አስቴር ኤልያስ
ያለመከሰስ መብታቸው ሳይነሳ ሙስና በሚል ሰበብ ወደ ወህኒ በተጋዙበት ወቅት ፈታኝ የሆኑ ጊዜያትን በማረሚያ ቤቱ ለማሳለፍ ተገደዋል፡፡ በቆይታቸውም የወገብ ህመም አጋጥሟቸው በብዙ አስቃይቷቸዋል፡፡
በማረሚያ ቤቱ በነበሩበት ወቅት ግራ ቀኙን እንዲሁም አሻቅበው ቢመለከቱም ከጠራው ሰማይ ውጭ አንድም ነገር ከጎናቸው ባለመኖሩ የሰው ያለህ አሰኝቷቸው እንደነበር አይዘነጉም፤ ቤተሰብም እንዲጠይቃቸው አለመፈቀዱን ያስታውሳሉ፤ የዛሬው የወቅታዊ ጉዳይ እንግዳችን የቀድሞው የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አባተ ኪሾ፡፡
አቶ አባተ በወቅታዊ ጉዳይና ቀደም ሲል ስለታሰሩበት ሁኔታ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉበትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅረን አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
አዲስ ዘመን፡- መንግስት ከአንድ ወር በፊት በትግራይ ክልል ሰላም የማስከበሩን ሂደት አጠናቆ ፊቱን ወደልማት መመለሱ ይታወቃልና በሰላም ማስከበሩ ሂደት ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ አባተ፡- አጠቃላይ ፖለቲካ የፈጠረው ተጽዕኖ ከሆነውና 27 ዓመት ሲመራበት ከነበረው የዚህች አገር ፖለቲካ በህወሓት የበላይነት እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ሰዎች በእያንዳንዳቸው ደጃፍ እስኪደርስ ጠብቀዋል እንጂ በአምባገነን አሰራርና በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ እጅግ የከፉ ነበሩ፡፡ በእርግጥ ርዕዮተ ዓለሙ በስብሶ እስኪወድቅ ጊዜ ስለተጠበቀ እንጂ ያበቃለት ጉዳይ ነበር፡፡
ይህ ርዕዮተ ዓለም ከመነሻው ሲታይ አብዮታዊ ዴሞክራሲ የማርክሲዝም ሌኒንዝም ጽንሰ ሐሳብ ሆኖ የመጣው ግን መልኩን ቀይሮ ነው፡፡ ሰው ብዙም ስላልተረዳውና አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚልም የተባበሰው ቅባት ስለነበረውና ሽፋን ስለተሰጠው መለየት ስላልቻለ እንጂ የአንድ ቡድን አምባገነንነትና የአንድ ፓርቲ የበላይነት ብቻ እንደነበረ ነው ማስተዋል የሚቻለው፡፡ ለዚህ ቁመናው ማሳመሪያ ይሆኑ ዘንድ በአምሳያው የተፈጠሩ ፓርቲዎች ነበሩ። እነዚህ የተፈጠሩ ፓርቲዎችም ብዙ እርባና ያላቸው ሳይሆኑ የአምባገነኑን ሥርዓት ሊነኩት እንዳይችሉ ቀይ መስመር ተሰምሮላቸው ነበር የቆዩት፡፡
እንዲያም ሆኖ የፓርቲው የመጨረሻ የመበስበሱ ደረጃ ላይ በመድረሱ በወቅቱ የተጻፈውንና ራሱም የበላይ ነው ብሎ ያስቀመጠውን ህገ መንግስት ያለማክበሩን በተግባሩ አረጋግጧል፡፡ ክልሉ ራሱ መንግስት ሆኖ በተለይ ደግሞ በዝግጅት፣ በአዕምሮና በማቴሪያልም ራሱን አሰናድቶ ሰራዊቱን ወደማጥቃት ነበር የገቡት፡፡
በዚህም የመንግስትን ትዕግስት ከመፈታተን አልፈው ያስጨረሱት ከመሆናቸውም በተጨማሪ በመንግስት የትዕግስት መብዛት የተነሳ ለምን በሚል በሰዎች አዕምሮ ሁሌም ጥያቄ እስከሚነሳ ድረስ መዝለቁ ይታወቃል። መንግስት በወቅቱ ማድረግ የሚገባው ነገር ነበር ወይ ብለን ስንጠይቅ አይችልም ነበር፡፡ አሁን በደረሰበት ደረጃ ደግሞ ኪሳራውን በቀነሰ ሁኔታ ብዙ ማህበረሰብም ሳይጎዳ መጠናቀቁ የመንግስትን ዝግጁነት በከፍተኛ ደረጃ እንዳደንቀው አድርጎኛል፡፡
ነገር ግን ቀሪው የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ በአጭር ጊዜና ሰዎችም በጠበቁት ልክ እየሄደ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ምክንያቱም ለብዙ ጊዜ ያንያህል የተደራጀ ኃይል በዚህ ፍጥነት ህግን በማስከበር እዚህ ደረጃ የማድረስ ጉዳይ በእኔ እምነት አላስበውም ነበር፡፡ እንዴት ቢባል የአንድ ወር ጊዜ በጣም ትንሽ ነው ብዬ ነው የማስበው። እንዲያውም ጉዳዩ ከዛም ጊዜ በላይ የሚፈጅ ነበር፡፡ መንግስት ግን በተደራጀና በተቀናጀ ሁኔታ ስራ ሰርቷል፡፡
ከዚህ የተነሳ ተጠቃሚዎቹ ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ከአምባገነኑ ቡድን ተጠቃሚ እንዳልሆነ ይታወቃልና ቡድኑ በመወገዱ ለእነሱ ፋይዳው ላቅ ያለ ነው፡፡ አምባገነኑ ቡድንም ህዝቡ ከእርሱ ጋር ያለ መስሎትም አስቦ የነበረ ቢሆንም አለመሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ለዚህም ነው ከህግ ማስከበሩ ጎን ለጎን የወደሙ መሰረተ ልማቶችን በፍጥነት የመገንባትና ለህዝቡ አግልግሎት እንዲሰጥ የማድረግ ስራ እየተሰራ ያለው፡፡ በዚህም መንግስት በተገቢው መንገድ እየተጓዘ ነው የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ በላይ ያለው ቀሪው ስራ የተመጣበትን አካሄድ ጠብቆ ይፈጸማል በማለት አስባለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ችግሩ ያለው በትግራይ ክልል ብቻ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ መታየት ያለባቸው ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎችም ጭምር ናቸው። የፖለቲካው ድፍድፍ በአግባቡ ሳይጠራ የጠጣ ኃይል እንዳለ ይሰማኛል፡፡ በመሆኑም እሱ ስካር እስካሁን ያለቀቀው አለና የሚሰራውን አያውቅም።
ምክንያቱም የበሰበሰው ርዕዮተ ዓለም አሁንም ድረስ አገሪቱን በማመስ ላይ ነው፡፡ የዚህ ርዕዮተ ዓለም ተከታዮችና የዚህ የበሰበሰውን ርዕዮተ ዓለም ለማሳካት የሚንገታገቱ ቡድኖች በየቦታው አሉና አንድን አካባቢ ብቻ ሳይሆን መመልከት ያለብን የበሰበሰው ርዕዮተ ዓለም ቫይረሱ በብዙ ቦታ የተዳረሰ ከመሆኑ አኳያ ሁሉንም በአግባቡ በመፈተሽ ቫይረሱን ማምከን የግድ ይላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለምሳሌ መንግስት የት የት አካባቢ ትኩረት ቢያርግ መልካም ነው ይላሉ?
