ሰላማዊት ውቤ
ሕይወት በተቃራኒ ጉዳዮች የተሞላች ናት። ዛሬ ብታስደስት ነገ ታስለቅሳለች። ዛሬ የተገኘ ሀብት ነገ ባልታሰበ አጋጣሚ እንደ ጤዛ ብን ብሎ ይጠፋል። ሲጠፋ ባለሀብቱ ብቻ ሳይሆን ኑሯቸውን በሀብቱ ላይ መስርተው የነበሩ ብዙ ከበስተጀርባው ያሉ ዜጎች ኑሯቸው ይዛባል።
ይሄ ዓይነቱ ክፉ ዕጣ በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባሉ አንዳንድ የማምረቻ ኢንዱስትሪ ባለቤቶችና የሕብረተሰብ ክፍሎች ላይ ደርሷል። ዕጣው ከደረሰባቸው ባለሀብቶች አንዱ መንግሥት የወሰደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ በክልሉ ሁለት ቦታዎች በነበሩ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎቻቸው የንብረት ውድመትና ዝርፊያ የተፈፀመባቸው አቶ አበራ ጣሰው ናቸው።
የተወለዱት ያኔ ጠቅላይ ግዛት እየተባለች በምትጠራው በዛሬዋ ትግራይ ክልል ውስጥ ነው። ጥቅምት 16 ቀን 1953 ዓ.ም አቶ አበራ የተወለዱባት ቦታ ቀድሞ በነበረው አጠራሯ እንደርታ አውራጃ ሥራ ወረዳ ትባላለች።
ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ትምህርታቸውን የተማሩት በዚሁ ወረዳ በምትገኘው ሳምረ ከተማ ነው። ከአምስተኛ እስከ 12ኛ ያለውን ትምህርታቸውን ደግሞ መቐለ ውስጥ ነው የተማሩት። የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ህግ ትምህርት ቤት ተምረው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘዋል።
በህግ ከተመረቁ በኋላ ከአዲስ አበባ ከተማ ሳይወጡ የጠቅላይ አቃቢ ህግ የከባድ ወንጀል ችሎት አቃቢ ህግ ሆነው ተመደቡ። ከዛም ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዛወር የከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ቀጥሎም ሰብሳቢ ዳኛ ሆነው ሰሩ። ከዚህ በኋላ አሁን እየሰሩበት ወዳሉት ጥብቅና ሙያ ተሸጋገሩ።
ወደ እዚህ ሥራ ከተሸጋገሩ በኋላ ከጓደኞቻቸው ጋር በጋራ ሆነው ጎን ለጎን ሲሰሩት ወደ ነበረው ወደ ንግዱ ዓለም ገብተዋል። ሲገቡ ከታዳጊነታቸው ጀምሮ በሀሳባቸው የሰነቁትን በእርሻና በከብት እርባታ ተሰማርቶ ሰፊውን የገጠር ማህበረሰብ መጥቀም ታሳቢ አድርገው ነበር። ወደ እርሻ ከገቡ አንዱን አስር ዓመት አጠናቅቀው ሁለተኛውን አስርት አሀዱ ብለዋል።
የመቐለን ከተማንና የዙሪያውን ገጠር ወረዳ ነዋሪዎች ለመጠቀም አስበው በወተት ልማት ከተሰማሩ ሁለተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል።
