የ ኦ (O) ደም ዓይነትና የአመጋገብ ስርዓት
ይህ የደም ዓይነት ከሌሎች ቀድሞ የነበረ ጥንታዊ ሲሆን ከእንስሳት አዳኞች የተወረሰ የደም ዓይነት ነው። የዚህ ደም ባለቤቶች ዓሣ፣ የባህር ምግብ፣ ቀይ ስጋ፣ ጨው፣ ዶሮ፣ ስኳር ድንችና የመሳሰሉትን ምግቦች እንዲያዘወትሩ ይመከራል። በዚያውም ልክ እንቁላል፣ የእንስሳት ተዋጽኦዎች፣ ስንዴና ባቄላን ከገበታቸው ማራቅ አለባቸው።
የ ኤ (A) ደም ዓይነትና የአመጋገብ ስርዓት
ይህ የሰው ልጆች ወደ እርሻ ሲገቡ በተፈጠረው የአመጋገብ ለውጥ ምክንያት የተከሰተ የደም ዓይነት ነው። በዚያ ዘመንም የሰው ልጆች ለመኖነት ፊታቸውን ወደ አትክልቶች በማዞራቸው ምክንያት በጊዜ ሂደት እጅግ የዳበረ የምግብ ማላም ስርዓትን አዳበሩ። በአንጀታችው ውስጥ የሚገኙት የባክቴሪያዎች ዓይነትና ቁጥርም እጅግ ተበራከተ።
የዚህ ደም ባለቤቶች ፖም፣ አቮካዶ፣ ሰላጣ፣ ካሮት፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ባቄላ፣ እርጎ፣ የስንዴ ዳቦና ፓስታ እንዲመገቡ ይመከራል። ነገር ግን እንቁላል፣ ስጋ እና ሌሎች የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በተገቢው መንገድ ለማብላላት አንጀታቸው አልዳበረም።
የ ቢ (B) ደም ዓይነትና የአመጋገብ ስርዓት
የጥንቶቹ አዳኞች ወደ ሒማሊያስ ተራሮች በመሰደድ እንስሳትንም በማላመድ የአርብቶ አደር ሕይወትን መምራት ሲጀምሩ የተፈጠረ የደም ዓይነት ነው። ቀይ ስጋ፣ ዓሣ፣ እርጎ፣ ዓይብ፣ ወተት፣ ሙዝ፣ አረንጓዴ ቅጠላማ አትክልቶች፣ ወይንና አናናስ ተስማሚ ከሚባሉት ምግቦች መካከል ሲጠቀሱ ዶሮ፣ ስንዴ፣ ቲማቲም እንዲሁም ለውዝ እንዳይመገቡ ይመከራል።
የ ኤቢ (AB) ደም ዓይነትና የአመጋገብ ስርዓት
ኤቢ የደም ዓይነት በቅርብ ጊዜ የተከሰተ ሲሆን ከዓለም ህዝብም በአምስት ፐርሰንቱ ውስጥ ብቻ ይገኛል። የዚህ ደም ባለቤቶች ስጋንና ሌሎች የእንስሳት ተዋጽኦዎችን መፍጨት ቢችሉም የጨጓራቸው አሲድ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት የተመገቡት ምግብ በስብ መልክ ይከማቻል።
ፍራፍሬዎችና አረንጓዴ አትክልቶች፣ ሀብሀብ እና ወይን፣ እንደ ቱና እና ሰርዲን ያሉ የባህር ምግቦችን ማዘውተር ተገቢ ሲሆን ከበቆሎ፣ የበሬና አሳማ ስጋ እንዲሁም ከአልኮልና ቡና መራቅ ያስፈልጋቸዋል። ምንጭ – ከኢትዮ − ሐኪም
አዲስ ዘመን ታሕሣሥ 22/2013