አቶ አባተ፡– ችግሩ ያለው ሁሉም የአገሪቱ ክፍል ነው ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያልደማ፣ ያልቆሰለና ወገኑ ያልሞተበት ሰው የለም። ያልተሰደደ፣ የህግ የበላይነት ያላጣ እና ሌላም ሌላ መከራ ያልደረሰበት አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ ያልተጎዳ አካል የለም፡፡ ቫይረሱ በሁሉም ስፍራ ነበርና ሁሉም ተጎድቷል፡፡ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ የተነሳ አፋችሁን በማስክ ሸፍኑ እንደሚባለው ሁሉ የቫይረሱ ችግር ያለበትንና የመፍለቂያውን ቦታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲያገኝ ማድረጉም ተገቢነት ያለው ነው፡፡ ቫይረሱ ተፈናጥሮ የሄደበት አካባቢ በሙሉ መፈተሽም ይኖርበታል፡፡
ሌላው ቀርቶ አሁንም መንግስት በውስጡ ባሉት አካላትም ፍተሻ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም አሁንም በስልጣኑ ላይ ያሉ አካላት ያንን የበሰበሰበ ርዕዮተ ዓለም ሲጋቱ ከርመው በአንድ ጀምበር ለማውጣት የተቸገሩ ይመስላሉ፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ በነበረው ርዕዮተ ዓለም መገለባበጥ የተለመደ ነው፡፡
በነገራችን ላይ አንድ ነገር ግልጽ ላድርግልሽና ቀድሞ በነበረው ርዕዮተ ዓለም የነበረው አካሄድ ውሽት መናገር መቻልና አድርባይ መሆን መቻል በሥርዓቱ ውስጥ ለመቆየት የሚያስችል መንገድ ነው። ስለዚህ አሁንም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉትን የመንግስት አካላት ከዚህ አይነቱ አካሄድ ነጻ ማድረግ የግድ ይላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የህወሓት ጽንፈኛ ቡድን ሲያርስ የነበረውን ግፍ እርስዎ ቀደም ሲልም ያውቁት እንደነበር ይታሰባልና ሴረኛነቱን እንዴት ይገልጹታል?
አቶ አባተ፡– እንደሚታወቀው ኢህአዴግ የአራት ብሄራዊ ድርጅቶች ውህድ ነበር፡፡ አፈጣጠሩ ደግሞ የተለያየ ነው፡፡ ህወሓት፣ ብአዴን፣ ኦህዴድ እና ደኢህዴን እንደየቅደም ተከተላቸው ሲሆን፣ ከአራቱ ሶስቱ ድርጅቶች በስም ይኑሩ እንጂ ተጽዕኖ ፈጣሪው ህወሓት ነው፡፡
ምክንያቱም ቀደም ሲል የነበረው ከጫካ ጀምሮ ተጽዕኖ ስፈጥር የነበርኩት እኔ ነኝ፤ ሌሎቹን የፈጠርኳቸው በአምሳያዬ ነው የሚል አስተሳሰብ ይዞ ነው በሌሎቹ ላይ ሲያቅራራ የነበረው፡፡ ቀሪዎቹም ድርጅቶች እንደተከታታይነታቸው ለእሱ እውቅና ሰጥተው ሲንቀሳቀሱ ነው የነበረው፡፡
ስለዚህም እኩል ነን የሚል አስተሳሰብ አልነበራቸውም፡፡ የስልጣን ሃይሉም ይመነጭ የነበረው ከህወሓት ነው፡፡ እኔ እስከቆየሁበት 1993 ዓ.ም ድረስ ያለውን አካሄዱ በአግባቡ ማየት ችያለሁ፡፡
ሌሎቹም ቢሆኑ ፌዴራል በሚል አደረጃጀት ክልል ተሰጣቸው እንጂ ክልሎቹ በህወሓት ቁጥጥርና አመራር ስር ብቻ ነበር የሚንቀሳቀሱት፡፡ ሌላው ቀርቶ ኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ክልሎችን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ በእነዚህ በሶስቱ ክልሎች የፖለቲካውንም ሆነ የመከላከያውን ክንፍ ከደህንነቱ ባሻገር ምንም እንኳ መዋቅሩ አለ ተብሎ ቢታሰብም በግልጽ ጠርንቆ ይዞ የነበረው ይኸው ህወሓት ነው፡፡ እነዚህ አካላት በምርጫ ውስጥ አይሳተፉም፤ ነገር ግን ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸው ከተመረጡትም በላይ ነበር፡፡