ባለሀብቱን ያገኘናቸው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለፈው አርብ በትግራይ ክልል ከሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪ ባለቤቶችና ኃላፊዎች ጋር ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ጋር በተያያዘ ስለደረሰባቸው ጉዳትና በቀጣይ መደረግ ስላለባቸው ሥራዎች ባወያያቸው ወቅት ነው። በወቅቱ እንደነገሩን በከፈቱት ትምህርት ቤት በፈጠሩት የሥራ ዕድልም ሆነ በሚሰጡት አገልግሎት ሰፊውን የገጠር ማህበረሰብና አካባቢውን ተጠቃሚ ሲያደርጉ ቆይተዋል።
በእርሻና በወተት ልማት የተሰማሩትም ከትርፍ በስተጀርባ ይሄንኑ ሰፊ የገጠር ማህበረሰብ ተጠቃሚነት ታሳቢ በማድረግ ነበር። በክልሉ በሚገኙ በነዚህ ሁለት ፋብሪካዎቻቸው እና ባጋጠማቸው ወቅታዊ ችግር አንጻር አነጋግረናቸዋል።
አቶ አበራ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ ሳባና የእርሻ ድርጅትና የኤጄጄ ወተት ማቀነባበሪያ የተሰኙ ፋብሪካዎች አሉ። አንደኛው ራያ ውስጥ መሆኔ አካባቢ የሚገኝ ሲሆን ሳባና ፋርሚንግ ተብሎ ይጠራል።
ወደ ማምረት ሥራ ከገባ አሥር ዓመታትን አጠናቅቆ ሁለተኛውን አስርት አሀዱ ብሏል። 457 ሄክታር ላይ የሰፈረ ነው። ሙሉ በሙሉ በመስኖ ነው የሚለማው። ብርቱካን፣ አቡካዶ፣ ማንጎ፣ ሎሚ፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ቃሪያና ሌሎች የተለያዩ በርካታ አትክልትና ፍራፍሬ ይመረትበታል።
በትግራይ ክልል አካባቢ ተፈጥሮ በነበረው ህግን የማስከበር እንቅስቃሴ ውድመትና ዘረፋው ሲደርስ የተከሏቸው ፍራፍሬዎች ምርት እየሰጡና ለገበያ እያቀረቡ እንደነበር ይናገራሉ። ደንበኞቼ የተለያዩ ነጋዴዎች ነበሩ። ወደ እርሻው በመምጣት ከማሳው ላይ እየገዙ መኪናቸው ላይ በመጫን ወደ ተፈለገው ቦታ ወስደው የሚያቀርቡ ናቸው። አዲስ አበባ፣ መቐለ፣ አዋሽ፣ መተማ ምርቱ ለገበያ ከሚቀርብባቸው ቦታዎች ይጠቀሳሉ።
ሌላው የወተት ፋብሪካ ‹‹ኤጄጄ›› ይሰኛል። የሚገኘው አዱ ጉደን ነው። አዱ ጉደን ከመቐለ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነች። ፋብሪካው በሦስት ሺህ ሄክታር ቦታ ላይ ነው የሰፈረው። ይህም ፋብሪካ በነበረው ችግር ጉዳት ደርሶበታል ይላሉ።
አቶ አበራ ሰርቶ ትልቅ ደረጃ መድረስና ባለሀብት መባል ያሳዩ ጠንካራ ሰው ናቸው። ታዲያ መነሻቸው ሀብት ማግኘት ቢሆንም ከዚሁ ጎን ለጎን ታሳቢ ያደረጉት የገጠሩንና የአካባቢውን ማህበረሰብ የመጥቀምና የማገልገል ህልማቸውን ማሳካት ጭምር ነው። ‹‹ለገጠሩ የማህበረሰብ ክፍል ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠርና አገልግሎቶችንም በቅርብ እንዲያገኙ ማድረግ እፈልግ ነበር።
መቐለ ከተማ ላይ ሕዝቡ የወተት አቅርቦት አልነበረውም። አዱ ጉደንም እንዲሁ ቢሆንም የተከፈተው የወተት ማቀነባበሪያ አቅርቦት ሁለቱንም ይደርሳል ብዬ በማሰብ ነው ያቋቋምኳቸው።›› ብለዋል።
