አቀፍ አነስተኛና ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ኤግዚቢሽንና ባዛር‹‹የተቀናጀ የገበያና የግብይት ድጋፍ ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ውጤታማነት›› በሚል መሪ ቃል ከጥር 23 እስከ 30 ድረስ ይካሄዳል፡፡
ከመላው የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ 85 አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች፣36 ከአጋር አካላት የተመለመሉ ኢንዱስትሪዎች እና ሥምንት በማኑፋክቸሪግ ኢንዱስትሪው ቀጥተኛ ድጋፍ ትስስር ያላችው ተቋማት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤- በኤግዚብሽንና ባዛሩ በርካታ ምርቶች እና አምራቾች በቀጥታ ፊት ለፊት ይገናኙበታል፡፡ በዋናነትም፤-የባህልና ዘመናዊ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርት ውጤቶች፣የቆዳ አልባሳትና የቆዳ ምርት ውጤቶች፣ባህላዊ የእደ- ጥበባትና ቅርጻ- ቅርጽ ሥራዎችና ውጤቶች፣ የብረታብረትና የእንጨት ሥራ ውጤቶች፣የአግሮ ፕሮሰሲንግ ምርቶች፣የኬሚካልና የማዕድን ውጤቶች፣ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና የፈጠራ ሥራዎች ለግብይት ይቀርባል፡፡ ከ20 ሺህ በላይ የሚሆን የህብረተሰብ ክፍል ይሳተፍበታል፤በዚህም ከአንድ ሚሊዮን 55 ሺህ 286 ብር ግብይት እንደሚፈጸም ገልጸዋል፡፡
በባዛርና ኤግዚቢሽኑ አገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ለምታደርገው ሽግግር በተግባር እየተከናወነ ያለውን ጥረት ዜጎች በአይናቸው ያያሉ ያሉት አቶ አስፋው፤ በቀጣይም በሰፊው በአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትዎች ዘርፍ ተደራጅቶ በማምረት፣ ምርቶችን በመሸመት እና የገበያ ትስስርን በመፍጠር የራሣቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዲችሉ ያደርጋል፡፡ የቴክኖሎጂ ልምድ ሽግግር ያግዛል፤የገበያ ትስስር ይፈጥራል፤ ሌሎች በርካታ ፋይዳዎችን ያስገኛል ሲሉ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አስፋው አበበ ተናግረዋል፡፡
ሙሀመድ ሁሴን