ቀሪዎቹ አጋር ተብለው የተፈረጁ ክልሎችም በሁሉም ዘርፍ ቢሆን ከሶስቱ ብሄራዊ ድርጅቶች በላይ ተጽዕኖ ሲደረግባቸው የቆዩ ናቸው፡፡ በውስጥ የነበሩ ፓርቲዎች ስለኢህአዴግ እንዲዘምሩ እና ከኢህአዴግ ዓላማ ዝንፍ እንዳይሉ የሚደረጉ ነበሩ። ወደዘጠኙም ክልሎች ተወካይ ይላክ የነበረው ከህወሓት እንጂ ከደቡብ ወይም ከኦሮሚያ አሊያም ከአማራ ክልል አንድም ተወካይ ቢሆን ወደ ትግራይ የሚላክ ሰው አልነበረም፡፡ ከትግራይ ግን ወደ ሁሉም ከልል ተልኳል፡፡ ፌዴራሊዝም የስም እንጂ የተግባር ላለመሆኑ ይህ ተግባራቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡
ተጽዕኖ መኖሩን ሊያሳይ የሚችል አንድ ምሳሌ ልጥቀስልሽ በወቅቱ እኔ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ነበርኩ፡፡ ጥፋት ባጠፋ መጠየቅ ያለብኝ በክልሉ በተዘረጋው ሥርዓት ነው፡፡ በ1993 ዓ.ም ህወሓት ሁለት ቦታ ሲከፈል የመለስን ቡድን አልደገፍክም በሚል ነበር ወደእስር የተጋዝኩት።
እዛም እያለሁ የአንጃ ደጋፊ ተብዬ ተፈርጅኩ። ምክንያቱም ደግሞ በ1987 ዓ.ም በክልሉ ውስጥ ያለው ስራ ተፈትሾ እኔ 1993 ዓ.ም ስታሰር 1987 ዓ.ም የፌዴራል መንግስት የገዛውን የመኪናዎች ግዥ፣ መገዛቱን የሚያሳይ ቢጫ ካርድ ከፋይላቸው ውስጥ አውጥተው ከሰሱኝ፡፡
ስታሰር ሌላው ቀርቶ በደቡብ ክልል ምከር ቤት ያለመከሰስ መብቴ ሳይነሳ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱም ሆነ ዳኛው የዚሁ የህወሓት ነው፡፡ በወቅቱም ችሎቱን ሲመራ ለነበረው ዳኛ “እኔ እኮ የታሰርኩት ያመከሰስ መብቴ እንኳ ሳይነሳ ነው” ብዬ ስጠይቅ ፖሊሱን ዞር ብሎ ‹ያመከሰስ መብቱ ያልተነሳለትን ሰው እንዴት አስርክ› ሲል ጠየቀው። የገረመኝ የፖሊሱ መልስ ነበር፤ ያለውም ‹መነሳታቸውን በዜና ሰምቻለሁ› ነበር ያለው፡፡
ይህንን ጉዳይ ዳኛው ሲሰማ የህዝብን እንደራሴ ልተከስ አትችልም ብሎ በማስቆም ፖሊሱን ማሰናበት በተገባው ነበር፡፡ ነገር ግን ዳኞቹ ስለሁሉም ጉዳይ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግስት መመሪያ ስለሚወስዱ ፍትህ የሌለበት ስራ ነው ሲሰራ የሚውሉት፡፡ ዳኛውም ቢሆን የፖለቲካ ተሽዋሚ ነው፡፡
በመሆኑም የሚያፈጽመው የፓርቲውን ተልዕኮ ነው። ይህን ሁሉ ግፍ ሲፈጽሙ የነበሩ ዳኞች ዛሬ ላይ ሆነው ምን አይነት ስሜት ሊሰማቸው እንደሚችል አላውቅም። ስለዚህ ይህ ያለፈው አይነት ቫይረስ አሁንም ቀጣይነት እንዳይኖረው ሁሉም ስፍራ ሊፈተሽ ይገባል፡፡ አለዚያ ግን የፌዴራሊዝሙን ጽንሰ ሐሳብ ስራ ላይ ማዋል አይቻልም፡፡
እኔ እውነተኛ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ይጠቅማል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህ ተግባራዊ ቢደረግ መልካም ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ተስፋ የማደርገው ብልጽግና ሆነ ሌሎች ፓርቲዎች ይህን በአግባቡ ቢያዩት የተሻለ ነው፡፡ ከዛ ውጭ ግን ኢትዮጵያዊነት ምንም ነው፡፡
እውነተኛ ፌዴራሊዝም ባለመኖሩ በተለይ ከ30 ዓመት ወዲህ ሰው ሁሉ ተጠራጣሪ ሆኗል፡፡ ክልል ከክልል ቀርቶ ቀበሌ ከቀበሌ ተጠራጣሪ ሆኗል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ከ80 በላይ የሆነ ብሄር ብሄረሰብ ሆኖ ሳለና በተለያየ ቦታ ከተለያየ ብሄር ጋር በስብጥር የምንኖር ሰዎች ሆነን ሳለን ያለፉት ዓመታት የተረጨው ቫይረስ በእጅጉ ህዝቡን ጎድቶታል።
ቫይረሱን ለማጥፋት ደግሞ መላ ህዝቡን ያሳተፈ መፍትሄ ይጠይቃል፡፡ ዋጋ መክፈልንና መተባበርንም የግድ ይላል፡፡ ለዚህም ነው እውነተኛ ፌዴራሊዝም ለዚህች አገር አስፈላጊ ነው የሚል እምነት ያለኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንዲያው ግን በወቅቱ የእርስዎ መታሰር ምስጢሩ ምንድን ነው? ሲባል የነበረው ከሙስና ጋር የተያያዘ ነውና እዚህ ላይ የጠራ መረጃ እንዲኖር የሚሉት ነገር ካለ? ለመታሰርዎ እንደ እነ አቶ ቢተው በየነ አይነት ሰዎች ሚና ነበራቸው ብለው ያስባሉ?