አቶ አበራ ህልማቸው ራሳቸውን በእውቀት በገንዘበ ማሳደግ ከዚሁጋር ተያይዞም ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ ቢሆንም የሰሞኑ ክስተት ግን ይሄንኑ ራዕያቸውን እንዳደነቀፈባቸው ይናገራሉ። ‹‹ ትልቅ ጥፋት ነው የደረሰብኝ። ሆኖም አንድ የሚያጽናናኝ ነገር አለ። ይሄውም የሰው ሕይወት በጠፋበት ሁኔታ ንብረት ወደመብኝ ብዬ አላማርርም። ከንብረት ይልቅ የጠፋው የሰው ሕይወት ነው የሚያሳዝነኝ።
በተለይ እርሻውን ብቻ በተመለከተ ከሁለት ዓመት በፊት ‹ጎልደን አፍሪካ› በሚባል ትልቅ አማካሪ ድርጅት ሀብቱ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ ጥናት ያስጠናሁበት ሁኔታ ነበር። በዚህ ጥናት ግኝት መሰረት በእርሻ ፋብሪካው ላይ የነበረው የሀብት መጠን 289 ሚሊዮን መሆኑን አውቂያለሁ።
የወተት ፋብሪካው የሀብት መጠን በትንሹ 35 ሚሊዮን ይሆናል። ወተቱ የሚገኘው በፋብሪካው ካሉኝ 153 የተሻሻሉ የሆላንድ የወተት ላም ዝርያዎች ነው። ይሄ የወተት ፋብሪካ ከነዚህ ላሞች በየቀኑ 12 ሺ ሊትር ወተት የመረከብ አቅም ነበረው። ከአዲ ጉደን ነዋሪዎች በተጨማሪ የመቐለና አካባቢው ነዋሪዎች፣ አከፋፋዮች፣ ባለ ሆቴሎችና ባለ ካፌዎች ይጠቀሙበታል። ይሄን ፋብሪካ ከገዛሁት ሁለተኛውን ዓመት ይዟል። ፋብሪካው ተተክሎ ወተት ወደ ማምረት የገባውም ወዲያው ነው።›› ይላሉ።
አቶ አበራ ራያ አካበቢ ስላለው ሁኔታም ሲያስረዱ፤ ራያ ያለን እርሻ ሁልጊዜ ለምለም ነው። እንደ መቐለ ብዙ የመኖ ችግር የለም። በመሆኑም ላሞቹን ለመኖ ብለን የወተት ፋብሪካው ካለበት አዲ ጉደም ወደ ራያ ወስደናቸው ነበር።
ሆኖም በአካባቢው የጦርነት ችግር ሲፈጠር ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ የእርሻ ፋብሪካው ሠራተኞች በሙሉ ሕይወታቸውን ለማዳን የሸሹበት ሁኔታ ነበር።
ትራክተሮቹ፣ መኪኖቹ፣ ማሽነሪዎቹ፣ ላሞቹ እዛው በቀሩበት አጋጣሚ ተወሰዱ። በአጠቃላይ ንብረቱ ተዘርፏል ሲሉ ይናገራሉ።
ፋብሪካው ከ100 በላይ ለሆኑ ሰዎች ቋሚ እና ከአንድ ሺህ ለማያንሱ ጊዜያዊ ሠራተኞች የስራ ዕድል መፍጠሩን አቶ አበራ ይናገራሉ። በተለይ ምርት በሚሰበሰብበትና የችግኝ ተከላ በሚካሄድበት ጊዜ ፋብሪካው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራተኛ በጊዚያዊነት ይቀጥራል።
እርሻው ለብዙ ዜጎች በተለይም ለአካባቢው ማህበረሰብ ከፍተኛ የሥራ ዕድል የከፈተ ነው። የወተት ፋብሪካው ደግሞ ለ30 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ሁሉም ሠራተኞች ፋብሪካው ያለበት ገጠር አካባቢ ነዋሪ ናቸው። በዚህም የስራ ባህል ይለማመዳሉ፤ ሰርቶ ማግኘትንም እንዲሁ።
በሁለቱም ፋብሪካ ያሉት ሠራተኞች በተፈጠረው የጸጥታ ችግር እና በባንኩ መዘጋት ምክንያት የሁለት ወር ደመወዝ አልተከፈላቸውም።
