የሰው ልጅ በህይወት ዘመኑ የተለያዩ ፈተናዎች ሊያጋጥሙት ይችላሉ፡፡ እንደአገርም በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ የማለፍ እድል ይገጥማል፡፡ ኢትዮጵያም ለበርካታ ጊዜያት በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ አልፋለች፡፡
በተለይ የግል ፍላጎታቸው ከሀገራዊና ከሰፊው ህዝብ ጥቅም የበለጠባቸው ጥቂት ቡድኖችና የውጭ ጠላቶች በፈጠሯቸው ውስብስብ ችግሮች ምክንያት ኢትዮጵያ ለበርካታ ዘመናት በድህነት ውስጥ እንድታልፍ ተገዳ ቆይታለች፡፡
ለምሳሌ ወደኋላ መለስ ስንል በመዘነ ቅኝ ግዛት ኢትዮጵያ ልክ እንደሌላው አፍሪካ አገራት ሁሉ ከፍተኛ ፈተና አጋጥሟታል፡፡ በተለይ በ1928ዓ.ም ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር ያደረገው ሙከራ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን በማንኛውም ጉዳይ ለውጭ ጠላት ራሳቸውን አሳልፈው የመስጠት የሞራል ዝቅጠት የላቸውምና ያንን በከፍተኛ ዘመናዊ የጦር መሳርያ የታጠቀ ወራሪ ሃይል አሳፍሮ መልሷል፡፡
ይህ ድል የመላ ጥቁር ህዝቦች ሁሉ ድል ለመሆን የበቃ እንደሆነ ሁላችንም በኩራት የምንናገረውና ዛሬም የሞራል ስንቅ የሆነን ትልቁ የድል ችቧችን ነው፡፡
ከዚያ በኋላም ቢሆን ኢትዮጵያ በርካታ የውጭ ወረራ እና የጥቃት ሙከራዎችን አስተናግዳለች፡፡ ለአብነትም በታላቁ ወንዛችን አባይ ምክንያት ግብፅ በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን ለማጥቃት አንዴ በጦርነት፤ ሌላ ጊዜ በዲፕሎማሲ ጫና ለማድረግ ሞክራለች፡፡
ጎረቤት ሶማሊያም ዳር ድንበራችንን አልፋ ወረራ የፈጸመችበት ታሪክ ብዙዎቻችን የምናስታውሰው ነው፡፡ ይሁን እንጂ አንዳቸውም የኢትዮጵያውያንን አንገት ማስደፋት አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን በዳር ድንበራቸውና በነፃነታቸው ለማንም የሚንበረከኩ አይደሉምና፡፡
ከዚህም ባሻገር በውስጥም ኢትዮጵያ የሚገባትን የቆየ ታሪካዊ የስልጣኔ አሻራዋን አስጠብቃ ከትውልድ ትውልድ እንዳታስተላልፍ ጋሬጣ የሆኑ በርካታ ደባዎች ተፈጽመውባታል፡፡
በተለይ በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ ስልጣን ላይ የሚወጡ መሪዎች እና እድሉን አግኝተው በየደረጃው ስልጣን ላይ የወጡ የአመራር አካላት ሀገርን ለማሳደግና የቀደመውን ስልጣኔ ለማስመዝገብ ከመጣር ይልቅ በግል ፍላጎት ላይ ተንተርሰው ከሀገር ጥቅም ይልቅ የግል ጥቅምን ብቻ ሲያሳድዱ ዘመናት ተሻገሩ፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ያልተገቡ ትርክቶችን በመፍጠርና ይህንንም በተለያዩ ሰነዶች በመሰነድ ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው በጋራ እንዲበለጽጉ ከማድረግ ይልቅ ልዩነት እንዲጎላና ትኩረት እንዲያገኝ በማድረግ በተሰሩ ደባዎች አንዱ በሌላው ላይ ቂም እንዲቋጥር፣ እንዲጠራጠር፣ እና በአምባገነንነት ሌላውን በመጨቆን ለራስ ጥቅም ብቻ እንዲቆም ሁኔታዎች በስፋት ሲሰሩ ተስተውለዋል፡፡
ይህ ደግሞ በዓለም መድረክ ጭምር ትልቅ ስም ያሰጡንን የቀደሙ የስልጣኔ አሻራዎች ይዘን እንዳንቆይ ከማድረግ ይልቅ ለዘመናት እድገታችን ቁልቁል እንዲሆን አድርገውን የበለፀጉ አገራት እና የምእራባዊያን መገናኛ ብዙሃን መዘባበቻ አድርጎን ቆይቷል፡፡