አቶ አባተ፡- በወቅቱ በወታደራዊ ክንፉ በኩል የነበረው ጄኔራል ኃየሎም ነው፡፡ እሱ ከተነሳ በኋላ የተተካው ሌላ ሰው ነው፡፡ ወታደራዊ ክንፉ ቀጥታ በፖለቲካው ሂደት ውስጥ ሳይሆን የሚገባው በጸጥታውና መግባት በሚገባበት ቦታ ነው፡፡ ይሁንና በፖለቲካው ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥሩት ናቸው ለእያንዳንዱ ቦታ የተመደቡት፡፡
በእርግጥ ቢተው ነበር እኛ ክልል የቆየው። በሚደረጉ መደበኛ ስብሰባዎች ላይ አብሮን ይሳተፋል። ነገር ግን ከፌዴራል መንግስት ተወካይ በስብሰባው ላይ ይሳተፋል የሚል አሰራር የለም፡፡ ህግ ባይኖርም ግን በምንወያየውና በምንወስነው ነገር ላይ ሁሉ አብረውን ነው ሲወስኑ የነበሩት፡፡
ምናልባትም አራት ኪሎ የመጀመሪያው መረጃ የሚደርሰው ከእነዚህ አካላት ነው፡፡ ይህ በደቡብ ክልል ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ክልሎች ላይ ተመሳሳይ ተወካዮች እንዳሉ አውቃለሁ፡፡
ቀደም ሲል ልጠቅስልሽ እንደሞከርኩት ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግስት በመጀመሪያ እርስ በእርሳቸው መበላላት የጀመሩት ራሳቸው ህወሓቶች ናቸው፡፡ የእነሱ ዳፋ ለእኛም ተርፏል፡፡ ምክንያቱም እነሱም ችግር ውስጥ ያገባቻቸው የጫካዋ የማርክሲዝም ሌኒንዝም መሰረት አድርገን ቁመናችንን እንፈትሽ ብለው መወያየት ሲጀምሩ አንዱ ‹አንተ ነህ ጥፋተኛ› ሲል ሌላው ደግሞ ‹አንተ ነህ ጥፋተኛ› መባባል ይጀምራሉ፡፡ ተጽዕኖ ፈጣሪው ፓርቲ ውስጥ ችግር ስለነበር ጎልቶ በመውጣቱ ለሁለት ተከፋፈሉ።
በሌሎቹ ሶስቱ ብሄራዊ ድርጅት ውስጥ በሂደት በጣም ብዙ ሰው ነው ሲባረርና ሲከፋፈል የቆየው። በዛ ሂደት ቆይቶ ነው እዛ ደረጃ ላይ የተደረሰው። እነሱ ዘንድ ግን ለሁለት ተከፈሉ ተብሎ ትልቅ ቀውስ መፈጠሩ በራሱ ምን ያህል ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆናቸውን የሚያሳይ እንደሆነ ነው የምረዳው።
ከዛ ውስጥ ግን ሁለት ቦታ የመከፈላቸው ሁኔታ ቀውስ ፈጥሮ ምን ያህል በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተጽዕኖ የፈጠሩ ስለመሆናቸው ማስታወስ ይቻላል። በዚህ በመከፈላቸው ሂደትም ‹አንተ ፈጥነህ እኔን አልደገፍክም› የሚል አተካራ ሲያነሱ የነበረ ሲሆን፣ የመለስን ቡድን የደገፈው ፈጥኖ መዳን ቻለ፡፡ ብአዴኖች ፈጥነው የመለስ ደጋፊ በመሆናቸው ዳኑ። የተወሰኑ የኦህዴድ አባላት እና በደቡብ ላይ ነበር ጉዳዩ የበረታው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በወቅቱ የማን ደጋፊ ነበሩ?
አቶ አባተ፡– በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽልኝ፤ እኔ እውነቱን መናገር ነው የምፈልገው፡፡ በወቅቱ ሲጠይቁኝ የሁለታችሁም ደጋፊ አይደለሁም ብዬ ብል ሰሚ አጣሁ። መለስ ማታ ላይ አንድ ሶስት ያህል ጄኔራሎችን ልኮብኝ እኔን ደግፍ አለኝ፡፡
‹እኔ መለስን ነው አሊያም እነስዬን ነው የምደገፈው ብዬ ማለት አሁን አልችልም፤ ሐሳቤን ለማወቅ ከፈለጋችሁ ግን በመድረክ ስንገናኝ ስብሰባ ላይ እገልጻለሁና እስከዛ ታገሱ› አልኳቸው፡፡ ምክንያቱም ኳሱ ያለችው በሜዳችሁ ውስጥ ነውና በመጀመሪያ እናንተ ተስማሙ እንጂ ወደ እኔ የምትመጡት ለምንድን ነው ስልም ተናገርኩ።
አገርን ሊወክል በሚችለው መድረክ ላይ መገናኘታችን አይቀርም፤ በዚያን ወቅት ያላችሁን ልዩነት ማቅረብ ይቻላል፡፡ እኔም የዚያን ጊዜ የሚሰማኝን አቋም እገልጻለሁ ነበር ያልኳቸው።
ነገር ግን ቀደም ብሎ የእኔ ደጋፊዎች አደርጋቸዋለሁ ብለው ያሰባቸውን አሰልፎ ስለጨረሰ ቀጥታ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እና አቶ አባተ ኪሾ መለስን አልደገፉም በሚል ነው ከውስጣቸው ተቆርጦ ከወጣው ቡድን ጋር የደመሩን። ከእነሱ ጋር አትደምሩን ብንልም ማንም ሊሰማን አልቻለም።
አንዴ ትዝ ይለኛል፤ በአሁኑ ወቅት በህይወት የሌሉት ዶክተር ነጋሶ ሁሌም የለውጥ ወር በሆነው መጋቢት 16 ቀን 1993 ዓ.ም የመጀመሪያውን ስብሰባ ተሰብስን ባለንበት ወቅት አቶ መለስን ‹‹አሁንስ ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያምን መሰልከኝ›› ያሉትን አስታውሳለሁ፡፡
በወቅቱ አንዱ ተባራሪ ሌላው አባራሪ በመሆን ሁለት ቦታ ተከፍለው ነበር የመጡትና፡፡ በዚህም እያንዳንዳቸው ደጋፊ ፍለጋ ነበር የመጡት። በዕለቱ ወደስብሰባ ያቀናሁትም ብዙዎች መለስን አይደግፉትም በሚል መንፈስ የነበረ ቢሆንም ሁሉም ግን የመለስ ደጋፊ ሆኖ መቀመጡን የተረዳሁት ከረፈደ ነበር። ምክንያቱም ሁሉም የየራሱን ያለመደገፍ አቋም ይዞ ወደ ስብሰባ እንደሚገባ ነበር የጠበቅኩት፡፡
እንዲያም ሆኖ በዛ መድረክ የመለስ ደጋፊዎች አይደላችሁም ተብለን ተፈረጅን፡፡ በወቅቱ ደግሞ አቤቱታ ልታቀርቢ የምትችይበት ቦታ ከፈጣሪ ውጭ በፍጹም አልነበረም፡፡ እኔ የማንም ደጋፊ አይደለሁም ብትዪ የሚሰማሽ የለም፤ ቀድመሽ ንስሃ ለምን አልገባሽም ትባያለሽ፡፡
ንስሃ ለመግባት የሚያስችል የኃጢአት ስርዬት እነርሱ ዘንድ ስለሌ በምድር መኖር የሚያስችለንን እድሜ እንኖራለን፤ ከገደላችሁንም ሞትን እንመርጣለን ብለን በወቅቱ በነበረው የስብሰባ መድረክ ተጋፍጠን ወጣን፡፡ ‹‹ዋጋችሁን ታገኛላችሁ›› የሚል ዛቻም ነበር፡፡ በወቅቱ ግን ዶክተር ነጋሶ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ስለነበሩ ሊያስሯቸው አልቻሉም፡፡እኔን ግን ወደወይኒ ወረወሩኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ትናንት የነበረው የህወሓት የበላይነት ዛሬም ለማስቀጠል በሚደረገው ጥረት የአገር መከላያ ሰራዊትን እስከመተናኮል አድርሷቸዋልና ዛሬም ድረስ ርዝራዡ እንዳልጠፋም የተለያዩ ማሳያዎች አሉ፤ ካልዎት ተሞክርዎ በመነሳት ምን ይመክራሉ?