በመሆኑም ከፍተኛ ችግር ላይ ናቸው። ብዙዎቹ የእርሻ መሬትና ቋሚ ገቢ የሌላቸው፣ ያገኙትን ስራ ሠርተው የዕለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑ የአርሶ አደር ልጆች እንደመሆናቸው የዕለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑበት ገቢ ያስፈልጋቸዋል። አሁን ላይ ወደ ሥራ አጥነት ተመልሰዋል።
ሆኖም ፋብሪካው በመውደሙና በመዘረፉ ምን እንደማደርጋቸው አላውቅም። ከውድመቱና ከዘረፋው በኋላ አሁን እርሻው ውስጥ ምንም ዓይነት ሠራተኛና ምርት የለም። ይሄ ሁሉ የጦርነትን አስከፊነት በደንብ አድርጎ የሚያሳይ ይመስለኛል።
እሳት ያገኘውን ነው የሚበላው፤ ጦርነትም እንደዛው ነው። ጦርነት ስነ ልቦና ይበላል፣ ሀብት ይበላል፣ ሕይወት ይበላል። ብዙ ነገር ነው የሚያሳጣው በማለት ይገልጻሉ። የሰላም እጦት ንብረት፣ የሰው ህይወት ያሳጣል፤ ከዚሀም በላይ ሰራተኛን ስራ አጥ በማድረግ ለረሀብ ጭምር ያጋልጣል።
‹‹ እኔ ለራሴና ለቤተሰቦቼ አንድ እንጀራ የትም ሄጄ አላጣም። ደግሞ ሌሎች አማራጮች አሉኝ። አዲስ አበባ ላይ ለ500 ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መቐለ እንዲሁ አብነት የሆነ‹ማጂክ ካርፔት› የተሰኘ ትምህርት ቤትና ሌሎች ድርጅቶች አሉኝ። በዚህ ላይ በሙያዬ ሰርቼ መኖር የምችል የህግ ባለሙያ ነኝ።
በመሆኑም ለራሴና ለቤተሰቦቼ አንድ እንጀራ የትም ሄጄ አላጣም። ››ይላሉ። አቶ አበራ በርካታ ቤተሰቦችን ያስተዳድራሉ። ከእርሳቸው ቤተሰብ በተጨማሪም ለብዙዎች የስራ ዕድል የፈጠሩ በመሆናቸው በእነሱ ስር ያሉትም እንዲሁ በርካታ እንደሚሆኑ መገመት አይከብድም።
እሳቸውም ሁለቱ ፋብሪካዎች በመውደማቸው እኛ ከሌሎች ድርጅቶቻችን በምናገኘው ገቢ ኑሯችንን ልንመራ እንችላለን። የኛ ጉዳይ እንብዛም ላያሳስብ ይችላል። ሆኖም በጦርነቱ የወደመውና የጠፋው ሀብት የሕዝብና የሀገር ሀብት ነው። ሀብቱ ብዙ የዕለት ገቢ የሌላቸው ዜጎች (ድሆች)እንጀራ በልተው የሚያድሩበት ነው። መንግስት ጉዳዩን መቃኘት ያለበትም ከዚህ አንፃር ነው።
መንግስት ድርጅቶቹ ወደ ሥራ የሚመለሱበትን መንገድ መፈለግ ማለት እዛ አካባቢ ያለው ሕብረተሰብ ወደ ትክክለኛ ሕይወቱ እንዲመለስ ማድረግ ነው። ለነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተፈጠረው የሥራ ዕድል ለአያሌ ዜጎች ትሩፋት ያለው መሆኑም ሊታሰብ ይገባል።
እያንዳንዱ ቤተሰብ አምስት፣ አምስት ቤተሰብ ቢኖረው በርካታ ቁጥር ያለው ዜጎች እንጀራ በልተው እንዲያድሩ የሚያደርግ መሆኑ መታየት አለበት። እነዚህ የአካባቢው ዜጎች አሁን ላይ ሲያገኙት የነበረው ገቢ ተቋርጧል።
ሥራ ፈተው ነው የተቀመጡት። ሥራ ፈተው ተቀመጡ ማለት ደግሞ የሚመገቡት የለም ማለት ነው። በአሁኑ ወቅት የሚቆጨኝ ፋብሪካው ሥራ በማቆሙ ምክንያት እኔና ቤተሰቦቼ ገቢያችን መንጠፉ አይደለም። ፋብሪካዎቹ ያሉበት አካባቢ ያሉት የሕብረተሰብ ከፍሎች ሥራ ማጣታቸው ነው።
አዲስ ዘመን ታሕሣሥ 22/2013