በተለይ በህዝቦች ቅሬታ ተወልዶና አድጎ ለስልጣን የበቃው የኢህአዴግ መንግስት ከህዝባዊ ዓላማ አፈንግጦ እና በጥቂት የጁንታው አባላት እኩይ ሴራ ተጠልፎ ሀገሪቷንም ላልተገባ ውድቀት ዳርጎ ቆይቷል፡፡ የሀገሪቷ ሀብትም በጥቂት ቡድኖች እጅ ውስጥ ገብቶ አብዛኛው ህዝብ ኑሮው ከጊዜ ወደጊዜ እንዲያሽቆለቁል ድህነት ዳግም እንዲያገረሽ አድርጓል፡፡
እነሆ ይህ የጁንታ ቡድን ጽዋው ሞልቶ በህዝቦች ትግል ከነበረበት ዙፋን ሲወርድ ግን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የደስታ አየር እየተነፈሰ ይገኛል፡፡ በተለይ ጁንታው ከሁሉም በላቀ ሁኔታ በትግራይ ህዝብ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ በቀላሉ የሚታይ አልነበረምና የትግራይ ህዝብም አዲስ የሰላም አየር መተንፈስ ጀምሯል፡፡
ቡድኑ በትግራይ ህዝብ ጉያ ውስጥ ተወሽቆና የተሳሳቱ ትርክቶችን ፈጥሮ ህዝቡን ለራሱ ዓላማ ለማሰለፍ ትልቅ የሴራ ፖለቲካ ሲጫወት ኖሮ በመጨረሻም ከሁሉም ሳይሆን ሽንፈትን ሊቀዳጅ ችሏል፡፡
በአሁኑ ወቅትም በትግራይ ሲካሄድ የቆው የህግ ማስከበር ስራ ተጠናቆ ክልሉ የሰላም አየር እየተነፈሰ ይገኛል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ቡድን ቢወገድም ቡድኑ ያስከተለው ውድመት ከባድ በመሆኑ ይህንን ቁስል ማከም ያስፈልጋል፡፡
በተለይ ቡድኑ ያወደማቸው መሰረተ ልማቶች አንዳንዶቹ የፈሪ ዱላ ያረፈባቸው በመሆናቸው ለማስተካከል ጥቂት ጊዜና ከፍተኛ ወጪ መፍጀታቸው የግድ ነው፡፡ ለምሳሌ በአንዳንድ ቦታዎች በቴሌኮም መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል፡፡ በመንገድና በሃይል አቅርቦትም ላይ ያደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡
ይሁን እንጂ አሁን የፌዴራል መንግስትና የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እዚህን ችግሮች ለማስተካከልና ለማረም ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ለማስተካከልና በቀጣይም የትግራይ ህዝብ የልማትና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል የህብረተሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡
በመሆኑም መላው የክልሉ ነዋሪ ፊቱን ወደልማት በመመለስና ከፌዴራል መንግስትና ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጎን በመሰለፍ ችግሮችን ለመፍታት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
በተለይ ከህግ ማስከበሩ ያመለጡና ተንጠባጥበው በየስርቻው የተወሸቁ የጁንታው አባላት በአንድ በኩል በየመንገዱ እንቅፋት እንዳይፈጥሩ በሌላ በኩል ደግሞ ላደረሱት ጥፋት ተገቢውን እና ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲያገኙ ህብረተሰቡ አካባቢን በንቃት በመጠበቅና በልማት ስራዎች ላይ በመረባረብ የበኩሉን ድርሻ ማበርከት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2013