አቶ አባተ፡– እኔ ርዕዮተ ዓለሙ አበቃ ብዬ የማስበው በ1993 ዓ.ም ላይ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ሲደረጉ የነበሩ ተሃድሶዎች ለርዕዮተ ዓለሙ ምንም ህይወት ሊዘሩለት እንዳልቻሉ ነው የተረዳሁት፡፡ ተሃድሶ ቢባል እንደገና ደግሞ ስሙን ቀይረው ዳግም ተሃድሶ ቢሉ በጭራሽ ሊታደስ አልቻለም፡፡
ነገር ግን የጉልበት አካሄዱ አቻ አይገኝለትም ነበር፡፡ ምክንያቱም መከላከያና ደህንነቱ ከውሸታም ካድሬ ጋር ተደምሮ ርዕዮተ ዓለሙን ወደፊት ለማስኬድ ከፍተኛ ሙከራ ሲያደርጉ ነበር። በዚህ አካሄዳቸው እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ህልፈት ድረስ ትንሽ ህይወት አግኝቶ ነበር፡፡ በኋላ ላይ ግን ሁሉም ነገር ከእጃቸው ቀስ እያለ መውጣት ጀመረ፡፡
በእርግጥ የርዕዮተ ዓለሙ ጠንሳሹም መለስ ነበሩ፤ ትልቅ ድርሻም የነበራቸው እርሳቸው ነበሩ፡፡ መለስ ከአምባ ገነንነት ባህሪያቸው ባሻገር በማንበብ ችሎታቸውና ነገሮችን ፈጥነው በመረዳቱ ረገድ የነበራቸውን ክህሎት አደንቃቸዋለሁ፡፡
በጣም የሚገርመው ነገር እርሳቸው ከሞቱ በኋላ ለካድሬነት ሲሰጥ የነበረ ስልጠና ነበር፡፡ በወቅቱ እነዚህን ስልጠናዎች ይሰጡ የነበሩት አባይ ጸሐዬ እና በረከት ስምዖን ነበሩ፡፡ መለስ ቁልፉን ይዘውባቸው እንደሄዱ ሁሉ እነሱም ቢሆን ይህን ርዕዮተ ዓለም በቅጡ የተረዱ አይመስለኝም።
ካድሬው ለረጅም ጊዜ ሰልጥኖ ከመጣ በኋላ ከጥቂት ወራት በኋላ ሁሉ ነገር አልቆበት ቁልጭ ሲል ስለሚታይ የመልካም አስተዳደር እጦቱም ሆነ እንደ ዘረፋ እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየባሰበት መጣ፡፡ በዚህም መሰረት በሁሉም አቅጣጫ በሚያስብል ደረጃ የዘረፋ መዋቅር ተንሰራፍቶ ነው የቆየው። ይህ የውጭ ትዝብቴ ነው። ይህ ሄዶ ሄዶ በ2010 ዓ.ም ላይ እስትንፋሱ አለቀ፡፡ ትግሉ ከውስጥ መውጣት በመቻሉ የአሟሟቱ ስርዓቱ እንዲፋጠን እገዛ አድርጓል፡፡
እነዚህ የህወሓት ቡድኖች ያችኑ ጽንፈኝነታቸውን ይዘው የገቡት መቀሌ ነው፡፡ እነርሱ መቀሌ በመግባታቸው ነገሮች ሁሉ አበቁ ማለት አልነበረም፡፡ እነርሱ ቤተ መንግስት በነበሩበት ወቅት መዋቅር ላይ አሳምረው ስራ በመስራቸው ከጎናቸው የነበረ አካል እንዳለ መረዳት አያዳግትም፡፡
በየአካባቢው በነበረው ህዝብ ላይ የፈጠሩት ተጽዕኖ ቀላል የሚባልም አይደለም፡፡ በየቦታው የእነሱ አምላኪ የሆኑ ዘራፊ ቡድኖች እንዲፈጠሩ ሆኗል፡፡ ሀብት ያካበተው ደግሞ ዕድሜውን ለማራዘም የተቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ነበር፡፡ ነገር ግን አካሄዳቸውን ላስተዋለ ባለአዕምሮ ተግባራቸው ሲታይ ሁልጊዜም ቢሆን ውሸት እንደሚሸነፍ ማረጋገጫ ይመስለኛል፡፡
በተለይ ደግሞ የአገር መከላከያ ሰራዊት ያደረሱት ጥቃት በጥቃትነቱ ብቻ የሚያልፍ መስሏቸው ሊሆን ይችላል፡፡ አይጥ ሞቷን ስትሻ ታሸታለች የድመት አፍንጫ ይሉት አይነት ተረት ሲሆን፣ ጉዳዩን የአይጥ ጥጋብ አይነት አድርጌ ነው የምወስደው፡፡ ምክንያቱም ድመቷ ስራዋን በአግባቡ አከናውናለች፡፡ ነገር ግን አይጦቹ ያሉት አንድ ቦታ ብቻ አይደለም፤ በብዙ ቦታ ናቸውና እነሱን የማደንና ህግን በተግባር የማስከበር ስራ ለመንግስት ብቻ የሚተው ሳይሆን ህብረተሰቡም ሊሳተፍ የሚገባው ነው፡፡
በነገራችን ላይ አምባገነንነትን ለም መሬት በመሆን የምናሳድገው እኛው የህብረተሰብ ክፍሎች ነን፡፡ ለምን ይሆን ከ2010 ዓ.ም በፊት ትግል ያልተጀመረው? ስለምንድን ነው ዋጋ ከፍለን ለውጥ እንዲመጣ ያላደረግነው? ይህን ማድረግ ካለመቻላችን የተነሳ አምባገነኖች እንደልባቸው ሲፋፉ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ደግሞ በተቃራኒው እንዲቀጭጭ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ ከጦርነት አዙሪት እንዳንወጣ አድርጎናል፡፡
ውሸትን፣ አድርባይነትንና ሆዳምነት በቃ ብለን ሁላችንም መታገል ካልጀመርን ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጠር ለማድረግ የሚያስችል ዋስትና የለንም። ስለሆነም ህብረተሰቡ ካለፈው ሁኔታ ትምህርት ወስዶ ይቺን አገር ዳግም ከዜሮ በመጀመር መገንባት ያለብን ይመስለኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ወደ እስር ቤት የገቡበት ምክንያት ከግዥ ጋር ተያይዞ ሙስና ስለነበር ነው ሲባል ነበር፤ እርስዎ ደግሞ ቀድመው እንደተናገሩት ከሆነ የታሰሩት በሙስና ምክንያት እንዳልሆነ ነውና እስኪ እዚህ ላይ የጠራ ነገር ይኖር ዘንድ ማብራሪያ ቢሰጡን?
