ከጥር 5 እስከ 12 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ 7ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርት ውድድር ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር እንደሚያግዝ የከተማዋ ስፖርት ኮሚሽን አመለከተ።
የአዲስ አበባ ከተማ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዮናስ አረጋይ ትናንት በተሰጠው መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤በአዲስ አበባ ከተማ ለ7ኛ ጊዜ የሚካሄደው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ስፖርታዊ ውድድር ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ አሻራውን በማሳረፍ የበኩሉን ሚና ይወጣል ብለዋል።
የውድድሩ አስፈላጊነት የተማሪዎች እርስ በእርስ ግንኙነትን በማጠናከር ሀገራዊ ስሜትን ብሄራዊ መግባባትን ለማበልጸግ የሚያስችል ተከታታይና የማያቋርጥ የውድድር መድረክ ለመፍጠር መሆኑን ጠቁመው፤በሰባተኛው የከተማ አቀፍ የውድድር መድረክ በስፖርት ሰላምን አንድነትን ለማምጣት ለሚደረገው አገራዊ እንቅስቃሴ እርሾ በመሆን ያገለግላል። በተጨማሪም በከተማችን የሚገኙ ተማሪዎችን በተደራጀ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማሳተፍና ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ገልጸው፤ የመደበኛ የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት የተግባራዊ እንቅስቃሴ ሂደት ለመፍጠርም የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ከተማ አቀፍ የተማሪዎች ውድድሩ ጥር አምስት ቀን በእንጦጦ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ በይፋ የሚጀመር ሲሆን በ20 የስፖርት አይነት እንደሚከናወን ተነግሯል። በዚህ መሰረት በውድድሩ 65 ቡድኖች 467 ወንድ እና 409 ሴት በድምሩ 876 ስፖርተኞች እንዲሁም 130 አሰልጣኞች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በውድድሩ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳዩ ተሳታፊ ተማሪዎች በመቀለ ከተማ ለሚካሄደው ሀገር አቀፍ የተማሪዎች የስፖርት ውድድር አዲስ አበባን እንዲወክሉ የሚመረጡ ይሆናል። በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው አገር አቀፍ የተማሪዎች የስፖርት ውድድር ከመጋቢት 14 እስከ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ይካሄዳል። የሀገር አቀፍ የተማሪዎች ውድድር የዝግጅት ሂደት ያለበትን ሁኔታ ከአስተናጋጇ ክልል ጋር ለመገምገም ወደ መቀሌ የሚመለከተው ቡድን መጓዙ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ጥር 21/2011
ዳንኤል ዘነበ