አቶ አባተ፡- እውነት ለመናገር በወቅቱ የክልሎች የመፈጸም አቅም በጣም ደካማ ከመሆኑ የተነሳ ያዝ የነበረው የፌዴራል መንግስት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ነው የያዘው፤ በወቅቱ ያሉትም ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ነበሩ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ኮሚቴ አዋቅሮ ለአራቱ ክልሎች ነው የመንገድ መስሪያ እና የውሃ መሳሪያ የተገዛው፡፡
ይህ መሳሪያ ሲገዛ የነበሩትም ራሳቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ ምናልናትም በክልሉ በጀት ላይ የፈረሙትም ሌሎች ከእኔ በታች ያሉት ሹማምንቶች ነበሩ፡፡ እኔ ጥቅል በሆነው ጉዳዩ ላይ በስራ አስፈጻሚ ስብሰባ እንጂ ከዛ ውጭ አንድም ፊርማም ውስጥ ሆነ አንድም ጉዳይ ውስጥ አልገባሁም፡፡ በነገራችን ላይ እውነት ለመናገር ዛሬም ቢሆን ርዕሰ መስተዳድሮች ግዥ ውስጥ እንደማይገቡ ሊታወቅ ይገባል፡፡
ፍርድ ቤቱ በመጀመሪያ ለአንድ ዓመት ያህል አከራከረና በወቅቱ የነበረ አንድ ደፋር የሆነ ዳኛ ነጻ ናቸው ብሎ ለቀቁን፤ ነገር ግን አቶ በረከት ስምዖን ዳኛውን ነው የከሰሰው፡፡ በወቅቱ በረከት የዳኞች ጉባኤ አስተዳደር ሰብሳቢ ነበር፡፡ እኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሳንሰጥ እናንተ በዳኝነት ትወስናላችሁ ወይ ነበር ያላቸው፡፡ እውነቱ ይህ ነው፡፡ በወቅቱ ብዙ ምስክር ለማስመስከር ሞክረው ነበር፤ አንድም የመሰከረ ሰው ግን አልነበረም፡፡ ሰነድም ለማቅረብ ሞክረዋል፤ ግን በዳኞቹ ፊት ሚዛን መድፋት ስላልቻለ ነበር ነጻ በማለት የወሰኑትና የተለቀቅነው፡፡
ለተወሱ ቀናት ተፈትቼ ሐዋሳ ቤቴ ቁጭ እንዳልኩ አንድ ሻለቃ ጦር ቤቴን ከበበው፡፡ ቤት በቆየሁበት ጊዜ ወደየትም መሄድ የሚያስችለኝ የጓሮ ማምለጫ በርም አልነበረኝም፡፡
ዋናው ነገር ግን የተካሄደው የፖለቲካ ውሳኔ ነው፡፡ በወቅቱ በአራቱ ክልሎች ማለትም በአማራ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ በኦሮሚያ አቶ ኩማ ደመቅሳ፣ በትግራይ ደግሞ አቶ ገብሩ አስራት በደቡብ እኔ ስሆን፣ አራታችንም የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ነበርን፡፡ እነዚህ አራቱ ክልሎች ለአቅም ግንባታ በተመላሽ በጀታቸው ይግዙ ተብሎ በሰኔ ወር ላይ የፌዴራል መንግስት ግዥውን አካሄደ፡፡ ከአራቱ ርዕሰ መስተዳድሮች የተከሰስኩት ደግሞ እኔ ብቻ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምናልባት ብዙዎቹ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ባለቤት ወይዘሮ አዜብ መስፍን በጉዳዩ አሉበት ይላሉና እዚህስ ላይ ምን ይላሉ?
አቶ አባተ፡– እውነቱን ለመናገር በእድሜዬ ከአዜብ ጋር ለሁለት ጊዜ ያህል የሚሆን ሰላምታ እንኳ የለኝም። ምናልባትም ወደ ክልሉ እንኳ የመጣችበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ አንዴ ከመለስ ጋር የመጡ ይመስለኛል። ከዛ ውጭ ከአዜብ ጋር የሚያገናኘን ነገር በጭራሽ አልነበረም፡፡ በዚህ ደረጃ ከእኔ ጋር የተወያየችበትም ነገር የለም፤ እኔም በዛ ደረጃ እርሷን አላውቃትም፡፡ ደግሞም በዚህ እድሜዬ ውሸት መናገር አልፈልግም፡፡ በማንም ላይ ያልተገባ ነገር መለጠፍም አልሻም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወሰው እርስዎ በወቅቱ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንደመሆንዎ ከፍተኛ ባለስልጣን ነዎት፤ በወቅቱም ሆነ ከዛ አስቀድሞ የሲዳማ ህዝብ የክልል ይገባኛል ጥያቄ ሲያነሳ የነበረ ቢሆንም ምላሽ ካለማግኘቱም በተጨማሪ ሎቄ በተባለ አካባቢ ይህንኑ ጥያቄ አንግበው በተንቀሳቀሱ ሰዎች ላይ ጭፍጨፋ ደርሶ ነበር፤ ይህንን ያደረገው አካል ማን ነው? ጥያቄውስ ስለምንድን ነው በወቅቱ ተቀባይነት ያጣው?
አቶ አባተ፡– የሎቄውን በውል መናገር አልችልም፡፡ ምክንያቱም እኔ ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ የነበርኩ ሲሆን፣ የሎቄው 1994 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ የተፈጸመ ነው፡፡ እስር ቤት ባለኝ መረጃ ግን እኔን ከስልጣን ካነሱኝ በኋላ ከትግራይ፣ ከአማራና ከኦሮሚያ አራት አራት ሰዎች ተመድበው ደቡብን እንደ አዲስ እንዲደራጅ ብለው ባሉበት ጊዜ ነው የሰው ጥያቄ የተነሳው፡፡
እንደሚታወቀው ቅጠል የያዘ ህዝብ ነው የተጨፈጨፈው፡፡ የትም ይሁን የት በሰብዓዊ መብት ላይ የተፈጸመ ወንጀል አድራጊውን አይለቅምና ወደፊትም ይህንን ጉዳይ ህግ እንደሚያጠራው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንደ ግለሰብ ጉዳዩን ፈጸሙ የተባሉትን ምንም እንኳ እኔ እስር ቤት የነበርኩ ብሆንም አንድ ሁሉት ብዬ በዝርዝር ማቅረብ እችላለሁ፡፡
ቀጥሎ ወዳነሳሽልኝ ጥያቄ ስመለስ፤ ይህ የክልል እንሁን ጥያቄ በሲዳማ ታሪክ 1969 ጀምሮ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ሲነሳ ነበር፡፡ ሶማሌ እንደ አገር በነበረችበት ጊዜ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ በሶማሌ ውስጥ ዓለም አቀፍ እውቅና አግኝቶ የደርግን መንግስት በከፍተኛ ደረጃ ይፋለም ነበር፡፡
ይህ በደርግ መንግስት ጊዜ በኢትዮጵያ ደረጃ ጥያቄ በማንገብ በአመጽ ደረጃ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ከነበሩ መካከል የሲዳማ አንዱ ነው፡፡ በሽግግሩ ጊዜ የንቅናቄው መሪ የነበሩት አቶ ወልደአማኡል ዱባለ እና ሌላው የንቅናቄው መሪ በሽግግሩ ውስጥ ገብተዋል፡፡
እኔ በወቅቱ ፓርላማ ውስጥም ህግ አውጭ አካልም አልነበርኩም፡፡ ፖለቲካውን የተቀላቀልኩት ከዛ በኋላ ነው። በወቅቱ 14 ክልል አድርገው ሲያደራጁ የሽግግር ፓርላማ ሰኔ 24 ቀን ያጸደቀው ቻርተር ህገ መንግስት ድረስ ህግ ሆኖ ያገለግል ነበርና በዛ ቻርተር ውስጥ የተዋቀሩ ክልሎች ሰፊ ክልል ሊፈጥሩ ይችላሉ የሚል በቻርተሩ የሰፈረ አንድ አንቀጽ አለ፡፡
እሱንመሰረት አድርገን ነው ደቡብን አምስት ክልሎችን ጨፍልቀን አንድ ያደረግነው ነው የሚሉት። ከ1987 ዓ.ም በኋላ ግን ህገ መንግስታዊ ነው የሆነው። ህገ መንግስታዊ ጥያቄዎች በህገ መንግስት አንቀጽ 47 ላይ በግልጽ የተቀመጡት ዞኖች ወይም ብሄረሰቦች ክልልን የመጠየቅና ክልል የማግኘት መብት አላቸው ተብሎ ሰፍሯል፡፡ ይህ ህጋዊ ስርዓቱን ተከትሎ እንዲፈጸም የተቀመጠ አንቀጽ ነው፡፡
ከዛ በፊት ግን እስከ 1987 ዓ.ም ድረስ ባለው ጊዜ በአገሪቱ ውስጥ የነበረው ሰኔ 24 የጸደቀው ቻርተር ነበር። አንድ እውነት መረዳት የሚገባው ምናልባት በጉልበት የመጣ ሰው አደረጃቱን የሚወስነው ራሱ ነው፡፡ በወቅቱ በፓርላማው ውስጥ ኦነግ፣ የሶማሌም፣ የሲዳማውም፣ ከደቡብም የተለያዩ የህዝብ መሪዎች ሁሉ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ ናቸው ያጸደቁት ይባል እንጂ የወሰነው ህወሓት ነው።
ኦነግም የተለየ ሐሳብ አቅርቦ በሌላ ሊቀይረው አልቻለም፤ ሌሎቹም ቢሆኑ ያን ማድረግ አልቻሉም፡፡ ተጽዕኖ መፍጠር ማለት በጉልበት ከመጣሽ የእኔን ዓላማ ማሳካት መንገዴንም መከተል አለብሽ ሲል ነው ህወሓት ጫናውን የሚያበረታው። ያለውን ሁሉ በመፈጸም ነው ሁሉ ሰው አጅቦት ሲሄድ የነበረው፡፡ እሱን የሚቃወሙትን ደግሞ ጠራርጎ ከፓርላማ አስወጣቸው፡፡
ከዛ በኋላ ነው ሁላችንም በኢህአዴግ አምሳያ የተፈጠርነው፡፡ ከ1987 ዓ.ም በኋላ እውነት ነው ህዝቡ የክልልነት ጥያቄ ጠይቆ ነበር፡፡ በ1997 ዓ.ም ላይም በሲዳማ ዞን ብሄር ምክር ቤት ተወሰነ፤ ቀጥሎም ወደፓርላማ ተላከ። ይህን ሲያይ በወቅቱ መለስ ወደ ሲዳማ ሄደ፡፡ ደርሶም ስለምንድን ነው ቅንጅት እንዲያ እያደረገኝ እናንተ ይህን የምትጠይቁኝ ብሎ የተወሰኑ ካድሬዎችን ቀይሮ ልማት በሚል አንድ ወደ በንሳ ያለችን መንገድ እንደማባበያ እንዲሰራ አድርጎ ተመለሰ፡፡ ይህ የሚያሳየው አምባገነኖች ስለሆኑ በህገ መንግስቱ የተቀመጠውን መብት ተግባራዊ ላለማድረግ ነው፡፡
አዲሱ የለውጡ መንግስት ግን ያኔ እነሱ የጻፉትን ህገ መንግስት ተግባራዊ አደረገው፡፡ ይህም የሚያሳየው አምባገነኖች መብትን የሚሰጡት በወረቀት ላይ እንጂ በተግባር አይደለም፡፡ በተግባር የማይተረጎም የተስፋ ዳቦ ሆኖ ብቻ ነው የሚቀረው፡፡ የክልልነት ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጥያቄዎችም ቢሆኑ በወረቀት ላይ ከሰፈረ መብት በዘለለ በተግባር የሚታዩ አልነበሩም፡፡ በእርግጥም እስካሁን ህገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የሚቀርቡ በርካታ ጥያቄዎች ስለመኖራቸው መደበቅ አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ከማረሚያ ቤት ከወጡ በኋላ የፖለቲካ ነገሩን እርም ብለው ትተው ወደሰብዓዊ መብት ስራ ያዘነበሉ ይመስላሉና አሁን ባለው ስራዎ ደስተኛ ነዎት?
አቶ አባተ፡– እውነት ነው ይህ ስርዓት እስካለ ድረስ ወደ ፖለቲካው ጉዳይ አልገባም ስል አቋም ይዤያለሁ፡፡ በእስር ላይ ሳለሁ የደረሰብኝ ግፍና በደል አሁን መዘርዘር ይከብደኛል፡፡ እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ እጅግ በጣም ከባድ ፈተና ውስጥ ነበርን፡፡ ማዕከላዊ ምርመራ የሚባለው እስር ቤት ነበር የቆየሁት፡፡ ግራ ቀኝ ቢባል ምንም የማይታይበት ቦታ ነው፤ ቀና ሲባል ደግሞ ከሰማይ ውጭ ማማተር የማይቻልበት ነው። ቤተሰብ የማይጠይቅበት ሁኔታ ውስጥ ከመሆኔም በላይ በጤናዬ ላይ እጅግ የከፋ ችግር በተለይ ወገቤን የታመምኩበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ በእስር ቤቱም የቆየሁት ለስድስት ዓመታት ነው፡፡
ተመልሼ ከወጣሁ በኋላ እኔ ፖለቲካው ከመሰረቱ የበሰበሰ ነው የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ በእርግጥ በወቅቱ እንደሌሎቹ ፖለቲከኛ ካድሬዎች አጥፍቼያለሁ፤ በስብሻለሁ፤ እንዲህና እንዲያ አድርጌያለሁ በማለት እድሜዬን ማራዘም እችል ነበር፡፡ የበሰበሰውን ርዕዮተ ዓለም ባህሪም ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ይሁንና ያንን ማለት ግን አልፈለኩም፡፡ ላለፈው ስህተቴም ፈጣሪ ምህረት እንዲያርግልኝ ጠይቄ ነው ወደግል ኑሮዬ ያዘነበልኩት፡፡ በእርግጥ ከአገር አልወጣሁም። የሚያኖሩኝ ከሆነ በአገሬ መኖር እሻለሁና ድንበር አልዘልም፤ ፖለቲካቸውንም አልነካም ወይም አልተችም፡፡ ወይም ደግሞ ከእነአካቴው መኖራቸውን ረስቼ መኖር እችላለሁ ብዬ ነው ቀሪ ጊዜዬን በመኖር ላይ ያለሁት፡፡
እግዚአብሄር ይመስገን ስለሁሉ ነገር ማለትን እወዳለሁ፡፡ አንዴ በተከሰስኩበት 70 ምናምን ሚሊዮን ብር ፍርድ ቤት ቀርቤ ሲጠይቁኝ በወቅቱ እንኳን የ70 ሚሊዮን ብር ቀርቶ የአንድ ወር ቀለብ በቤቴ አልነበረም። በእርግጥ አልኳቸው 70 ሚሊዮን የሚያወጣ የሰው ፍቅር አለኝ ስል መለስኩላቸው።
ይህን ስናገር አውቄ አልነበረም፤ ከጊዜ በኋላ ግን ተረዳሁ፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ህዝብ ያደረገልኝ ብዙ ነገር ነው፡፡ በእስር እያለሁ ለአንዴ እንኳን ቢሆን የቧንቧ ውሃ አልጠጣሁም፡፡ ምግብ ይመጣልኝ የነበረው ከአዲስ አበባ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ከቤቴ አልነበረም፡፡
ስለዚህ ከዚህ በኋላ ወደፖለቲካ ህይወት መግባት አንደኛ ቤተሰቦቼንም ማስቃየት ነው የሚሆነው። ስለዚህም የተፈቀደፈልኝን ያህል እድሜ ልኑር ብያለሁ፡፡ ነገር ግን ለውጥ እንደሚመጣ አውቅ ነበር። ይህ የመጣውን ለውጥም እጠብቅ ነበር፡፡ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ሐዋሳ መጥተው ህዝቡን ባነጋገሩበት ወቅት መስክሬላቸዋለሁ፡፡ እርሳቸውም ተመሳሳይ ሃሳብ ሰጥተውኛል፡፡
እኔ ከዚህ በኋላ በቤተ ክርስትያን አገልግሎት የምሰጥ ሽማግሌ፤ በማስታረቁም የምሳተፍ አባት መሆንን እሻለሁ፤ ወይም ደግሞ በሰብዓዊ መብት ላይ ይህ ጉድለት አለ ሲባል ሊሰማ የሚችል መዋቅርና አስተዳደር ይፈጠራል ብዬ ነው ትኩረት አድርጌ የምሰራው፡፡ በእርግጥም የኢትዮጵያ እርቀ ሰላም ኮሚሽን ሆኜ ተመርጬያለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሮች ስር ሰደው ይስተዋላሉ፡፡
አገሪቱ ያለፉ ስርዓቶችም የፈጠሯቸው ቂም፣ ቁርሾና በደሎችም አሉባት፤ እነዚህ ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መቋጫ ካላገኙ ላለማድበስበስ ሰፋ ያሉ መርሃ ግብሮች ተነድፈው ስራ ጀምረናል፡፡ ስራው ግን ውስብስብ ነው፡፡ በዚህ መንገድ ሄደን ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት አይነት እርቅና ሰላም የማውረዱ ጉዳይ አልተሳካልንም፡፡
ነገር ግን ይህ ነገር ጊዜ ይወስዳል እንጂ ማድረግ የሚገባንን ጥረት ሁሉ እያደረግን ነው። የሰሞኑን ህግ የማስከበሩ ጉዳይ ሲሰራበት የነበረው ችግር ፈጣሪው አካል እነዚህ እኔ ያለሁባቸው አይነት ተቋማት ስራቸውን በአግባቡ እንዳይሰራ የማደናገር እቅድ ስለነበረው ነው፡፡ አሁን ግን ቆሻሻው ተጠርጓል የሚል እምነት አለኝ፡፡
እኛ ደግሞ ያሉን እሴቶች እንኳን እርስ በእርሳችን ቀርቶ ሌላውንም አገር ለማስታረቅ የሚያስችል ነውና ስራችን ይቀላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህም ደግሞ የሚፈለገውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የበሰበሰ ነው ያሉት ርዕዮተ ዓለም ስለተቀየረ ወደፖለቲካው የመምጣት ፍላጎት የልዎትም?
አቶ አባተ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው፡፡ እግዚአብሄር ጤና ከሰጠኝ እስኪ መጀመሪያ ይህቺን አምስት ዓመት ልያትና ሁለተኛ ዙር ላይ ልሞክር ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም ተግባራዊነቱን በአግባቡ ማየት አለብኝ የሚልም አተያይ አለኝ፡፡ የፖለቲካው መቀየር በተግባር መፈተን አለበት፡፡ በአሁኑ ወቅት እኔ በነጻነት እናገራለሁ። በመናገሬ ደግሞ እታሰራለሁ የሚል ስጋት የለብኝም።
በመናገሬም ደህንነት አያጅበኝም። ወደ ቤቴ ደህንነት ተከትሎ አያስገባኝም። ቀደም ሲል ቢሆን ኖሮ በደህንነትና በስውር ጥበቃ ውስጥ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ አሁን እየኖርኩ ያለሁት በነጻነት ነው፡፡ ምናልባትም ለምርጫው ውስን ወራት ስለሚቀረው እስከዛ ድረስ ሃሳቤን ልቀይርም እችል ይሆናል፡፡ ይህ ግን ገና የሚታይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡኝ ሰፊ ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ አባተ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2013